ተዓምር ፈጣሪው ፀባይ

ዝምንታ የምንፈራ ሰዎች አለን። ነገር ግን ጫጫታ በበዛበትና ሁሉም ሩጫ ላይ በሆነበት ዓለም ስክን ብሎና ተረጋግቶ በዝምታ ውስጥ የሚያስብና የሚወስን ሰው ሃያል ነው። ሁሉም የአንተን ትኩረት፣ ቀልብ ለመስረቅ፣ ለመሻማት በሚሯሯጥበት ዘመን ላይ የተረጋጋ ሰው መሆን፣ በዝምታ ማሰብ ትልቅ የስኬት ሚስጥር ነው። የምትፈልገውን ነገር የምታሳካበት መንገድ ነው።

ዝምታ አእምሮህን እንድትጠቀምበት ያደርግሃል። ብዙ እድሎች ወደ ሕይወትህ ይመጣሉ። ጥድፊያና ውክቢያ ላይ ከሆንክ ግን እድሎችህን አታያቸውም። ያመልጡሃል። እድሎች ደግሞ ብዙ ጊዜ እንደፈጣን ባቡር ናቸው። ካመለጡ በኋላ በጣም ጥሩ ሆነው ሊመጡ ይችላሉ። አልያም ደግሞ የከፉ ሆነው ሊመጡ ይችላሉ። ላይደገሙም ይችላሉ።

በስራህ፣ በትምህርት፣ በገንዝብ፣ በፍቅር ግንኙነት፣ በትዳር ወዘተ በማንኛውም ግንኙነት ያንተን በሳል ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ። እነዚህን ውሳኔዎች ስትወስናቸው መቼም አይቆጭህም። ይሄን አድርጌው ቢሆን ኖሮ የማትልባቸውን ምርጥ ውሳኔዎችን እንድትወስን ያግዝሃል። ስለዚህ በዚህ ፅሁፍ ዝምታ ምን ያህል ሕይወትህን እንደሚቀይረውና ተዓምር እንደሚፈጥር ታያለህ። ከሁሉ በላይ ግን ዝምታን እንዴት ፀባይህ ማድረግ እንደምትችልና ለስኬትህ እንደምትጠቀምበት ትማራለህ።

የመጀመሪያው የዝምታ ሃይል የማስታወስና የማሰብ አቅምን ማሳደግ ነው። እ.ኤ.አ በ2013 በተሠራ አንድ ጥናት በቀን ለሁለት ሰአት በዝምታ የሚያሳልፉ ሰዎች በአእምሮ ውስጥ ‹‹ኢፖካምፓስ›› የሚባለው ቦታ ላይ ያሉ የአእምሮ ህዋሶች እንዲያድጉ ያደርጋል። ይህ ማለት እነዚህ ሴሎች የማስታወስ፣ የገንዘብ፣ ራስን የመቆጣጠርና የስሜት ብስለት የማግኘት እድላችንን ያሰፉታል።

ዝምታ ሲባል ግን እንደው ዝም ብሎ ያለ ስራ ለሁለት ሰአት መቆየት ወይም ቁጭ ብሎ መቅረት አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሰው በየቀኑ የአርባ ደቂቃ የዝምታ ጊዜ ሊያሳልፍ ይችላል። ይህን አርባ ደቂቃ ለሶስት ሊከፍለው ይችላል። አስር፣ ሃያ፣ አስር እያለ። የመጀመሪያውን አስር ደቂቃ ቁጭ ብሎ ትልቁ ዓላማውን ወይም የረጅም ጊዜ ግቡን ያወጣል፤ ይፅፋል። የአጭር ጊዜ ግቡንም ያወጣል ይፅፋል። ትናንትና ያሳካቸውን ነገር ይፅፋል። ዛሬ ደግሞ በቀን ውስጥ ማሳካት ያለባቸውን ተግባራት ይመዘግባል።

ይህን አድርጎ አስር ደቂቃውን እንደጨረሰ ለቀጣይ ሃያ ደቂቃዎች ደግሞ ስሜቱንና መንፈሱን የሚያረጋጉ ፅሁፎችን ሊያነብ ይችላል። ይህም የመረጋጋትና የመስከን ስሜት ውስጥ ይከታል፤ ደስታም ይሰጣል። ካዛ የመጨረሻውን አስር ደቂቃ በጥሞና ሊያሳልፍ ይችላል። ጥሞና ሲባል ግን በልዩ ተመስጦ ውስጥ ሆኖ፣ ዓይን ተጨፍኖ ትንፋሽን እያዳመጡ አየር ወደ ውስጥና ወደውጭ እያስገቡ፣ የልብ ምትን እያዳመጡ ሰውነት ውስጥ የሚካሄደውን ነገር ለማወቅ መሞከር ነው።

የመጨረሻው አስር ደቂቃ የትኩረትና የተመስጦ ጊዜ ነው። በዛ የተመስጦ ጊዜ ውስጥ ግን አንድ ሰው ከፈለገ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት አልያም ደግሞ የእለቱን ሥራ በደምብ አድርጎ ሰርቶ በአእምሮ ማሰብን ሊሆን ይችላል። እንዲፈጠር የሚፈልጉትን ነገር በዛ ቅፅበት በአእምሮ ለማሰብ መሞከር የተመስጦ ጊዜ።

እንግዲህ ይህ አርባ ደቂቃ በጣም ወርቃማ ጊዜ ነው። ለምን? ካላችሁ ዓላማዎችን፣ የረጅም ጊዜ ህልምን ለመፃፍና ለማዘጋጀት ያግዛል። በጣም የሚያረጋጋና ሰላም የሚሰጥ ነገርን ለማንበብና ወደ አእምሮ ጥሩ ነገር ለማስገባት ይረዳል። በዚህ ዓለም የትኛውም ጭንቀትና መከራ ቢመጣ መረጋጋት ውስጥ መግባት ስለሚቻል ጥሩ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ይጠቅማል። ስለዚህ የመጀመሪያው የዝምታ ጥቅም የአእምሮህን የማስታወስና የማሰብ አቅም ያሳድጋል።

ሁለተኛው የዝምታ ሃይል ከጭንቀት ማሳረፉ ነው። ኑሮ፣ ሕይወት፣ ሥራ ፣ትምህርት፣ ጓደኛ፣ በየተሰብ፣ ትንሹ፣ ትልቁ ሊያስጨንቅህ ይችላል። ያንተን ትኩረት የሚፈልጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ስለዚህ ትጨነቃለህ። አእምሮህን ብዙ ሃሳቦች ይቆጣጠሩታል። ስለዚህ ለአስር ደቂቃ ስክን ያለና ዝም ያለ ጊዜ ስታሳልፍ ትረጋጋለህ። ያስጨነቀህን ነገር አስፍተህ ታየዋለህ። በሌላ መንገድ ትረዳዋለህ። መነፅርህን እንድተቀይር ያደርግሃል። ምን አልባት ከዝምታ በኋላ የሆነ እረፍት ይሰማሃል። መፍትሄ ብልጭ ይልልሃል።

አንዳንድ ጊዜ እኮ ስልክ ሲደነዝዝና አልታዘዝ ሲልህ እንደገና ታስጀምረዋለህ። ድሮ እኮ ቤተሰቦቻችን ‹‹ኧረ! ይሄ ቲቪ እንዳይደነዝዝ ቀኑን ሙሉ ሲሠራ ነው የቆየው፤ እስኪ አሳርፉት›› ይላሉ። ለምንድን ነው? ምክንያት አላቸው። ቲቪው መልሶ ሲነሳ በጥሩ ጉልበት እንዲሠራ ነው። ስለዚህ ዝምታ ማለት የአእምሮ እረፍት እንደማለት ነው።

ሶስተኛው የዝምታ ሃይል አስተዋይ ማድረጉ ነው። ሰው እድሜው ሲጨምር እየበሰለ ከዛ ደግሞ የሚያወራው ነገር እየቀነሰ ዝምታው እየበዛ ይሄዳል። እንደውም የታሪክ መዛግብቶች አንዳንድ ጠቢባን ሊሞቱ በደረሱባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ ረጅም ጊዜ ዝም ብለው ነበር ወይም ጥቂት ቃላት ብቻ ነበር የተነፍሱት ይላሉ። ዝም ስትል እንደሰከረ ዝንጀሮ ሃሳብህ ከአንድ ዛፍ ወደ ሌላ ዛፍ፣ ከአንድ ነገር ወደ አንድ ነገር እየዘለለ ሊያስቸግርህ ይችላል።

