አርሶ አደር አሕመድ ረሺድ በስልጤ ዞን ምስራቅ ስልጢ ወረዳ ምዕራብ የቁጪ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በቀበሌያቸው ስልጢ አባያ ሃይቅ ያለ ቢሆንም፣ እሳቸውም ሆነ የቀበሌው አርሶ አደሮች ሃይቁን ከመመልከት ባለፈ ተጠቅመውበት አያውቁም። ይልቁንም ከ30 ዓመት በፊት በሃይቁ ዙሪያ በቀደሙ አባቶቻቸው የተተከለውን ባህር ዛፍ እየሸጡ ገቢ ሲያገኙ ኖረዋል።
ይህ ግን ብቻውን ኑሯቸውን ሊደጉሙላቸው ባለመቻሉ ዘወትር መንግሥት የሚሰጠውን ሴፍትኔት ይጠብቁ ነበር። ሃይቁ ዙሪያ ባላቸው መሬት ላይ የተወሰኑ ሰብሎችን ለማልማት ቢሞክሩም በባህር ዛፉ ስር ምክንያት ምርታማነቱ እዚህ ግባ የሚባል አልሆን አላቸው፤ በዚህ የተነሳም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሚባል እንደነበር ያስታውሳሉ።
አርሶ አደር አሕመድ የ‹‹ስልጢ አባያ ሃይቅ ዙሪያው ለረጅም ዓመታት በባህር ዛፍ ተከቦ የኖረ ነው። አካባቢው ለምና ምቹ ቢሆንም፣ ባህር ዛፍ እየቆረጥን ከመሸጥ በዘለለ ሕይወታችን ላይ ጠብ የሚል ልማት አልነበረም›› ይላሉ።
ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን የወረዳውና የዞኑ ግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደር አሕመድንም ሆነ መላውን የቀበሌያቸውን ነዋሪ ለችግር የዳረገውንና የጠባቂነት ሥነልቦና እንዲያዳብሩ ምክንያት የሆናቸውን ባህር ዛፍ መንጥረው በምትኩ ሙዝ ቢያመርቱ ኑሯቸውን እስከ ወዲያኛው እንደሚቀይሩ ይመከሯቸዋል። እነሱም ምክሩን ተቀብለው ወደ ተግባር ለመቀየር ጊዜ አልወሰዱም፤ እሳቸውና የተወሰኑ አርሶአደሮች ተሞክሮ ለመቅሰም ወደ ሙዝ ማዕከሏ አርባ ምንጭ አቀኑ። ልምድና ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን ምርጡን የተሻሻለውን የአርባ ምንጭ ሙዝ ችግኝ ይዘው ተመለሱ።
አርሶ አደር አሕመድና ጎረቤቶቻቸው በማህበር ተደራጁ፤ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም በሃይቁ ዙሪያ ያለውን ሃያ ሄክታር መሬት ከባህር ዛፍ ወረራ አፀዱ፤ በምትኩም ያመጡትን ሙዝ ተከሉ። የባህር ዛፍ ምርት ለማግኘት ሰባት ዓመታትን መጠበቅ ግድ ይላቸው የነበሩት እነዚህ አርሶ አደሮች፤ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሙዙን ችግኝ አባዝተው በመሸጥ በኪሳቸው ብር ማስገባት ጀመሩ። ምርቱም ደረሰና አካባቢውን ሁሉ በሙዝ አጥለቀለቁ። ጎን ለጎንም እንደ ሽንኩርትና ጎመን ያሉ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ለቤተሰባቸው ምግብ ፍጆታም ሆነ ለገበያ ያቀርባሉ።
“ለሌሎች አርሶ አደሮች የሙዝ ችግኝ እንሸጣለን፤ ምርቱም ሰፊ በመሆኑ ከቀበሌያችንና ወረዳችን አልፈን በአጎራባች ዞኖች በሚገኙ ገበያዎች ላይ በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነናል›› ይላሉ። አሁን የገቢ አቅማቸው በከፍተኛ ደረጃ በመጎልበቱ ምክንያት የቤተሰቦቻቸውን የእለት ጉርስ ከመሸፈን አልፈው ተጨማሪ ቤትና ሱቅ መስራት መቻላቸውን ነው አርሶአደሩ የሚናገሩት። ‹‹በአሁኑ ወቅት ገቢያችን ጨምሯል፤ ኑሯችን ተሻሽሏል፤ ልጆቻችንን እያስተማርን ነው›› በማለትም ገልጸዋል።
ለዚህ ለመድረሳቸው የወረዳውና የዞኑ ግብርና ባለሙያዎች ድርሻ የጎላ እንደሆነም ጠቅሰው፣ ‹‹ባለሙያዎቹ ከእኛ ቀድመው ማሳችን ላይ ይገኛሉ፤ ሁሌም የሙዝ ማሳችንን የልጃቸው ያህል ይንከባከባሉ። በጠራናቸው ቁጥር ፈጥነው ይመጣሉ›› ሲሉ ይገልጸሉ። በተለይም ወረዳው የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብ፣ ማዳበሪያና መሰል የግብርና ግብዓቶችን በፍጥነትና በፈለጉት መጠን እንዲያገኙ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉንም አርሶአደሩ ይጠቅሳሉ።
አርሶ አደር አሕመድ እንደሚናገሩት፤ መላው የማህበራቸው አባላት የሙዝ እርሻውን የማስፋፋትና ጎን ለጎንም ሌሎች ሰብሎችን በማምረት ማዕከላዊ ገበያን መቀላቀል ይፈልጋሉ። ሆኖም በአካባቢያቸው በተለይም ምንም አይነት የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመዘርጋቱ ምክንያት ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ አልቻሉም። ዘንድሮ እንኳን ሰፊ የሙዝ ምርት ቢገኝም አቅርቦቱ ከተጠቃሚው ፍላጎት በላይ በመሆኑ ምክንያት ጥቂት የማይባለው ሙዝ ለብልሽት እየተዳረገባቸው ነው።
‹‹በስልጢ አባያ ሃይቅ ዙሪያ ያሉ ቀበሌዎች በሙሉ ለምለም ናቸው፤ ይህን ምቹ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም የሙዝ፣ የፓፓያና የአባኮዶ ምርት በስፋት እያመረትን ነው፤ ምርታችን ከዚህ በላይ የማስፋትና ለማዕከላዊ ገበያ የማቅረብ ፍላጎቱም ሆነ ብቃቱ ቢኖረንም ግን በተለይ በአካባቢያችን የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩና ገበያ ማቅረብ ባለመቻላችን ምርታችን ለብልሽት እየተዳረገ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ። የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ለዚህ የመንገድና የገበያ ትስስር ችግር በፍጥነት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
የምዕራብ የቁጪ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ አሕመድ መሃመድ በበኩላቸው፤ በሀይቁ አካባቢ ለበርካታ ዓመታት የኖረው የባህር ዛፍ በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ላይ በተለይም በስልጢ አባያ ሃይቅ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በሚመለከት ከወረዳውና ከዞኑ አመራሮች ጋር በመሆን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራቱን ያስታውሳሉ። ከነዋሪው ጋር መተማመን ከተፈጠረ በኋላ ከተመረጡ አርሶአደሮች ጋር በመሆን አርባምንጭ ተሞክሮ ለመቅሰም በሄዱበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ መነሳሳትና ቁጭት ያደረባቸው መሆኑን ይገልፃሉ። ‹‹ባየሁት ነገር ከፍተኛ ቁጭት ስላደረብኝ እንደተመለስን የራሴን ባህር ዛፍ በመቁረጥ ነው ለሌሎች ተምሳሌት ሆኜ ሥራውን ያስጀመርኩት›› ሲሉ ተናግረዋል።
አርሶ አደሩም ሳያመነታ ወዲያውኑ ዛፉን ቆርጦ ወደ ሙዝ ማምረት ሥራው መግባቱን ጠቅሰው፤ ሙዙ እስከሚደርስም የሙዝ ችግኝ እያፈሉ ለሌላ ቀበሌ አርሶአደሮች በመሸጥ እንደሚጥሚጣ፣ ሽንኩርት እና ድንች የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ርዳታ ጠባቂ የነበረውን የቀበሌውን አርሶ አደር ሕይወት መቀየር መጀመራቸውን ያመላክታሉ። ‹‹ከዚህ ቀደም ከ450 በላይ የሚሆነው የቀበሌያችን ነዋሪ የሴፍትኔት ተጠቃሚ ነበር፤ አሁን ግን የሙዝ ምርቱ በፈጠረው የሥራ እድል ከጠባቂነት ወደ አምራችነት ተቀይረዋል›› ሲሉም ያስረዳሉ።
አቶ አህመድ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሙዝ ችግኝ በድጋፍ መልክ መስጠታቸውን ይጠቁማሉ። ‹‹ በግሌ በችግኝ ብቻ እስከ 15 ሺ ብር አግኝቻለሁ፤ ሌሎችም በተመሳሳይ ችግኝ በማፍላትና ሙዝ በማምረት የቤተሰባቸውንና የራሳቸውን ኑሮ እየለወጡ ነው›› የሚሉት አቶ አሕመድ፤ ይህም የቀበሌው አርሶአደር ጥረት ከቀበሌው ባሻገር ለወረዳው የንግድ እንቅስቃሴ እና ልማት መስፋፋት ትልቅ አቅም እየሆነ መምጣቱንም ያብራራሉ።
የቀበሌው ሊቀመንበር እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም ማንኛውም የቀበሌያቸው ነዋሪ አንድ ኪሎ ሙዝ ለመግዛት ቡታጀራ አልያም ወራቤ መሄድ ይጠበቅበት ነበር። አሁን ግን ከራሳቸው አልፈው ለምስራቅ ስልጢ በሙሉ ማቅረብ ጀምረዋል። አሁን ላይ የቀበሌያቸው አርሶአደሮች ሙዝንም ሆነ ሌሎች ፍራፍሬና አትክልቶችን በስፋት ለማምረት ርብርብ እያደረጉ ናቸው።
ይሁንና በማዕከላዊ ገበያ ትስስር ያልተፈጠረላቸው በመሆኑ እሳቸውም ምርቱ ይበላሻል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። የገበያ ትስስሩ መፍጠር ከተቻለ ግን በርካታ የአካባቢው ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከመንገድ መሠረተ ልማት አኳያ አርሶአደሮቹ ያነሱትንም ችግር ሊቀመንበሩም ይጋራሉ። ‹‹በወረዳችን ካሉት 11 ቀበሌዎች ውስጥ አራቱ በበጋ መሥራት የማይቻልባቸው ናቸው። ሰባቱ ቀበሌዎች ግን ፍራፍሬም ሆነ ሌሎች ሰብሎችን በስፋት ማምረት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ አለ። ሆኖም የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሰን ማምረትም ሆነ ያመረትነውን ገበያ ማድረስ ተቸግረናል›› ሲሉ ያብራራሉ። ይህን ችግር በሚመለከት ከወረዳውና ከዞኑ አመራር ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውንና ችግሩ ብዙ ባልረዘመ ጊዜ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመላክተዋል።
የምስራቅ ስልጢ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ሃሰን እንደሚሉት፤ የስልጢ አባያ ሃይቅ የዞኑ ማዕከል ተደርጎ የሚቆጠር ቢሆንም፣ እስካሁን ልማት ላይ ባለመዋሉ አመራሩ ይወቀስ ነበር። ከባህር ዛፍ ውጪ ለልማትም ሆነ ለቱሪዝም መስህብነት ያለመዋሉ ጉዳይ የብዙ የአካባቢው ተወላጆችም የዘመናት ቁጭት ሆኖ ቆይቷል። ይህን ቁጭት መነሻ በማድረግ አመራሩ በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ተጨባጭና ሊተገበሩ የሚችሉ የልማት እቅዶችን በመያዝና ታች ድረስ ወርዶ ባከናወናቸው ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት መጥቷል።
‹‹በተለይም ሃይቁን የመታደግ አጀንዳ ቀዳሚ ሥራ አድርገን የተነሳን ሲሆን፤ ያለንንም እምቅ አቅም በመጠቀም የወንዙን ዙሪያ ማልማት ይገባል የሚል መግባባት ይዘን ነው ርብርብ ያደረግነው›› የሚሉት አቶ ጀማል፤ የአዋጭነት ሰነድ በማዘጋጀት እድሜ ጠገቡን ግዙፍ ባህር ዛፉ ጥቅምና ጉዳት ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ መከናወኑን ያስረዳሉ። ለዚህ ደግሞ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ጥናት መደረጉንና የአካባቢው ማህበረሰብ በጉዳዩ ዙሪያ እንዲወያይ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መግባባት በተፈጠረበት ሁኔታ ወደ ልማት መገባቱን ያብራራሉ።
ባህር ዛፍ የመንቀል ሥራም ከአመራር መጀመር አለበት የሚል አቋም በመያዙ እሳቸውም የራሳቸውን የባህር ዛፍ መሬት በማፅዳት በሙዝ መተካታቸውን ይጠቅሳሉ። ‹‹ይህንን ባህር ዛፍ የመመንጠር ሥራ ስንጀምር አርሶአደሩ በአንድ በኩል መሬታቸው ወደ ቀድሞ ለምነት ይመለሳል የሚል ተስፋ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባህር ዛፉ ብዙ ዓመት ከመቆየቱ የተነሳ ሙሉ ለሙሉ የመመንጠር አቅም ላይኖረን ይችላል፤ ምርትም እንደታሰበው ላይገኝ ይችላል የሚል ስጋት ነበረው›› ይላሉ።
ዞኑና የወረዳው አመራር በመቀናጀት መስኖ ገብ በሆኑ ሰባት ቀበሌዎች ላይ የሙዝ ማልማት ሥራው መጀመሩን ያመለክታሉ። ከፍተኛ ወጪ በመመደብ የሙዝ ችግኝ ለአርሶአደሩ በማከፋፈልና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በስፋት ማልማት መቻሉን፤ አርሶአደሮቹ በአጭር ጊዜ ውስጥም ምርታማ በመሆናቸው ኑሯቸውም ከታሰበው ጊዜ ፈጥኖ መሻሻል ማሳየቱን ያስገነዝባሉ።
በወረዳዋ በተገኘው ፈጣን ውጤትና ምርታማነት ከፌዴራል ጀምሮ ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በሰባት ዙር ጉብኝት መደረጉን ጠቅሰው፣ ወረዳዋም እንደምርጥ ተሞክሮ ለሌሎች ተምሳሌት ሆና እየቀረበች መሆኑን አስታውቀዋል።
በስልጢ አባያ ሃይቅ ዙሪያ 105 ሄክታር መሬት በሙዝ መልማቱን በዚህም ከ262 ሺ በላይ አርሶአደሮች ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረው፤ ‹‹በወረዳው ከፍተኛ መነቃቃት ስለተፈጠረ ክረምት ላይ ብቻ ሳይሆን በጋ ላይም በመስኖ ሙዝ እየተተከለ ነው። የሴፍትኔት ተጠቃሚ የነበረ አንድ አርሶአደር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ችግኝ በመሸጥ 30 ሺ ብር ያገኘበት አጋጣሚ አለ›› በማለት ያስረዳሉ። መስኖ የሌለባቸው ቀበሌዎች ወጣቶች ሳይቀሩ በሙዝ ምርት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የሥራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል ይላሉ።
በተለይም ደግሞ በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር አማካኝነት አርሶአደሩ በክላስተር እንዲደራጅ በማድረግ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ መደረጉ በዘርፉ ከፍተኛ እምርታ መመዝገቡን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ ይገልፃሉ። ይህም ለአመራር ምቹ ያደረገው ከመሆኑም ባሻገር ችግሮች ሲያጋጥሙ በፍጥነት ለመፍታት ትልቅ አቅም የፈጠረ እንደሆነ ነው ያነሱት። ‹‹ሙዝ ሲተከል ዘርፈ ብዙ ጥቅም ነው ያለው፤ ለምሳሌ እዚህ ባህር ዛፍ ነቅለን በተከልነው ሙዝ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ያገኘነው ጎን ለጎን በተከልናቸው የጓሮ አትክልቶች ነው›› ሲሉም አስረድተዋል።
የወረዳውን ግብርና አሠራር ከማዘመን አኳያ በተለይ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ባላቸው ቀበሌዎች ላይ በተደረገው ርብርብ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መካናይዝድ የሆነ የእርሻ ሥራ መጀመሩን ይጠቅሳሉ። በተጓዳኝም በተፈጠረው መነቃቃት ብቻ ዓምና ሁለት አርሶአደሮች በራሳቸው አቅም ትራክተር መግዛታቸውን ያመለክታሉ። ወደፊትም በአንድ ቀበሌ ቢያንስ አንድ ትራክተር ፤ በአንድ ወረዳ አንድ ኮምባይነር መኖር አለበት የሚል አቋም ተይዞ እየተሠራ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት።
አቶ ጀማል ከገበያ ትስስርና ከመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ጋር በተያያዘ በአርሶአደሮቹ የተነሱ ስጋቶችን በሚመለከት ‹‹በአርሶአደሮቹ የተነሱት ስጋቶች ተገቢና እኛም የምንጋራቸው ናቸው፤ በተለይም ወቅቱን ጠብቆ ከመጠገን አንፃር ክፍተቶች እንዳሉ እኛም እናምናለን›› ብለዋል። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን ድረስ ያሉ አመራሮች ተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ማቅረባቸውን ያነሳሉ። ሆኖም የቀድሞ ደቡብ ክልል ከነበረው የተበታተነ አሠራር አኳያ የሚጠየቅም አካል ባለመኖሩ ለዓመታት የሕዝብ መልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ያስታውሳሉ።
ወረዳው ባለው አቅም መንገዶችን የመጠገን ሥራ እየሠራ ቢሆንም ችግሩ ሰፊ በመሆኑ በወረዳው አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ከሚመለከተው የክልል አመራር ጋር ውይይት እየተደረገበት ስለመሆኑ ምክትል አስተዳዳሪው ይገልፃሉ። ከገበያ ትስስሩ አኳያ ግን እንደዞንም ሆነ እንደ ወረዳ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የቅዳሜእና የእሁድ ገበያዎችን በማዘጋጀት አርሶ አደሩ ምርቱን የሚሸጥበት እድል መመቻቸቱን ይጠቁማሉ።
‹‹ከዚህም ባሻገር እንደወረዳችን ከ350 በላይ አባላት ያሉት የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር አደራጅተናል፤ እውቅና አግኝተናል፤ በመሆኑም ከወረዳው ተጠቃሚዎች የተረፈውን ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ጭምር ማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ትስስር ለመፍጠር እየሠራን ነው፤ በመሆኑም የወረዳችን የሙዝም ሆነ ሌሎች ምርቶች ለውጭ ገበያ ጭምር በማቅረብ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ አቅም እንሆናለን የሚል እምነት አለን›› ሲሉም አብራርተዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም