አራት ዙሮች ያሉት የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ ወሳኙ ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ይገኛል። የዓለም ዋንጫው በዶሚኒካን ሪፐብሊክ አዘጋጅነት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ መካሄዱን ተከትሎ አፍሪካን በመወከል በመድረኩ ተሳታፊ የሚሆኑ ሀገራት የሚለዩበት ይህ ጨዋታ ሶስተኛ ዙር ላይ ደርሷል። በዚህ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ከኬንያ አቻው ጋር ከቀናት በኋላ የመልስ ጨዋታውን በማድረግ ቀጣይ እርምጃውን ይለያል።
በአሰልጣኝ ራውዳ አሊ እየተመራ ካለፈው ወር አጋማሽ አንስቶ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኬንያ አቻው ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን በሜዳው ቢያደርግም ውጤት ማስመዝገብ እንዳልቻለ ይታወሳል። ባለፈው ዓርብ የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያለምንም ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ናይሮቢ ላይ የሚደረገው የመልስ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ ወሳኝ ነው። አራተኛው ዙር ጨዋታ ከሚቀላቀሉ ስድስት ቡድኖች መካከል የተሻሉት ሶስት ቡድኖች በዓለም ዋንጫው አፍሪካን የሚወክል መሆኑን ተከትሎም ቡድኖቹ ጠንካራ ፍልሚያ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ከፌዴሬሽኑ ጋር የተፈራረመችው ራውዳ አሊ ቡድኗ የተገኘውን አጋጣሚ መጠቀም እንዳልቻለ ጠቁማለች። የኬንያ ቡድን ዘግቶ ለመጫወት የሞከረ ቢሆንም በኢትዮጵያ በኩል የተገኙትን እድሎች መጠቀም ባለመቻሉ ቡድኖቹ ያለ ግብ ሊለያዩ ችለዋል። ቡድኑ የታዳጊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከመጓጓት ስሜት እንዲሁም የኬንያዊያኑን አጨዋወት ባለመረዳታቸው የተቀናጀ ጨዋታ ማድረግ አልቻሉም ነበር። በእርግጥ ከዚህ ቀደም የኬንያ ብሄራዊ ቡድኑን የአጨዋወት ሁኔታ ለማወቅ አለመቻሉ ለዚህ እንደምክንያት የሚነሳ ሲሆን፤ ከቀናት በፊት የተደረገው ጨዋታ ግን ለመጪው 90 ደቂቃ ጠቃሚ ይሆናል። በመሆኑም ‹‹ግባችንን ሳናስደፍር አጥቅተን በመጫወት ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ ጥረት እናደርጋለን›› ስትልም አሰልጣኟ ጠቁማለች።
በማጣሪያው ምድብ ሁለት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ተደልድሎ የነበረው የኬንያ ብሄራዊ ቡድን በጨዋታው እንደማይሳተፍ ባሳወቀው ተጋጣሚው ምክንያት በፎርፌ ወደ ሶስተኛው ዙር ማለፉ የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ሚልድሬድ ቼቼ የሚመራው ቡድኑ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በነበረው ጨዋታ መከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ቢሆንም በመጨረሻው ሰዓት ግን ጫና ለመፍጠር ሞክሮ ነበር። በተያዘው ሳምንት መጨረሻ በሜዳው ላይ የሚያደርገው ጨዋታ ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ ወሳኝ እንደመሆኑ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይታመናል። ይህን ተከትሎም
በዓለም ዋንጫው ከስድስቱ አህጉራት የተወጣጡ 16 ቡድኖች ሲካፈሉ፤ አፍሪካ በሶስት ሀገራት ትወከላለች። ቡድኖቹን ለመለየትም 25 ሀገራት ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን ካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ አንስቶ በማጣሪያው ጨዋታ በማሳተፍ ላይ ይገኛሉ። አራት ዙር ባለው ማጣሪያም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን በመርታት ለሶስተኛ ዙር ማለፉ የሚታወስ ነው። ከቀናት በኋላ በሚደረገው የኢትዮጵያ እና ኬንያ በመልስ ጨዋታው አራተኛውን ዙር የሚቀላቀለው ቡድን ከጅቡቲና ብሩንዲ አሸናፊዎች ጋር ይጫወታል። ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን በሶስት ቀናት ልዩነት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያደርጉ መሆኑ ይታወቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም