“ትውልዱ ያለውን ሀብት በቁጠባ ተጠቅሞ ለቀጣዩ ትውልድ በኃላፊነት ስሜት ማስተላለፍ ይጠበቅበታል” -አቶ ኃይሉ ጀልዴ የአዳማ ከተማ ከንቲባ

በኦሮሚያ ብሔራዊ፣ ክልላዊ መንግሥት፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን የምትገኘው የስምጥ ሸለቆዋ እንቁ አዳማ፤ የንግድ፣ የቱሪዝምና የኮንፍረንስ ማዕከል መሆኗ ይታወቃል። በስድስት ክፍለ ከተማ እና በ 19 ወረዳዎች በተዋቀረች በዚህች ከተማ፤ ከቱሪዝምና ከኮንረፍረንስ ከተማነቷ ጎን ለጎን ብልጽግናን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ያለመሰልቸት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ናቸው። በከተማዋ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አንዱ ሲሆን፣ ይህንንም ስኬታማ ለማድረግ ለወጣቶችና ለሌሎቹ ሥራ አጦች የሥራ እድል በመፍጠር ለተሻለ ለውጥ እየተሠራ ነው፡፡

ከሰሞኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ በጋራ በመሆን በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ የመስክ ምልከታን ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን በአዳማ ከተማና በዙሪያዋ እየተከናወነኑ ያሉ ሥራዎችን ማየት ተችሏል። የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች፤ በተለያየ የሥራ መስክ በመሠማራታቸው ከተሞች በገጠራማው ክፍል የሚመረተውን ብቻ ተቀምጠው እንዳይጠብቁ ማድረጋቸው አንዱ ማሳያ መሆን መቻላቸውን አስተውለናል፡፡

ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በአዳማ ከተማ እና ዙሪያ ባሉ የተወሰኑ ክፍለ ከተማዎችና ወረዳዎች ላይ ያደረግነውን የመስክ ምልከታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ጋር ቆይታ አድርገናል።

 አዲስ ዘመን፡- ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በተያዘው በጀት ዓመት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ምንድን ናቸው?

አቶ ኃይሉ፡- በ2016 በጀት ዓመት ዋና የሥራዎቻችን ማዕከል የሆኑት የሕዝብን ችግር የምንፈታበት ተግባራት ናቸው። ከዚያ ውስጥ እንደከተሞች የተቀመጡ ግቦች አሉ። በክልላችን በተቀመጠው እቅጣጫ መሠረት በአዳማ ከተማ ልናሳካ የሚገባን እና የሁሉም እቅድ መነሻ የሚሆነው አራት ግቦች አሉን።

ከዚያ ውስጥ አንዱ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሲሆን መሠረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ የትኛውም ሥራ አሊያም ደግሞ የምንሰጠው አገልግሎት ይሁን የሥራ እድል ፈጠራም ድምር ውጤቱ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። አምርተን ወይም ደግሞ ከሌላ ቦታ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታን ፈጥረን ሊሆን ይችላል፤ ዋናው ትኩረታችን ግን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው።

በሁለተኛነት ደረጃ የተቀመጠው ግብ ክህሎት እና ፈጠራ ጋር የተያያዘ ነው። ሥራን ሊያበረታታ የሚችል ክህሎት እንደከተማችን መሠራት አለበት የሚል ነው። ይህም ክህሎት ያለው ማኅበረሰብ የመፍጠር እንዲሁም የሥራ ባሕል የማሳደግ ሥራ ነው፡፡

እንደ ከተማ አስተዳደር ልናሳካ ይገባል ብለን በአቅጣጫችን መሠረት የምንተገብረው ሶስተኛው ግብ ደግሞ ኢንተርፕርነርሺፕ ማስፋት እና መፍጠር ነው። ራስን ሆኖ መገኘት እና ኢንተርፕርነር ላይ በአግባቡ መሥራት ነው። ራሱ መንግሥት የኢንተርፕርነርን እሳቤ የተላበሰ እና አመቻች መንግሥት እንዲሆን፣ እስከታች ባለው የመንግሥት መዋቅር በዚህ መልኩ እንዲሆን እየሠራን ነው ያለነው።

በአራተኛ ደረጃ የመንግሥትን አገልግሎት ማሻሻል ነው። እንዲህም ሲባል የሚሰጠውን አገልግሎት ማዘመን ማለት ነው። በሒደትም ወደ ኢ-ገቨርነንስ (E-Gov­ernance) የማሸገጋገር ሥራ ነው። የእነዚህ ግቦች ዋና ዓላማው በተለይ አራተኛው የመንግሥትን አገልግሎት የማሻሻል እና የማዘመን ግብ ለሶስቱ ግቦች ወሳኝ ነው።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት አገልግሎት ማሻሻል ሲባል መገለጫው ምንድን ነው?

አቶ ኃይሉ፡- ጠንካራ መንግሥት የማይኖር ከሆነ፣ አቅዶ መፈጸም የማይችል መንግሥት ከከተማ አስተዳደር እስከወረዳው ድረስ ባለው ሰንሰለት የማይታይ ከሆነ ሶስቱም ግቦቻችን ሊሳኩ አይችሉም። እኛም ስንሠራ የነበረው ይህንን አቅጣጫ ይዘን ነው። ከዚህ አንጻር አራቱንም ግቦች የሥራ እድል ፈጠራ ያካትታል ብዬ ገምታለሁ።

በመሆኑም በ2016 ዓ.ም ዋና የሥራ እድል መፍጠሪያ ማዕከል ያደረግነው ማነሳሻዎችን (ኢንሼቲቮችን) የማሳካት ሥራ ነው፤ ማነሳሻዎቹ (ኢንሼቲቮቹ) ብዙ ናቸው። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል የሥራ እድል መፍጠር አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው የሕዝባችንን የኑሮ ሁኔታ እና የአመጋገብ ሥርዓት የመቀየር እና ብቁ ዜጋ የመፍጠርን ራዕይ ነው።

ለምሳሌ የእንቁላል ዶሮ እርባታ ልማት ሥራ አንዱ ማዕከል ነው። ሁለተኛ የወተት ልማት ሥራ ሲሆን፣ ሶስተኛ የሥጋ ልማት ስራ ነው። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ የዓሳማ እርባታ ሥራ፣ የንብ ማነብ፣ ኮቴጅ ኢንዱስትሪ፣ አትክልትና ፍራፍሬንም ጭምር የሚጠቀሱ ሥራዎች ናቸው።

እነዚህን ማዕከል አድርገን በሠራነው ሥራ እስካሁን አጠቃላይ ሲደመር ወደ 900 ሼዶችን ገንብተን የሥራ እድል መፍጠሪያም እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠራ ነው፤ እነዚህ ሼዶች ለከተማውም ምርት የሚያቀርቡ ይሆናሉ። የሕዝብንም ችግር ይቀንሳሉ በሚል አቅደን ወደሥራ በገባነው መሠረት እስካሁን ወደ አንድ ሺ 300 በላይ ሼዶችን መገንባት ችለናል።

በእነዚህ በተገነቡ ሼዶች የእንቁላል ዶሮ የሚያረቡትን፣ የወተት ከብት የሚያረቡትን፣ የሚያደልቡት እና ሌሎችንም ወደሥራ ማስገባት ችለናል። በማሳ ደረጃ ደግሞ አትክልት እና ፍራፍሬው ላይ እየሠራን ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አቡካዶውና ፓፓያ በመተከሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚደርስ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ሥራዎች የምታከናውኑት እንዴት ነው? የተቀመጠላቸው አሠራር ምን ይመስላል?

አቶ ኃይሉ፡- የዚህ ድምር ውጤት የምናሳካበት ደግሞ አቅጣጫዎች ነበሩን። የምናሳካበት እና የሚኖረን ሀብት ለመለየት የምንሠራበት አቅጣጫ እንዴት ነው የምናሳካው የሚለው አንዱ እቅድ ነው፤ እቅዱ ላይ የተቀመጠውም ማን ምን ይሥራ የሚል ነው። 900 ሼዶችን መገንባት እንዴት እንችላለን? ብርስ ከየት ይመጣል? ይህን ከመንግሥት በጀት ብቻ ብናወጣ ብዙ ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ ነው። በመንግሥት ብቻ ስለማንችል በእቅዱ ላይ ያስቀመጥነው ሞዳሊቲውን ለይተን ነበር። በክልል ደረጃ በክቡር ፕሬዚዳንቱ የተቀመጠ አቅጣጫ ስለነበረ እነዚህን ግቦች ለማሳካት አንደኛ የተጠቀምነው የጋራ አቅምን ነው። የጋራ አቅም የምንለው በሌላ ሴክተር በሌላ መልኩ የሚገለጽ ነው።

በሥራ እድል ፈጠራ ባለው ብቻ መግለጽ ካስፈለገ የአዳማ ባለሀብቶች ብር በማዋጣት ሼድ ሠርተዋል። ካላቸው ማሽነሪ ቀንሰው ሰጥተዋል። በሚችሉት ሁሉ እየደገፉን ነው። ዶሮ እና ላም ገዝተን እንድናስገባ በብዙ ረድተውናል። ስለዚህ አንድ ማዕከል ሙሉ በሙሉ በባለሀብት የተገነባ ሼድ ዶሮ ገብቶበት በመልማት ላይ ይገኛል። ሌሎችም በየወረዳውና በየክፍለ ከተማው በብዛት ተሠርቷል። በጋራ አቅም የሠራነው ከ35 እስከ 40 በመቶ ከጠቅላላው ሥራዎቻችን ይሸፍናል፡፡

ሁለተኛውና ዋናው ነገር የሥራዎቻችን ማጠንጠኛው የሥራ እድል ፈጠራን ቦታ ማእከል ያደረገ እንቅስቃሴ ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ የምግብ ዋስትናን የማናረጋገጥ ይሆናል። የምግብ ዋስትናን የምናረጋግጥበት መንገድ አንዱ የቤተሰብ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው፡፡

የቤተሰብን ብልጽግና የምናረጋግጠው ራሱ ቤተሰቡን በሥራው ተሳታፊ እንዲሆን በመቀስቀስ ነው። ቤተሰብ ውስጥ ያልተጠቀምንበት አቅም አለ። መሥራት የሚችል ጉልበት እና ክህሎት አለ። መነሻ ካፒታል አላቸው። ትንሽ ድጋፍ ካደረግንላቸው ምን እንደሚሠሩ በተግባር አይተናል። እሱም ከ55 እስከ 60 በመቶ ይዟል። እኛ ወደሥራ የገባነው እሱን አደራጅተን ነው።

በሶስተኛ ደረጃ የተጠቀምነው የመንግሥት አቅምን ነው፤ መንግሥት ይህን ሁሉ በሃሳብ መምራት እና መሥራት እንዲሁም ሁሉንም አቅሞች ማቀናጀት አለበት። ያለውን ሀብት ለዚህ ሥራ ማዋል አለበት። ከዚህ ጎን ለጎን ሀብትን በቁጠባ የመጠቀም ባህል ማሳደግና ያለውን ሀብት ለሥራ እድል መፍጠሪያና ለአራቱ ግቦች ማሳኪያ እንዲውል መመደብም አለበት። እኛም ያንን መድበን ወደሥራ ገባን፤ በዚህ መልኩም የተወሰኑ ሼዶች መሥራት ችለናል፡፡

ትልቁን ቦታ የያዘው ጉዳይ ሁለት ነው፤ አንደኛው በሥራ እድል ፈጠራ የሕዝብን አቅም በአግባቡ መጠቀም ሲሆን፣ እሱ የስኬት ምንጭ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የቤተሰብ አቅምን በደንብ መጠቀም ነው፤ ቤተሰብ በራሱም ይሠራል፤ ተመልሶም የሥራ እድል መፍጠሪያ ማዕከል ሆኗል። እስካሁን ባየነው ነገር ይዘን እየሄድን ያለነው እነዚህን ነው። ብዙ ሥራዎችም በዚህ መልኩ ተሠርተዋል፡፡

በእርግጥ እነዚህን ሥራዎች ገና ስንጀምር የምንፈጽምበት አቅጣጫዎች ላይ ጭምር ግልጽ አልሆነልንም ነበር። ግልጽ ከሆነልን በኋላ እንኳ ሀብት የምናገኝበት መሆኑን አልተረዳነውም ነበር። በማስቀጠል ግን ሥራውን መሥራት ጀመርን፤ ከተማችን ለሼዶች ብቻ ከመቶ ሔክታር በላይ ምንም ካሳ ያልተከፈለበት ያለሥራ ተቀምጦ የነበረን መሬት ለዚህ ሥስራ ማዋል ቻለ።

ምናልባት የተወሰኑት በሕገ ወጥ የተያዙ እንዲሁም በተወሰኑ አካላት ተይዘው የነበሩ ሲሆን፣ ወደሕጋዊነት የማምጣት ሥራ በመሥራት የሥራ እድል መፍጠሪያ ማእከል ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ ቻልን። አጠቃላይ ድምር ውጤቱ ሲታይ ብዙ ሀብት ለዚህ ሥራ ውሏል ማለት ይቻላል። ብዙ ሀብት ለዚህ ሥራ በመዋሉ ብዙ ወጣቶች እና ሥራ አጦች የሥራ እድል አግኝተዋል።

ይህም በገንዘብ ሲሰላ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለሥራው ማዋል ተችሏል። ይህ ማለት ለአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለንብ ቀፎ የተደረገውን ዝግጁነት ሳይጨምር ማለት ነው። ይህ ወጪ ከመንግሥት የወጣው ትንሹ ሲሆን፣ እሱም ከሃያ በመቶ አይበልጥም። ምክንያቱም መንግሥት ሥራው ሼድ መገንባት ብቻ አይደለም። የመንግሥት ሃላፊነት ሁሉም ማዕከላት ላይ እንደ ውሃ እና መብራት ያሉ መሠረተ ልማቶች እንዲኖራቸው የማመቻቸቱን ተግባር በትጋት መወጣት ነው፤ ይህ የእኛ ድርሻ ስለሆነ ተግባራዊ አድርገነዋል። ስለዚህ ዘንድሮ በዚህ በኩል ያለውን ችግር ፈተናል ማለት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ግን ጌጠኛ ድንጋይ አንድም ኪሎ ሜትር አልሠራንም። ትኩረታችንን ያደረግነው የሕዝብን ኑሮ መቀየር በሚችሉ ፕሮጀክቶ ላይ ብቻ ነው። በዚህም ሥራችን ውጤት ማየት ችለናል። መሠረተ ልማት ያስፈልጋል። የአስፓልት መንገድ ያስፈልጋል። ነገር ግን ማስቀደም የተገባንን ማስቀደም የግድ ስለሆነ እሱን አስቀድመናል። በእርግጥ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ከዚህ ቀደም ሠርተናል፤ ይሁንና እንደ አሁኑ ትኩረት አልሰጠነውም ነበር። ሥራውን አጠናክረን የጀመርነው ዘንድሮ ነው፤ ይህ በቀጣይ ተጠናክሮ የሚሠራበት ይሆናል፤ የሠራነው ያለንን ሀብት ይበልጥ በቁጠባ በመጠቀም የሕዝብን ችግር የሚፈታ እና ኑሮን የሚያሻሽል እንዲሆን በማድረግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሥራ እድል በዚህ መልኩ መፍጠር በመቻላችሁ የመጣ ለውጥ አለ ይላሉ?

አቶ ኃይሉ፡- የሥራ እድል ፈጠራው በርካታ ችግሮችን ፈቷል ብለን እናስባለን። አንደኛ ለብዙ ወጣቶች እና ሥራ አጦች የሥራ እድል ፈጥሯል። የሥራ እድል መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው የሥራ እድል የተፈጠረላቸው አካላት የከተማው ዋስትና መሆን ችለዋል። ብዙ ምርት ወደከተማ እንዲመጣ ምክንያት ሆነዋል። ይህ ማለት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መትረፍ ችለዋል እንደ ማለት ነው። በአሁኑ ሰዓት ብዙ ምርት ወደከተማ መጥቷል።

ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ ሁለት ነገሮችን መጥቀስ እፈልጋለሁ። ይህን እቅድ ስናቅድ የእንቁላል ዋጋ በአማካይ 13 ብር ነበር። በዓመቱ መጨረሻ ልንደርስበት የነበረውን በስምንተኛ ወር አካባቢ ልናሳካው ችለናል። በአሁኑ ሰዓት የአንድ እንቁላል ዋጋ በአማካይ ከስምንት እስከ ሰባት ብር በመሸጥ ላይ ነው። ይህ ትርጉሙ ብዙ ነው። በአንድ ነገር ላይ ተባብረን የምንሠራ ከሆነ የሕዝባችንን ችግር መፍታት ይቻላል የሚለየውን መለየት ችለናል።

በኮቴጅ ኢንዱስትሪ ብናይ ብዙ አሉ። አጠቃላይ የሥራ እድል ፈጠራ ሴክተር የሁሉም ሴክተር እንዲሆን ተደርጓል። ሁሉም ሴክተር ተሳትፎበታል። የሆነው ነገር ቢኖር በከተማው ያለ ሀብት የሥራ እድል መፍጠሪያ ማዕከል እንዲሆንና ተመልሶ ወደሕዝብ እንዲሰራጭ ነው። በእስካሁኑ ሒደት ጅማሮው ጥሩ የሚባል ነው ብለን ገምግመናል።

አዲስ ዘመን፡- አቅምን ለማጎልበትና ቴክኖሎጂንም በግብዓትነት ለመጠቀም በቀጣይ ያቀዳችሁት ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ ኃይሉ፡-እስካሁን በሠራነው ሥራ ለብዙ ወጣቶች እና ሥራ አጦች በርካታ የሥራ እድል ተፈጥሯል። የሥራ ልምምድም አድርገናል። ያልተለመዱ ሥራዎችን መተግበር ጀምረናል። ብዙ ምርት ማምረትም እንዲሁ ጀምረናል። አሁን ላይ ቆም ብለን ስናይ ግን አንደኛ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ አለብን። የጀመርነው በቅርብ ነው። ይሁንና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በአግባቡ መሠራት አለበት።

ለምሳሌ የዶሮ እርባታው ቀጣይነት የሚኖረው የኢንቨስትመንት ወጪውን መቀነስ ስንችል ነው። እንዲህም ሲባል በኢንቨስትመንቱ ላይ የሚወጡ ሀብቶችን እዚሁ በእዚሁ እንዲሆን ማድረግ ነው። ለምሳሌ እንደሚታወቀው የዶሮ መኖ የሚመጣው ከሌላ ቦታ ተጭኖ ነው። ይህን የዶሮ መኖ እዚሁ በማምረት ከሌላ ቦታ ማምጣቱን ሙሉ ለሙሉ መተው አንድ ርምጃ ወደፊት እንደመሄድ ነው።

ይህ አይነት አካሔድ ብቻ ሳይሆን በየማዕከሉ የማዘመን ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል። የምናረባው ዶሮ ጤንነት መጠበቅ አለበት። ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ሥራውን ወደእርሻ እየቀየርን እርሻዎቹ ክሊኒክ እንዲኖራቸው እየሠራን ነው። በአሁኑ ሰዓት እየተከናወነ ያለው እንቅስቃሴ ቀጥለን ለምንሠራው ሥራ ማዕከል እንዲሆን ታስቦ ነው።

ይህ ብቻ ሳይሆን የሥራ እድሉ የተፈጠረላቸው ወጣቶች በተለያየ የሥራ መስክ ግንዛቤው ይኖራቸው ዘንድ ታስቦ ሥልጠና ወስደዋል። ዘንድሮ ወደሥራ የገቡት ወጣቶች በልዩ ኢንሼቲቭ ለመለየት ጥረት አድርገናል። ሙሉ በሙሉ በዲጂታል አይ.ዲ (Digital ID) እንዲመዘገቡና በጉዳዩ ዙሪያ ሥልጠና ወስደው ወደሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። አሁንም ሥራው ያለቀ ሳይሆን ክትትልን የሚጠይቅ ነው። በእነርሱ ላይ ያለመሰልቸት መሥራት ያስፈልጋል። ተከታታይ የሆኑ ሥልጠናዎችን በመስጠት ማጠናከር ግድ ይላል፡፡

ሥልጠና መስጠት እና ክትትል ማድረጉ ላይ በአግባቡ ከሠራን ቀጥሎ የሚመጣው የሥራ ባህል ነው። በአሁኑ ወቅት የኮቴጅ ኢንዱስትሪው በብዛት እያመረተ ነው። በኮቴጅ ኢንዱስትሪው ልብስ፣ ጫማ፣ ካልሲ እና የምንገለገልበትን ሁሉ በማምረት ላይ እንገኛለን። በዚህ መልኩ ለገበያ አቅርቦት የሚውል የምንጠቀምባቸውን ቁሳቁስ እናምርት በሚል ወደትግበራ ገብተናል፤ ውጤትም እያመጣን ነው። ነገር ግን ይህን በአግባቡ ማስፋትና ማስቀጠል ይጠይቃል። የምናመርተውን ምርት ይበልጥ ማሳደግን ይጠይቃል። ምርት ለመጨመር የሥራ ባህልን ማሳደግ ወሳኝ ነው። ሌላው ምርት የምንጨምር ከሆነ እና ወጣቶች ጠንክረው እንዲሠሩ በሥልጠና የምንደግፋቸው ከሆነ ቀጥሎ የሚመጣው የገበያ ሁኔታ ነው። የገበያ ችግር እንዳይገጥመን ከወዲሁ በእቅድ ይዘን ስንሠራ ቆይተናል።

ለኢንሼቲቩ በሙሉ የሚሆን አስር የገበያ ማዕከላትን ለመገንባት አቅደን በእስካሁኑ ሒደት ስድስቱን ማጠናቀቅ ችለናል። ስለዚህ በዚህ አይነት ሁኔታ ቀሪዎችንም እየገነባን ከመጣን የገበያ ችግር አይኖርባቸውም። እኛ እየሠራን ያለነው ወጣቶቹ የሥራ እድል እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይነቱም ዋስትና እንዲሆን ጭምር ነው፡፡

በጌጠኛ ድንጋይ (በኮብል ስቶን) መንገድ መሥራትን ትተን በጀቱን ወደማምረት የምናዞረው ለሥራ አጦች ሥራ ፈጠርን ለማለት ብቻ አይደለም። ከሥራ እድል ፈጠራ ባሻገር በቀጥታ ጠቀሜታው ኅብረተሰቡ ድረስ እንዲዘልቅ በማሰብ ነው። የአንድ እንቁላል ዋጋ ከ13 ብር ወደ ስምንት ብር ዝቅ ያለው እንዲሁ በምኞት አይደለም። እኛ ለመሥሪያ ቦታ የሚሆኑ ሼዶችን በአግባቡ ገንብተን፣ ለሼዶቹ መብራት አስገብተንና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አሟልተን ነው። በሌላ አገላለጽ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚከፈል ዋጋ አለው ማለት ነው። ይህ ክፍያ የመጣው ግማሹ በመንግሥት፤ ግማሹም በኅብረተሰቡ ትብብር ነው። ይህ ትብብር ተደምሮ መድረስ ያለበት ራሱ ኅብረተሰቡ ዘንድ ነው። ወደኅብረተሰቡ ይደርስ ዘንድ ገበያ ወሳኝ ነው። ከዚህ የተነሳ የገበያ ሰንሰለቱን በደንብ መጠበቅ ይጠይቃል። ስለዚህ እንደ ከተማ የምናመርተውን ምርት መቆጣጠርና ወደገበያ በአግባቡ መድረስ መቻሉን ማረጋገጥ አለብን። ይህ የሚሆነው ግን በእኛ ደረጃ ባለው ሁኔታ ነው። ሀገራዊ እና ዓለምአማቀፋዊ ሁኔታ ከፍ ሊል ይችላል።

ምርት እንጨምራለን ወጣቶች ይጠነክራሉ። ገበያው ደግሞ አለ፤ ቀጥሎ የሚመጣው ቁጠባ ነው። ወጣቶቹ የሥራ ባህላቸውን ካሳደጉ፣ ያለንን ሀብት ጨርሰን መሔድ አይፈቀድም ማለት ነው። አሁን እያልን ያለነው ትውልድ፣ ያለውን ሀብት በቁጠባ ተጠቅሞ ለቀጣዩ ትውልድ ኃላፊነት በተሞላው ስሜት ማስተላለፍ የሚጠበቅበት ይሆናል። ቀጥሎ ያለው ወጣት ይጠብቃል። አንደኛ የሠራነው ሥራ መሸጋገር አለበት። ተሞክሮውም ሥራውም ሁሉም ዘንድ መድረስ አለበት። ሥራው ራሱ ራሱን መግለጽ መቻል አለበት። ሁለተኛ ደግሞ ሀብቱም መሸጋገር መቻል አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከወጣቶቹ የሚጠበቀው ምንድን ነው?

አቶ ኃይሉ፡- ቁጠባ ነው፤ ወጣቶቹ እንዲቆጥቡ ማድረግ ይጠበቃል፤ ይህ ግዴታም ጭምር ነው ። ይህን ሒደት መንግሥት ማቀናጀት፣ መደገፍ እና ሁኔታውን መከታተል ይጠበቅበታል። ሁሉም በስንቄ ባንክ አካውንት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ስለዚህ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል።

ከቆጠቡ በኋላ በቀጣዩ ዓመት በርካቶቹ ወደ መለስተኛ ኢንዱስትሪ እንዲሁም ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር መቻል አለባቸው። ለዚህ አሠራር ደግሞ ክልላችን ግልጽ ሕግ አለው። አርሶ አደሩም ጭምር ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚገባበት ግልጽ አሠራር አለ። የራሱ የሆነ መመሪያ እና ደንብም ተዘጋጅቶለታል።

ወጣቶችም በዚያ መልኩ በልዩ ማበረታቻ ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡበት ሕግ አለ። ስለሆነም እነርሱን ለዚያ ማዘጋጀት አለብን። የፈጠርነው የሥራ እድል ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አሁን የያዝናቸውን ይዘን ወደሚቀጥለው መሔድ ይጠበቅብናል። እሱን ደግሞ ጀምረነዋል። ዋና ማነቆዎች ናቸው የሚባሉትን እየፈታን እና መፍትሔ እያበጀን የማበረታቻ ጥቅሎችን እያጠናከርን የምንሔድ ከሆነ አንደኛ እነርሱ የሚሠሩት ሥራ ለሕዝባችን የሚተርፍ ይሆናል። ሁለተኛ ደግሞ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ማዕከላት ማቀነባበሪያ እየሰፋ እንዲሔድ ለሚቀጥለው ዘመንም ሰፊ እቅድ ይዘን እየሠራን እንገኛለን።

ግራም ነፈሰ ቀኝ የሥራ እድል መፍጠሪያ የሆኑትን አራቱን ግብ ማሳካት የግድ ነው። በተለይ ደግሞ ሶስቱን ግብ ማለትም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የክህሎት መፍጠሪያ ማዕከል ለመሆን እና ኢንተርፕነር መፍለቂያ ለመሆን መትጋት ይጠበቅብናል። ይህን ክንውን ግማሹን የመንግሥት ሴክተሮች የሚይዙት ይሆናል። ግማሹን እዛው ማዕከል ፈጥረን ማሠልጠኑን ተያይዘነዋል። የኮቴጅ ኢንዱስትሪውን ደግሞ ኃላፊነቱን ለኮሌጁ ሰጥተናል። ኮሌጁ በዚህ ዘርፍ በአግባቡ እየሠራ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ እናመሰግናለን።

አቶ ኃይሉ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You