የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት በሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ስር በተዋቀሩ ፌዴሬሽኖች አማካኝነት ከብሄራዊው ፌዴሬሽን በሚወጡት ሕግና ደንቦች ላይ ተመስርቶ ይመራል:: ክልላዊ ፌዴሬሽኖች ደግሞ የሀገሪቱን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራትን በየፊናቸው ያከናውናሉ:: በቅርብ ጊዜ ከተቋቋሙትና ጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኙት ክልላዊ የእግር ከኳስ ፌዴሬሽኖች መካከል የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይጠቀሳል:: ክልሉ በበኩሉ ያለውን እምቅ የእግር ኳስ አቅም አሟጦ ለመጠቀም በጥረት ላይ ይገኛል::
በሲዳማ ክልል በተለይም ሃዋሳ ከተማና አካባቢዋ ከፍተኛ የእግር ኳስ እምቅ ተሰጥኦዎች የሚገኙበትና በርካታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን መወክል የቻሉ ተጫዋቾች የወጡበት ነው:: ከተመሠረተ አራት ዓመት ያስቆጠረው ፌዴሬሽኑ የክልሉን እግር ኳስ ለማሳደግ በዞኖችና በወረዳዎች እንደየደረጃው አስተዳደሮችን በማዋቀር የተሻለ እንቅስቃሴን በማድረግ ላይ ነው:: ፌዴሬሽኑ በቅርብ ጊዜ የተመሠረተ ቢሆንም ባሳየው የላቀ የሥራ አፈጻጸም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሁሉም ፌዴሬሽኖች ቀዳሚ ነው:: የተለያዩ የውስጥ ውድድሮችን ማካሄድ እና ሀገራዊ ውድድሮችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድም ትልቅ ሚናን በመወጣት ላይ ይገኛል::
በክልሉ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሶስት የታዳጊ እግር ኳስ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በቂ የሚባል ባለመሆኑ ቁጥሩን ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው:: ይህም ከፍተኛ ፋይናንስን የሚጠይቅ በመሆኑ ለዛ እንዲረዳ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል::
በክልሉ የሚገኙትን ሁለት በፕሪምየር ሊግ በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙትን ክለቦች (ሃዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለቦችን) ከማጠናከርና ከማገዝ ባለፈ ተጨማሪ ክልሉን የሚወክሉ ክለቦችን ለመፍጠር ሂደቶችን ጀምሯል::
የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ተፈራ፣ ፌዴሬሽኑ አማተር ባለሙያዎችን በመያዝ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ያስረዳሉ:: ፕሮጀክቶችንም ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ ነው:: የሚያስፈልጉትን የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል፣ የመሣሪያ እንዲሁም ሜዳ ለማሟላት ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም እና ስፖርት ኮሚሽኑ የድጋፍ ማመልከቻ ደብዳቤ በማስገባት ተጠይቋል:: ለአሠልጣኞች እና ሠልጣኞች የሚያስፈልገውን የትጥቅና ሌሎች ነገሮች ለማሟላት የሚያስችል ዝግጀትም እየተደረገ ነው:: ፕሮጀክቶቹን ይዘው ማሠልጠን የሚችሉና በሙያቸው ብቁ አሠልጣኖችን በማሠልጠን የቅድመ ዝግጅት ሥራም ተከናውኗል::
የክለቦችን ቁጥር ለመጨመር በሚደረገው ጥረት ሁለት ክለቦች ወደ አንደኛ ሊግ አድገው ውድድራቸውን ማድረግ ቢችሉም አንዱ በበጀት እጥረት በመቅረቱ ቀጣይ የሚወዳደሩትን ክለቦች ለመያዝ ከስፖርት ኮሚሽኑ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል:: የበጀት እጥረቱን በመቅረፍ ዘላቂነት ያላቸውን ክለቦች ለመፍጠር ከአካባቢ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ክለቦች የሚደገፉበት ሁኔታም ይፈጠራል::
ክለቦቹ ውድድር ሲያካሄዱ ወረዳን፣ ዞንን እና ከተማን በመወከል የሚመጡ በመሆኑ ከክለቦቹ ጋር የሚተሳሰሩበትን እና መደገፍ የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ተጨማሪ ጠንካራ ክለቦችን ለማፍራት ታቅዶ እየተሠራም ይገኛል::
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ድምቀትን እየፈጠሩ የሚገኙት ከሃዋሳና ዙርያዋ የወጡ እግር ኳስ ተጫዋቾች በርካታ ሲሆኑ ይሄን አጠናክሮ ለመቀጠል ፕሪምየር ሊጉን ጨምሮ በከተማዋ የሚደረጉ ውድድሮች የክልሉን የእግር ኳስ እምቅ አቅምን አውጥቶ ለመጠቀም እድል እንደሚፈጥር ኃላፊው ይጠቁማሉ::
የፕሮጀክቶችን እና ቡድኖችን ቁጥር ለመጨመር በሚደረገው ጥረት የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ከባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመነጋገር በጀት ለማስመደብና የተለያዩ የውስጥ ገቢዎችን በመፍጠር እግር ኳሱ እንዲጠናከርም ይሠራል::
ከወረዳዎች ዞኖችና ከተሞች የተውጣጡ 10 ቡድኖች እተካሄደ በሚገኘው የክልሉ የክለቦች ቻምፒዮና እየተፎካከሩ ሲሆን የሚያሸንፉ ክለቦች ክልሉን ወክለው በክልል ክለቦች ቻምፒዮና፣ ማሸነፍ ከቻሉ ደግሞ በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ክልሉን ወክለው ይወዳደራሉ:: በዚህም መሠረት አንደኛና ሁለተኛ የወጡ ክለቦች ክልሉን በመወክል የክልል ክለቦች ቻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ ይሆናል:: ውድድሩ ክልሉን የሚወክሉ ክለቦችን ከመፍጠር ባሻገር ታዳጊ ተጫዋቾች እራሳቸውን እንዲያሳዩና ልምድ ቀስመው ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ መንገድ እንደሚከፍት ተጠቅሷል::
እግር ኳሱን ለማሳደግ ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል የማዘውተርያ ሥፍራ (ሜዳ) በመሆኑ በሃዋሳ ከተማ የሚገኙ ሜዳዎችን የማስተካከልና ያልታጠሩትን የማሳጠር እና በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ሜዳዎችን በሙሉ በክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር እንዲተዳደሩ የማድረግ ሥራዎች ለማከናወንም ታቅዷል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም