ልዩ ትኩረት የሚሻው የማዳበሪያ ሥርጭት

የኢትዮጵያ ግብርና ወይም እርሻ ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለውለታ፣ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዋልታና መከታ፣ ለገጽታ ግንባታ መታያና መመልከቻ ነው። ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት መጎልበትም እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ ዘመናዊ ግብአቶች እጅጉን ወሳኝ ናቸው።

የሀገራችን መሬት ማዳበሪያ የግድ ካለ ዓመታት ተቆጥረዋል። መሬቱም ያለ ማዳበሪያ ተፈላጊውን ምርት እየሰጠ አይደለም። ለነገሩ ለሺህ ዓመታት ሙሉ ሲታረስ የነበረ መሬት አሁንም ምርታማ መሆኑ ሊያስመሰግነው እንጂ ሊያስወቅሰው አይገባም። ተፈጥሯዊው ማዳበሪያ የሰው ሠራሹን ያህል ሁሉንም አስፈላጊ ኬሚካሎች ወይም ንጥረ ነገሮች በተሟላና በበቂ ሁኔታ ይዟል ተብሎ ባይታመንም ጠቀሜታው ግን የሚናቅ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ይነግሩናል።

መንግሥትም ይሄንን ተገንዝቦ ከተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ጎን ለጎን በግዢ የሚመጣውን ማዳበሪያ እያቀረበ ነው። ማዳበሪያ ሰኔ በመጣ ቁጥር መሰማት የሚጀምር የአርሶ አደሮች ድምፅና የመገናኛ ብዙሃኑ አብይ ጉዳይ ነው።

ለግብርና ግብዓት ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ የሆነው የአፈር ማዳበሪያ የምርታማነት ሞተር ቢሆንም ቀደም ባሉት ዓመታት በግዢ የዘገየ፣ በሥርጭት ችግሮች የተተበተበ ሆኖም ቆይቷል። አስቀድሞ ስለዋጋው መወደድ ይጮህ የነበረው አርሶ አደርም በኋላ ላይ ደግሞ ከነጭራሹ ማዳበሪያው ስላለመኖሩ ሲጮኽ ሰምተናል።

ለማዳበሪያ ጥያቄው ምላሽ ለመስጠት መንግሥት በየዓመቱ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እንደሚያደርግ መረጃዎች ያመላክታሉ። 20 ቢሊዮን ብር ለሀገራችን ምን እንደሚሰራ ስናስበው እነዚህ አሻጥረኛና ስግብግብ የምንላቸውን አንዳንድ ባለስልጣንና ነጋዴዎች ምን ያህል በአቋራጭ እንከበሩበት ስናስብ ቁጭት ያንገበግበናል።

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በዋጋ ጭማሪ፣ በመጠንና በጊዜ መስተጓጎል እንዲሁም ለሕገ ወጥ ተግባር በመዋል ከወትሮው በተለየ ግብርናችንን እየፈተነው ያለ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። በ2015 እና በ2016 ዓ.ም የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ላይ በሕገ ወጥ መንገድ በተሰማሩ ግለሰቦች ምክንያት እጥረት በማጋጠሙ በአርሶ አደሮች ላይ መስተጓጎል ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህ ምክንያትም የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ አለመድረስ፣ ዋጋውም ከፍተኛ ጭማሪ ማምጣቱ ሁሉ ተደምረው የምርት መጠን እንዲቀንስ፣ የግብርና ምርቶች ዋጋም እንዲንር በማድረግ ነዋሪውን ለከፍተኛ ጫና ዳርጓል።

አርሶ አደሮች ስላለፈው ዓመት የእርሻ ሥራቸው ሲያስታውሱ ዛሬም ስጋት አላቸው። ምክንያታቸው ደግሞ አምና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ማጣታቸው የምርት ውጤቱ ዝቅ እንዲል አድርጎባቸዋል። ያለፈው ዓመት እጥረት እንዳይደገም ግብዓቱ ቀድሞ ሊቀርብላቸው እንደሚገባ የሚናገሩ ገበሬዎች በርካታ ናቸው።

ባለፈው በልግ የነበረው የማዳበሪያ እጥረት መግጠሙና ዘግይቶም በመቅረቡ ምርታማነት ላይ ተፅእኖ አሳድሯል። ግብዓቱ ከውጭ ከመግባቱ አንፃር ቀደም ብሎ ሊሰራ የሚገባ ተግባር ነው። ከአምናው ጉድለቶች መማር ያስፈልጋል።

በርግጥ ዘንድሮ የአምናው ድራማ እንዳይደገም ግብርና ሚኒስቴር ቀደም ብሎ የማዳበሪያ ግዢ ማዘዙና ሀገር ውስጥ አስገብቶ እያሰራጨ መሆኑንና አሁን ላይ በቂ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አሳውቋል።

ባለፉት ዓመታት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ያልደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ ችግር አስቀድሞ ለመፍታት እየተሠራ ይገኛል። በዘንድሮው ዓመት በአጠቃላይ 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ስለመፈፀሙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል።

ወቅቱ የበልግ ወቅት ነው። ገበሬውም እያረሰ ነው። የበጋ ስንዴ ሥራው እየተከናወነ ነው። ይህ የግብርና ሥራ ውጤታማ የሚሆነው በግብዓት አቅርቦት ነው። በዚህ ረገድ ያለፈው ዓመት ስህተት እንዳይደገም ቀድሞ መሥራት ያስፈልጋል። የአፈር ማዳበሪያና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ሥርጭት ክትትል መለየት የማይገባው ሥራ መሆን አለበት።

በርግጥ ግብርና ሚኒስቴር እንደገለጸው 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ መፈፀሙ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ የማዳበሪያ ግዢ ነው። ከዚህ ውስጥ 25 በመቶው ለመስኖ የግብርና ሥራ/ስንዴ ብቻ ሳይሆን ለአትክልትን ፍራፍሬ/ ፣ ለበልጉ 20 በመቶው ቀሪው 55 በመቶው ደግሞ ለመኽር ወቅት የሚሆን ነው።

እንደ እውነቱ መንግሥት አስቀድሞ መግዛቱና ሥርጭት መጀመሩ በራሱ ጥሩ ነው። ዋናው ነገር ግን አርሶ አደሩ እጅ መድረሱ ነውና የመንግሥት ጥረት እስከ አርሶ አደሩ ጓዳ ድረስ ሊዘረጋ ይገባል። መቼም የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም አካል ከሁሉ በላይ ግብርናው ይመለከተዋል። በየቦታው የምናገኛቸው አርሶ አደሮቻችንን ጩኸት የመስማት ግዴታ አለብን።

ትልቁ ነገር ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን የገባውን ማዳበሪያ ለሁሉም አርሶ አደር እስካልተሰጠ ድረስ ‹‹ማዳበሪያ ቀርቧል›› ብሎ በሙሉ ልብ መቀመጥ አይቻልም። ማዳበሪያን በመጋዘን ውስጥ ይዞ አርሶ አደሩን ማስጮህ ተገቢ ባለመሆኑ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ማዳበሪያ ወስደው ወደ አርሶ አደሩ ማድረስ አለባቸው። ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የማድረስ ጉዳይ አንገብጋቢና የሌሎችን ዕገዛ የሚፈልግ ነው።

የማዳበሪያ ጉዳይ የእያንዳንዱ ዜጋ ጉዳይ በመሆኑ በወቅቱ አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስና ምርታማነት መጨመር እንዲያስችል ሥርጭቱ ላይ እየሠሩ ያሉት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጊዜን መሠረት ያደረገ ፈጣን የሥርጭት ሥራ ሊሰሩም ይገባል። ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ማሰራጨት እየተቻለ ማዳበሪያን መጋዘን ውስጥ ማስቀመጡ ለተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት አመቺ በመሆኑ ይህ ተጣርቶ ሕጋዊ ርምጃ መወስድም እጅጉን ተገቢ ነው።

መገናኛ ብዙሃንም ሙያው እንደሰጣቸው ኃላፊነት ግብዓቱ ለአርሶ አደሩ በአግባቡ መድረስ አለመድረሱን መከታተልና ማጣራት አለባቸው። በየዞኑ ወደሚገኙ የግብርና ጽሕፈት ቤቶች እየደወሉና በአካል በመገኘት በየቀኑ ዜና በመሥራት መረጃ መስጠት አለባቸው። አርሶ አደሩንም ማነጋገር የሚጠበቅባቸው ተግባር ነው።

‹‹ለመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ ያህል የአፈር ማዳበሪያ ደርሷል፤ በመጋዘንም አለ›› የሚለው መልስ ብቻውን በቂ አይደለም። ብዙ ጊዜ እንደታዘብነው አሁን እያየነው ያለው ማዳበሪያ ጊዜው ሲቃረብ ክንፍ አውጥቶ የበረረ እስኪመስል ድረስ ይጠፋልና አሁኑኑ ለአርሶ አደሩ በተተመነለት ዋጋ ሊቀርብለት ይገባል።

የግብርና ምርትና ምርታማነት ካለበቂ ግብዓት አይታሰብም። የኢኮኖሚ መሠረቷን ግብርና ላይ ያደረገች ሀገር ደግሞ የእርሻ ሥራው ሊደርሰው የሚገባው ግብዓት አያጠያይቅም። የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ደግሞ መሠረታዊ ናቸው። በየዓመቱ ለእርሻ ሥራ የአፈር ማዳበሪያ የሚጠይቀው አርሶ አደር በተገቢና በተመጣጣኝ ዋጋ ማሳው ላይ ሊቀርብለት ይገባል።

ያለፉት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያ አሻጥሮች፣ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች፣ የግል ጥቅም አሳዳጅ ደላሎች እኩይ ተግባር ዘንድሮ እንዳይደገም ወገብን ጠበቅ አድርጎ መሥራት የግድ ይላል። መንግሥትም ከፍተኛ ወጪ መድቦና በእቅድ ቀድሞ ከውጭ ወደ ሀገር እንዲገባ ዋጋ የሚከፍልበት እንደመሆኑ እያንዳንዱ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት በጥብቅ ሥርዓት የሚመራ ከአሻጥረኞች የፀዳና ታች የአርሶ አደሩን ኪሱን በማይጎዳ፣ ምርትን በተሻለ ማምረት በሚያስችል መንገድ ሊፈፀም ይገባል።

የአፈር ማዳበሪያ አጀንዳ እንዲሁ ጉንጭ ለማልፋት የሚገለፅ ሳይሆን በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ ባለመሰራጨቱ በሚያስከትለው ችግር ተያያዥ አንዱ እንቅፋት ሌላውን የሚያስከትል በመሆኑ ነው። ለአብነትም በወቅቱ ካልደረሰ በቂ ምርት ከማሳ እንዳይሰበስብ፣ አምራች ከሸማች መሀል ሽንቁር ፈጥሮ የምግብ ዋጋ ሰማይ እንዲታከክ፣ የኑሮ ውድነቱም እያንዳንዱ ጓዳ እንዲገባ ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ያለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ተግዳሮች የሥርጭት ሂደቱ ባስከተለው ክፍተት ፈተናውን አይተነዋልና ከግምት የዘለለ ርግጥኝነትን አሳይቶን አልፏል። ስለዚህም ካለፈው ስህተት መማር የብልህ ነው። በርግጥ እየጣለ ያለው ዝናብም ለበልግ እርሻ አመቺ በመሆኑ በቂ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እንዲቀርብ ይጠበቃል።

ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ብቻ ሳይሆን የት ደርሷል፣ እንዴት እየተዳረሰ ነው፣ በማን እየተሰራጨ እንደሆነ የቅርብ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። የአፈር ማዳበሪያውን ከግብርና ሥራ ውጭ የሚጠቀሙና ሕገ ወጥ ተግባራት የሚፈፅሙ መኖራቸው ከልምዳችን አውቀነዋል። እናም ጥብቅ የክትትል ሥራ ያስፈልገዋል። ግብርና ሚኒስቴርም የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ብቻ ሳይሆን ሥርጭቱ ላይ መሥራት ይጠበቅበታል።

ከሁሉ በላይ ግን ከ85 ሚሊዮን በላይ በግብርና የሚተዳደር ሕዝብ ያላት፣ የወጪ ንግዷ የአንበሳ ድርሻ የግብርና ውጤቶች ለሆኑባት፣ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መግባ ለምታድር ሀገር ከምንም ነገር በፊት የማዳበሪያ ፋብሪካ ያስፈልጋታል። ለዚህ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን ነው።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You