በእስራኤል የሚገኘው የአልጀዚራ ጣቢያ ተዘጋ

በእስራኤል የሚገኘው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ መዘጋቱ ተዘገበ፡፡ “ጣቢያው የተዘጋው የሐማስ አፈ ቀላጤ ሆኗል’’ በሚል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ “የእስራኤል ካቢኔ ጣቢያው እንዲዘጋ ወስኗል” ብለዋል። ይህን ተከትሎ ፖሊስ በጣቢያው ቢሮ ኢየሩሳሌም፣ አምባሳደር ሆቴል ብርበራ አድርጓል።

እስራኤል “አልጀዚራ ለብሔራዊ ደኅንነቴ ሥጋት ነው” ማለቷን ጣቢያው፣ “ቀሽም ነገር ግን አደገኛ ውሸት” ሲል አጣጥሎታል። ጣቢያው በሕግ መብቱን እንደሚያስከብርም ዝቷል።

የእስራኤል የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ሽሎሞ ካርሂ በድንገተኛ ወረራው አንዳንድ ቁሳቁሶች ተወስደዋል ብለዋል። በዚሁ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የኤክስ ገጽ በተለጠፈ ተንቀሳቃሽ ምሥል ፖሊሶች ወደ ሆቴሉ ገብተው ሲበረብሩ ያሳያል።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ወደ ሥፍራው አቅንተው የነበረ ቢሆንም ወደ ውስጥ እንዳይገቡ፣ ክስተቱንም እንዳይቀርጹ ተከልክለዋል ተብሏል።

ሮይተርስ እንደዘገበው የእስራኤል ሳተላይት አገልግሎት አልጀዚራ ይታይበት በነበረ ምሥል አሁን የጽሑፍ መልእክት ብቻ እየታየ ይገኛል፤ መልእክቱም “መንግሥት በወሰነው መሠረት በእስራኤል የአልጀዚራ ሥርጭት እንዲቆም ተደርጓል” የሚል ነው።

አልጀዚራ በሳተላይት ይታገድ እንጂ አሁንም በእስራኤል በፌስቡክ እየታየ ነው። የሰብአዊ መብት ድርጅቶች መንግሥት አልጀዚራን ለመስጋት መወሰኑን አውግዘዋል።

የሲቪል መብቶች ኅብረት በእስራኤል ድርጊቱን ከኮነነ በኋላ ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን እንዲቀለብስ ጥያቄ ማቅረቡን ተናግሯል።

ይህ የእስራኤል የሰብአዊ መብት ኅብረት እንደሚለው አልጀዚራ የሐማስ ድምጽ ነው የሚለው ክስ “ውሃ አያነሳም።’’

አልጀዚራ እንዲዘጋ የተወሰነው በብሔራዊ ስጋት ምክንያት ሳይሆን የፖለቲካ ዉሳኔ ስለሆነ ነው፤ ድምጽን ለማፈን የሚደረግ ሙከራ ነው ብሏል ኅብረቱ።

የውጭ ሚዲያዎች ማኅበር በእስራኤል በተመሳሳይ የአልጀዚራን መዘጋት “አሳሳቢ” ሲል ገልጾታል።

የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ ፕሮግራም ዳይሬክተር ካርሎስ ማርቲኔዝ ዴ ላ ሰርና የእስራኤል መንግሥት በተለይ በጦርነት ጊዜ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በነጻነት እንዲሠሩ ማድረግ ሲገባው በተቃራኒው አልጀዚራን መዝጋቱ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ቢሮም የእስራኤል መንግሥት ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነው ጠይቋል።

የውጭ ሚዲያዎች ጋዛ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም። ብቸኛው በጋዛ ሪፖርተሮች የነበሩት አልጀዚራ ነበር። የእስራኤል ባለሥልጣናት ለዓመታት አልጀዚራን ‘’ጸረ-እስራኤል’’ በሚል ሲከሱ ቆይተዋል። ይህ ክሳቸው በተለይ ሐማስ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ከገደለ በኋላ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ 34ሺህ 683 ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል፤ 70ሺህ 18 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስትር እንደሚለው ከሟቾቹ መካከል የሚበዙት ሴቶችና ሕጻናት ናቸው።

የአልጀዚራ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው ኳታር ሲሆን ይቺ ሀገር በሐማስና በእስራኤል መካከል ቁልፍ አሸማጋይ እንደሆነች ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ኳታር ሁለቱን ተዋጊዎች አሸማግላ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ተደርጎ፣ 105 እስራኤላዊ ታጋቾች መለቀቃቸው አይዘነጋም። አልጀዚራ እንደሚለው እስራኤል የጣቢያውን ጋዜጠኞች ሆን ብላ ገድላለች።

ከነዚህ መካከል መላ ቤተሰቡ የተገደለበት የአልጀዚራ የጋዛ ቢሮ ኃላፊ ዋ’ል አልደህዱህ የበኹር ልጅ ሐምዛ አል-ደህዱህ የተገደለበት ሁኔታ ይጠቀሳል። እስራኤል ይህን ክስ ታስተባብላለች።

አልጀዚራ በእስራኤል መዘጋቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “እስራኤል ነጻ ፕሬስን በማፈን የምትፈጽመውን ግድያ መሸፍን አትችልም። ከዚህ ቀደም ጋዜጠኞቻችንን በመግደልና በማሰር ልታቆመን እንዳልቻለችው ሁሉ አሁንም የጋዜጠኝነት ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።” ብሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2016 ዓ.ም

Recommended For You