ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድል

ዛሬ የአርበኞች ቀን ነው።የፋሲካ በዓል ቀኑ ስለሚቀያየር አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዓመት ከአርበኞች ቀን ጋር ተገጣጥሟል።

በዚህም ምክንያት የዛሬው የአርበኞች ቀን ከዚህ በፊት በተለመደው ድምቀት እንደማይከበር ግልጽ ነው።ሌላው አጋጣሚ ደግሞ በዚህ ዓመት አዲስ አበባን የማስዋብ አካል የሆነው የኮሪደር ልማት የድል ሀውልት ያለበት ቦታ (አራት ኪሎ) በግንባታ ሥራዎች ምክንያት ለማክበር ምቹ አይደለም።

በሁለቱም ምክንያቶች የዘንድሮው የአርበኞች ቀን በመገናኛ ብዙኃን ከዚህ በፊት በተለመደው ትኩረት ላይታወስ ይችላል።ለእምነቱ ተከታዮች ‹‹እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ!›› እያልን በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 83 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን እናስታውሳለን።ከዚያ በፊት ግን ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭሩ እናስታውስ።

የተጀመረበት ትክክለኛ ቀን ‹‹በዚህ ቀን ነው›› ባይባልም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ እንቅስቃሴው የተጀመረው የሠራተኞች መብት ‹‹የላብ አደሮች ቀን›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በዚህ ሳምንት ተከብሯል።‹‹የላብ አደሮች ቀን፣ የወዝ አደሮች ቀን፣ የሠራተኞች ቀን…›› በሚሉ የአማርኛ ስያሜዎች የሚከበረው ይህ ቀን በውጭው ዓለም ደግሞ ‹‹ሌበር ዴይ›› እና ‹‹ሜይ ዴይ›› በሚሉ የእንግሊዘኛ ቃላት ይታወሳል።ሚያዚያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዕለቱ በዚሁ ዓምዳችን ዝርዝር ታሪኩን የሰራን መሆኑ ይታወሳል።

ሌላው የዚህ ሳምንት ክስተት፤ ከ135 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም የተፈረመውና ለዓድዋ ጦርነት ሰበብ የሆነው የውጫሌ ውል ነው።

የዉጫሌ ውል በአሁኗ አምበሳል ወረዳ ውጫሌ በምትባል ቦታ በአጼ ምኒልክና በጣሊያኑ ንጉስ ኢምቤርቶ ተወካይ ኮንት አንቶሎኒ መካከል ተፈረመ።ውሉ 20 አንቀጾች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ አንቀጾች ውስጥ ሰበበኛዋ አንቀጽ 17 ለጣሊያን የውርደት ካባ ያለበሰውን የዓድዋን ጦርነት አስከተለች፤ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ድል በማጎናጸፍ የጥቁርን ጀግንነት ያስመሰከረ ክስተት ሆነ።

አንቀጽ 17 በአማርኛ ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከአውሮፓ ነገስታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል›› የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈቀደ ወይንም ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግስታት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅስ ነው።

የአንቀጹ የጣሊያንኛ ትርጉም ግን ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ሀገር መንግስታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል›› የሚል ነበር።ይህም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት በቀጥታ በጣሊያን በኩል እንዲከናወን የሚያስገድድ ነበር።

በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን የውሉን ሀሳብ በጣሊያንኛ በመቀየር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገርሰስ የጣልያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ እያበጀች ነው ብለው ነገሥታቱ እና መኳንንቱ ስለተገነዘቡ የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት አሳወቁ።

የጣሊያን መንግስት ውሉን ለማፍረስ አሻፈረኝ በሚልበት ጊዜ፣ የውጫሌ ውል እንዲፈርስና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባለቤት የሆኑት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል።

እቴጌዋ ‹‹እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም።ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ›› ብለው የተናገሩት እነሆ ታሪክ ሆኖ ይታወሳል!

ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን ሚያዚያ 27 1928 ዓ.ም ታዋቂው ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ተወለደ።ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር የታሪክና የማህበራዊ ጉዳዮች አዋቂ ቢሆንም ብዙዎች የሚያውቁት ግን ‹‹ትኩሳት›› እና ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› በተሰኙ ሁለት መጽሐፎች ብቻ ሆኗል።በኢትዮጵያ ባህልና ወግ ባልተለመደ ሁኔታ በእነዚህ መጻሕፍት ወሲባዊ ቃላትን በመጠቀሙ ከሌሎች መጽሐፎቹ ይልቅ በእነዚህኞቹ አጀንዳ ሆነ።ያም ሆነ ይህ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ለየት ባለ የሕይወት ፍልስፍናው እና በስነ ጽሑፍ ሥራዎቹ ሲታወስ ይኖራል።

አሁን በዝርዝር ወደምናየው የአርበኞች የድል ታሪክ እናልፋለን።

በዓድዋ ጦርነት ሽንፈት የተከናነበው ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ዝግጅት አድርጎ ዳግም ወረራ ሞክሮ ነበር።ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በለመዱት የጀግንነት ስልትና ወኔ ባደረጉት ተጋድሎ ነፃነታቸውን አስከብረዋል።ይህ ድል የኢትዮጵያውያን የወታደራዊ ጀግንነት እና የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ውጤት ነበር ማለት ይቻላል።

የተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ›› የባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› መጽሐፎች በዝርዝር ይነግሩናል።

ኢትዮጵያ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ ነፃነቷን ያስመለሰችው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ መንግሥት ሲሰቅሉ ነው።

የሚያዝያ 27 የንጉሰ ነገስቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓለማ መስቀል ሌላው ታሪካዊነቱ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን መሆኑ ነው።ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ደርጅታ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረች።ከአድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች።

የወቅቱ ሃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም ነበር።

የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በመርዝ ጋዝና በአውሮኘላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣልያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ፣ እምቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ።ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ አቀረቡ።የሚሰማቸው ግን አላገኙም።የኢትዮጵያ አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀዳጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛ ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው።

ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩት።

በዚህ መሃል እንግዲህ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበረው።ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች።ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ።

ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው ፤ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እረዷቸው።

በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ በደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ ፤ ከዚያም በሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ።

በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ‹‹ጌዲዮን›› ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ።

በመካከለኛው ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ።

ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ።በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ናኜ።

ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ።

መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ።

እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ አጼ ኃይል ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው።

ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ።አፄ ኃይለ ሥላሴም ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱ።ንጉሰ ነገስቱም አዲስ አበባ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ።አዲስ አበባ ገብተውም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።

‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ነዉ። አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው ዐጥንታቸውን ከስክሰው በነፃነት ያቆዩልን ሀገራችንን ወደ ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ዠምሮ ስለሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታዉቁት ነዉ። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በሗላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግስታት ማሕበር ወደ ወዳጆቻችን መንግስታቶች መጣን፤ እዚህ ስንነጋገር በቆዬንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ ዓላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነዉን ዠግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በዠግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸዉ አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት አመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዋዕታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።

የሀገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ!

ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታዋንም ለልጆቿ የምትገልጽበት ቀን ነዉ። የኢትዮጵያ ልጆች ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለዓለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት አመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደዉና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላለቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በያመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚዉልበት ነዉ። በዚህም ቀን ለሚዎዷት ላገራቸዉ ነፃነት ለንጉሰ ነገሥታቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብር ከአባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለዚህም ለጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።

ባለፈው አምስት አመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያልቁ ያገኘናቸው መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነውን ሰራተኛነት አንድነት ህብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈው ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነው። በአዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክልና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። ሀገር የሚለማበትን ሕዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርትና ጥበብ የሚሰፋበትን የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን የሀገር አስተዳደርም በአዲሱ ስልጣኔ ተለውጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ስራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ።

የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ድል አድርጎ ለመያዝ ችሎት ከሰጠው መሳሪያ በቀር ኢትዮጵያን ለመግዛት ሌላ ተስፋ ያደረገው ነገር ነበር ይኸውም የኢትዮጵያ የነገድ ልዩነት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ እርሱ ሃሳብ አንደኛው ወገን ከሴም ዘር የመጣው የትግሬና የሸዋ፣ የጎጃም፣ የበጌምድር፣ በጠቅላላው አማራ የሚባለው፣ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ምዕራብና ደቡብ የሚገኙትን እነወለጋ፣ እነጅማ፣ እነሲዳማ፣ እና አሩሲ እነዚህን የመሳሰሉት ሀገሮች ከካም ዘር የመጡ በነገድም በቋንቋም በሃይማኖትም የተለያዩ ናቸው ። አንደኛው ወገን ቢያመልጥብኝ ሁለተኛውን ወገን ይዤ አጠፋዋለሁ የማለት ተስፋ ነበረውና ይህንንም ሊሰራበት እንደጣረ በጉልህ ታይቷል። ዳሩ ግን የ3ሺህ አመት ባለው የነፃነቱ ዘመን በታሪኩ ውስጥ ምንም የሚያሳፍር ገጽ የሌለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን አሳይቶ ለጠላቱ ሳይመች ቀረ።›› ብለው ነበር ንጉሡ።

ይሄ የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት የሆነው የአርበኞች ቀን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ነው።በዚህ ጦርነት ውስጥ ምላጭ ስቦ ጥይት ከተኮሰው አርበኛ በተጨማሪ በየቤቱ ሆኖ የተባበረውም ቀላል አልነበረም። በትግሉ ጊዜ የአርበኞች ዋናው ችግር ቀለብ ነበር። ቀለባቸውን የሚያገኙትም ከአርሶ አደሩ ቤት ነው። ይሄ ነገር የሚሆነው ታዲያ በግድም በውድም ነበር።ፈቃደኛ የማይሆን አርሶ አደር ካለ ፋኖ እስከማሰማራትም ተደርሶ ነበር።በተለይም ከጠላት ጋር የሚያብሩ ሰዎችን ደግሞ እህላቸው እንዲዘረፍና ለሰራዊቱ ቀለብ እንዲሆን ተደርጓል።

ሰራዊቱ ‹‹ደረቅ ጦር›› እና ‹‹መደዴ ጦር›› ተብሎ ለሁለት ተከፍሎም ነበር።ደረቅ ጦር የተባለው ሙሉ በሙሉ ውጊያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ‹‹መደዴ ጦር›› የተባለው ደግሞ እንደ ሁኔታው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል። ነገሩ ሲከፋ ግን አርበኞች ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠልና የዱር አውሬ ሁሉ እየበሉ ተዋግተዋል።እናቶች ከሰራዊቱ ጋር አብሮ በመዝመት ምግብና ውሃ ከማቀበል በተጨማሪ ባህላዊ ህክምና እየሰጡ ሰራዊቱን ታድገዋል።የወደቀውን በማንሳት የቆሰለውን በመጠገን ተሳትፈዋል።ይህ የአርበኞች ቀን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ድል ነው ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ነፃነቷን ማስከበሯ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከአራቱ ልዕለ ኃያላን አገራት (አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ) ጋር ለውይይት እንዲትቀመጥ ክብር ሰጥቷታል።የአውሮፓውያን ቅኝ ተገዢ የነበሩ የአፍሪካ አገራት ዕጣ ፋንታ ምን ይሁን ተብሎ ሲመከር ኢትዮጵያ ግን የሚመከርባት ሳትሆን አብራ የምትማከር ነበረች።ሃሳቧን እንድታዋጣ የምትጠየቅ ነበረች።የአርበኞች ቀን የወታደርም የዲፕሎማሲም ድል ውጤት ነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You