
የሩሲያ ጦር በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ውስጥ በአዲስ መልክ እያረገ ባለው ጥቃት አምስት መንደሮችን መያዙን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዩክሬን ባለሥልጣናት በዩክሬን ካርኪቭ ክልል እና ሩሲያ ድንበር ላይ በሚገኙት “ግራጫ ዞን” ውስጥ የሚገኙትን መንደሮች በሩሲያ እጅ ስለመውደቃወቸው እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
የዩክሬን ጋዜጠኞች እንደዘገቡት ከሆነ ግን ቦሪሲቭካ፣ ኦሂርቴሴቭ፣ ፒሊና እና ስትሪሌቻ የተባሉ መንደሮች ባሳለፍነው አርብ በሩሲያ ወታደሮች እጅ ወድቀዋል።
ሩሲያ የፕሌቴኒቭካ የተባለች መንደርም በጦሯ ቁጥጥር ስር መሆኗን አስታውቃለች።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ከትናንት በስቲያ ምሽት በሰጡት መግለጫ፤ በስትሪሌቻ እና ፕሌቴኒቭካ እንዲሁም በክራስኔ፣ ሞሮኮቬትስ፣ ኦሊኒኮቭ፣ ሉኪንቺ እና ሃቲሽቼ በተባሉ መንደሮች ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
“ወታደሮቻችን በጦር ግንባሮቹ የዩክሬናውያንን ድንብር ለማስጠበቅ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እየወሰዱ ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ።
እንደ አዲስ ያገረሸውን የሩሲያ ጥቃት ተከትሎ በርካታ ዩከሬናውያን ከመኖሪያቸው ለመልቀቅ መገደዳቸውም ነው የተነገረው።
የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በክልሉ ያገረሸው ጥቃት ከአንድ ሺህ 700 በላይ የዩክሬን ዜጎች በግጭቱ አቅራቢያ ካሉ ሰፈሮች ውስጥ ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
ሩሲያ ከትናንት በስቲያ ቮቭቻንስክ የተባለች መንደርን በአየር እና በሮኬት መደብደቧ የቀጠለች ሲሆን፤ ፖሊሶች እና በጎ ፍቃደኞች ነዋሪዎችን ለማስወጣት ሲሯሯጡ ታይተዋል።
ሩሲያ ካሳለፍነው የካቲት ወር ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትሰነዝረውን ጥቃት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፤ ዩክሬን በበኩሏ የምእራባውያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ በወቅቱ አለመደረሱ ሩሲያ በጦር ግንባር የበላይ እንድትሆን እያደረጋት ነው ብላለች።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ ከሳምንት በፊት በጦር ግንባር ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን መግለጻቸው ይታወሳል።
ዩክሬን ቁልፍ ወታደራዊ ሥፍራዎችን ማጣቷን ያመኑት ዋና አዛዡ፤ ሞስኮ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ታክቲካዊ ስኬትን አስመዝግባለች ብለዋል።
ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ አክለውም ዩክሬን ጦር የሚያስፈለግውን የጦር መሣሪያ ድጋፍ ከአሜሪካ ከማግኘቱ በፊት ሩሲያ ያላትን የወታደርና የጦር መሣሪያ ቁጥር ብላጫ በመጠቀም ቦታዎችን እየተቆጣጠረች መሆኑን አስታውቀዋል።
አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ለዩክሬን የ61 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኗ ይታወቃል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም