ከፍተኛ ሊግ የተቀላቀሉ አራት ክለቦችን ተለይተዋል

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር በሀገሪቱ የሊግ እርከን ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝና በርካታ ክለቦች የሚፋለሙበት ነው። በውድድሩ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ እና ውጤት ያልቀናቸው ወደ ክልል ክለቦች ቻምፒዮና የሚወርዱበትም መድረክ ነው። ዘንድሮ በሁለት ምድቦችና በሁለት ዙሮች ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሲጠናቀቅ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደጉ አራቱም ክለቦች ተለይተው ታውቀዋል።

በህዳር ወር በሁለት ምድቦች ተካፍሎ በርካታ ክለቦችን በማፋለም የተጀመረው ጉዞ በ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር የሚሳተፉ ክለቦች ሲለዩበት ከከፍተኛ ሊጉ የሚወርዱትን አምስት ክለቦች በመተካት በሁለተኛው የሀገሪቱ ሊግ የሚወዳደሩ ይሆናል። ለመጫወት የሚያስችላቸውን ውጤት ማስመዝገብ በመቻላቸው ሊያድጉ ችለዋል። የመጀመሪያው ዙር ምድብ የ“ሀ” በጅማ ከተማ እና የምድብ “ለ” ውድድሮች በሶዶ ከተማ ተካሂደው ከተጠናቀቁ በኋላ የውድድር ስፍራ ለውጥ በማድረግ መጋቢት 1/2016 ዓ.ም የምድብ “ሀ” ወድድሮች በሆሳዕና ከተማ የምድብ “ለ” ጨዋታዎች ደግሞ በአርባምንጭ ከተማ በመከናወን ከየምድቡ ሁለት ሁለት ክለቦችን በመለየት ነበር ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደጉት ክለቦች የተለዩት።

ከምድብ “ሀ” ዱራሜ ከተማ እና አምቦ ከተማ፤ ከምድብ “ለ” ደግሞ ሱሉልታ ክፍለ ከተማ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ማደጋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሆነዋል።

ከአራቱ ክለቦች ቀድሞ ማደግ የቻለው ሱሉልታ ክፍለ ከተማ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን ዙር 5ኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ቢያጠናቅቅም፤ በሁለተኛው ዙር አስደናቂ ጉዞን በማድረግና ከፍተኛ ነጥቦችን በመሰብሰብ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደግ ችሏል። ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት ከ31 ጨዋታዎች 60 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነባር የመጀመሪያው አዳጊ ክለብ መሆን የቻለው። በ31ኛው ሳምንት ከቡታጅራ ከተማ ጋር ባካሄደው ጨዋታ 3 ነጥብ ማሳካቱን ተከትሎ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ10 ነጥቦች በመራቁ ወደ ከፍተኛ ሊግ ካደጉ ክለቦች መካከልም ሆኗል።

አምና በከፍተኛ ሊግ ሲወዳደር የነበረው አምቦ ከተማ ከአንድ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ሁለተኛው አዳጊ ክለብ በመሆን ወደ ነበረበት መመለስ ችሏል። ከ33 ጨዋታዎች በሰበሰባቸው 67 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃ ላይ የነበረውን ክለብ በአራት ነጥቦች በልጦ ነው ዳግም ከፍኛ ሊጉ ያደገው።

ዓመቱን በሙሉ የምድብ “ለ” ደረጃ ሰንጠረዥን በወጥነት እየመራ ማጠናቀቅ የቻለው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከበርካታ ዓመታት የአንደኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ሶስተኛ ክለብ በመሆን ከፍተኛ ሊጉን ተቀላቅሏል። 33 ጨዋታዎችን በማድረግ 62 ነጥቦችን ሰብስቦ ሱሉልታን በመከተልም ነው ማደጉን ያረጋገጠው። 2008 ዓ.ም ላይ ወደ ከፍተኛ ሊግ ከወረደ ስምንት ዓመታት በኋላም ነው ተመልሶ ማደግ የቻለበትን ታሪክ ያስመዘገበው።

የመጨረሻው ዱራሜ ከተማ ሲሆን፤ እሱም በ2015 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወርዶ በዓመቱ ተመልሶ ማደጉን ያረጋገጠ ክለብ ሆኗል። በዚህም ካደረጋቸው 34 ጨዋታዎች 67 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከምድቡ አምቦ ከተማን በመከተል ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ማደግ ችሏል።

የምድብ ሀ ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ የተጠናቀቁ ሲሆን፤ አምቦ ከተማ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል። ዱራሜ ከተማ ሁለተኛ እና ቡራ ክፍለ ከተማ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ሲያጠናቅቁ፤ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫውን ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወስዷል። በምድብ “ለ” ሱሉልታ ክፍለ ከተማ ውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና አቃቂ ቃሊቲ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ፈፅመዋል። ቡሌ ሆራ ደግሞ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ አሸንፏ።

ከምድብ “ሀ” አራት ክለቦች ከምድብ “ለ” ደግሞ ሶስት ክለቦች በድምሩ ሰባት ክለቦች በተለያዩ ምክንያቶች ውድድራቸውን ያቋረጡ ሲሆን፤ ከየ ምድቡ ሁለት- ሁለት ክለቦች ወደ ክልል ክለቦች ቻምፒዮና መውረዳቸው ተረጋግጧል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You