በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የትንሳኤ /የፋሲካ/ በዓል አንዱ ነው፡፡ ይህ ታላቅ በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡
የበዓሉን መቃረብ የሚያመለከቱ በርካታ ሁነቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ያለው ሁኔታ እንደሚያመለክተው፤ ገበያው መሟቅ ጀምሯል፡፡ የምግብ ሸቀጦች በዓይነት በዓይነቱ በብዛት በገበያው መታየት የጀመሩ ሲሆን፣ ምርቶቹ በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫዎች እየገቡ የእሁድ ገበያን ጨምሮ በተለያዩ የገበያ ማዕከላት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶቹ በስፋት እየቀረቡ ናቸው፡፡
መንግሥት እንደ ሀገር እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማርገብና ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተለያዩ የገበያ አማራጮችን በማዘጋጀት የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ለሕዝቡ ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ምርቶቹ ለሕዝቡ ተደራሽ ከሚደርጉባቸው ገበያዎች መካከል የእሁድ ገበያ አንዱ ነው፡፡ በእሁድ ገበያ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለከተማው ነዋሪ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርብ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከእሁድ ገበያዎች በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላትን በማቋቋም አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቹ ማቅረብ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ይህም ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዲችልና የኑሮ ውድነቱ የሚያደርስበት ጫና እንዲቀልለት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በተለይ በበዓል ወቅት ያለውን ፍላጎት ምክንያት በማድረግ የሸቀጦችን ዋጋ ከሚያንሩ ስግብግብ ነጋዴዎች ሸማቹን ለመታደግ መሰል ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ ነው፡፡ ከሰሞኑንም መጣሁ መጣሁ ለሚለው የፋሲካ በዓል ሸማቹ የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችን ባገኘው የገበያ አማራጭ ያለ ምንም ችግር መሸመት እንዲችል ከተማ አስተዳደሩ በየአቅጣጫው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ከገበያ አማራጮቹ መካከል ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ አጠገብ የግብርና ምርቶች የቀረበበት የበረከት ገበሬዋ ሱቅ አንዱ ነው፡፡ እዚህ ሱቅ ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች በአርሶ አደሩ ዋጋ ቀርበዋል፡፡ በዚሁ ሱቅ ሽንኩርት ስትገዛ ያገኘናት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ወርቄ ጣሰው መኖሪያዋ ጀሞ አካባቢ ቢሆንም የሥራ ቦታዋ ስድስት ኪሎ በመሆኑ ከበረከት ገበሬዋ ሱቅ የመሸመት አጋጣሚን አግኝታለች፡፡ ለሥራ በወጣችበት አጋጣሚ ወደ ግዥ የገባቸው ዋጋው ቅናሽ በመሆኑ ነው፡፡
በሱቁ ሁሉም ዓይነት የግብርና ምርቶች አሉ፡፡ ዋጋቸውም ተመጣጣኝ በመሆኑ ተመራጭ ናቸው ያለችው ወይዘሪት ወርቄ፣ እሁድ ገበያ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ50 እስከ 55 ብር ይሸጣል፤ እዚህ ግን አንድ ኪሎ ሽንኩርት 38 ብር ነው ስትል ገልጻለች። ሌሎች ካሮት፣ ጥቅል ጎመን፣ ድንች የመሳሰሉትም የተወሰነ ቅናሽ እንዳላቸው ጠቅሳ፣ ገበያው ለዚህ አካባቢ ነዋሪ ተመራጭ ነው ብላለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ በተለይም ሽንኩርት ለበዓሉ እጅግ አስፈላጊ እንደመሆኑ ከእሁድ ገበያ በተጨማሪ በዚህ መንገድ መቅረቡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ሸማቹ ባመቸው መንገድ መግዛት እንዲችል ያደርገዋል፡፡ አምራቹ በቀጥታ ሸማቹ ዘንድ መድረስ መቻሉ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት ያስችለዋል፡፡ ስለዚህ በየአካባቢው እንዲህ ዓይነት የገበያ አማራጭ ቢኖር መልካም ነው፡፡ በማለት አሁን ላይ ምርቶች በስፋት እንደገቡና ዋጋውም ተመጣጣኝ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
እንዲህ ዓይነት የገበያ አማራጮች መስፋታቸው በጣም ጥሩ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ጽጌ ረጋሳ በበኩላቸው፣ ከሱቁ ሽንኩርት በ38 ብር፣ ድንች በ28 ብር እና ሌሎች ምርቶችንም እንዲሁ ውጭ ካለው ዋጋ ባነሰ መሸመት እንደቻሉ ተናግረዋል። ከሱቁ በተጨማሪም በአካባቢው የእንቁላል ገበያ መኖሩን ጠቅሰው፤ የአበሻ እንቁላል 11 ብር ፤ የፈረንጅ እንቁላል በስምንት ብር መግዛት እንደቻሉና ገበያው የተሻለ አቅርቦት እንዳለ ነው የጠቆሙት፡፡
ወይዘሮ ጽጌ፤ የሽንኩርት ዋጋ በጣም የናረበት ወቅት እንደነበር አስታውሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቅናሽ እያሳየ መሆኑ በጣም ጥሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ሽንኩርትን ጨምሮ እንቁላልና ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ሸቀጦች በስፋት እየታዩ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ ዋጋቸውም ቢሆን ካለፈው የገና በዓል አንጻር ሲታይ በጣም የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ሌላም የዘይት ዋጋ ግን እየጨመረ መምጣቱን ወይዘሮ ጽጌ ጠቅሰው፣ ዘይቱም እንደ ሌላው ምርት ሁሉ ዋጋው ቢስተካከል ጥሩ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋን ለማረጋጋት በከተማዋ የመግቢያ በሮች የገበያ ማዕከላትን ገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ማዕከላትም አምራች ገበሬዎችን ጨምሮ ጅምላ አከፋፋዮች የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በዓሉን አስመልክቶ ምርት በስፋት እንዲቀርብ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኮሚሽን መጪው የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ የምርት እጥረት እንዳይከሰት በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ከሰሞኑ ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ኃብተይስ ዲሮ እንዳሉት፤ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኮሚሽን ከዚህ ቀደምም የገበያ ማረጋጋት ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለሸማቹ አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ሸቀጦችን ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለዚህም አስቀድሞ አቅዶ ሥራውን ሊመራ የሚችል ኮሚቴ በማዋቀር በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለሸማቹ ለማቅረብ ከክልሎች ጋር ትስስር በመፍጠር ምርት ወደ ከተማዋ ማስገባት ተጀምሯል፡፡ በተለይም ለበዓሉ እንደ ጤፍ፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ የቁም እንስሳት፣ እንቁላልና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ወደ ከተማው እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡
አብዛኞቹ ምርቶቹ ከኦሮሚያ ክልል በስፋት እየገቡ ሲሆን፤ የቁም እንስሳት ከሰዴታን ጮራ፣ ሎሜ አዳማ፣ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ ወደ ከተማዋ እየገባ ይገኛል፡፡ እንቁላል ከከተማ ግብርና ከኤልፎራ እንዲሁም ከተደራጁ ወጣቶች ጭምር በማሰባስብ ወደ ገበያው እየገባ ነው፡፡ እንቁላልን በሚመለከት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከአምስት መቶ ሺ በላይ እንቁላሎች ወደ ገበያው ገብተዋል፡፡ በቀጣይ በተለይም ከከተማ ግብርና በስፋት የሚገባ በመሆኑ እጥረት ሳያጋጥም በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ይቀርባል፡፡
የሥጋን በተመለከተም እንዲሁ በከተማዋ በሚገኙ 246 በሚሆኑ የሸማች ሥጋ ቤቶች በኩል ጥራት ያለው ሥጋ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየተሠራ ነው፡፡ በከተማዋ ከሚገኙ ሥጋ ቤቶች ጋር ትስስር በመፍጠር በሬዎችን ወደ ከተማ የማምጣትና ሥጋ ለሸማቹ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ሥጋውን የሸማች ሱቆችና መዝናኛ ክበቦችን ጨምሮ በአጠቃላይ ስምንት መቶ በሚደርሱ የሸማች ሱቆችና መዝናኛ ክበቦች ለማቅረብ ኮሚሽኑ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
ኮሚሽኑ በዩኒየኖች አማካኝነት ምርቶች በበቂ ሁኔታ መግባት እንዲችሉ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ኃብተየስ፤ በተለይም በ246 የሸማች ሥጋ ቤቶች ሥጋ ለማህበረሰቡ ማቅረብ ያለባቸው በምን ያህል ዋጋ ነው የሚለውን ጭምር በማኔጅመንት ተወስኗል ብለዋል፡፡ የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ ከ400 እስከ 460 እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ ዋጋው የሚወሰነው እንደ በሬው ዋጋ ነው መሆኑን ጠቅሰው፣ ዋጋው ከሉካንዳ ቤቶች ጋር በመነጋገር መስማማት ላይ የተደረሰበት ጉዳይም ነው ብለዋል፡፡
ለበዓሉ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ጤፍ፣ በሬ፣ ሽንኩርት፣ እንቁላልና ሌሎች ግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማስገባት በቂ ዝግጅት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ኃብተየስ፤ ምርት ከማስገባት ባለፈ ምርቱ በትክክል ማህበረሰቡ ዘንድ መድረስ እንዲችልም ኮሚሽኑ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል። ኮሚሽኑ ከምርት አቅርቦቱ ጎን ለጎን ለቁጥጥርና ክትትል ሥራውን አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም እስካሁን ባለው ዝግጁነት ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶችን ለማቅረብ በቂ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል፡፡
አቅርቦት ላይ እጥረት እንዳይፈጠር በሚል ኮሚሽኑ አስቀድሞ ፍላጎት መሰብሰቡን ተናግረው፣ ከየክፍለ ከተሞች በተሰበሰብ ፍላጎት መሠረት ምርቶቹ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡ የተሰበሰበውን መረጃ መነሻ በማድረግ አቅምን ባማከለ መንገድ ምርቶችን ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀው፤ ለአብነትም በከተማዋ በሚገኙ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ሉካንዳ ቤቶች ብቻ የሚቀርቡ አራት ሺ 610 በሬዎች ፍላጎት መለየቱን አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይም ሌሎች ምርቶችም እንዲሁ በፍላጎት መሠረት እንደሚቀርቡ ተናግረው፣ የአቅርቦት እጥረት እንደማያጋጥም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በተለይም ጤፍ በልዩ ሁኔታ በስፋት ወደ ገበያው ማስገባት የተቻለ ሲሆን፤ መጠባበቂያ ጭምር ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ ለዚህም ባለፉት ሶስት ወራት በልዩ ሁኔታ በከተማ አስተዳደሩ እየተመራ በቂ ምርት እንዲገባ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ህብረት ሥራ ኮሚሽን የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫነ አዱኛ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ህብረት ሥራ ኮሚሽን በዓሉን አስመልክቶ በርካታ የአቅርቦት ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ከምግብ ሸቀጦች ጋር ተያይዞ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ ከተማው እንዲገቡ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል፡፡ ይህም ህብረተሰቡ በዓሉን በሰላም ማሳለፍ እንዲችልና የኑሮ ጫናውን እንዲያቀልልት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ማህበረሰቡ በዓሉን በሰላም እንዲያሳልፍና የኑሮ ጫናውን እንዲያቀል ተብሎ የገባው ምርት በተገቢው መንገድ ማህበረሰቡ ዘንድ መድረስ እንዲችል መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ለዚህ ሥራ ቡድን ተደራጅቷል፡፡ ይህ ቡድንም የቀረበው ምርት በትክክል ሕብረተሰቡ ዘንድ መድረሱንና ዋጋዎቹም በሁሉም ህብረት ሥራ ማህበራቱ ተመሳሳይ መሆኑን ለማረጋጋጥ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡
ይህም በዓሉን በማስመልከት በተገቢውና በተጠናከረ መንገድ እንደ ተቋም የሚሠራ ሲሆን፤ እንደ ከተማ አስተዳደርም ከጸጥታና ሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት በልዩ ሁኔታ ይሰራበታል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ በዓሉን በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ማሳለፍ እንዲችል ኮሚሽኑ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኮሚሽን ለውጥ ላይ ያለ ተቋም መሆኑንና እያደረገ ያለው ሪፎርምም ሁለንተናዊ ሪፎርም ነው ያሉት አቶ ተጫነ፤ ይህም ለተገልጋዩ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ እና ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይም በዓሉን አስመልክቶ ምንም ዓይነት የዋጋ ንረት እንዳያጋጥም ምርቶችን ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በማምጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማቅረብ እየተሠራ ነው፡፡ ምርቱ በተባለለት ዋጋ ሸማቹ ዘንድ መድረስ እንዲችል በሸማች ህብረት ሥራ ብቻ ሳይሆን በግብረ ኃይል ጭምር ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሸማቹ ማንኛውም ዓይነት ችግር ሲያጋጥመው በነፃ የስልክ መስመር 8779 ደውሎ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኮሚሽን የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ በአጠቃላይ ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ በሚገመት ገንዘብ የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለሸማቹ እንደሚቀርብ ተመላክቷል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም