በማደግ ላይ ለሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የቴክኖሎጂ ፋይዳው ከምንም በላይ ትልቅ መሆኑ አያከራክርም። ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን ከግምት በማስገባት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ነክ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች። ሀገሪቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር የተለያዩ ዘርፎችን ለማዘመን ማለትም፣ ለትምህርት ለግብርና ለጤና ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥታለች።
የእዚሁ አካል የሆነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ከመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል። ለሦስት ሳምንት በዘለቀው ዓውደ ርዕይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ‹‹ስታርት አፖች›› ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።
ወጣት ቴዎድሮስ እስጢፋኖስ በዚህ አውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ነው። ወለጋ ተወልዶ አዲስ አበባ ከተማ ያደገው ቴዎድሮስ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትሏል። በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸር ምህንድስና በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
በተማረበት የሙያ መስክ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ የቆየው ቴዎድሮስ፤ ከዚህ ሥራው ጎን ለጎን ዲጂታል መተግበሪያዎች ሠርቷል። ቀጥሎ (ራይድ አዲስ) የሚል የመኪና ማሻሻጫ መተግበሪያ እንዲሁም በተለይ ትኩረቱን ፋሽን ላይ ያደረገ (ሎሚነት) የሚል ስያሜ የተሰጠው ዌብሳይት እና የሞባይል መተግበሪያ በመስራት አገልግሎት ላይ መዋል ችሏል።
ከልጅነቱ ጀምሮ ቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች ቀልቡን ይገዙት እንደነበር የሚናገረው ቴዎድሮስ፤ የአርክቴክቸር ምሩቅ ሆኖ መካኒካል ወደሆነው ማሽን ወደ ማምራት የገባበትን አጋጣሚ ሲናገር በአንድ ጓደኛው ምክንያት እንደሆነ ያስረዳል። “ ጓደኛዬ የሻማ ማሽን ነበረው። ይህንን ማሽን መሸጥ ፈልጎ አልሸጥ ብሎት ሲያማክረኝ እኔ ጋር የመኪና ማሻሻጫ ቴክኖሎጂ አለ። ማሽኑን በዚህ አማራጭ ለመሸጥ እሞክራለሁ ብዬ በመተግበሪያው አማካኝ ማስታወቂያ አወጣን። በሁለት በሶስት ቀን ተሸጠ። ይህ አጋጣሚ ወደ ማሽን ምርት እንድገባ ምክንያት ሆነኝ” ይላል።
ወጣት ቴዎድሮስ ከጓደኛው ጋር በመሆን በአምስት ሺህ ብር ካፒታል ተጨማሪ ማሽን በማምረት ይህ በቀላሉ ገዥ ሲያገኝ የምርት ፍላጐት መኖሩን በመረጋገጥ (ኢትዮጵ ማሽነሪ) የተሰኘ የማሽን አምራች ኩባንያ በማቋቋም ሙሉ በሙሉ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ማሽኖችን ወደ ማምረት እንደገባ ይናገራል።
‹‹ ዲጂታል ማርኬቲንግን በተመለከተ ግንዛቤ ነበረኝ” የሚለው ቴዎድሮስ፤ ዲጂታል በሆነ መንገድ የሻማ ማሽኑን የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት በመስራት ውጤታማ ግብይት ማከናወን ከቻለ በኋላ ምርቱን በስፋት በማምረት እንደቀጠለ ይናገራል። የሻማ ማሽን ማምረት ላይ እንዳለ የሽንኩርት መፍጫ ማሽን እንዲሰራ ከደንበኞች በመጣ ጥያቄ የተለያዩ ጥናቶችን በመስራት ማለትም ገበያ ላይ ያሉ ማሽኖች ምን አይነት ናቸው? በምን መልኩ ይሰራሉ? የሚሉትን በመለየት ወደ ሥራ በመግባትና ውጤታማ ሥራ በመሥራት የማሽን ማምረት ሂደቱ ሁለተኛ ምዕራፍ እንደቀጠለ ይናገራል።
ከዚህ በመቀጠል ‹‹የአረቄ ማሽን ለምን አትሰሩልንም?” የሚል ጥያቄ ቀጠለ የሚለው ወጣት ቴዎድሮስ፤ የምርት ፍላጎት ጥያቄው የመጣው ከአርሲ አካባቢ መሆኑን ይናገራል። አካባቢው የተለያዩ ደረጃዎች ባሉት የአረቄ ምርት በስፋት የሚታወቅ በመሆኑ፤ ሁለት የአረቄ ማሽን ወደዚያ አካበቢ ከሄደ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የደንበኛ ጥያቄ መጣ። ማሽን የማምረት ሥራው በወረፋ የሚሰራ ሆኖ እንደቀጠለ ይገልጻል።
ራዕያቸው ትልቅ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ቴዎድሮስ፤ ‹‹የመጀመሪያውን የሻማ ማሽን ስንሰራ የድርጅቱን ስያሜ ኢትዮጵ የሻማ ማሽን ማምረቻ
አይደለም (ኢትዮጵ ማሽነሪ) ነበር። የእዚህ ምክንያት ደግሞ ወደፊት የተለያየ ምርት መስጠት የሚችሉ ማሽኖችን ማምረት እንጂ በአንድ ነገር ላይ የተገደበ ዓላማ የለንም። ” ይላል።
ወደ ማሽን ማምረት ሲገቡ በሴክተሩ ውስጥ ያለው ችግር ምንድን ነው? ለምሳሌ አንድ ሰው የሳሙና ማሽን ለመስራት ሲያስብ የሚያስቸግረው ነገር ምንድን ነው? ገበያው ላይ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚሉትን በጥናት መለየት መቻላቸውን ይናገራል። ወጣት ቴዎድሮስ፤ በዚህም አብዛኛው ሰው ማሽን ከውጭ ሀገር በውጭ ምንዛሬ እንደሚያስመጣ፤ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ደግሞ ረዥም ጊዜ እንደሚወስድበት እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላም ማሽኑን ለማንቀሳቀስ እንደሚቸገር ማወቃቸውን ያመለክታል።
‹‹አንዳንድ ጊዜ በጣም ቀላል በሆነ ብልሽት ምክንያት መጠገን በቀላሉ ስለማይቻል ማሽን ተበላሽቶ ሰዎች ከገበያ የሚወጡበት አጋጣሚ አለ። ይህ ትልቅ ክፍተት በመሆኑ ሰው ወደ ዘርፉ ለመግባት ይቸገራል። ›› ካለ በኋላ፤ እነዚህን ክፍተቶች ለመቅረፍ ወደ ሥራ በመግባት ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ይናገራል።
ወጣት ቴዎድሮስ፤ አንድ ሰው ወደ ኢትዮጵ ማሽነሪ መጥቶ ማሽን ሲያዝ ከውጭ ሀገር ገዝቶ ከሚያገኘው አገልግሎት በተሻለ አገልግሎቱን የሚያገኘው ማሽኑን እንዴት ማንቀሳቀስና ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለበት ሙሉ ስልጠና ይወስዳል። ከዚህ በተጨማሪ የአንድ አመት ዋስትና ስለሚኖረው ማሽኑ ከዛሬ ነገ ተበላሽቶ ከገበያ እወጣለሁ የሚል ስጋት ሳያድርበት ሥራውን በተረጋጋ ሁኔታ መሥራት እንደሚችል ይናገራል።
ሌላው ማሽን አምርቶ ከመሸጥ በተጨማሪ ለምሳሌ አንድ ሰው የአጃክስ ሳሙና ማምረቻ ማሽን ሲገዛ ሳሙናውን ለማምረት ምን ምን አይነት ኬሚካል ያስፈልጋል? አዋጭ የሚሆነው በምን መልኩ መሥራት ሲቻል ነው? ኬሚካሎችን ከማንና ከየት ማግኘት ይቻላል? የሚለውን የግንዛቤ ስልጠና እንደሚሰጡ የሚናገረው ወጣት ቴዎድሮስ፤ ስለዚህ አንድ ግለሰብ ከውጭ አስመጥቶ ወይም ወደ ሌላ ኩባንያ ሄዶ ከሚያገኘው አገልግሎት በተለየ መልኩ ውጤታማ የሚያደርገውን ነገር በማወቅ ወደ ገበያው ስለሚገባ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ሆኖ እንደሚወጣ ይናገራል።
