አሜሪካ ለእስራኤል በሰጠቻቸው ቦምቦች ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን አመነች

ለፍልስጤም ነፃነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር ጦርነት የተቀሰቀሰው።

እስራኤል በሐማስ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ባለችው መልሶ ማጥቃት ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል። ፕሬዚዳንት ባይደን ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ” ለእስራኤል በሰጠነው ቦምብ ንጹሃን ተገድለዋል” ብለዋል።

“ወደ እስራኤል ቦምብ አንልክም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ እስራኤል ወደ ራፋህ ጦሯን እንዳትልክ እና ንጹሃንን እንዳትጎዳ ለጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መናገራቸውንም ጠቅሰዋል።

እስራኤል ጦሯን በርካታ ስደተኞች ወደ ተጠለሉበት ራፋህ ከላከች ተጨማሪ ርምጃዎች ሊወሰድ ይችላል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ በቃለ መጠይቃቸው ላይ ተናግረዋል።

ይሁንና የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሐማስ ታጣቂዎች በራፋህ እንደሚገኙ እና እነሱን ለመደምሰስ ጦራቸው ወደ ራፋህ መግባቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ወደ ራፋህ እንዳንገባ የሚከለክለን አካል የለም ያሉ ሲሆን ስለ አሜሪካ አዲስ ውሳኔ እስካሁን በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል።

በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን የአሜሪካ ውሳኔ የሚያበሳጭ ነው ያሉ ሲሆን ዋሽንግተን ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ ማቆም የለባትም ብለዋል።

ከአሜሪካ በተጨማሪም ካናዳ እና ሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት ለእስራኤል የጦር መሳሪያ እንዳይሸጥ እገዳ ጥለዋል።

እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ለማድረግ፣ ታጋቾችን ለመልቀቅ እና ሌሎችንም ጉዳዮች ለመመለስ በሚል የሰላም ስምምነት ለመፈራረም የተስማሙ ቢሆንም አዲሱ የራፋህ ጥቃት ስምምነቱ እንዲፈርስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል አልአይን ኒውስ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You