ሩሲያ ናዚ ጀርመንን ያሸነፈችበትን የድል በዓል እያከበረች ነው

ሩሲያ በትናንትናው ዕለት ከ79 ዓመት በፊት ሶቪየት ህብረት የናዚ ጀርመን ወራሪ ኃይልን ያሸነፈችበትን የድል በዓል እያከበረች ነው።

ሶቪየት ህብረት ከፈራረሰች ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቀዩ አደባባይ በሚካሄደው በዓል ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።

ሞስኮ ከዩክሬኑ ጦርነት በኋላ አነስ ያለም ቢሆን ወታደራዊ ትርኢት እንደምታሳይ ነው የተነገረው።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ጀርመን እና የፋሽስት ጣሊያን ኃይልን ለማሸነፍ ከተባበሯት ሀገራት ጋር ግንኙነቷ ይበልጥ በሻከረበት ወቅት የሚከበረው የድል በዓል ለሩሲያውያን ትልቅ ስፍራ አለው።

“አባት ሀገራቸውን ለመጠበቅ መስዋዕትነት ለከፈሉት ሁሉ ትልቅ ክብር አለኝ” ለሚሉት ለፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የበዓሉ ትርጉም ከፍ ያለ ነው።

አባታቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ጀርመን ኃይልን መዋጋታቸውንና ጦርነቱ ያስከተለውን ጠባሳ ደጋግመው የሚያነሱት ፑቲን፥ ምዕራባውያን ሶቪየት ህብረት የሂትለርን ጦር በማሸነፉ ረገድ የነበራትን ድርሻ ዘንግተዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።

የ71 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ከትናንት በስቲያ ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን ቃለ መሃላ ሲፈጽሙም የዩክሬኑ ጦርነት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሶቪየት ህብረትን ብርታት ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ መራሹ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋትንም ከናዚ ጀርመን ፍላጎት ጋር እንደሚያመሳስሉት አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ዩክሬንና ምዕራባውያን አጋሮቿ ግን ሉዓላዊ ሀገር በመውረር መሬት የመያዝ “ያረጀ የንጉሳዊ አገዛዝ” እየተከተሉ ያሉት ፑቲን ናቸው በማለት ይወቅሳሉ።

የዩክሬንን ከ18 በመቶ በላይ ግዛት በቁጥጥሯ ስር ያስገባችው ሞስኮ በበኩሏ ጦርነቱ ከኬቭ ጋር ሳይሆን አይዞሽ ከሚሏት “የናዚ አስተሳሰብ አራማጅ” ምዕራባውያን ሀገራት ጋር እንደሆነ ትገልጻለች።

በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸው የዩክሬን መሬቶችም ከዓመታት በፊት የታላቋ ሩሲያ አካል እንደነበሩና በመጥቀስ ወቀሳውን ውድቅ ታደርጋለች።

ዛሬ እያከበረችው ያለውን የድል በዓልም ብርታቷን ለዓለም ለማሳየት ትጠቀምበታለች።

ሶቪየት ህብረት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ27 ሚሊየን በላይ ዜጎቿን ማጣቷ ይነገራል።

ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን “አክሲስ ፓወር” በሚል ዓለምን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ “ከተባበሩት ኃይሎች” አሜሪካ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ጋር ያደረጉት ጦርነት በርካታ ሀገራት የተሳተፉበትና ከወቅቱ የዓለም ሕዝብ 3 በመቶው ያለቀበት ነው።

በዩክሬን ምክንያት ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋቱ ባየለበት በዚህ ወቅት ሩሲያ ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ሙከራ እንዲጀምር አዛለች።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አብረዋት የተሰለፉት ሀገራት አሁን ዋነኛ የደህንነት ስጋት እንደሆኑባት ገልጻለች።

አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ለዩክሬን ከጦር መሳሪያ እስከ ወታደር በመላክ ኬቭን ከሞስኮ ጋር ሃይላቸውን የሚፈታተሹባት የጦር ሜዳ ካደረጓት ከሁለት ዓመት በላይ ተቆጥሯል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You