በገበያው ውስጥ ካሉ ተመሳሳይ ምርቶች የኢትዮጵ ማሽነሪ ምርቶችን ልዩ የሚያደርጋቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ። ከእዚህ ውስጥ አንዱ ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆኑ ነው የሚለው ቴዎድሮስ፤ ‹‹ገበያው መረጋጋት የጀመረው እኛ ወደዚህ ሥራ ስንገባ ነው። የሻማ ማሽን እኛ 25 ሺህ ብር እየሸጥን ተመሳሳይ ምርት ከውጭ ሲገባ ብቻ አርባና ሃምሳ ሺህ ብር ይሸጥ ነበር። ይህ አግባብ ስላልሆነ ዋጋው ተመጣጣኝ እንዲሆን በተሰራው ሥራ ከመጣን በላይ ትርፍ ማጋበስ ቀርቶ አማካይ በሆነ ዋጋ ገበያው እንዲረጋጋ ጥረት አድርገናል” ይላል።
በአምስት ሺህ ብር ካፒታል የተጀመረው (ኢትዮጵ ማሽነሪ) አሁን ጠቅላላ ሀብቱ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ የሚናገረው ወጣት ቴዎድሮስ፤ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ውጭ በቋሚነት 7 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንዳገኙ ያስረዳል። ከዚህ በላይ የሚያስደስተው ግን እስከ አሁን በኢትዮጵ ማሽነሪ አማካኝነት ከዘጠኝ በላይ የሳሙና ማሽን ጨምሮ ሌሎች ማሽኖችን መሸጥ ተችሏል። አንድ ማሽን ለማንቀሳቀስ ደግሞ ከአምስት እስከ አስር ሰው ያስፈልጋል። ስለዚህ ሰዎች ማሽን ገዝተው ሲሄዱ ቢያንስ ለአስር ሰው የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፤ ስለዚህ የሥራ ዕድል ፈጠራው አዲስ ማሽን በተመረተ ቁጥር እየሰፋ የሚሄድ እንደሆነ ይናገራል።
እንደ ሀገር ማኑፋክቸሪንግን ለማበረታታት ትላልቅ ኢንዱስሪዎች ላይ ብቻ ትኩረት ከተደረገ ወደ መሬት የሚደርስ ለውጥ ማምጣት አዳጋች ነው የሚለው ቴዎድሮስ፤ ዛሬ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ የዓለማችን ሀገራት ታይላንድ፣ ህንድ፣ ቻይና እና የላቲን አሜሪካ አብዛኞቹ ሀገራት በማሽነሪ ምርት ከፍተኛ እምርታ ያሳዩት በእዚህ ዘርፍ ላይ በተወሰደ የፖሊሲ ለውጥ ማለትም በቀላሉ ሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ እቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ አንዱ የፖሊሲ ማሻሻያ ነው ይላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጆክና ማስታጠቢያ የፀጉር ማበጠሪያ ሳይቀር ከውጭ እንደሚገባ የሚናገረው ወጣት ቴዎድሮስ፤ ይህ አካሄድ አሳዛኝና መቅረት ያለበት ነው። መንግሥት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ነገር ግን በቀላሉ በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ይናገራል።
እንደወጣት ቴዎድሮስ ገለፃ፤ የፖሊሲ ማሻሻያው ከንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ፣ የብድር አቅርቦትን ጨምሮ መካሄድ አለበት። ለአብነት የማሽን ሊዝ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ለማሽን አምራች ኢንዱስትሪ ቅድሚያ መስጠት ከተቻለ ዘርፉን ማሳደግ ይቻላል፤ አዲስ እየተነሳ ያለ ሴክተር እንደመሆኑ ከቀረጥ ጋር ባሉ ጉዳዮች እንዲሁ ጀማሪ የማሽነሪ አምራች ድርጅቶች ማበረታታት ቢቻል፤ ልማት ባንክ ቅድሚያ ሰጥቶ የብድር አቅርቦት ከሚያቀርብላቸው ዘርፎች አንዱ ቢሆን የማሽነሪ ኢንዱስትሪውም ሊበረታታ እንደሚችል ይናገራል።
ማሽን አምራች ኢንዱስትሪው ለብቻው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባው ዘርፍ ነው የሚለው ወጣት ቴዎድሮስ፤ ይህ ከሆነ የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል አቅም መገንባት ይቻላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እንዳለበት ሀገር ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል።
(ኢትዮጵ ማሽነሪ) እንደ ዓላማ ይዞ የተነሳው ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን በሀገር ውስጥ ማምረት ነው የሚለው ቴዎድሮስ፤ አንድ ሀገር ትልቅ ወጪ የምታወጣው አንደኛ ማምረቻ ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ስታስገባ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የተመረቱ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ስታደርግ ነው። ስለዚህ ማሽነሪ መምጣቱን በማስቀረት እዚሁ ማምረት መቻል ለሁለቱም የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ያስችላል ይላል።
ሌላው ከኢትዮጵያ እስቴ ሳይጨመርባቸው በጥሬ እቃነት የሚወጡ ምርቶች አሉ፤ ለአብነት ቡና አሁንም በጥሬው ለውጭ ገበያ ይቀርባል። ይህ አካሄድ ቀርቶ ማጠቢያ፣ መውቅያ፣ መፍጪያ ማሽን ደረጃውን ጠብቆ መስራት ከተቻለ ከዋጋ አንፃር ቀድሞ ከነበረው ሁኔታ በተለየ መልኩ እንደሀገር ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስችል ይናገራል።
ወጣት ቴዎድሮስ እንደሚናገረው፤ ‹‹የተለያዩ ጥናቶችን በመስራት ባገኘነው ግኝት እንደ ሀገር ትልቅ ችግር ያለው በምርት አሰባሰብ ሂደት ላይ ነው። በኢትዮጵያ ከማሳ እስከ ገበታ ባለው ሂደት ሁሉም ነገር የሚከናወነው በባህላዊ መንገድ ነው። በዚህ ምክንያት ከጠቅላላ ምርቱ እስከ አርባ በመቶ የሚሆነው ይባክናል፤ ይህንን ሁሉ አካሄድ ዘመናዊ አሰራር በመከተል ከተሰራ መቅረፍ ይቻላል። ስለዚህ ዘርፉን መንግሥት በሙሉ አቅሙ መደገፍ እንዳለበት ይገልጻል።
ወጣት ቴዎድሮስ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበረው ቆይታ የራሱና የድርጅቱ የወደፊት እቅድ ምን እንደሆነ ሲናገር፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ የማሽን አቅራቢ ኩባንያ መሆንና በረዥም ጊዜ ሂደት ደግሞ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ትልቋ ማሽን አቅርቢ ሀገር ማድረግ እንደሆነ ተናግሯል። ‹‹ይህንን ዓላማ ለማሳካት ያሰብነው እኛ በግል በምንሰራው ሥራ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር በዘርፉ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር በሚሰራ ሥራ ነው። ወጣቶችን በማሰልጠን የልምድ ልውውጥ በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ወደዚህ ዘርፍ በማምጣት የሚሳካ እቅድ አለን። ” ይላል።
በመጨረሻም ቴዎድሮስ ለወጣቶች ባስተላለፈው መልዕክት ችግሮች ሁልጊዜ መኖራቸው የማይቀር ነው። ችግሮች ሲያጋጥሙ መሥራት አይቻልም ብሎ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ፤ ወጣቱ ‹‹ራዕዬን ማሳካት እችላለሁ›› ብሎ በመነሳት፤ በቁርጠኝነት በመውሰድ መንቀሳቀስ አለበት። በሁለተኛ ደረጃ በየጊዜው እራሱን በማሻሸል ነገ ለሚጠብቀው ውድድር ዝግጁ መሆን እንዳለበት ተናግሯል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም