የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋዮች /ካፒታል/ ገበያ በካፒታል ገበያ አዋጅ መሠረት በኢትዮጵያ መንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የተቋቋመ የመጀመሪያው ኩባንያ ነው:: የገበያው ዋና ዓላማ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማሳለጥ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ማበረታታት እና ለኢትዮጵያውያን ጥሪት (ሀብት) መፍጠር ነው::
ገበያው ድርጅቶች ካፒታል የሚሰበስቡበትን መድረክ በመፍጠር የኢንቨስትመንት ዕድል በማመቻቸት እንዲሁም የድርጅቶች መልካም አስተዳደርና ግልጽነትን በማበረታታት ገበያው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የለውጥ ጉዞ ላይ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግንም ያለመ ነው::
ገበያው የተቋቋመው በወርሃ ጥቅምት 2016 ዓ.ም ሲሆን፣ መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል የ25 በመቶ የተፈቀደ ካፒታል ድርሻ ሲይዝ፣ የግል ዘርፉ ደግሞ ቀሪውን 75 በመቶ ድርሻ የያዘ ነው:: በዚህም መሠረት ካፒታል የማሰባሰብ ሥራው ተከናውኗል::
በካፒታል የማሰባሰብ ሂደት የታየው ከፍተኛ ተነሳሽነትና ፍላጎት እንዲሁም ርብርብ ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለችው የፋይናንስ ዘርፍ ልማትና ኢኮኖሚ የገበያው ተግባራዊ መሆን ዓይነተኛ ድርሻ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎችም ይናገራሉ::
የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለገበያው የሚያስፈልገውን ሀብት የማሰባሰብ ሥራ ሂደት በስኬት መጠናቀቁን አስታውቋል:: በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው፤ ገበያው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ የሀብት ማሰባሰብ ሥራውን ከታቀደው በላይ ማሳካት ተችሏል፤ ይህን ካፒታል የመሰብሰብ ሥራም በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ ተችሏል:: በዚህም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ተሳትፈዋል::
የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል እንዳሉት፤ ገበያው በካፒታል ገበያ ሥርዓት ውስጥ ማዕከላዊ የሚባል ዋና ሚና ይጫወታል፤ በመንግሥት በኩል ገበያውን የማቋቋም ኃላፊነት የወሰደው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሲሆን፣ እሱም የ25 በመቶ ካፒታል ድርሻውን ጨምሮ ገበያውን የማቋቋም ኃላፊነቱን ተወጥቷል::
የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ በበኩሉ ቀሪውን 75 በመቶ ካፒታል ከግሉ ዘርፍ የማሰባሰብ ኃላፊነቱን በመወጣት የሀብት ማሰባሰብ ሥራውን በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል ሲሉ ዶክተር ጥላሁን አስታውቀዋል:: ለዚህም የውጭ የኢንቨስትመንት አማካሪዎችን በመቅጠር ጭምር መሥራቱን ጠቅሰው፤ የአዋጭነት ጥናት፣ የቢዝነስ ፕላንና ሌሎች የቴክኖሎጂ ፍላጎቶችና ኩባንያውን ለማቋቋም የሚያስፈልጉ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይልና የሕግ ሥርዓቶችን የመሥራት ተግባሮች መከናወናቸውን ተናግረዋል::
ኩባንያው በተቋቋመ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የኩባንያው ቦርድ በፍጥነት እየተገናኘ የካፒታል ማሰባሰብ ሥራውን ሲሰራ እንደቆየ አመልክተው፣ በዚህም በአጠቃላይ የተገኘው ውጤት አስደሳች እንደሆነና ለመሰብሰብ ከታቀደው ካፒታል 631 ሚሊዮን ብር (11.07 ሚሊዮን ዶላር) በላይ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር (26.6 ሚሊዮን ዶላር) ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል:: ይህም የዕቅዱን ከ220 በመቶ በላይ የሚበልጥ ሲሆን፤ በዚህም 48 በፋይናንስና ከፋይናንስ ውጭ ባሉ ዘርፎች የተሰማሩ ተቋማዊ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች መሳተፋቸውንም አስታውቀዋል::
ዶክተር ጥላሁን እንዳብራሩት፤ ከእነዚህም መካከል በዋናነት 16 የሀገር ውስጥ ባንኮች፣ 12 ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና ሌሎች 17 ከፋይናንስ ተቋም ውጭ ያሉና በአምራች ኢንዱስትሪዎች የተሰማሩ ተቋማት ተሳትፈዋል:: ከውጭ ባለሀብቶች መካከልም የናይጄሪያ ትሬድ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ባንክ ግሩፕ እና ሌሎች ኩባንያዎችን ጨምሮ በጋራ 250 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ገንዘብ ተሳታፊ የሆኑ ድርጅቶች ናቸው::
ይህም ትልቅ ውጤት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ጥላሁን፤ በተለይም ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በዋናነት ከተሰራው የሀብት ማሰባሰብ ሥራ በላይ አጋርነትን ለመፍጠር የተሄደበት ረጅም ርቀት ውጤታማ እንደነበር ጠቅሰዋል:: በዚህም ከተቋማቱ ጋር በተደረጉ የተለያዩ ውይይቶች የመዋዕለ ነዋዮች ገበያን ምንነት እንዲረዱ ዕድል መስጠቱን ተናግረው፣ ኢንቨስትመንቱም ከ10 ሚሊዮን እስከ 150 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል::
እነዚህ ባለሀብቶች የሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ባለቤት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አገልግሎት አቅራቢ እንዲሆኑ ፍላጎት አለ ሲሉ የጠቀሱት ዶክተር ጥላሁን፤ አሁንም ቢሆን የመዋዕለ ነዋይ ሰነዳቸው በካፒታል ገበያ ላይ ሙሉ ለሙሉ መተማመን እንዳላቸውና ለሌሎች አገልግሎቶችም ዝግጁ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው ብለዋል:: ገበያው በተለይም አገናኝ አባላት የሆኑ ብሮከሮች እንደሚያስፈልጉት አመልክተው፣ አገናኝ ሆነው የመምጣት ዕድሎች እንዳላቸውም አስረድተዋል::
‹‹የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ተስፋ ያለውና ብዙ ሥራ ሊሰራበት የሚገባ ነው›› ያሉት ዶክተር ጥላሁን፤ አብዛኞቹ ባለሀብቶችም ይህንኑ በመረዳት የአጭር ጊዜ ትርፍን ሳይመለከቱ ስትራቴጂክ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ ኢንቨስት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል:: ስትራቴጂክ ድጋፍ ወይም ስትራቴጂክ ኢንቨስተር ማለት ደግሞ በአጭር ጊዜ ከሚገኝ የግል ጥቅም በላይ ሀገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ማለት እንደሆነ አብራርተው፣ ለዚህም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ኩባንያዎች ከፍ ያለ የካፒታል ፍላጎት ባሳዩ ጊዜ በገበያ ሥርዓት ውስጥ ገብተው መገበያየት ይችላሉ:: ይህም ለእያንዳንዱ ኩባንያ እሴት እንዲጨምር ያስችለዋል:: ከዚህም ባለፈ የፋይናንስ ተቋማት ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትና ለማሻሻል እንዲሁም ለአዳዲስ ጀማሪ የፋይናንስ ተቋማት ጭምር በር ይከፍታል፤ የፋይናንስ ተቋም ላልሆኑ ድርጅቶችም እንዲሁ ካፒታል ገበያ የረዥም ጊዜ የፋይናንስ ማግኛ አማራጭ ሆኖ ያገለግላል::
‹‹በአብዛኛው የአክሲዮን ገበያ ሽያጭም ሆነ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ዋጋን የሚወስነው ገበያው ቢሆንም ኩባንያው ቁጥጥር ያደርጋል›› ያሉት ዶክተር ጥላሁን፤ ቁጥጥር የሚያደርገውም በሁለት ዓይነት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል:: አንደኛው ሁልጊዜ ገበያው ሲጀመር ከዚህ ዋጋ በላይ እንዳይጨምር እንዳይቀንስ በማለት ወስኖ ሊጀምር ይችላል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህም ተገበያዮች በምን ያህል የዋጋ መጠን እንደሚገበያዩ አውቀው እንዲጀምሩ ዕድል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል::
ሌላው ከሚሸጡ አክሲዮኖች ጋር የተገናኘ ልዩ የሆነ የዋጋ ገደብ ሊወጣላቸው እንደሚችልም ጠቅሰው:: ይህም ብዙ ጊዜ በታዳጊ ሀገራት የተለመደ ነው ብለዋል:: ገበያው ሲጀምር የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ዋጋን በመቆጣጠር ደህንነቱ የተጠበቀ የገበያ ሥርዓት እንዲሰፍን ማድረግ ዋነኛ ሥራው እንደሆነ ገልጸዋል::
የአክሲዮን ሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ሽያጭን በተመለከተ በቀጣይ የቴክኖሎጂ፣ የልምድ ልውውጥ ማድረግና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል ያሉት ዶክተር ጥላሁን፤ በተለይም ገበያው ላይ መጥተው ለሚሳተፉ ኩባንያዎች ስለ ገበያው ሥርዓት ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠርን፤ ባለሀብቶችንም እንዲሁ ማስተማርን ይጠይቃል ብለዋል::
እሳቸው እንዳስታወቁት ግንዛቤ መስጠቱ ወይም ትምህርቱ በዋናነት ቁጠባን ለማስለመድ ሲሆን፤ ለአብነትም ዛሬ ላይ በትንሹ ከ5000 እስከ 15000 ብር ካወጣ፣ በቀጣይ ይህ ገንዘብ ቢያንስ አንድ አክሲዮን ሊያስገዛ እንደሚችል በማስረዳት በተለይም የረጅም ጊዜ የቁጠባ መንገድ የለንም የሚሉ ወጣቶች ከአምስትና አስር ሺ ብር ጀምረው እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ከመሳሰሉ ተቋማት አክሲዮኖችን መግዛትና ከኩባንያው ዕድገት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ማስተማርና ማሳወቅ ይጠበቃል::
ስለዚህ አሁን ላይ ጊዜው ለኢንቨስተሮች የቁጠባ ጊዜ ሲሆን፤ ለአገልግሎቶች ደግሞ የዝግጁነት ጊዜ ነው:: ስለዚህ ኩባንያዎች ገበያውን ለመምረጥ ሳይሆን የሚዘጋጁት ለራሳቸው የፋይናንስ ፍላጎት፣ የኮርፖሬት አደረጃጀታቸውን ለማሻሻል፣ ዋጋቸውን ለማሻሻልና ካፒታል በቀላሉ መሰብሰብ ሲያስችላቸው እሱን አጥንተው ወደ ገበያው ለመምጣት ይሆናል::
ለዚህ ዝግጅትም ድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ዶክተር ጥላሁን፤ በተለይም የመንግሥት የልማት ድርጅት ከነበሩ አምስት ኩባንያዎች ተመርጠው በጋራ መሥራት እንደተቻለና ዝግጁነታቸውን ለማገዝም ድጋፍና ክትትል ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል:: አምስቱ የልማት ድርጅቶችም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተቀጥያ የሆኑ መስራች ኩባንያዎች ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ናቸው::
የካፒታል ገበያ ሥርዓት ሲዘረጋ ዋና መርሆው ኢንቨስተሮችን የመጠበቅ ሥራ ነው የሚሰራው ያሉት ዶክተር ጥላሁን፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች መሠረት ለሕዝብ አክሲዮን እየሸጡ ያሉና ለሕዝብ የዕዳ ሰነድ እየሸጡ ያሉ ኩባንያዎች ማሟላት ያለባቸውን ሕግ የሚያወጣና የሚቆጣጠር እንደሆነ ነው ያስረዱት:: ስለዚህ ተቋማቱ ወደ ኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በመሄድ አክሲዮናቸውን ያስመዘግባሉ:: ካስመዘገቡ በኋላም ገበያው ላይ አክሲዮኖቻቸውን የሚገበያዩ ኩባንያዎች ደግሞ ተጨማሪ የገበያው ሥርዓት የሚስቀምጣቸውን መረጃዎች ለገበያው ያቀርባሉ ሲሉ አብራርተዋል::
ለአብነትም ለሕዝብ አክሲዮን የሸጠ አንድ ኩባንያ የፋይናንስ ሪፖርት አያቀርብ ይሆናል:: እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ግን በዋና ገበያ ላይ የተመዘገበ በመሆኑ ቢያንስ በዓመት አራት ጊዜ የፋይናንስ ሪፖርቶችን እንዲሰጥ እንዲሁም በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ኦዲትድ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት መስጠት ይጠበቅበታል:: የእነዚህ እና መሰል ሕጎች ዋና ዓላማም ኢንቨስተሮች ስለ ኩባንያው የተሻለ መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው ይህም ኩባንያዎችን የሚደግፍና የራሳቸውን የውስጥ አሠራር እንዲያሻሽሉ ያደርጋል ሲሉ አመልክተዋል::
ካፒታል ገበያ ባንኮችን፣ የንግድ ድርጅቶንችን እና መንግሥትን በማገናኘት እንደ አክሲዮን፣ ቦንዶች እና ተዋጽኦዎች ያሉ የተለያዩ የፋይናንሺያል መሳሪያዎችን በማውጣት እንዲሁም በመገበያየት የረጅም ጊዜ ገንዘብ የሚሰበስቡበት መድረክ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በሌላ በኩል የባንክ ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ በቁጠባና ተጠቃሚዎች እና በተበዳሪዎች መካከል ያለውን የገንዘብ ፍሰት በማመቻቸት፣ አስፈላጊ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በመስጠት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚደግፍ እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ::
ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት ካፒታል ገበያ የተባለውን ትልቅ ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች የምትገኘውም በዚሁ ምክንያት ነው::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የስቶክ ማርኬት አለመኖሩ በድርጅቶች መካከል ውድድርና ፈጠራ እንዳይዳብር ሆኗል፤ ስቶክ ማርኬትን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት የውድድርና የፈጠራ አቅም ከፍተኛ ፍጥነት አለው:: ስለዚህ ካፒታል ማርኬትን በሀገሪቱ ተግባራዊ በማድረግ ይጠበቃል:: በተለይም የፋይናንስ ተቋማትና የተለያዩ ድርጅቶች ለዚህ ተግባር የመሪነቱን ሚና የሚወስዱ በመሆናቸው መንግሥትን ጨምሮ ከተቋማቱ ብዙ እንደሚጠበቅ ይታመናል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም