አዋሽን እናልማ

መነሻውን የጊንጪን ዳገት አድርጎ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ጅቡቲ ድንበር አካባቢ አፋር ክልል ውስጥ በወንዙ ከተፈጠሩ ሐይቆች መካከል አንዱ በሆነው አፋንቦ በሚገኘው አቤ ሐይቅ መዳረሻውን አድርጓል። በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ ከሚገኙት 12 ተፋሰሶች እና ሐይቆች መካከል በውስጡ ከያዘው እምቅ የልማት አቅም፣ ካለው የቆዳ ስፋት እንዲሁም በአካባቢው ከሚኖረው የሕዝብ ብዛት እና ከሌሎች ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ባህሪው አንፃር የአዋሽ ተፋሰስ ከዓባይ ቀጥሎ ይጠቀሳል። አዋሽ ካለው አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ውስጥ 85 በመቶ ለእርሻ ምቹ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 200ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ይገኛል።

የአዋሽ ወንዝ ውለታ ብዙ ነው። ለመጠጥ ውሃ፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለአሳ እርባታ እና ለቱሪዝም አገልግሎትም እየዋለ ነው። እነዚህን ጥቅሞች እያስገኘ ቢሆንም ግን ካለው እምቅ አቅም አንፃር የሚገባውን ጥቅም እያስገኘ አለመሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ለእዚህ መሠረታዊው ችግር የውሃ አስተዳደር ክፍተት ስለመሆኑም ይጠቀሳል። ይህን እና ሌሎችም ችግሮችን ለመቅረፍ ከሰሞኑን ሁሉንም ያሳተፈ የጋራ ራዕይ ያለው ዕቅድ (ቤዚን ፕላን) በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ስምምነቱን እና በተፋሰሱ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- አዋሽን ለማልማት ስለተዘጋጀው ዕቅድ ትንሽ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር አብርሃ፡- የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የአዋሽን ተፋሰስ የውሃ ሀብት ከተፈጥሮ ሀብት ጋር በማዛመድ ከባለድርሻ አካላት ጋር አሳታፊ በሆነ መንገድ አዘጋጅቶ ፕላኑን ይፋ አድርጓል። ይህን ሥራ ወደ መሬት ለማውረድ ኃላፊነት ያለበት ጽሕፈት ቤቱ ወይም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የጋራ ዕቅድ ብቻ ሳይሆን ዕቅዱን በጋራ ለማስተግበር መድረክ ፈጥሮ ውይይት እያደረገ ነው።

ይህ ሁሉ እየሆነ ያለበት ምክንያት በኢትዮጵያ ባሉ የውሃ ተፋሰሶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት አለ። ሀብቱን ለማህበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል ደግሞ ግዴታ ነው። ይህንን መሠረት በማድረግ የውሃ ሀብትን አሳታፊ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ የውሃ ፖሊሲ አስቀምጧል። ይህ የውሃ ፖሊሲ ሀብቱን በተቀናጀ መንገድ መምራት፣ ማስተዳደር እና መንከባከብ እንዲሁም መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ያሳያል።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የቤዚን ፕላኑን እንደመሳሪያ የሚወስደው ነው። የቤዚን ፕላኑ ውስጥ ያሉትን ውሃ እና ሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶችን በጋራ በጥራት እና በመጠን በመለየት ይህንን ሀብት የሚጋሩ እና የሚጠቀሙ አካላት በጋራ ሆነው ከዕቅድ ጀምሮ እስከ አጠቃቀም የሚገለገሉበትን ዝርዝር ሁኔታዎች ይዟል። በተጨማሪ በቤዚኑ ሁሉም ተሳታፊ የሚሆኑበት እና ፍትሃዊነቱን የሚያረጋግጡበት፣ በጋራ ሀብቱን የሚጠቀሙበት እና ግጭትን የሚስወግዱበት ሥርዓት ለመፍጠር የተዘጋጀም ነው።

በትግበራው ላይም አንዳንዶቹ እየተተገበሩ የሚሠሩ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ እየታቀደባቸው የሚኬድባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ቀድሞም መደላድል የፈጠርንባቸው በመሆናቸው ለመተግበር የሚያስቸግሩ አይደሉም። ዋናው ጉዳይ ግን ይሄ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር በአተገባበር ረገድ ገና በጅምር ላይ ያለ ነው። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሀገራትም ጀምረውት ብዙ ያልሔዱበት ነው። ለእኛ ግን ዋና ብቸኛ ተደርጎ የሚወሰድ እና ያለንን የውሃ ሀብት በተቀናጀ መንገድ ለማልማት የግድ መጠቀም እንደሚገባ መረጃዎች ያሳያሉ።

የአዋሽ ቤዚን በርከት ያለ ሀብት ያለበት ነው። ይህን መሠረት በማድረግ በ1960ዎቹ የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር በሚል ተቋቁሞ በጣም በርካታ ሥራዎች ተሰርቷል። እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ ውሃን ለመስኖ መጠቀምን ያስተዋወቀ፤ በተለይ አሚባራ ብለን በምንጠራው አካባቢ የመስኖ እርሻን እንዲስፋፋ ያደረገ ቋሚ አካባቢ ነው። ከዛ በኋላ በነበሩት ሂደቶች የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር በተለያየ መዋቅር ላይ አልፏል።

ራሱን አዋሽ ቤዚን ባለስልጣን ብሎ አደራጅቶ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ ነበር። ከዛም በኋላ በተፋሰሶች ልማት አስተዳደርም አንድ ጽሕፈት ቤት ሆኖ ሥራውንም ሲሠራ ነበር። አሁን ደግሞ የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር በሚል በአዲሱ ሪፎርምም በአሁኑ መንገድ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል።

ይህንን ሀብት በተመሳሳይ ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ስንመለከት ምንም ዓይነት የተግባር መሸራረፍ የሌለበት፤ የውሃ ሀብቱን ለማስተዳደር ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል። ስለዚህ አዋሽን ለየት የሚያደርገው ከሀገራችን መንጭቶ ድንበር ሳይሻገር እዚሁ ሀገራችን የሚቀር ለእኛ ሊጠቅም የተዘጋጀ ተፋሰስ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ተፋሰስ በአካባቢው ባለበት ጫና እና የሕዝብ ብዛት በሁለቱ ከተማ መስተዳድር(አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ) ላይ ባለው ኢንዱስትሪ ብክነት ስላገጠመው በመጠንም፣ በጥራትም ለክፍተት ተጋልጧል። ይህን ክፍተት ለማስተካከል ከፍተኛ ፍላጎትን እና ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ይታወቃል።

እንደ ሀገር ከ65 በመቶ በላይ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙት በአዋሽ አካባቢዎች ነው። አዲስ አበባ እና የአዳማ መስተዳደሮች በዚህ በተፋሰሱ ክልል የሚገኙ ናቸው። ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣው ውሃ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያመጣ የሚታወቅ ነው። ለዚህ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ሳያስፈልግ የአቃቂን ወንዝ ማየት ብቻውን በቂ ነው። ስለዚህ በተፋሰሱ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦቻችን በውሃው ላይ ባለው ብክለት የቆዳ በሽታ እና ሌሎችም ችግሮች እንዳጋጠሟቸው ይታወቃል። እነዚህ ችግሮች ምንጫቸው ይህን የጋራ ሀብት የሚጠቀሙ አካላት በጋራ ሆነው ባለማቀዳቸው እና ባለመሥራታቸው የመጣ ነው።

ስለዚህ በጋራ አቅደው ዕቅዱን መተግበር የሚችሉበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ይህን ተከትሎ የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ ሀብቱ ፍትሃዊነትን በጠበቀ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለኢኮኖሚው እና ለማህበረሰቡ አስተዋጽኦ ባለው መልኩ፤ አቅዶ ተግባራዊ ለማድረግ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እየተንቀሳቀሰ ነበር።

ይሁን እንጂ በጋራ የተዘጋጀውን ዕቅድ ባለድርሻ አካላትም በራሳቸው ዕቅድ ውስጥ አስገብተውት፤ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል እና በጀት መድበውለት መንቀሳቀስ አልቻሉም። በመሆኑም በተበጣጠሰ መንገድ መሥራት በመጀመራቸው የተፈለገውን የተፋሰስ ዕቅድ መተግበር አልተቻለም። ስለዚህ የአሁኑ የተፋሰስ ዕቅድ ግን በጋራ ተዘጋጅቷል፤ ከማቀድ ጀምሮ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል። አጠቃላይ የሚስፈልገው ሀብትንም መለየት ተችሏል። ይሄን ለመምራት የሚያስችሉ ስልቶችም ተነድፈዋል። የትኩረት አካባቢዎችም ተቀምጠዋል።

የተበታተነ እና የተቆራረጠ ብቻ ሳይሆን ድግግሞሽን ባስወገደ መልኩ በጋራ ለመሥራት ውይይት እየተካሄደ ነው። ዕቅዱ በስድስት አካባቢዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን፤ ስለዚህ የሚተገበሩት እነዚህን መሠረት በማድረግ መሆን እንዳለባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል። አንደኛው ትኩረት በውሃ ምደባ ላይ ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ የተቀመጠ ነው። ያለንን የውሃ ሀብት መጠኑን እና ቦታውን ከለየን በኋላ ተጠቃሚዎችን በጥቅም በመለየት ክፍፍል ልናደርግበት የምንችል የውሃ ምደባ ሥርዓት ይኖራል።

ሌላኛው በውሃ ጥራት ላይ ያተኮረ ነው። በአዋሽ ዙሪያ በርካታ የከተማ መስተዳደሮች እና ኢንዱስትሪዎች ያሉበት በመሆኑ እንዲሁም በተፋሰሱ አካባቢ በጣም ብዙ ነዋሪ ስለሚኖር ለብክነት የተጋለጠ ነው። በተጨማሪ ለእርሻ አመቺ የሆነ መሬት በመኖሩ የውሃ ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀም ችግር ይፈጥራል። ስለዚህ በውሃ ጥናቱ ላይ ጥራት ሁለተኛው አቅጣጫ ተደርጎ ተለይቷል።

ውሃው የሚገኘው ከጊንጪ ተራሮች እስከ አፋምቦ ሲሆን፤ 1200 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። ውሃው ተጠቃሚ በቆፈረው ጉድጓድ ወይም ሰው ከሚያቆረው እና ከሚገድበው ግድብ ሳይሆን ውሃው የሚመጣው ተፋሰሱ ላይ በሚሠራው ሥራ ነው። ስለዚህ ሶስተኛው ቤዚን ፕላኑ ያስቀመጠው ሌላኛው ጉዳይ የተፋሰስ እንክብካቤ እና ልማት ሥራ ነው።

ይሄ ተፋሰስ ጥሩ ነገሮች እንዳሉት ሁሉ ለታችኛው የተፋሰስ አካባቢዎች በተለይ በአፋር ክልል የስጋት ምንጭ ነው። በተደጋጋሚ በበጋ ጊዜ የውሃ እጥረት ያጋጥማል። በክረምት ደግሞ ጎርፍ ሆኖ ሕብረተሰቡን ያፈናቅላል። ስለዚህ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ድርቅ ለመከላከል የጎርፍ እና የድርቅ አስተዳደር በሚል ተለይቷል።

ስድስተኛው የውሃውን መጠን በመለየት ለማከፋፈልም ሆነ ለመጠበቅ የተፋሰስ ሥራ ለመሥራት እንዲሁም ጎርፍ እና ድርቅን ለመከላከል የመረጃ ሥርዓትን ለማስተዳደር የመረጃ ሥርዓት ጉዳይ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አዋሽ ተፋሰስ በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ ሚናው ምን ያህል ነው?

ዶ/ር አብርሃ፡– አዋሽ ተፋሰስ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ልማት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው። አንደኛው በተፋሰሱ ውስጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ዕቅዶች ይተገበሩበታል። 200 ሺህ ሄክታር የሚለማ መሬት አለው። አራት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ያለው ሲሆን፤ ይህም በቂ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። የከርሰ ምድር ውሃ አቅሙ እንዳለ ሆኖ ይህ በመስኖ የግብርና ልማቱ ላይ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል። ከዛ ባሻገር አዋሽ ለቱሪስት መስዕብም በከፍተኛ መጠን ተደራሽ የሆነ አካባቢ ነው።

አንደኛው በቱሪስት መስዕብነቱ የሚታወቅበት ምክንያት አጠቃላይ በአዋሽ አካባቢ የሚኖሩትን ባህል እና ቅርሶች መጎብኘት ብቻ ሳይሆን የዳለሎ ዝቅተኛው ቦታ የሚገኘው አፋር ውስጥ አዋሽ ተፋሰስ አካባቢ ነው። በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ የሚገኙ ጂኦሎጂስቶች እና ከሥነ ምድር ጋር የተያያዙ ጥናቶችን የሚያካሂዱ ሰዎች መዳረሻቸው በዚሁ ተፋሰስ አቅራቢያ ነው። ከዛ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም መዳረሻነቱ ከፍተኛ መሆኑ ይገለፃል።

ሌላው አዋሽ አሁን ባለው ሁኔታ ጥቅም ላይ የሚውሉ የተለያዩ የኃይል ማመንጫዎችን ለመሥራት አቅም ያለው ነው። ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል የውሃ አቅም አለው። ከፍተኛ የሆነ የፀሐይ ኃይል ያለበት ነው። ከንፋስም ጋር ተያይዞ የአዳማ የንፋስ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ ሌሎችም ኃይል ማመንጫዎች በዚሁ ተፋሰስ ላይ የሚገኙ ናቸው። ስለዚህ ከኢነርጂ አንፃር ታዳሽ ኃይል የምንላቸው የፀሐይ የንፋስ የውሃ ኃይል ለማመንጨት ያግዛል። የቱሪስት መዳረሻ ነው። ለኢንዱስትሪዎችም ምቹ የሆነ ቦታ ነው።

ስለዚህ አዋሽ ለኢንዱስትሪውም ለቱሪዝምም ሆነ ለኢኮኖሚ ዘርፉ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ትልቁ ጉዳይ ውሃችን በኢትዮጵያ መንጭቶ እና እዚሁ የሚቀር መሆኑ ያለ ምንም የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት መጠቀም የምንችለው ሀብታችን ነው።

አዲስ ዘመን፡- አዋሽ ካለው ስፋት እና ከሚይዘው የውሃ መጠን አንፃር የሰጠው ጥቅም በቂ ነው?

ዶ/ር አብርሃ፡– 200 ሺህ ሄክታሩ መሬት ያለማል የሚባለው አሁን ባለን ቴክኖሎጂ ብቻ የታሰበ ነው። ግን ሌሎችም ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ቢቻል፤ ለምሳሌ የመሬት ስበትን ከመጠቀም ባሻገር ውሃውን ስቦ ለማውጣት የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎችን ብንጠቀም ከ300ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማልማት ይቻላል። በተጨማሪም በዓመት ሶስት ጊዜ ለማልማት ይቻላል። የሚለማውን ሁለት መቶውን ወደ 600 ማድረስ የሚቻልበት ዕድል አለ። ይህን ማድረግ ይቻላል ያልነው ያለከርሰ ምድር ውሃ እና በዚህ በተለመደው መስኖ ስንጠቀም ነው።

አዋሽን ለመጠቀም የመስኖ ሥርዓታችንን ማዘመን ከቻልን፤ የውሃ ሥርዓታችንን ቆጣቢ በሆነ መንገድ መጠቀም እንችላለን። የከርሰ ምድሩን እና የገፀ ምድሩን ውሃ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም ከቻልን ከዚህ በላይ የማልማት አቅም እንዳለው ታይቷል። ዞሮ ዞሮ ግን አሁንም የገፀ ምድሩን ውሃ በፍትሃዊ መልኩ በሚፈለገው መጠን እየለማ አይደለም። ምክንያቶቹ የተለያዩ ናቸው። ለምሳሌ ተንዳሆ አካባቢ ስልሳ ሺህ ሄክታር የሚያለማ ለስኳር ተብሎ የተገነባ አንድ ግድብ አለ። ይህ ግድብ ግን ከስኳር እና ከፋብሪካው ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች ስላሉበት ውጤታማ መሆን አልቻለም። አሁን መንግሥት ውጤታማ ለማድረግ ሥራ ጀምሯል።

በግድቡ አካባቢ የኮንትራት እርሻ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ነው። የአካባቢው ማህበረሰብን በማስተባበር ማልማት የሚቻልበትን ሁኔታም እየተቀየሰ ነው። በአጠቃላይ ስልሳ ሺህ ሄክታሩ በዚህ እንዲለማ ታስቧል። ከሰም ግድብ ላይም ሃያ ሺህ ሔክታር ይለማል ተብሎ እስከ አሁን አልለማም።

በግድቦች በድምሩ እየለማ ያለው ከ3ሺህ ሄክታር የሚበልጥ አይደለም። በዕቅድ ደረጃ ትልቅ አቅም ናቸው ተብለው የተቀመጡት በትክክል መሬት ላይ እያለሙ አይደለም። ይህን እንዴት እናልማ የሚለውን ለመመለስ፤ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴርንም ሆነ ግብርና ሚኒስቴርን እንዲሳተፉ ጥሪ የምናቀርበው ውሃ አስተዳደራችንን በአግባቡ ለማሻሻል እና እነዚህንም ግድቦች ለመጠቀም ነው። ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ለመጠገን እና መሠረታዊ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ቀይረን የጥቅማቸውንም ይዘትም ለስኳር ከነበረ እና ለስኳር ካልዋለ ለስንዴ እንዲውል ነው። ሰፊ የስንዴ ምርት አቅም አለ፤ አሁን ወደ እዛ በመቀየር አማራጮችን አብረን እያየን ነው።

ከዛ ባሻገር አሚባራ ላይ ድሮም ቢሆን እየለማ ነው። አሁንም ግን ሲታይ ብዙ ጊዜ በጋ ላይ የውሃ እጥረት ያጋጥማል። ስለዚህ መካከለኛው አዋሽ ላይ ያልተገደበውን ብንገድብ 19 ሺህ ሔክታር በተጨማሪነት ማልማት እንችላለን። ከዛም ባሻገር ሎጊያ ላይ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ውል ሰጥቶ የተጀመረ ግድብ አለ። እርሱ ግድብ ወደ ሥራ ሲገባ ተጨማሪ ውሃ ይይዛል። አምስት ሺህ ሄክታርን ማልማት ያስችላል፤ በዚህ ምክንያት የጎርፍ ችግርንም ይከላከላል የሚሉ ናቸው።

ከላይ አካባቢ ኢሉ፣ ቦራ፣ ሰበታ፣ ሃዋስ የምንላቸው ኦሮሚያ አካባቢ ያሉት በአብዛኛው የስንዴ እርሻን እያለሙ ናቸው። ነገር ግን በሙሉ አቅማቸው እየተጠቀምንባቸው ነው ማለት አይቻልም። በሙሉ አቅም እንዲጠቅሙ ለማድረግ የክልሉን መንግሥት ጋብዘን እየተነጋገርን ነው። ፈንታሌንም ማልማት እንጀምራለን። ከዛ ባሻገር አጠቃላይ አቃቂን ይዞ የምናያቸው ሰፊ የልማት ሥራዎች ለአዲስ አበባ የመጠጥ ውሃ ትልቅ አቅም ናቸው። የቆቃ የቃሊቲ ዌል ፊልድ የምንላቸው ድሬ እና ገፈርሳ ግድቦች የእዚሁ አካል ናቸው።

ስለዚህ አዋሽ ለአዲስ አበባ ከተማ፣ ለድሬዳዋም ሆነ ለአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ምንጭ ነው። ለእርሻዎች መነሻ የሆነ እነ መተሃራ የመንግሥት እርሻዎችም መሠረት ሲሆን፤ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ የአዋሽ ጥቅም ብዙ ነው። ነገር ግን እኛው ራሳችን በፈጠርናቸው ተቀናጅቶ ያለመሥራት ችግር ሳቢያ ብዙዎቹ ሳንጠቀምባቸው በዋዛ ያለፉ መሆናቸው ያሳያል። በርግጥ ያለፈው አልፏል። ነገር ግን በቁጭት ከሠራን ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- በርግጥ ከአዋሽ ብዙ መጠቀም ይቻላል። በሌላ በኩል ግን የአዋሽ አካባቢ ነዋሪዎች ተጎጂ የሚሆኑበት አጋጣሚ መኖሩን በተደጋጋሚ ታይቷል። ለምሳሌ በድርቅ እና በጎርፍ ይጠቃሉ። እነዚህ ጉዳቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ የመከላከል ሥራን በማከናወን በኩል ምን እየተሠራ ነው?

ዶ/ር አብርሃ፡- በርግጥ አዋሽ በተለይ አፋር አካባቢ የሚታወቅው በሚያስከትለው የጎርፍ ጉዳት ነው። በየዓመቱ የጎርፍ አደጋ ይደርሳል። በመሠረቱ ጎርፍ አደጋ ሳይሆን ሀብት ነው። ነገር ግን በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻላችን አደጋ ሆኗል። ነገር ግን ችግሩን ለማቃለል የተቀናጀ የጎርፍ አስተዳደር ፕሮጀክት ከዓለም ባንክ ጋራ አሁን ተፈራርመናል። እስከ አሁን ግን የአዋሽ ጎርፍ መንስኤ ወንዙ ሞልቶ ውሃው ከወንዝ በላይ ወጥቶ ሳይሆን፤ ተፋሰሱ ላይ ሥራዎች ባለመሰራታቸው ነው። በወንዙ ውስጥ ደለል በመሙላቱ ወንዙ መያዝ የሚችለውን ውሃ መያዝ አልቻለም። በተሞላው ደለል ምክንያት ከባንኩ ወጥቶ ማህበረሰቡን የሚያጥለቀልቅ መሆኑ አንዱ ችግር ነው።

ሁለተኛው የአዋሽ ወንዝ እንደሚታወቀው መሬቱ ጠንካራ አይደለም። ስለዚህ በቀላሉ ውሃው ይወጣል። አካባቢው ላይ ያለው አርብቶ እና አርሶ አደር ሕይወቱ ከውሃው ጋር የተቆራኘ ነው። በትንሽ ብልሽት ውሃው ሰብሮ የመውጣት ሁኔታ ያጋጥማል። ሌላው አዋሽ በባህሪው ሲታይ የሚሄደው እጅግ ጠመዝማዛ በሆነ መስመር ነው። ስለዚህ በቀላሉ ወጥቶ አደጋ ለማድረስ ቅርብ ነው። ይህ ችግር እንዳይከሰት ከዓለም ባንክ ጋር ባለን ፕሮጀክት የአዋሽን ጎርፍ ወደ ጥቅም ለመለወጥ ጥናት ተካሂዷል።

ጥናቱ ከአማራ ክልል ከቦርከና የሚወጣውን ደለል ያስቀራል። በተመሳሳይ ጎርፉንም ይይዛል። ከዛ ባሻገር መካከለኛው አዋሽ ላይ ግድብ እንስራ የምንለውም እዚህ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል ነው። አንደኛ በበጋ ከላይ የሚመጣውን ከአምቦ ከጊንጪ ተራሮች የሚመጣውን በሙሉ ውሃ መካከለኛው አዋሽ ላይ በማስቀረት በክረምት ወቅት የታችኛውን ተፋሰስ እንዳይጎዳ ነው። በበጋ ጊዜ ደግሞ እጥረት እንዳያጋጥም ያገለግላል ብለን ሁለቱንም ግድቦች በዚህ መሠረት ማስተካከያ ለማድረግ ጥናቱ አልቋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ታችኛው አዋሽ ላይ አሚባራ ላይ ትልቅ የጎርፍ አደጋዎች አሉ። እነርሱንም የመከላከያ ባንክ ለመሥራት ማስተካከያ ለማድረግ ጥናት ተጠንቷል።

አዲስ ዘመን፡- ጥናቶች ይጠናሉ፤ በአዋሽም ሆነ በሌሎች ተፋሰሶች ዙሪያ ውይይቶች ይካሔዳሉ። ነገር ግን በተግባር የሚገኙት ለውጦች ውስን ናቸው። ጥናቶችን በመተግበር ዙሪያ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምን ያህል ይሠራል?

ዶ/ር አብርሃ፡- በርግጥ ተደጋጋሚ ጥናቶች እና ውይይቶች ይካሔዳሉ። ውይይቶቹ ከባለድርሻ አካላት እና ከሕዝብ ጋር የሚካሄዱ ሲሆኑ፤ እስከ አሁን በተሠሩት ሥራዎች ግንዛቤ መፍጠር የተቻለ ቢሆንም፤ በቂ ጥናቶችን መሬት በማውረድ በአጠቃላይ ወደ ተግባር በመግባት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማምጣት አልተቻለም። የውሃ ሀብት አስተዳደሩ መሬት ላይ ወርዶ ፍትሃዊ የሆነ ተጠቃሚነት የሚኖረው እና ዘላቂነት የሚያገኘው የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሲኖር ነው። ይህን ለማድረግ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አድርገን በሚኒስትሩ ውስጥ አንድ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተቀምጧል። በተጨማሪ በተናጥል ደግሞ ብሔራዊ ፕሮግራም ተብሎ አጋሮቻችን እና ሌሎች የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች የክልል መስተዳድሮች ያሉበት በጋራ የሚወያያ መድረክ (ፕላት ፎርም) ተፈጥሯል።

በፊት የነበረው ግንዛቤ እኛ ጥናት አጥንተን ከባለድርሻ ጋር ስንወያይ፤ ከዛ ላይ የሚቀመጡ ገንዘቦች እና የሚከናወኑ ሥራዎች የሚኒስትሩ ሥራ እንደሆኑ የመገንዘብ ዝንባሌ ነበር። ዋናው ጉዳይ ዕቅዱን እንጂ ሥራውን የምንሠራው ተፋሰሱን ስለምናስተዳድር እኛ ብቻ ሳንሆን፤ ከሌሎችም ጋራ የሚሰራ ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተወሰኑ ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን፤ ሌሎችም ሚኒስትሮች እዛው ተፋሰስ ውስጥ የራሳቸውን ሥራ ሲያቅዱ የጋራ ፕላኑን በማካተት እንዲሠሩ ለማድረግ ነው። ይሄ አንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ይሠራል እንጂ ሥሩ ብሎ ማዘዝ ስለማይችል የተፋሰሶች ምክር ቤት ተቋቁሟል።

ይህ የተፋሰስ ምክር ቤት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን፣ ሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን፣ የሁሉም ክልል ፕሬዚዳንቶች ያሉበት የምክክር ተፋሰስ ምክር ቤት በፌዴራል ደረጃ አለ። በክልል ደረጃ ደግሞ ሌሎች ዘርፎቻቸውን ይዘው የሚመሩበት ሁኔታ አለ። ይህ ሲደረግ የክልል ፕሬዚዳንቶች በዕቅዳቸው ውስጥ እንዲያካትቱ ለማድረግ ነው። ከዛም ከተመለሱ በኋላ በክልላቸው ካቢኔ ላይ እያንዳንዱ ዘርፍ የሚይዘው ዕቅድ እንዲያቅዱ እና ዕቅዳቸው መሬት እንዲወርድ ሥራ ይሰራል ማለት ነው።

ይህን ወደ መሬት ለማውረድ ሰሞኑን ከክልል የመጡ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመፈራረም የፊርማ ሰነዱን እና አጠቃላይ የተሰሩትን ጥናቶች በመያዝ ወደሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛው ምክር ቤት በመሄድ ከጠቅላይ ሚኒስትር እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር በመሆን እነርሱ በሚመሩት መንገድ ለማቅረብ እየሠራን ነው። ይህንን ያደረግነው ሥራውን ወደ መሬት ለማውረድ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖር አለበት ብለን ነው። ይሄ በሌለበት ወደ ትግበራ መግባት አይቻልም።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።

ዶ/ር አብርሃ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You