ተስፋ የተጣለበት ልዩ የመምህራን ስልጠና

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያረጋግጡት የአንድ ስልጠና፣ በተለይም የመምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ስልጠና አቢይ አላማው ግልፅ ነው። እሱም መምህራን ወደ ሥራው ዓለም በሚገቡበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ፤ እንዲሁም፣ አቅማቸው ጎልብቶ የመማር ማስተማሩን ሂደት በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ፣ መምህራኑ ከስልጠናው በተጨማሪ አጋዥ መጽሐፎችን በማንበብና የተሻሉ ልምዶችን በመውሰድ የማስተማር ክህሎታቸውን አዳብረው የተማሪዎችንና የራሳቸውን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በሙሉ አቅም እንዲሠሩ ማስቻል ነው። በተጨማሪም መምህራን ወደ ክፍል ከመግባታቸው በፊት በሚያስተምሩት ትምህርት ዙሪያ በቂ ዝግጅት አድርገውና ከተማሪዎቻቸው ቀድመው በመገኘት አርዓያ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው።

የስነ-ትምህርት ሣይንስ ምሁራን እንደሚነግሩን የመምህራን በቂ ዕውቀት ያለመኖር፣ ተዘጋጅቶ አለመግባት፣ ሰዓት አለማክበር፣ አለባበስ፣ የፀጉር አቆራረጥ፣ ንፅህና፤ እንዲሁም፣ ተማሪዎችን በአንድ ዓይን አለማየት ለተማሪዎች አለመረጋጋትና ለክፍል ውስጥ ፀጥታ መደፍረስ ቁልፍ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህም መምህራኑ ጊዜያቸውን በአግባቡ ሳይጠቀሙና የሚፈልጉትን ነገር ሳያደርጉ ከክፍል እንዲወጡ የሚገደዱበት ጊዜ አለ። እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት ስልጠና የግድ አስፈላጊ ይሆናል።

መምህራን በአግባቡ አቅደውና በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ክፍል ከገቡ በራስ በመተማመን ማስተማርና ተማሪውም የሚፈልገውን ዕውቀት እንዲጨብጥ ማድረግ እንደሚችሉ፤ መምህር በትምህርት ቤትም ሆነ ከትምህርት ቤት ውጪ ሁሌም የመልካም ነገር መሪ መሆን እንዳለበትና በማኅበረሰቡም ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚገባ፣ ለተሳለጠ የትምህርት አሰጣጥ መምህር ለተማሪው ተቆርቋሪ መሆን እንዳለበትና መቆርቆሩ ወደ አላስፈላጊ ነገር ሊመራው እንደማይገባም የስነ-ትምህርት ባለሙያዎች አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። ስልጠና እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንደሚያቃልል እና የመማር-ማስተማሩን ስራ ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚወስደው ያስረዳሉ።

ለምሳሌ የእንግሊዝኛ ቋንቋን በመጠቀም በክፍል ውስጥ ማስተማር፣ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት፣ ትምህርቱ በሚሰጥበት ወቅት፣ ከተሰጠ በኋላ፤ እንዲሁም፣ የክፍል አያያዝን መሠረት ያደረገ ስልጠና እንደሚያስፈልግ፤ ይህም በቀላል እንግሊዝኛ ሰዋሰውን አስተካክሎ መጠቀም፣ ምሳሌዎችንና አያያዦችን በአግባቡ በመጠቀም ተማሪዎችን ማስተማር እንዲችሉ እንደሚያደርግ፤ የማስተማር ስነ-ዘዴ፣ የዕቅድ አዘገጃጀት፣ የምዘና መስፈርቶች እንዲሁም ከስነ ምግባር አኳያ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ በስልጠናዎች መዳሰስ ያለባቸው ስለ መሆናቸው በመምህራን ስልጠናዎች ወቅትና ሂደት ሊታሰብባቸው የሚገቡ መሆናቸውም በባለሙያዎቹ ይጠቅሳሉ።

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ምሬሳ በዘንድሮው የ50 ሺህ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ስልጠና ሂሳብ፣ እንግሊዝኛ እና ሳይንስ ልዩ ትኩረትን እንደሚያገኙና ከሌሎቹ በተለየም በእነዚህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአንድ ስልጠና አንድ መምህር ወደ ክፍል ከመግባቱ በፊት የማስተማሪያ እቅድ ማቀድ፣ በቂ ዝግጅት ማድረግ፣ ለትምህርት ይዘቱ ማውጣት ያለበት ፈተና፣ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ከተማሪዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት፣ የሰዓት አጠቃቀምና አለባበስን ጨምሮ ትልቅ ግንዛቤ ይዞ ሊወጣ የሚገባ ስለመሆኑም ስለ ስልጠናዎች አስፈላጊነት በተነሳ ቁጥር ሳይጠቀሱ የማይታለፉት ናቸው።

ወደ ትምህርት ተቋማትም ስንመጣ የምናገኘው የስልጠና አስፈላጊነትን ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ተልዕኮው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ጥራት፣ ተገቢነትና በኢንዱስትሪው መሪነት የባለሙያዎች የሙያ ብቃት በምዘና በማረጋገጥ ደረጃውን የጠበቀ ብቁና ተወዳዳሪ ትምህርትና ሥልጠና ተቋም እና ባለሙያ መፈጠሩን ማረጋገጥ ነው።

እሴቶቹ ደግሞ ለትምህርትና ስልጠና ጥራት ቅድሚያ መስጠት፣ የሙያ ስነምግባር፣ የላቀ ምዘና፣ በጋራ መስራት፣ በዕውቀትና በእምነት መስራት፣ ተጠያቂነት፣ ለሕግ መገዛትና የላቀ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ናቸው። መምህራን በሚያስተምሩበት የትምህርት ዓይነት የተሻለ እውቀት ኖሯቸው ብቁ ተማሪዎችን እንዲያፈሩ የሚያግዘው የመምህራን ስልጠና በዘንድሮው ክረምት እንደሚጀመር የተናገሩት የዛሬው እንግዳችን ወ/ሮ አሰገደች ምሬሳም በሰጡን ማብራሪያ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ያጠናከሯቸው እነዚህኑ ነው።

በዘንድሮው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ50 ሺህ መምህራን ልዩ የክረምት ስልጠና ለመስጠት፤ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወቃል። ይህ የተገለጸው የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ የ2016 ዓ.ም. የሁለተኛው ሩብ አመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በየካቲት 26 ቀን 2016 ዓ•ም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ሲሆን፤ ስልጠናው የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን አቅም ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም በሚኒስትሩ ተገልጿል።

በሪፖርቱ የአጠቃላይ ትምህርት የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ እና ትግበራ የደረሰበት ደረጃ የተገለጸ ሲሆን፤ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ለትምህርት ቤት አመራሮች እና መምህራን ስለሚሰጡ ስልጠናዎች ማብራሪያ መቅረቡ ይታወሳል። ባሉበት ሁኔታ ጥሩ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ስልጠና በመጪዎቹ ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት እንደሚሰጥ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ስልጠናውም በሥራ ላይ ላሉ መምህራን በልዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናነት የሚሰጥ ሲሆን፤ ስልጠናው መምህራን ባሉበት የትምህርት ደረጃ እና በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት ስነ-ዘዴ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ልዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በተመለከተ ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት በሚያስችል መልክ ከሚመለከታቸው የሥራው ኃላፊ ጋር ቆይታ ያደረግን ሲሆን፤ እንግዳችን የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ምሬሳ የሚከተለውን መረጃ አካፍለውናል።

እነዚህን ስልጠናዎች ለማከናወን የሚያስችሉ ሞጁሎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን የዴስክ ኃላፊዋ ወይዘሮ አሰገደች ምሬሳ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ የገለጹ ሲሆን፤ በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ የተነገረለት ይህ ስልጠና ይበልጡኑ ትኩረት የሚያደርገው፤ የሁለተኛ ደረጃ የሂሳብ፣ የሳይንስ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቶች ላይ መሆኑንም ኃላፊዋ አስረድተዋል።

አቅም ማጎልበቻ ስልጠናው የመምህራንን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን በማሰብም፤ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን የተዘጋጀ መጠየቅ ተበትኖ፣ ተሰብስቦና ተተንትኖ በተገኘው ውጤት መሰረት የተዘጋጀ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊዋ፤ ይህ ብቻም ሳይሆን በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎችም የተሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ ስልጠናውን የሚወስዱት መምህራንና የትምህርት አመራር ባለሙያዎች በወሰዱት ስልጠና ልክ በትምህርት ስራው ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ሀገር ተረካቢ ተማሪዎቻቸውን ያበቃሉ። የተሻለ ትውልድ የመፍጠሩን ሰፊ ሥራ ይበልጥ ያጠናክራሉ ተብሎ እንደሚታሰብ የሚናገሩት የዴስክ ኃላፊዋ፤ ከአንድ መምህር ጀርባ ቢያንስ 300 ተማሪዎች መኖራቸውን፤ ከሦስት መቶ ተማሪዎች ጀርባ በሺዎች የሚቆጠሩ ወላጆች፤ ከወላጆችም ጀርባ ሀገርና ሕዝብ መኖሩን ማሰብ እንደሚያስፈልግም የተናገሩ ሲሆን፤ ስልጠናው በዛ ልክ ለውጥና መሻሻልን ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድረዋል። በአጋዥ መጻሕፍት (ሞጁሎች) መታገዙም ሆነ ለወደፊት አሰራር ያመች ዘንድ የተለያዩ መመሪያዎች፣ ደንቦች ወዘተ ተዘጋጅተው ወደ ተግባር መሸጋገሪያ ወቅት ላይ መገኘታቸውም የትምህርት ሥርዓት ለውጡን ውጤታማ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

እንደ ዴስክ ኃላፊዋ ገለጻ በሀገራችን ከሚገኙት 800 ሺህ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች (የመንግሥት) ከ94 በመቶ በላይ የሆኑት ተገቢው የትምህርት ደረጃ (ማስረጃ) ያላቸውና የሚሰሩበትን የስራ ዘርፍ/መደብ/ የሚመጥን ነው። ይሁን እንጂ ብቃትን ለማረጋገጥ በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም ሆነ የተማሪዎች የፈተና ውጤት (በተለይ ባለፈው አመት የተመዘገበው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤት) የሚያሳየው በሙያው የሚፈለገውን የትምህርት ደረጃና ማስረጃ ይያዙ እንጂ የአቅም ክፍተት መኖሩን ነው። በተለይ በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት ሳይቀር ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ታይቷል፤ በጥናትም ተረጋግጧል። በመሆኑም ይህ ልዩ ስልጠና አስፈልጓል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችንን በተመለከተም ያለባቸው ኃላፊነት በዴስክ ኃላፊዋ የተነሳ ሲሆን፤ እርሳቸው እንዳብራሩት በሀገራችን 28 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንን ያሰለጥናሉ። ያሉት መምህራኖቻችንም ከእነዚሁ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የወጡ ናቸው። አሟልተዋል ተብለው ወደ ሥራ የተሰማሩ ናቸው። ውጤቱ ግን የተጠበቀውን ያህል ሆኖ አልተገኘም።

የሁሉም ትምህርት ተቋማት የትምህርት አሰጣጥና ፋሲሊቲ እኩል አይደለም። የጊዜ አጠቃቀማቸውም ሆነ የማስተማር ስነ ዘዴያቸው የተለያየ ነው። በአመራር በኩልም እንደዛው። በመሆኑም ወደ አንድና የተሻለ አሰራርና አሰለጣጠን መምጣት አለባቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ አሁንም የምናሰለጥነው በእነዚሁ ዩነቨርሲቲዎች ነው፤ ሌላ ተቋም የለንም፤ የትም ወስደን ልናሰለጥናቸው አንችልም። ያለችን እቺው ሀገር ስለሆነች እዚሁ ነው ማሰልጠን የምንችለው። በመሆኑም መምህራኖቻችንን የሚያሰለጥኑት ተቋማት ብቁ ሆነው፤ የተሻለ የሰው ኃይል ለማውጣት ዝግጁ ሆነው መገኘት ይገባቸዋል። ራሳቸውን ማብቃት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ነው በኃላፊነት ላይ የተመሰረተ አስተያየታቸውን የሰጡት።