እሱን ፀጥ ማስባል ከፈለክ ግን ዝም ባልክበት ወቅት ትንፋሽህን አድምጠው። የደም ዝውውርህን ለማድመጥ ሞክር። የልብ ምትህን አድምጠው። ከዛ ሃሳብህ በአንድ ጊዜ ተኖ ይጠፋል። ያስጨነቀህ፣ የድሮ ቁጭትህ፣ ትዝታህ፣ የሚያንገበግብህ ይሆናል፤ ብቻ እነዛ ነገሮች በሙሉ አሁን ትቆጣጠራቸውና አንተ ሃሳብህ አንድ ነገር ላይ ይሆናል። ሃሳብህ አሁን የሚፈጠረው ጉዳይ ላይ ይሆናል። በሰውነትህ ላይ እየሆነ ባለው ነገር ላይ ታተኩራለህ። ይህ ሊገለፅ የማይችል የውስጥ መረጋጋትና ሰላም ይሰጣል። ከዛ ግን አእምሮህ ተመልሶ ወደሃሳቦችህ ይሄዳል። የሆነ ነገር ያስጨንቅሃል።

በዚህ ጊዜ ቶሎ ብለህ ምን ታደርጋለህ መሰለህ! ትንፋሽህን ወደ ማድመጥ ተመለስ። የልብ ምትህን አድምጠው። ከዛ ትረጋጋለህ። በዚህ ልምምድ ውስጥ መረጋጋትን ትለምዳለህ። ራስህን ማብረድ ትችልበታለህ። አንዳንድ ጊዜ የሚናደዱ ሰዎች እንዲህ አይነት የትንፋሽና የሜዲቴሽን ሥራዎች ስሜታቸውን ያስተካክለዋል። አንተም ይህንኑ አድርግ። ከዚህ ልምድ በኋላ ቁጭ በልና የገጠመህን ችግር ተንትነው፤ ፃፈው።

በምክንያት ማስብ ጀምር። ችግሩ ገጥሞኛል፤ እንዴት ላድርገው ብለህ በግብታዊነትና በስሜት በምክንያት እንድታሰብ ያደርግሃል ይህ መረጋጋት። ከዛ በኋላ የሚመጡልህን መፍትሄዎች ፃፋቸው። ከዛ በቶሎ ወደ ድርጊት ግባ። ወደ ለውጥ፤ ወደ ተግባር ግባ። መረጋጋት ሲኖርህ ጥርት አድርገህ ታስባለህ። ስሜትህ አይነዳህም። ከዛ ቶሎ ወደ መፍትሄ ትሄዳለህ። ስለዚህ ትልቁ የዝምታ ሃይል አእምሮህን እንድትጠቀምበት ያደርግልሃል። አስተዋይ ያደርግሃል።

አራተኛው የዝምታ ሃይል ተአምራዊ ለውጥ ማየት ማስቻሉ ነው። ሕይወታችንን ከፍም ዝቅም የሚያደርገው በየቀኑ የምንወስናቸው ትላልቅና ትናንሽ ውሳኔዎች ናቸው። እየውልህ! በጣም ጠቃሚ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ መወሰን ሲኖርብህ አትቸኩል። ሰዎች ‹‹ቶሎ በል እንጂ ውሳኔህን አሳውቀን፣ ምን አሰብክ፣ ንገረን እንጂ!›› ምናምን ሊሉህ ይችላሉ። ሕይወትህን የሚቀይር ወይም የሕይወትህን አቅጣጫ የሚወስን ጉዳይ ከሆነና ተራ ካልሆነ ‹‹ቆይ ጊዜ ስጡኝ፤ የዝምታ ጊዜ ስጡኝ›› በላቸው። ፀጥ ብለህ የእግር ጉዞ አድርግ። እቤት ውስጥ ከሆንክ ዓይንህን ጨፍነህ ራስህን ለማረጋጋት ሞክር።

አባቶች እኮ ሰዎች ሲያስቸኩሏቸው ‹‹ይሄ ሃሳብ ቆይ ትራስ ይንካው›› ይላሉ። ቆይ ልተኛበት፣ ሌሊቱን ላሳልፍበት፣ ጊዜ ስጠኝ፣ ላስብበት እንደማለት ነው። አየህ! ተኝተህ ስትነሳ ራሱ የሆነ የሚሰማህ አዲስ ስሜት አለ። አዲስ ሃሳብ ሊፈጠርልህ ይችላል። ስለዚህ ዝምታ እያንዳነዱ የምትወስነው ጉዳዮች ላይ ካስገባኸው ተአምራዊ ለውጥ ይሰጥሃል። አንድ ነገር አትርሳ! በሕይወትህ በጣም ምርጥ የምትለውን ውሳኔ የወሰንከው በጣም በተረጋጋህበትና ደስተኛ በሆንክበት ወቅት ነው። ዝምታ ያንን እድል ይሰጥሃል። ብዙ ችግርህን መፍታት ከፈለክ፣ የማሰብ ሃይልህን መጠቀም ከፈለክ ዝምታን ልማድህ ልታደርገው ይገባል።

አምስተኛውና የመጨረሻው የዝምታ ሃይል ደስታን መጨመር ነው። ይህም በሳይንስ የሚደገፍም ጭምር ነው። እንደውም ሳይንሱ ‹‹በዝምታ የምታሳልፍባቸው ጥቂት ደቂቃዎች በአዕምሮህ ውስጥ ያለውን ‹‹አሚግዳላ›› የተባለውን ከጭንቀትና ከፍርሃት ጋር የሚገናኘውን የአዕምሮህን ክፍል ማስተካከል ብቻ ሳይሆን የደስታ ሆርሞኖችን ለምሳሌ ሴሮቶኒም፣ኢንዶርፊንና ኦክሲቶሲን የሚባሉ ደስታ የሚፈጥሩ፣ ወደመረጋጋት የሚያመጡ ሆርሞኖችን እንዲለቀቁ ያደርጋል›› ይላል።

ይህ ማለት ዝም በምትልባቸው ቅፅበቶች ውስጥ የተረጋጋና ደስተኛ የሆነ ስሜት ውስጥ ትገባለህ ማለት ነው። እንዳንዴ እኮ ስልክህ አያርፍም፤ ይደወላል። እቤት ስትገባ ደግሞ የሆኑ የሚያሳስቡ ጉዳዮች ይኖራሉ። ሃላፊነት ይኖርብሃል። ከዛ ቲቪ ታያለህ ትተኛለህ በማግስቱ ሥራ ትገባለህ። በየቀኑ ሩጫና ጥድፊያ ላይ ነህ። ከራስህ ጋር ተረጋግተህ የምታወራበት፤ ችግርህን የምታይበት ጊዜ የለህም። ምን አልባት ዝም ብለህ ቁጭ ስትልና ከራስህ ጋር ስታወራ ወዴት እየሄድክ እንደሆነ ታስባለህ። ዓላምህን ታስታውሳለህ። ‹‹እኔ ግን ምን እያደረኩ ነው? ምን ላስተካክል?፣ ገቢዬን እንዴት ልጨምር?፣ በሕይወቴ እንዴት ደስተኛ ልሁን?፣ መንፈሳዊ ሕይወቴን እንዴት ላስተካክል? የማለት እድል ይሰጥሃል ዝምታ!

ግን ጥድፊያ ላይ ከሆንክ ወዴት እየሄድክ እንደሆነ እንኳን አታውቅም። ወደምስራቅ መሄድ ሲገባህ ወደ ምእራብ እየተጓዝክ ሊሆን ይችላል። ከዓላማህ በተቃራኒ ድርጊቶች እየወሰድክ ሊሆን ይችላል። ለዛ ነው ብዙ ሰዎችን የዛሬ አምስትና አስር ዓመት ያስቀመጧችኋቸው ቦታ ላይ የምታገኟቸው። ይሮጣሉ! ይሮጣሉ! አንድም ቀን ግን ወዴት እየሮጡ እንደሆነ የማሰብ እድል ለራሳቸው አይሰጡትም። ዝምታ ግን ያንን እድልና ሃይል ይሰጥሃልና ተጠቀምበት።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You