እርግማን

እኚህ ጋሽ ተፈሪ የተረገሙ ሠው ናቸው። ሠይጣን ይሁን እግዜር ማን እንደረገማቸው እንጃ ብቻ የሚያጋጥማቸው ሁሉ ከሠው እርግማን በላይ ነው። ደግሞ ጋሽ ተፈሪ ያልታደሉ፣ የተረገሙ፣ እድለ ጠማማ መሆናቸውን ማንም ሳይሆን እርሳቸው ራሳቸው ናቸው የሚመሰክሩት።

ገድላቸው ሲተረክ ገና በልጅነታቸው ወፍ አዳኝ ነበሩ። እንደ እርኩስ መንፈስ በጠራራ ፀሀይ ሳይቀር በየጉራንጉሩ እየዞሩ ወፍ አድነው ይገድላሉ። የእናታቸው ሙቀጫ ውስጥ ያጠራቅሟቸዋል።

ለምን?

እንዲያው ብቻ ለገዛ ክፋታቸው።

ከፍ ሲሉ የሰው ሚስት እያማገጡ ስንት ጊዜ ተደብድበው አፈር ልሰው ተነስተዋል። ኋላም በስተርጅና የሀገር ሽማግሌ ሆነው ፍርድ ሲያዛቡ ኖሩ።

እጃቸው የሚንቀጠቀጠው እንኳን ድመት ገድለው ነው አሉ። ብቻ እኚህ ጋሽ ተፈሪ የተረገሙ ሰው ናቸው። ልጆች ከተባሉ ግን አራት ልጆች ወልደዋል። ታዲያ አራቱም ከተለያዩ ሴቶች የተወለዱ እንጂ ከአንድ እናት ማህፀን የወጡ ወንድምና እህት አይደሉም።

ምነው ቢሏቸው …

‹‹እኔ ወትሮም ዕድሌ ጠማማ ነው። ባይሆን ከልጆቼ መሃል አንዳቸው የተባረከች እናት ብታጋጥማቸው ብዬ›› አሉ። ግን እርሳቸው እንዳሰቡት ወይም እንደሰጡት ምክንያት ሳይሆን ቀርቶ የመጀመሪያው ልጃቸው ባቡር ደፍጥጦት ሞተ። ሰርቆ ለማምለጥ ሲሞክር ነው አሉ የፉርጎ ሲሳይ ሆኖ የቀረው።

ሁለተኛዋ አርግዛ ብትወልድ ግማሽ ሰው ግማሽ አውሬ። ሲጠናባት ልጇን ገድላ ሞተች። ሦተኛው ልጃቸው አሁንም ጢም አቀምቅሞ መደብ ላይ የሚሸና መፃጉዕ ነው።

ከእነዚህ ሁሉ ልጆች መሃል መቼም ሴቷ አበባ ትሻላለች። በአስራ ስድስት አመቷ ድፍን መንደሩ ወይዘሮ ብሎ ያከበራት ሴተኛ አዳሪ ናት። ‹‹እስቲ ተውኝ… ወንዱ ሁሉ ሀሞቱን ጅብ በልቶበት እንኳን ለገላ ሽጦ አዳሪ ለሚስትም የከፋ ዘመን ሆኗል›› ትላለች አንዳንድ ቀን ገበያው ጭር ሲልባት።

ለነገሩ መቼ ሞልቶላት ያውቃል ሁልጊዜ የሚመርጠው ያጣ አርፋጅ ነው ይዟት የሚሄደው። አንዳንዱም ለነፍስ ትሆነኝ ብሎ። ባስ ካለም ዕብድ እና ወፈፌ ያነጋባታል። እንግዲያስ የውበቷ ነገር ከተነሳ እከክ ሰጥቶ ጥፍር የማይነሳው ጌታ ውበቷን ከአፍሮዳይትም፣ ከክሊዮፓትራም ጥቂት ጥቂት ቀናንሶ የአረብ ልዕልት አስመስሏት ነበር። ይህ እግዜር የሚሉት የዓለሙ ሰሪ ተንኮለኛ ነው። አሳይቶ ሲነሳት አንድ እግሯን እንደ አርባ ቀን ዕድሏ ሰባራ አደረገው። እናቷ እሷን እርጉዝ ሆነው ጋሽ ተፈሪ ሆዷ ላይ በከስክስ ረግጠዋት ነበር አሉ። እሳቸው ሳይሆኑ አይቀሩም እግሯን ሰንክለው ያሳጠሩባት።

ጋሽ ተፈሪ አሁን እንግዲህ ስድሳ አምስት ዓመት አልፏቸው በሦሶት እግር መጓዝ ጀምረዋል። ጥርሳቸው ቆሎም አይቆረጥም፣ ወግ ይደጋግማሉ፣ ጆሯቸው ቃል ያባክናል። ታዲያ የአባቷን የሽምግልና አይቻል አመል ችላ የምትጦራቸው አበባ ናት። ብቻ አንድ ማታ ቀይ የበግ ወጥ ራት ቀርቦ ሲበላ … ‹‹እንዲያው ለመሆኑ ስራሽ ምንድን ነው ልጄ?›› ብለው ጠየቋት ጥርሳቸው የቅልጥም ስጋ አልነጭ ብሎት እየታገሉ። ስጋ መረቅ ናፍቋቸው ነበር።

‹‹ስጋ … ስጋ ነው የምሸጠው አባዬ›› አለቻቸው። ‹‹ዋጋው ደህና ነው ስጋ?›› አሏት። ‹‹ምንም አይልም አንተን ውድ አባቴን እጦርበታለሁ›› አለቻቸው ቶሎ ለመውጣት እየተጣደፈች። ‹‹ታዲያ ስጋ ሌትን ይሸጣል ወይ ዘንድሮ? ሠው ሲበላ ነው የሚያድረው እንቅልፍም የለው?›› አንድ ጊዜ ከቅልጥሙ ደህና አድርገው ነጩ – ስጋ። ‹‹ሲበላ ነው የሚያድር አባዬ እንቅልፍም የለው ወንዱ። ››

‹‹እሰዬ… ደግሞ ወንዱ ብቻ ነው የሚበላው?››

‹‹ታዲያ ወንዱ ነው እንጂ ሴቱማ ሲመሽ ከቤቱም አይወጣ›› አለቻቸው። ‹‹እንደ አራዊት በሌት?››

‹‹እንደ አራዊት በሌት። ››

ተነስታ እጇን ታጠበች።

‹‹በይ ለበሽተኛው ለወንድምሽ መድሃኒቱን ግዥለት። እኔን መረቅ ያበላሽኝ እግዚአብሄር ንግድሽን ይባርክልሽ የኔ ልጅ!››

አበባ አሜንም ሳትል ተጣድፋ ወጣች።

ያን ቀን አለወትሮው መንደሩ ጭር ብሏል። በቀያይ የበረንዳ መብራት ነዶ የተገጠገጠውን ቀጭን የኮብል ስቶን መንገድ አልፋ ቀንጠስ እያለች ወደ ላይ ወጣች። አልፎ አልፎ ብቻ ለወትሮው የምታውቃቸው ሴተኛ አዳሪዎች ቆም ቆም ብለው ደንበኛ ይጠባበቃሉ። የጎዳና ውሾችም ለጥበቃ የተሠማሩ ይመስል በየጥጋጥጉ ተሸጉጠው አድፍጠዋል። ‹‹ምን ጉድ ፈላ›› እያለች በልቧ ወደ መቆሚያ ቀጣናዋ ስትሄድ አንድ ቦታ ላይ በርከት ያሉ የሷ ቢጤዎች አንድ ጉድ ከበው ይዋከባሉ። ጠጋ ስትል የተሰማን ላዳ አየቻት። ተሰማ ተገልብጦ ይሆን እንዴ እያለች ወደተሰበሰበው ሠው ብትጠጋ ላዳዋ ጭረትም የላት። ተሰማ ብቻ መሪዋን በክብር እንደጨበጠ በቁመቱ የአባቷን የጋሽ ተፈሪን ከዘራ የሚያክል ፌሮ ልቡ ላይ ተቀብቅቦበት ከነ ግርማ ሞገሱ ተሰውቷል። በአፍና በአፍንጫው የወጣው የደም ወጥ ጢሙን አረስርሶት መረቁ ነጭ ሸሚዙ ላይ ረግቷል። አበባ ልክ እንዳየችው ራሷን ያዘች። ተሠማ ከደንበኞቿ ሁሉ ወረት የማያውቅ ታማኝ፣ አንድ እግሯ ቢያጥርም ለዚያ ታጥቦ ለሚጠጣ ውበቷ ከፍተኛውን የገንዘብ መስዋዕት የሚገብርላት ውድ አስተዳዳሪዋ ነበር። አበባ ድርጅቷ የታሸገባት፣ ፋብሪካዋ በጥሬ እቃ ማጣት ምክንያት የተዘጋባት መሰለች። በዚያ የተሰበሰበው የእሷ ቢጤ ሴተኛ አዳሪ በሙሉ አይኑ እሷ ላይ አተኮረ። አንዳንዱ በኀዘኔታ፣ አንዳንዱ በምቀኝነት ደስታ። አበባ ግን ቅስሟ እንደ ጎመን ተቀንጥሷል። ዛሬ አዳር ቀጠሮዋ ከእሱ ጋር ነበር። ያን ገመምተኛ ወንድሟን ሀኪም ያዘዘለትን መድሃኒቱን እንደምትገዛለት ቃል የገባችለትን እያሰበች ቤቷ ስትገባ ጋሽ ተፈሪ ከእንቅልፋቸው ነቅተው ከእራት የተረፋቸውን ስጋ መረቅ ሲወጥቁ አገኘቻቸው።

‹‹ምነው ልጄ ተመለስሽ?›› አሏት ልክ እንደገባች።

‹‹ስጋዬን የምመትርበት ካራዬ ጠፋ አባዬ›› ብላቸው ገብታ ተኛች።

በማግስቱ ዕኩለ ቀን ገደማ ያ ገመምተኛ ወንድሟ መድሃኒቱ አልቆበት መደብ ላይ ድርቅ ብሎ ተገኘ አሉ። ወትሮም እኚህ ጋሽ ተፈሪ የተረገሙ ሠው ናቸው፣ የእሳቸው እርግማን ልጆቻቸውን ጨረሳቸው።

እዩኤል ወርቁ

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You