የሰዎችን እይታና ውበት ከሚቀይሩ ነገሮች ውስጥ ፀጉርና አለባበስ ቀዳሚ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማሙበታል።
ለወትሮው ስለ ጸጉራቸው ውበትና ጤንነት ተጨንቀው እና ‹‹እንዴት እናድርገው›› ብለው በማሰብ ረጅም የሚባል ሰዓትን በውበት ሳሎን የሚያሳልፉት ሴቶች ናቸው ። በሴቶች የውበት ሳሎን ውስጥ ጸጉርን ከመሥራት አገልግሎት ባሻገር የተለያዩ ከውበት ጋር የተያያዙ እንደ ጥፍር መሰራት ፣ ሜክ አፕ አልያም ደግሞ የተለያዩ ለጸጉር እና ለፊት ተብለው በሚዘጋጁ ውህዶች የጸጉር እና የፊት ስቲም አገልግሎት ዓይነት ሥራዎችም ይከናወናሉ።
በአንጻሩ ወንዶች ጸጉራቸውን የሚስተካከሉበት ሳሎን ደንበኛው በፈለገው አይነት ጸጉሩን ከማስተካከል እንዲሁም ጢሙን ከመላጨትና ከመሳሰለው ውጪ ሌላ አገልግሎት አይሰጥም፤ ወረፋ ከሌለው በቀር በጸጉር ቤቱ ረጅም የሚባል ሰዓትን አንድ ወንድ ላያጠፋ ይችላል ፤ አሁን ላይ ግን ይህ አመለካከት የተቀየረ ይመስላል።
በዛሬ የፋሽን ገጻችን በወንዶች የውበት ሳሎን ሥራ ከሁለት ዓመት በላይ ልምድ ካለው እና በአሁኑ ሰዓት በተለየ መንገድና ሃሳብ የራሱን የውበት ሳሎን በአዲስ መልክ ከፍቶ እየሠራ ካለ ወጣት ጋር ባደረግነው ቆይታ ባለሙያው ጋር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወንዶች የውበት አጠባበቅ ልምድ እየተቀየረ መምጣቱን ገልጾልናል።
ይህ ባለሙያ ወጣት አድናን ሡልጣን ይባላል። የዞያ የወንዶች የውበት ሳሎን ማናጀር ሲሆን በሙያው ከሁለት ዓመት በላይ ሠርቷል። ከዚህ ቀደም የነበሩ የወንዶች የውበት ሳሎኖች ወንዶች ጸጉራቸውን ተቆርጠው እና አራግፈው የሚሄዱበት ነበር የሚለው አድናን፣ አሁን ግን ይህ ተቀይሮ የወንዶች የውበት ሳሎኖች የሚሰጡት አገልግሎት እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራል።
ዞያ የወንዶች የውበት ሳሎን በመጠኑ ሰፊ የሚባል ሲሆን፣ ከውጭ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቤቱን ወደውት ሊስተናገዱበት እንዲችል ተደርጎ ዲዛይኑ ተሠርቷል። የጸጉር መታጠቢያ ቦታ ፣ ጸጉራቸውን የሚስተካከሉበት ሥፍራ እና በልዩነት መገልገል ለሚፈልጉ ደግሞ የቪአይፒ የብቻ ክፍልንም የያዘ ነው። በክፍሉ ውስጥ የተለያዩ ታሪኮችን የሚያስታውሱ በሀገራችን ከሚገኙ ጥንታዊ ከተሞች የጅማን እና የጅማ አባ ጅፋርን ታሪክ የያዙ ምስሎች ተመለከትን። ምስሎቹ በእርግጥም ለክፍሉ ተጨማሪ ውበት ሆነዋል። ‹‹ ትውልድና እድገቴ ጅማ በመሆኑ በሳሎኑ ውስጥ ጅማን የሚያስታውሱ ነገሮችን ማድረግ እፈልጋለሁ ›› ሲል አድናን አብራርቷል፡፡
በሳሎኑ የሚሰጡ አገልግሎቶች አንድ ደንበኛ ጸጉሩን ከተቆረጠ በኋላ እንደ ፍላጎቱ መታጠብ ፣ ቀለም መቀባት ፣ የተለያዩ ለፊት ቆዳ የሚሆኑ ውህዶችን መቀባት ፣ የፊት እና የጸጉር ስቲም አገልግሎትን ማግኘት ይችላል። ‹‹ በቪ አይፒ ክፍል የሚገለገሉ ደንበኞቻችን በአብዛኛው ብቻቸውን ሆነው መስተናገድ የሚፈልጉ ፣ አገልግሎቱን እየተጠቀሙ ራሳቸውን ማረጋጋት እና ማዳመጥ የሚፈልጉ ናቸው ›› ሲል አድናን ጠቅሶ፣ በቪአይፒ ክፍሉ በቤት ውስጥ የተዘጋጁ ልዩ ውህዶችን የሚያገኙበት ሁኔታም እንዳለ ይናገራል ።
ብዙ ሰዎች ጸጉራቸውን ለመሠራት የለመዱበትን እና አንድ ጊዜ ሞክረው የወደዱበት ቤት ደንበኛ ሆነው መዝለቅ ይፈልጋሉ ። ‹‹ታዲያ በዚህ ሥራ አዲስ ደንበኛ ማፍራት ከባድ ይሆን›› ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስ ‹‹በእኛ የውበት ሳሎን ደንበኛ ክቡር ነው ። ይህንንም ለምንቀጥራቸው ሠራተኞች ሁሉ እንነግራቸዋለን ። ደንበኞቻችንም የሚፈልጉትን አገልግሎት አግኝተው እስከሚወጡ ድረስ ቡና ቢፈልጉ ውሃ እንደየፍላጎታቸው በነጻነት የማስተናገድ ባህል አለን ። ይህ ተግባር ደግሞ ተመልሰው እንዲመጡ ያደርጋል›› በማለት አገልግሎታቸው ምን ድረስ እንደሆነ አብራርቷል።
አድናን በውበት ሳሎኑ ውስጥ 20 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ጸጉር ከመቁረጥ ባለፈ የተለያዩ አገልግሎቶች ያሉት የውበት ሳሎን ለመክፈት ምክንያት የሆነው እሱ ጸጉሩን ለመስተካከል በሚሄድበት አንድ የውበት ሳሎን ውስጥ ያለው አገልግሎት እና ጥራት ነው።
እሱ እንዳለው፤ አገልግሎቱ በደንበኞች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ አብዛኛዎቹ ጸጉራቸውን ከመቆረጥ ባለፈ ሌሎች አገልግሎቶችን ተጠቅመው ይሄዳሉ ። በሴቶች የውበት ሳሎን ውስጥ የተለመደው የጸጉር ስቲም በወንዶች የውበት ሳሎንም አለ። አሁን ወንዶችም ጸጉራቸውን ቂቤ ተቀብተው እና ፊታቸውን በቤቱ የተዘጋጀ ውህድ ተቀብተው ለተወሰነ ደቂቃ የጸጉር እና የፊት ስቲም ውስጥ ይቆያሉ።
‹‹ እኛን የሚያውቁ ደንበኞቻችን የሚፈልጉትን አገልግሎት ይነግሩናል ፤ አዲስ ከሆኑ ደግሞ እንድንገልጽላቸው እና የሚፈልጉትን ይጠቀማሉ›› በማለት አንድ ደንበኛ እነርሱን መርጦ ከመጣ በኋላ የሚያልፈውን ሂደት አብራርቷል፡፡
ወንዶች ምንም እንኳን የተለመደው ወደ ውበት ሳሎን የሚሄዱት ጸጉራቸውን ለመቆረጥና በተለያየ ቅርጽ ለመስተካከል ቢሆንም፣ ጸጉራቸውን አሳድገው የተለያየ አይነት የሹሩባ ዲዛይኖችን የሚሠሩ ፣ ከርል የጸጉር አይነትን ምርጫቸው የሚያደርጉ ደንበኞችም ወደ ሳሎኑ እንደሚመጡ አስታውቋል። የራሳቸውን የሹሩባ ዲዛይን ከማህበራዊ ገጽ ላይ ይዘው የሚመጡም እንዳሉ ይናገራል።
ይህንንም የሚሰሩ ሴቶች በሳሎኑ ውስጥ ይገኛሉ ያለው ወጣት አድናን፣ አንድ ደንበኛ ጸጉሩን ተስተካክሎና ሌሎች አገልግሎቶችን አግኝቶ ለመጨረስ ከ45 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ሊወስድበት እንደሚችልም ይገልጻል። አንዳንድ ደንበኞችም አስቀድመው ቀጠሮ በማስያዝ ወደ ሳሎኑ እንደሚመጡ ነግሮናል።
ደንበኛው ለተጠቀመው አገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያ እንደ የውበት ሳሎኑ እንደሚለያይ አመልክቶ፣ በዞያ የውበት ሳሎን ጸጉሩን ከተቆረጠ በኋላ ታጥቦ፣ ፊቱን ደግሞ ስክራፕ ተቀብቶ 700 ብር እንደሚከፍል አስታውቋል። የቤቱን ውህድ ከተጠቀመ እስከ አንድ ሺህ ብር እና ሌሎች አገልግሎቶችን እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ እንደሚከፍልም ጠቁሟል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም