ለዓይን የምታሳሳ ልጅ ናት። ከአፏ የሚወጡ የተቆራረጡ ድምፆች እንጂ ትርጉም ያለው ቃል መናገር አትችልም። ፀጉሯ መልኳ፤ ካላት የእንቅስቃሴ ችግር ጋር ተደምሮ ውስጥን የሚሰረስር የማዘን ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። ይህች ቆንጆ ልጅ ሰሟ ሄለን ይባላል። ሄለን በማህበሩ ውስጥ ከሚኖሩት ተደራራቢ የጤና ችግር ካለባቸው ልጆች መካከል አንዷ ናት። የሄለን ለየት ያለ ባህሪዋ አሳዳጊዎቿ ከሌሎች ህጻናት ቀድመው ሂሉዪ የኔ ቆንጆ ብለው ሰላም ካላልዋት ታለቅሳለች። አሳዳጊያቸው ሲስተር አሳየች ይርጋ ከዚህ ባህሪዋ የተነሳ ቀኑብሽ የሚል ቅፅል ስም ሰጥታታለች።
በተጨማሪ ሄለንን ጨምሮ ሁሉም ልጆች እናታቸውን ሲስተር አሳየችን በሽታ ይለይዋታል/ ያውቋታል። እናም ሄለን ሲስተር አሳየች ወደ አጠገቧ ከቀረበች ልብሷን መያዝ፤ በጣም እቅፍ አድርጋ መያዝ ትወዳለች። ይህ ታድያ የሚያሳየው አንድ እናት አርግዛና ወልዳ ከምታገኘው የወላጅነት ፍቅር በተጨማሪ ላልወለደችው፣ የስጋ ትስስር ከሌላት ልጅ ጋር በከባድ ሁኔታ መተሳሰር እንደሚቻል የሚያሳይ አስደናቂ የፈጣሪ ጥበብ ነው።
ሄለን አትናገርም፣ አትሰማም፣ አትሄድም፣ ተደራራቢ የጤና ችግሮች አሉባት። ይህ ሁሉ ቢሆንም ቅሉ እናቷ ማን እንደሆነች ማወቋና የወላጅነትና የልጅነት ትስስርና ቁርኝት ማግኘቷ በጣም ልብ የሚነካና ሰውኛ ስሜት የሚፈጥር ነው። ለማንም ሰው ቢሆን ተደራረቢ የጤና ችግር ያለው አንድ ልጅን ለመያዝ በሚቸገርበት በዚህ ዘመን ንፁህ የእናትነት ፍቅር እየሰጠች በርካታ ልጆችን የምታሳድገው ሴት፤ ካልወለደቻቸው ልጆች ጋር እውነተኛ እናታዊ ቁርኝት ካላት ሴት ጋር ቆይታ አድርገናል።
በርካታ ሞግዚቶች፤ ፅዳት ሰራተኞች የሞሉበት በፅዳት የተያዙት ክፍሎች ለዓይን ይስባሉ። ልጆቹ በራሳቸው ማድረግ የሚችሉት ነገር ባለመኖሩ ሁሉም የሰውን ድጋፍ ይሻሉ። ሙሉ ለሙሉ ንፅህናቸው ተጠብቆ በልተው ጠጥተው፤ ደህንነታቸው ተጠብቆ መዋል ማደራቸውን እናታቸው ሲሰተር አሳየች ትከታተላለች። የእነዚህ ልጆች እናት፤ ሌሎች እናታቸው ጋር ሆነው ለሚታገዙ ከሁለት መቶ ሃምሳ በላይ ወላጆች ቀኝ እጅ የሆነችውን ሲስተር አሳየች ይርጋ ለዛሬው የህይወት እንግዳ አድርገን አቅርበናታል።
ከውልደት እስከ ትምህርት ቤት
ሲስተር አሳየች ይርጋ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። ከወይዘሮ አለምነሽ ካሴና ከአቶ ይርጋ ተክለማርያም በርካታ ልጆች መካከል አንዷ የሆነችው ሲስተር አሳየች የሕፃንነት ዘመኗ አልቆ እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ አቃቂ በሚገኘው በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ገብታ ተማረች።
ከልጅነቷ ጀምራ የእግዚአብሔርን ቃል አውቃና አጥንታ ያደገችው ሲስተር አሳየች ፤ መልካምነት ከነፍሷ ጋር አብሮ እንዳደገ ትናገራለች። በትምህርት ቤታቸው ለየት ያለ መመሪያ እንደነበረና መመሪያው ከልቧ እንደማይጠፋ ትናገራለች። መመሪያውም ልብን አእምሮንና እጅን በሶስት መአዘን ቅርፅ አስተሳስሮ መስራት እንደሚገባ የሚናገር መሆኑን ታስረዳለች። ያ ማለት በጎ ማድረግን፤ ቅንነትንና መታዘዝን፤ ለእግዚአብሔርን መታዘዘን ጨምሮ መልካም ስነ ምግባርን መመሪያ አድርጎ የመኖር ሃሳብ ያለው ነው። እነዚህን ሶስት ነገሮች ከተቀናጁ ለማህበረሰቡ፤ ለሀገርና ለራስ ለወገን በጎ ነገርን ማበርከት የሚችል ትውልድ የሚኖር መሆን ትናገራለች።
በልጅነቷ መዝሙሮችን፤ መንፈሳዊ ድራማዎችና ግጥሞችን እየፃፈች ማቅረብ የምትወድ ልጅ እንደነበረች ትናገራለች። ልጅነቷንና የአፍላ ወጣትነት ጊዜዋን በመልካም ቤተሰብና ትምህርት ቤት መልካምነትን እየተማረች ያደገችው ልጅ በወቅቱ ከፍተኛ ወጤት በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባች። ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃን ማጠቃለያ ፈተና ወስዶ ሶስት ነጥብ ማምጣት በጣም ትልቅ ውጤት እንደነበረ የምትናገረው ሲስተሯ፤ በወጤቷ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባት ቻለች። በውጤቷ ዩኒቨርሲቲ መግባት ብትችልም እሷ ግን የልጅነት ህልሟ ነርስ መሆን ስለነበር ከፍቷት የነበረ መሆኑን ታስታውሳለች።
በወቅቱ ነርሲነግ ኮርስ ይሰጥ የነበረው ጎንደር ብቻ ስለነበር ቤተሰቦቿ ከእነሱ ርቃ መሄድ እንደማትችል ነግረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተመደበችበት መማር ጀመረች። የመጀመሪያው አመት ትምህርት አልቆ ሁለተኛው ሲመጣ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተመደበች። ታሪክ ጭራሽ ከእርሷ ህልም ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ዝም ብላ ሌሎች አማራጮችን መመልከት ጀመረች። በልጅነቷ የምታያቸው ፊልሞች ላይ የካቶሊክ ሲስተሮች በጦር የተጎዱ ሰዎችን ሲያክሙ፤ በተለያየ ሁኔታ ያሉ ህሙማንን ሲረዱ መመልከቷ እንደእነርሱ መልበስ መናገር በአጠቃላይ እንደእነርሱ የመሆን ፈላጎት እንዳሳደረባት የምትናገረው ሲሰተር አሳየች፤ በሙያ ሰውን ረድቶ የማዳነ ህልሟን የሚተካ ምንም አይነት የትምህትት ክፍል አላገኘችም ነበር።
ያንን ነጭ ልብስ ለብሶ ከማገልገል የበለጠ ምንም ነገር የማይታያት ወጣት የመመዝገቢያ ቀን እንዳያልፍባት ታሪክ ዲፓርትመንት ብትመዘገብም አሁንም ግን ህልሟን የምተሳካበት የልቧ የሚሞላበት አማራጭ ማየት አላቆመችም ነበር። ፈጣሪም ህልሟን ኑሪ ሲላት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነርስ እንደሚፈልግ የሰማች አብሮ አደግ ጓደኛዋ ትነግራታለች። በወቅቱ አምጡ የተባሉትን የትምህርት ማስረጃ በሙሉ ይዘው የቀረቡት ሲስተር አሳየችና ጓደኞቿ ከተመዘገቡት አምስት መቶ ሰዎች መካከል ተወዳድረው ያለፉት ስምንት ሰዎች መካከል ሆኑ። ከዛም አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የነርስነት ትምህርቷን ተማረች። በወቅቱ ነርስ መሆን የነፍሷ ጥሪ የነበረው ወጣት በጥሩ ውጤት ትመህርቷን አጠናቀቀች። በመቀጠል በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚሰራው ትኩረት ለሴቶችና ለህፃናት የሚል ተቋም ካቋቋመች በኋላ በሶሺዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታ ሶሺዮሎጂስት ለመሆን በቃች።
ከአባት ወደ ልጅ የታላለፈ ደግነት
በርካታ ልጆች ያደጉበት ቤት ውስጥ ያደገችው ሲስተር ገነት አባቷ በልጅነቷ ያደርጉት የነበረውን የበጎነት ስራ መቼም እንደማትረሳው ትናገራለች። በልጅነታቸው አባት ለለቅሶም ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮች ገጠር ደረሰው ሲመለሱ አሳዳጊና ረዳት የሌላቸውን ልጆች ይዘው ይመጡ እንደነበር ታስታውሳለች። ከአንድ እናትና አባት የተወለዱ ልጆች አስር ቢሆኑም አባታቸው በየጊዜው ይዘዋቸው የሚመጡ ልጆች ተጨምረው የቤተሰቡ ቁጥር ወደ ሃያ ሁለት ደርሶ፤ ከእነርሱ መሃል ሆና ማደጓን ትናገራለች። ቤት ውስጥ የሚያግዙ ሰዎች ፤ አባቷ የነበራቸው የእህል በረንዳ ንግድ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ሲጨማመሩ ሰፊ ቤተሰብ አብሮ መኖሩ እና በጋራ ማደግ የተለያዩ ትርፎች እንደነበሩት ታብራራለች።
ቤታቸው ውስጥ የሚኖሩ ልጆችም ሆኑ ቤት ውስጥ የተወለዱት በእኩልነት በመተጋገዝ መንፈስ ማደጋቸው፤ አንዱ ባለቤት አንዱ የጥገኝነት ስሜትን የያዘ አለመሆኑ ሁሉም ልዶች በፍቅር አድገው ለቁም ነገር እንዲበቁ እንዳደረገላቸው ትናገራለች። በዓል ሲሆን አባታቸው በሬ አርደው ለተቸገሩ ሰዎች ቅርጫ ያከፋፍሉ እንደነበር የምታስረዳው ሲስተር፤ በበዓል በር ላይ መጥተው ከሚወስዱ ሰዎች በተጨማሪ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ቤታቸው ድረስ በማድረስ መርዳትን ደግነትን ስትለማመድ ማደጓን ትናገራለች።
በእንግድነት ከገጠር የሚመጡትን ሰዎች እግር ማጠብ፤ ምግብ ማቅረብ፤ መኝታን ማዘጋጀት የመሳሰሉ ሰዎችን የመንከባከብ ልምምዶችን ስታደርግ ያደገችው ሲስተር፤ እሷም ሰዎችን መርዳት ህልሟ ሆኖ እስኪሳካ ድረስ መትጋቷን ትናገራለች። ቤት ውስጥ ያለውን ሙያ ጥንቅቅ አድርጎ ከመማር አንስቶ እህል በረንዳ ላይ ያለውን የንግድ ስራ ማገዝ ፤ በትምህርት መጎበዝ ባለው ሰአት ሁሉ መጣጣርና መልፋት ልምምድ ስታደርግ ማደጓን ተናገራለች።
በየእለቱ የሚሰሩ የእህሉን ሂሳብ ተቀብሎ መስራትን፤ እያንዳንዱን እንቅፋት በጥንካሬ ማለፍን፤ ኃላፊነት መሸከምን ፤ ከልጅነቷ ጀምራ ስትለማመድ ቆይታ የሰላች የጠነከረች ባለደግ ልብ ሴት ለመሆን በቃች። ከአባቷ የተማረችውን ደግነት፤ በነርስነት ሙያ ውስጥ የተለማመደችውን ርህራሄ በአንድ አቀናጅታ ለሰው መኖርን ደግነትን የምትሰራበት ተቋም ለመመስረት ስታልም የኖረችው ሲስተር የዛሬ አስራ ሰባት አመት ህልሟን እውን ማድረግ ቻለች።
ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር ምስረታ
ርህራሄ መገለጫዋ የሆነው ሲስተር አሳየች ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር በይፋ ከመመስረቱ በፊት በኤችአይቪ/ኤድስ እና በሌሎች ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት እጆቿን መዘርጋት ጀመረች። የምትኖረው ትንሽ ቤት ተከራይታ ቢሆንም ቤቷ ውስጥ
ከልጅነቷ ጀምራ የእግዚአብሔርን ቃል አውቃና አጥንታ ያደገችው ሲስተር አሳየች፤ መልካምነት
ከነፍሷ ጋር አብሮ እንዳደገ ትናገራለች ጥቂት ልጆችን ለማምጣት ቆርጣ በመነሳት ከምታገኘው ትንሽ ገቢ እያካፈለች ህይወታቸውን ለማስቀጠል መታገል ጀመረች። በእራሷ ጥረት ባላት ትንሽ ገቢ ለመደገፍ የምትሞክራቸው ልጆች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መጣ።
ከሰው ለምና ተበድራ የእለት ጉርሳቸውን ልታቃምስ ብትሞክርም ብዙ ሕፃናት ወደ ተከራየችበት ቤት በመምጣታቸው የተነሳ የቤቱ ባለቤት ቤት እንድትለቅ ነገሯት። ደርሳ ነክታ የማትጨርሰውን ችግር እንደነካካች የተረዳችው፤ ሲስተሯ እንደዚህ አይነት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች አላማዬ ብላ ከተነሳችበት ህልም ሊያስቀራት እንዳይችል መታገል ጀመረች። መቸገር ከሩጫዋ ሳያቆማት ጥንካሬ ሆኗት፤ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ሆነች ። በዚህ ነው እንግዲህ የሕፃናት እና ሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ሁኔታን ለማሻሻል የሚሰራ ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር ከአስራ ሰባት አመታት በፊት አንድ ብሎ የተመሰረተው።
በማህበሩ ያለመችውን ለማሳካት እየታተረች የምትገኘው ሲስተር አሳየች በርካቶች በጥረቷ ህልሟ የተሳካላት ሴት ቢሏትም፣ እስካሁን ያለመችው ህልም ጋር ልትደርስ ባለመቻሏ አልረካችም። በማህበሩ ውስጥ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተጨማሪ ልጆች መርዳት ትፈልጋለች። ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕፃናት ልዩ የሆነ ሁለንተናዊ እንክብካቤ ማዕከል ሠርታለች። ይህ ማእከልም የግራር መንደር ተብሎ ይጠራል። በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው።
ሲስተር አሳየች በገንዘብ ነክ ፈተናዎች ወቅት፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናት እና ፕሮጀክቱን ለመደገፍ የራሷን ቤት ለመሸጥ ተገድዳለች። ሲስተር አሳየች አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን እና የተቸገሩ ሴቶችን በመርዳት የራስ ነፍሷን የምታስደስተው ይህች ሴት ባለትዳርና የሶስት ወንድ ልጆች እናት ነች። ሲስተሯ ከ17 ሺ በላይ ሴቶችንና ሕፃናትን የሰው ፊት እንደ እሳት እየገረፋት ስትረዳና ስትደግፍ ቆይታለች። ይቺ ልበ ብርቱ ሴት በአንድ ማዕከል ውስጥ እያኖረች የእናትነትና የቤተሰብ ፍቅርን እየሰጠች የምታሳድጋቸው ወላጅ እና አሳዳጊ ተንከባካቢ ያልነበራቸው በርካታ ሕፃናቶችም አሏት።
ሲስተር አሳየች ሕፃናቶችን የምታኖራቸው የግለሰብ ቤት ተከራይታ ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈለች ስታኖራቸው የቆየች ቢሆንም፤ አሁን ግን መንግሥት ጋርመንት ግራር ሰፈር አካባቢ በሰጣት ቦታ ላይ አጋዥ አካላትን በማፈላለግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕፃናት ምቹ እና ማራኪ የሆነ ዘመናዊ ቅንጡ ለአካባቢውም እጅግ ማራኪና ሳቢ የሆነ ባለሁለት ፎቅ የሆነውን አኬዢያ ቪሌጅን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብታ 538 የሚደርሱ ሕፃናቶችን እናቶችን የተሻለ ኑሮ እያኖረች እና እየተንከባከበች ትገኛለች።
ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር በማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙትን ወላጅ የሌላቸውን ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ሴቶችን እንዲሁም ተደራራቢ የጤና ችግር ማለትም የአእምሮ እድገት ውስንነት፣ አካላዊና አእምሮአዊ እድገት ውስንነት፣የዓይን ብርሃን ማጣት፣ የመስማት ችግር፣ ሙሉ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሕፃናትና እናቶቻቸውን ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ ህይወታቸው እንዲለወጥ ማስቻልን አላማ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።
ሲስተር አሳየች በሀገራችን ካሉ በጎ አድራጊ ባለ ቅን ልቦች መካከል አንዷና ብዙ ያልተዘመረላት ደግ ሴት ነች። ትኩረት ለሴቶችና ሕፃናት የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥርታ ለ17 አመታት ያህል ጥቃት በሚደርስባቸው ሴቶች እና ተደራራቢ የጤና እክል ያለባቸው ሕፃናት ላይ ትኩረቷን አድርጋ እየሰራች ሲሆን፤ ይህንኑ የበጎ አድራጎት ስራ በስፋት ለመቀጠል አቅዳ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
የነገ ህልም
ይህቺ ልበ ቅን ድምጿን አጥፍታ ትልቅ ስራ እየሰራች ያለች መልካም ሴት አሁንም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ሁለተኛ የሆነውን ባለዘጠኝ ፎቅ አኬዢያን ህንጻ ለመገንባት እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች።
በመሬቱ ላይ ያሉ ሕንፃዎች መገንባት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ትምህርት ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ ሙአለ ሕፃናት፤ ፊዘዮ ቴራፒ አገልግሎቶች የሚሰጥበት ማእከል፤ የአመጋገብ እና የመዝናኛ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይህም ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናት አካላዊ፣ ቁሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ስሜታዊ፣ ትምህርታዊ እና የጤና ፍላጎቶቻቸውን በማሟላት የኑሮ ሁኔታን በእጅጉ ያሻሽላል። ሴትን የሚያበረታታ ማዕከል መገንባት ከልጆቻቸው ጋር እኩል እየተሰቃዩ ያሉ እናቶች ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ እድገትን ያመቻቻል። ይህም ሕፃናት እና እናቶች የተከበረ ህይወት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። የዚህ ህልም ፕሮጀክት እውን መሆን ልዩ ፍላጎት ላላቸው ብዙ ልጆች እና እናቶቻቸው ጥያቄ መልስ ይሆናል።
በዚህ ቤት እናቶች የጤና ምርመራ አድርገው ልጆቻቸው ብዙም ሳይጎዱ ሊወለዱ የሚችሉበት ህክምና ሊኖር እንደሚችል የምትናገረው ሲስተር አሳየች፤ ማእከሉ ለድምፅ አልባዎቹ ድምፅ ሊሆን፤ ትኩረት ለተነፈጋቸው ትኩረትን ሊሰጥ ሰፊ ራይን ሰነቆ የሚሰራ መሆኑን ታስረዳለች።
በዓል በሲስተሯ ቤት
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር ወደ ሁለት መቶ ስልሳ ለሚሆኑ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆችና እናቶቻቸው ይደግፋል። አሁንም የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ ተደራራቢ የጤና ችግር ላለባቸው ከሁለት መቶ ሃምሳ እናቶች ውስጥ መቶ ሰባ አምስት ለሚሆኑ ሕፃናት እናቶቻቸው ዱቄት፣ ዘይት ዶሮ እና እንቁላል እንዲሁም አንድ ሺህ 500 ብር የኪስ ገንዘበ ስጦታን አበርክቷል።
ለስጦታው የሚሆን ገቢ የተገኘው ለተለያዩ ለጋሾች በቀረበ ጥያቄ ሲሆን፤ በተጨማሪም የኦቲዝም ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀ የማስ ስፖርት ማህበሩ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ በርካታ ሰዎች በራሳቸው ዶሮ እንቁላልና ገንዘበ አበረክተዋል። ሙገር ሲሚኒቶ ፋብሪካ በየአመቱ ለአዲስ አመትና ለፋሲካ በአላት ድጋፍ ስለሚያደርግ ለእናቶቹ የሚሰጠው ስጦታ አይነቱ በዛ እንዲል ሆኗል።
በአኬዥያ መንደር ውስጥ ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸው 18 ሕፃናት የሚገኙ ሲሆን፤ በጤና፣ በምግብ፣ በመጠለያ፣ በትምህርት እና የሥነ-ልቦና አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን እዛ ለሚገኙት ልጆች ለጋሾች የሚሰጡት የአመት በአል መዋያ፤ የወረዳ መስተዳድሩ የሚያመጡት በጎችና ሌሎች በዓል ማድመቂያዎች የሚደረጉ መሆኑን ተናግራለች።
ሲስተሯ እና ቤተሰቧ በዓልን የሚያከብሩት በግራር ማእከል ውስጥ መሆኑን የምትናገረው ሲስተር፤ በዓልን በመኖሪያ ቤቷ የምታከብረው ከአስር ሰአት በኋላ እንደሆነ ትናገራለች። በጠዋት ማእከሉ ውስጥ ያሉት ልጆች የበዓላት እለት ልብስ ለብሰው በጠዋት የደረሰውን ለበዓል ማደመቂያ የተዘጋጀ ምግብ በልተው የሚጀምሩ ሲሆን፤ እዛው ያሉ ልጆችና ሰራተኞች ዶሮም በግም መስራት ላይ አብረው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ትናገራለች።
በተቋሙ ተደራራቢ የጤና ችግር ካላቸው ልጆች በተጨማሪ ጤነኛ ልጆች በመኖራቸው የተነሳ፤ ከበዓል ዋዜማ ጀምሮ ሸንኩርት መላጥ፤ ዳቦ መድፋት ሌሎች ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ የሚደረግ መሆኑን ትናገራለች። ይህም የሚደረግበት ምክንያት ልጆቹ የራሳቸውን ህይወት ሲመሰርቱ ትዳር ሲይዙ የሚያውቁትን የበዓል አከባበር ቤታቸው እንዲተገብሩ የሚረዳቸው መሆኑን ታስረዳለች።
በበዓሉ ቀን ምሳ አብረው በልተው ቡና ተፈልቶ ዳቦ ተቆርሶ ማእከሉ ያሉ ልጆች ከተደሰቱ በኋላ የራሷን ቤት እንደምታስታውስ ታስረዳለች። በዚህ ስራ እሷ የበለጠ ተሳትፎ ቢኖራትም እህት ወንድሞቿ እና እናቷ ለበዓልም ሆነ ሌሎች ግዥዎች ላይ የቀኝ እጅ እንደሆኗት ትናገራለች። ቤተሰቦቿ ልጆች በሙሉ አጋር እንደሚሆኑም ትገልፃለች።
ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸውን ልጆች እጅግ አስቸጋሪዎች በመሆናቸው እነሱን ይዘው ያለ ምንም ገቢ የሚኖሩ እናቶችን መደገፍ የሁሉም ማህበረስብ ኃላፊነት ነው ትላለች። ሕፃናቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ሲገለሉ የኖሩ ሲሆን፤ የሚገባቸውን ድጋፍ እና እንክብካቤ ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ለተለያዩ የጤና፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የስነልቦና ቀውስ ተጋላጭ ሆነዋል። ይህንን ለመቅረፍ ደግሞ ሁሉም ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ትላለች።
ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማህበር ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸውን ሕፃናት ማቆያ፣ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ኦሮሚያ ክልል ፣ ሸገር ከተማ፣ ፉሪ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 1 ልዩ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፤ ላለፉት 17 ዓመታት አዲስ አበባን ጨምሮ በአራት ማዕከላት በማህበረሰብ ውስጥ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ድጋፍና እንክብካቤ እንዲሁም የኤች አይ ቪ ስርጭት ለመቀነስ ወደ 12 ሺህ ገደማ የኅብረተሰብ አካላትን ተጠቃሚ እያደረገ መቆየቱን በመጠቆም፤ ለቀጣይ ጊዜም በተሻለ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ማሰባቸውን ታብራራለች።
‹‹ማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን ተደራራቢ ችግር ለመቅረፍ መነሳት ጠንካራ ልብ የሚያስፈልገው ተግባር መሆኑ የማእድ መጋራቱ እለት ተገኝቼ የተመለከትኩ ሲሆን፤ በእለቱ ከልጆቻቸው ጋር በበዓሉ ላይ ተገኝተው የነበሩት እናቶች ለምርቃት ተነስተው ያለ ከልካይ ግድቡን ጥሶ የሚወርደውን እንባቸውን መመልከት ብቻ በቂ ነበር።›› ስትል ትናገራለች።
‹‹ምንም እርዳታ የመከፋታቸውን ጥግ ይዳስሰዋል ተብሎ በማይባል ልክ ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸውን ልጆች የያዙ እናቶች የሚያዝኑ መሆኑ በእለቱ ተመልክተናል።›› የምትለዋ ሲስተር አሳየች፤ የእነርሱ መኖር የልጆቻቸውን እስትንፋስ የሚያቆይላቸው የሚመስላቸው፤ የልጆቻቸውን መዳን በጉጉትና በተስፋ የሚመለከቱ፤ ድህነት በጠንካራ እጁ የሚደቁሳቸውን እናቶች መመልከት የሚያሳምም መሆኑንም ተናግራለች።
ሀዘናቸው ተጋብቶባት ልብ የሚናጥ ጠጋ ብሎ ስለችግራቸው ሲጠየቅ፤ አሳዛኝ ስሜት ውስጥ የሚከቱ እነዚህን ሰዎች ከፈጣሪ በታች ደጋግ ልቦች ያላቸው ሰዎች መኖራቸው መልካም መሆኑን በመጥቀስ እነርሱን ያበርክትልን ትላለች።‹‹ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነውና ይህንን የማህበረስብ ችግር በመረዳት ሁሉም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ይወጣ።›› በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ተናግረው ማሳመን የማይችሉ፤ ለምነው ማግኘት አይደለም የተሰጣቸውን እንኳን በአግባቡ መጉረስ የሚሳናቸውን ማገዝ፤ ልብ በቅንነት ካልሰፋ የማይነካ ነውና በዓልን ከድምፅ አልባዎቹ ልጆቿ ጋር ያሳለፈችውን ይህችን ሴት በረከቷን ያብዛልሽ፤ ቅን ልብሽን አይቀይርብሽ በማለት የዛሬውን ፅሁፍ ቋጭተናል። ቸር ይግጠመን!
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም