የወጣት እጅ ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ ፈተና

የአፍሪካ ዞን አምስት የወጣቶች (ከ18 እና 20 ዓመት በታች) እጅ ኳስ ውድድር ነገ በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት ይጀመራል። በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግን የበጀት እጥረት ለዝግጅቱ ፈተና ሆኖበታል። ቡድኑ ዝግጅቱን ከጀመረ ከሁለት ሳምንታት በላይ ቢያስቆጥርም ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚለቀቀው በጀት በመዘግየቱ በሆቴል ተሰባስቦ ተገቢውን ዝግጀት ማድረግ አልቻለም።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና ከዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ይህ የአፍሪካ ቀጣና አምስት ከ18 ዓመትና ከ20 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ውድድር ነገ ይጀምራል። ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ለማስተናገድ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ቢሆንም የበጀት እጥረቱ በቡድኖቹ ላይ ጫና መፍጠሩ አልቀረም። የሁለቱ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞችም ይህንኑ ገልፀዋል። ሰፊ ዝግጅት ለማድረግ የብሄራዊ ቡድን ምርጫ ቀድሞ ቢደረግም ሆቴል ገብተው ዝግጅታቸውን ማድረግ እንዳልቻሉና ከየቤታቸው በመምጣት እየሰሩ ይገኛሉ።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ ለዝግጅት የተመደበው ገንዘብ መዘግየቱን አምኖ ችግሩ የተፈጠረው በአሠራር ሂደት እና ቀድሞ የታቀደ ባለመሆኑ ቢሆንም ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ጠቁሟል።

አሠልጣኝ ተስፋዬ ሙለታ ከ18 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ሲሆኑ፤ ቡድናቸው ልምምዱን ከጀመረ ከአስር ቀን በላይ ቢሆነውም ሙሉ ዝግጅት እንዳልሆነ ይናገራሉ። የስፖርተኞቹ ተነሳሽነት ታክሎበት እየተሠራ ቢሆንም ሰፊ ከፍተት አለ። ተወዳዳሪዎቹ ሆቴል ባለመግባታቸው ከረጅም ርቀት የሚመጡት የመጓጓዣ፣ የምግብና ሌሎች በርካታ ችግሮችን ተቋቁመው ለውጤታማነት ዝግጅት እያደረጉ ነው። የቡድን መንፈሱን ለመፍጠርና የስፖርተኞቹ ሥነ ልቦና እንዳይጎዳም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያነሳሉ።

ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሙሉጌታ ግርማ በበኩሉ በሆቴል በመሰባሰብ በቀን ሁለት ጊዜ ለመሥራት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ባለበት የበጀት እጥረት ምክንያት እንደተጠበቀው አለመሆኑን ያመላክታል። በዚህም የተነሳ በቀን አንድ ጊዜ በመዘጋጀት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ ተችሏል። የቡድን መንፈስን የማነሳሳት ሥራዎችን በማከናወን ወደ ውድድር የሚገባም ይሆናል።

ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነው ዳንኤል ደረጀ ዝግጅቱ እየተደረገ የሚገኘው በአሠልጣኞችና ተጫዋቾች ጥረት እንጂ ያለ ምንም ድጋፍ መሆኑን ይገልጻል። አስፈላጊው ድጋፍ በወቅቱ አለመደረጉ በርካታ ፈተናዎችን እንዲጋፈጡ ምክንያት ቢሆንም በውድድሩ ተፎካካሪ ለመሆን ተዘጋጅተዋል። ሌላኛው የቡድኑ አባል ዳግማዊ ኃይሉም ለዝግጅት መሟላት የነበረባቸው ቁሳቁስና አቅርቦቶች ባለመሟላታቸው እሱና የቡድን አጋሮቹ ችግሮችን ተቋቁመው ለመዘጋጀት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የባለሙያ እና የትጥቅ ድጋፍ ቢያደርግም ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ እጥረት ፈተና እንደሆነባቸው የሚገልጹት ደግሞ የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ናቸው። የገጠሙ ችግሮች ቢኖሩም ባለው አቅም ውድድሩን ለማዘጋጀትና የብሄራዊ ቡድኑን ተሳትፎ ውጤታማ ለማድረግ ዝግጅቶች ተደርገዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ባለበት ኃላፊነት ማገዝ ያለበት ሲሆን፤ ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች ስፖርቱን ለማሳደግና መሰል ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል። ፌዴሬሽኑ ባሳየው ጥሩ የመስተንግዶ እንቅስቃሴ ሌሎች ውድድሮችን የማዘጋጀት ዕድሎች ቢኖሩም በችግር ለመቀበል እንደተቸገሩ ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የውድድር ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳርጌ፤ ለቡድኑ የሚደረገው የበጀት ድጋፍ መዘግየቱን ያምናሉ። ለዝግጅቱ ከመወዳደርያ ስፍራ ዝግጅት፣ ብሄራዊ ቡድኑን ለመደገፍ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ችግሩ የተፈጠረው ውድድሩ በድንገት የመጣና ፌዴሬሽኑም በወቅቱ ባለማሳወቁ ጉምሩክ ኮሚሽን ከቀረጥ ነጻ ፍቃድ እስኪሰጥ እና የመንግሥት አሠራር ሥርዓትን ማለፍ አስገዳጅ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ የሚገቡትን ሀገራት ለመቀበል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በቂ ዝግጀትና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ውድድሩ ቀደም ብሎ ታቅዶ ለሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ባይገባም፣ ፌዴሬሽኑ ያቀረበው የበጀት ጥያቄ ለሚኒስትር ዴኤታው ቀርቦ እና ተመርቶ በሂደት ላይ በመሆኑ ለመልቀቅ እና ክፍተቶችን ለመድፈን እተሠራ ነው። እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ፌዴሬሽኖች ቀድመው በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ወድድሮች በጀት እንዲያሲዙ የአሠራር ሥርዓት መመርያ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You