በስልጠናው የሚካተቱ መምህራንን በተመለከተም ጠይቀናቸው “በዚህ ዙር ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚያስተምሩ መምህራን ነው እድሉን የሰጠነው። እንደ አጠቃላይ ግን ሁሉም መምህራን በሂደት ይህንን ልዩ ስልጠና የመሰልጠን እድል ያገኛሉ፤ የስልጠናው ተጠቃሚም ይሆናሉ ብለን ነው ያቀድነው። በተለይ በጥናት ላይ የተመሰረተው ይህ ልዩ ስልጠና የማስተማር ሥነዘዴ፣ ብቃት ማጎልበት እና መምህራኑ በሚያስተምሩበት ቴክስትቡክ (የማስተማሪያ መጻሕፍት) ላይ የተመሰረተ (የሚያተኩር) እንደ መሆኑ መጠን ሁሉም መምህራን የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግን ታሳቢ አድርጎ የተዘረጋ መርሀ-ግብር ነው” በማለት መልስ ሰጥተውናል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታየ ሀገራችን ከፍተኛ መምህራን አሏቸው ከሚባሉት ሀገራት የምትመደብ መሆኗን የሚናገሩት ወይዘሮ አሰገደች፤ ብቃት ላይ ግን ተደጋግመው የሚነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን ያሰምሩበታል። “ከዚህ በፊት የብቃት ምዘና ተሰጥቷቸው ያንን፣ የሚያስተምሩትን ትምህርት መሰረት ያደረገ ፈተና ማለፍ የቻሉት መምህራን 24 በመቶ ብቻ ናቸው” ሲሉም የዚህን ስልጠና መነሻ እና መድረሻ፤ እንዲሁም የሌሎች ስልጠናዎችንም አስፈላጊነት ይገልፃሉ።

ለትምህርት ሥራ ዋና አስኳል የሆኑትን የትምህርት አመራሮችን፣ ማለትም ርዕሳነ መምህራን፣ ምክትል ርእስ-መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የሚባሉትን የሚያካትተው ይህ ልዩ ስልጠና፣ መምህራንን ብቻም ሳይሆን ከ29 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎቻችንንም ያሰበ መሆኑን የሚናገሩት ዴስክ ሀላፊዋ፣ የመምህራን ብቃት ከሌለ ውጤታማ ተማሪ ሊኖር እንደ ማይችልና ተማሪዎች የመምህራኖቻቸው ፍሬዎች መሆናቸውንም ይገልፃሉ።

ከዚሁ ከስልጠና ጋር በተያያዘ በየዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በክረምት ኮርስ (ሰመር ፕሮግራም) ሲከታተሉ የነበሩ፣ ነገር ግን “ድንገት” (ያቋረጡት መምህራን እንደሚሉት) እንዲያቋርጡ የተደረጉትን በተመለከተም ጠይቀናቸው ነበር፤ እሳቸው እንደሚሉት ፕሮግራሙ የአመራር ክፍተት የታየበት፣ ወጥነት የሌለው፣ ግማሹ በሁለት ወር፣ ግማሹ በሁለት ዓመት፤ ያሰኘው ደግሞ ባሰኘው ጊዜ የሚያስመርቁበት፤ የተዘበራረቀና መምህራን ተመልሰው የትምህርት ጥራትን ሊያመጡ በሚችሉበት አይነት ዝግጅት አልነበረም እየተካሄደ የነበረው። በመሆኑም፣ ጥናት ተደርጎ በጥናቱ ግኝት መሰረት ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል።

በፕሮግራሙ 8ሺህ አካባቢ የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ) እና 34ሺህ አካባቢ ሁለተኛ ዲግሪ (ኤምኤ) መርሀ ግብሮችን የሚከታተሉ መምህራን ነበሩ። አካሄዱ የተሳሳተ ነገር ስላለው ተቋርጧል ያሉት ኃላፊዋ “ይቀጥላሉ?” ወይስ • • •” ላልናቸውም “አዎ፤ ይቀጥላሉ” በማለት መልሰውልናል።

በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ ብለናቸውም “ትምህርት ማህበራዊ ጉዳይ ነው። ባለቤቱም ማህበረሰቡ ነው። በመሆኑም ለትምህርት ጥራት መጠበቅም ሆነ አለመጠበቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁሉም ኃላፊነት አለበት። በተለይ ባለ ድርሻ አካላት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ወላጆች ቀጥተኛ ተሳታፊዎች በመሆናቸው እየተከናወነ ካለው የትምህርት ሥርዓት ለውጡ ጎን ሊቆሙ ይገባል። በትምህርት ላይ የሚሰሩ ተቋማትም ከእኛ (ትምህርት ሚኒስቴር) ያልተናነሰ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ አብረን በጋራ ልንሰራ ይገባል” ብለዋል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም

Recommended For You