አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመንን በትውስታ፤ ትዝታን ይዞ 50 ዓመታትን ወደኋላ…ከሀገር ውስጥ እስከ ባህርማዶ፤ የዓለማችንን የኋላ ታሪክና አስገራሚ እውነታዎችን እናገኝበታለን። በዚያን ጊዜ… የመብራት ኃይሉ ሠራተኛ፤ ከመጠጥ ቤት አሊያም ከአሳቻ ስፍራ ሳይሆን፤ ከዚያው ከመሥሪያ ቤቱ ሠገነት ላይ በባልደረባው አምስት ጥይቶችን አርከፍክፎ፤ የገዛ ግንባሩንም በጥይት በመንደል፤ ሁለቱም ጎን ለጎን ተዘርረዋል። በጩቤ አስፈራርቶ፤ አህያ የሚሰርቀው ሌባስ፤ ምን ዓይነቱ ሌባ ይሆን…የ80 ዓመቷ አዛውንት፤ ለድፍን ስምንት ዓመታት የጠፋችውን ድመታቸውን በመፈለግ፤ በሬዲዮና በጋዜጣ ሳይቀር አፋልጉኝ እያሉ ሀብት ንብረታቸውን አንጠፍጥፈውላታል። አስገራሚውን ታሪክ፤ ከጥቂት የጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎች ጋር ትውስታን እናጭርባቸው።

የመብራት ኃይል ሠራተኛ ጓደኛውንና ራሱን ገደለ

አዲስ አበባ ኢ.ዜ.አ፡- ካሳዬ ኃይሌ የተባለ የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ባልደረባ፤ ሰይድ አብደላ የተባለውን የዚሁ መሥሪያ ቤት ሠራተኛ ትናንት ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁናቴ በሽጉጥ ተኩሶ ከገደለው በኋላ፤ ራሱንም በያዘው ሽጉጥ ተኩሶ የገደለ መሆኑን ከፖሊስ የተገኘው ዜና ገለጠ።

ገዳይ ካሳዬ ኃይሌ ዕድሜው 30 ዓመት፤ ሟች ሰይድ አብደላ ዕድሜው 28 ዓመት በደጎል አደባባይ አጠገብ የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በዋጋ ትንተና ክፍል ይሠሩ ነበር። የሁለቱም አስክሬኖች ከመሥሪያ ቤቱ 3ኛ ፎቅ ላይ ተዘርረው መገኘታቸውን የሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ቃል አቀባይ አስታውቋል።

የፖሊስ ጣቢያው ምርመራ ማረጋገጫ ክፍል፤ ካሳዬ ኃይሌ የተባለው ቁጥር 96 ፖ 218 በሆነ አነስተኛ የአሜሪካ ኮልት ሽጉጥ 5 ጥይት ተኩሶ ሰይድ አብደላን ከግራ ዦሮው አጠገብና ከቀኝ እግሩ ባቱ ላይ በመምታት የገደለው መሆኑንና አምስቱም የተተኮሱት ጥይቶች ቀለህ፤ በዚያው በበረንዳው ላይ መገኘቱን አመልክቷል።

እንዲሁም ገዳዩ በድጋሚ አምስት ጥይት አጉርሶ በአንድ ጥይት ራሱን በገዛ እጁ ከግንባሩ ላይ መትቶ የገደለ መሆኑንና የቀሩት 4ቱ ጥይቶች ከነሽጉጡ መገኘታቸውንና የሁለቱም ሬሳ በወለሉ ላይ እንዳለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ቴክኒካዊ ማስረጃዎችን ከወሰደ በኋላ አስክሬኑን ለምርመራ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተላከ መሆኑን ገልጧል።

( አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 1966ዓ.ም)

አህያ የሰረቀው 3 ዓመት ተፈረደበት

አህያ ከታሰረበት ፈትቶ የሰረቀው የሱፍ ሐጂ አብዱላሂ፤ በ3 ዓመት እስራት እንዲቀጣ የሐረር ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ፈረደ።

የሱፍ ሐጂ አብዱላሂ ይህንን ወንጀል የፈጸመው፤ በድሬዳዋ ከተማ ባለፈው ነሐሴ 15 ቀን 62ዓ.ም ነው። ባለንብረቱ በዚያው ዕለት የተወሰደውን አህያ ከነኮርቻው ከአንድ ዛፍ ጥግ አስሮ ውሀ ለማመላለስ ወረፋ ይጠባበቅ እንደነበር አንድ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ገልጧል።

ተከሳሹ አህያውን ከታሰረበት ሥፍራ ፈትቶ በወሰደበት ወቅት፤ ባለቤቱ ተከታትሎ ደርሶበት ነበር። ነገር ግን ተከሳሹ ባለቤቱን በጩቤ አስፈራርቶ አህያዋን በኃይል መውሰዱ በሕግ ምስክሮች ተረጋግጦበታል። በዚህም ምክንያት ፍርድ ቤቱ በየሱፍ ሐጂ አብዱላሂ ላይ የ3 ዓመት እስራት በይኗል። አህያው 65 ብር እንደሚያወጣ የተገመተ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አስረድቷል።

(አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 ቀን 1962ዓ.ም)

ብታምኑም ባታምኑም

የ80 ዓመቷ አዛውንት ድመታቸውን ፍለጋ ተሰደዱ

ሚስስ ግላዲስ ሞርቶን የተባሉ የ80 ዓመት አዛውንት አብራቸው የኖረች እንደልጅ ያሳደጓት ድመት ከስምንት ዓመት በፊት ጠፍታባቸው በሬዲዮ፤ በጋዜጣ ማሳወጅና ለአፈላላጊ ወሮታ ከ5ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርገዋል።

አሁንም ተስፋ ሳይቆርጡ የመጨረሻውን ፍለጋ ለማድረግ ቤታቸውን ቆላልፈው ከወጡ 15 ቀን ሆኗቸዋል። እስካሁንም ወደቤታቸው አልተመለሱም።

ሰው አስገድዶ ወስዶብኝ መሆን አለበት እንጂ፤ ድመቴ እኔንና ቤቷን እንደምትወድ አውቃለሁ። አሁንም ቢሆን፤ ልታገኘኝ የምትችልበት ዘዴ ጠፍቷት ይሆናል እንጂ፤ በልቧ ሳታስበኝ አትቀርም በማለት ሊያጽናናቸው ለመጣ እንግዳ ሁሉ አዛውንቷ የሚያዋዩት ይህንኑ ነው።

ፑ የተባለችው የሚስስ ሞርቶን ድመት የጠፋችው እ.ኤ.አ. በ1963ዓ.ም በሰኔ ወር ነው።

ሚስስ ሞርቶን በነዚህ ዘመናት ሁሉ ፑን ለማግኘት ያልወሰዱት ርምጃ ያላዩት ሰው የለም። ጧት ጧት ሁል ጊዜ በየመንደሩ እየዞሩ ድንገት ድምጼን ሰምታ ትመጣ ይሆናል በማለት “ፑ” እያሉ ሲጣሩ ይውሉ ነበር።

ሚስስ ሞርቶን ድመታቸው ከተለየቻቸው ጀምሮ ኑሯቸውን አስተሳሰባቸውንና ጠቅላላ ሁኔታቸውን ያየ ሁሉ ከንፈሩን የማይመጥ የለም።

ድመታቸውን ለመፈለግ በማለዳ እየተነሡ ፍለጋና ጥሪ በማድረግ ጎረቤቱን ማስመረራቸው ታውቋል። የእኚህኑ አዛውንት ጭንቀት የተመለከቱ ብዙ ሰዎች የፑን መሰል ድመት እያመጡ ተገኘች እያሉ ቢደልሏቸውም አልመስል እያላቸው አልተቀበሉም።

ድመታቸውና እርሳቸው አብረው በሚኖሩበት ጊዜ የነበራቸውን ደስታና ኑሮ ሲያስታውሱ ብቻቸውን ከማልቀሳቸውም ሌላ፤ ለሰው ሲናገሩም የሰማውንም ሰው ሆድ ያባባሉ።

“ከእንግዲህ ወዲህ እኔና ድመቴ ወጣት አይደለንም፤ ያለኝንም ሀብት በማፈላለጊያ ጨርሻለሁ፤ የሕይወቴም ጊዜ እያለቀ መሔዱ ነውና በሕይወት እንዳለሁ እርሷን ላገኘልኝ ሰው ያለኝን ሀብት ለመስጠት ቃል ገብቻለሁ” በማለት በሬዲዮና በጋዜጣ አሳውጀው አሁንም በፍለጋ ላይ ናቸው።

(አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 1964ዓ.ም)

ከእርስዎ ለርስዎ

_አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

*ጸጉሬ ባፈገፈገ ቁጥር የደመና ግላጭ ጸሐይን መቋቋም አቅቶኛል። ምን ይሻለኛል?

_ የአንበሳ ጎፍር ለጥፍበት እንዳልልህ ወደ ኬንያ መሻገር ሊኖርብህ ነው። የእኛዎቹ እንደሆን በአደንና በስደት አልቀዋል።

*አቶ ጌታቸው ደስታ ሀሙስ ማታ በሚያዘጋጀው የእንግሊዘኛ ዘፈን ፕሮግራም አብዶ እየሠራ አስቸግሮናል። ይኸውም ያንኑ ዘፈን እየደጋገመ በየሳምንቱ ያሰማናል።

ቴውድሮስ ዓለማየሁ(ከገለምሶ)

-ይሉሃል!።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 1965ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You