በየዓመቱ በቼክ ሪፐብሊክ በሚካሄደው የፕራግ ማራቶን በሳምንቱ መጨረሻ ለ30ኛ ጊዜ ሲካሄድ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ውድድሩን በድል አጠናቀዋል። ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከፍተኛ ፉክክር አስተናግዶ በወንዶች አትሌት ለሚ ብርሃኑ፣ በሴቶች ደግሞ አትሌት በዳቱ ሂርጳ አሸናፊዎች ሆነዋል።
በዚህ የውድድር መድረክ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል አንድ ብሎ የጀመረው ውድድሩ በጀመረበት እአአ በ1995 ነበር። የድሉ ባለቤትም አትሌት ቱሞ ቱርቦ ሲሆን፤ ዘንድሮ የተመዘገበውን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን በፕራግ ማራቶን ከአስር ጊዜ በላይ አሸናፊዎች ሆነዋል። ለመጨረሻ ጊዜ እአአ 2019 በወንዶች አትሌት ዳዊት ወልዴ ሲያሸንፍ፤ በሴቶች ወርቅነሽ ኢዴሴ ያለፈው ዓመት ባለድል መሆኗ የሚታወስ ነው።
ውድድሩ እአአ በ2020 እና በ2021 በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከስት ምክንያት ከሁለት ዓመት መቋረጥ በኋላ ወደ ፉክክር ከተመለሰ ወዲህም ቢሆን ኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች በድል ጎዳና መጓዝ ችለዋል። ስምንት ሴት አትሌቶች በተሰለፉበት የአሁኑ መድረክ፣ በዳቱ ሂርጳ ያስመዘገበችው ውጤት በሴቶች የተገኘ ሶስተኛ ተከታታይ ድል ለመሆን ችሏል። እንደተለመደው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከኬንያዊያን ጋር ብርቱ ፉክክር ቢገጥማቸውም አትሌቷ ውድድሩን በድል ማጠናቀቅ ችላለች። በዳቱ ሂርጳ ኬንያዊቷን ዶርካስ ቱኢቶክን አስከትላ በመግባት ነው የበላይነቱን የያዘችው።
አትሌቷ ከዚህ ቀደም ባደረገቻቸው ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች በተደጋጋሚ ድል መቀዳጀት የቻለች ሲሆን እአአ በ2018 በፍራንክፈርት ማራቶን 2፡21፡32 በሆነ ሰዓት በመግባት ሶስተኛ ደረጃን ስትይዝ፣ ያስመዘገበችው ሰዓትም የግሏ ምርጥ በመሆን ተይዞላታል። ከ5 ዓመታት በፊት በቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ በተካሄደው ውድድር የተመዘገበው 1፡12፡11 የሆነ ሰዓት ደግሞ በግማሽ ማራቶን የገባችበት የግሏ ቀዳሚ ሰዓት መሆን ችሏል።
በርካታ አትሌቶች ለድሉ ተጠብቀው 26 አትሌቶች ደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተው ባጠናቀቁት የፕራጉ ፍክክር 2፡23፡41 ሰዓት በማስመዝገብ ውድድሯን በበላይነት አጠናቀለች። ብርቱ ተፎካካሪዋ የነበረችው ኬንያዊቷ አትሌት ዶርካስ ቱኢቶክን 2፡24፡50 በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። አትሌት ሸዋረግ አለነ ደግሞ 2፡27፡32 በሆነ ሰዓት ገብታ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሯን ፈጽማለች። ጽግነሽ መኮንን፣ አፌራ ጎድፋይ፣ ሙሉሃብት ጸጋ እና ዝናሽ ደበበ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ የኢትዮጵያዊያኑን የበላይነት አስመስክረዋል። የአምናዋ የመድረኩ ባለድል አትሌት ወርቅነሽ ኢዴሳ 2፡20፡42 ሰዓት በማስመዝገብ ከኢትዮጵያዊያን የመድረኩ አሸናፊ አትሌቶች የተሻለውን ሰዓት ይዛ ትገኛለች።
በወንዶች መካከል በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ፉክክር አትሌት ለሚ ብርሃኑ በበላይነት በማጠናቀቅ ውድድሩን ማሸነፍ ችሏል። አትሌቱ ከኬንያዊያን እና ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች የገጠመውን ብርቱ ፉክክር በመርታት ኬንያዊያኑን በማስከተል በቀዳሚነት አሸንፏል። ውድድሩን ለማጠናቀቅም 2 ሰዓት ከ 08 ደቂቃ ከ 44 ሴኮንድ ፈጅቶበታል። አትሌቱ የመጀመርያውን የማራቶን ውድድሩን የሮጠው እአአ በ2014 ዙሪክ በተካሄደ ሩጫ ሲሆን 2፡10፡40 በመግባትም አሸናፊ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላም በዱባይ ማራቶን አስገራሚ ብቃት በማሳየት፣ ቀድሞ ዙሪክ ላይ አስመዝግቦ የነበረውን ሰዓት ከ 5 ደቂቃ በላይ በማሻሻል ማሸነፍ ችሎ ነበር። በብዙ የጎዳና ላይ ውድድሮች በመሳተፍና በማሸነፍ ብዙ ድሎችን ማቀዳጀት እንዲሁም ከፍተኛ ልምድን ማካበት ቻለው አትሌቱ የፕራግ ማራቶንም አንጸባራቂ ድሉን ቀጥሏል። በትልልቅ የዓለም የጎዳና ላይ ወድድሮች ያካበተው ልምድና የአሸናፊነት መንፈስ ፉክክሩን ተቋቁሞ ለድል እንዲበቃ አስችሎታል። አንጋፋውን የቦስተን ማራቶንን ጨምሮ በትልልቅ የጎዳና ውድድሮች በማሸነፍ ከዓለም ምርጥ 15 የረጅም ርቀት ሯጮች ተርታ ለመሰለፍ የቻለበት ወቅትም ነበር። 2 ሰዓት ከ 04 ደቂቃ ከ33 ሴኮንድ የማራቶን የግል ምርጥ ሰዓቱ ሲሆን 1 ሰዓት ከ 01 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ የግማሽ ማራቶን የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።
ይህንን ውድድር ሲያሸንፍም ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች የተመዘገበ 7ኛውን ፈጣን ሰዓት መያዝ ችሏል። የእሱ ተፎካካሪ የነበረው ኬንያዊው አትሌት ኪፕሮኖ ኪፕኬሞኢ በ2 ደቂቃዎች ዘግይቶ በማግባት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። ኮጎ ጆሹአ ከኬንያ 2፡10፡51 ሰዓትን አስመዝግቦ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ጨርሷል። 2019 አትሌት ዳዊት ወልዴ ሲያሸንፍ ያስመዘበው 2፡06፡18 ሰዓት በኢትዮጵያዊያን ወንድ አትሌቶች የተመዘገበ የቦታው ፈጣን ሰዓት በመሆን ተመዝግቧል።
በመድረኩ ከዚህ ቀደም በወንዶች አትሌት ቱሞ ቱርቦን ጨምሮ ዳሬሳ ጪሚሳ፣ ገብረጻዲቅ አብረሃና ዳዊት ወልዴ ድል ማድረግ ችለዋል። በሴቶች ላይላ አማን፣ ፍሬህይወት ዳዶ፣ የብርጓል መለሰ፣ በቀለች ጉደታ እና ወርቅነሽ ኢዴሳ ያሸነፉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በመሆን ተመዝግበዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2016 ዓ.ም