ቋሚ ኮሚቴው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሪፎርም ሥራውን ወደ ተግባር እንዲለውጥ አሳሰበ

-ተቋሙ በበኩሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል

አዲስ አበባ፡- የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተቋማዊ የሪፎርም ሥራውን ወደ ተጨባጭ ተግባር የመለወጥ ሥራ መሥራት እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። አገልግሎቱ በበኩሉ ተቋሙ ረጅም ጊዜያትን የተሻገሩ ችግሮች ያሉበት መሆኑን በመጥቀስ መፍትሔው ላይ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ትናንት የአገልግሎቱን የዘጠኝ ወር አፈጻጸም በመገምገም ሚያዝያ ሦስት በአገልግሎቱ ያደረገውን የድንገተኛ ምልከታ ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በአገልግሎቱ የተጀመሩት ሥራዎች ጥሩ እና ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም በተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን እና የተገልጋይን ቅሬታ መፍታት እንዳልተቻለ ጠቁሟል።ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ብለው በሚደርስባቸው እንግልትና ስቃይ ምክንያት በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ በድንገተኛ ምልከታ መመልከቱን ገልጿል።

በዋና መስሪያ ቤቱ ተገልጋይ በተቋሙ ሠራተኞች መሰደብ፣ መመናጨቅ እንዲሁም መገፍተር ጭምር የሚደርስበት በመሆኑ ተገልጋይ በሥነ ምግባር መስተናገድ አለበት።የተገልጋይ እርካታን የማሳደግ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል።

ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚሰሩ ሥራዎች ጥሩ ቢሆኑም ሁሉንም ዜጋ ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች መሠራት አለባቸው ብሏል።ቋሚ ኮሚቴው በድንገተኛ ምልከታው በአዲስ አበባ ካሳንቺስ አካባቢ የሚገኘዉ የውጪ ዜጎች አገልግሎት ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ኢትዮጵያን የማይመጥን፣ምቹ ያልሆነ እና የንጽህና ጉድለት ያለው በመሆኑ እንዲስተካከል አሳስቧል።

የአገልግሎቱ ዋናው መስሪያ ቤት ለአገልግሎት ምቹ ያልሆነ፣ሕንፃው የቆየ እና አስፈላጊዉን የማሻሻያ ጥገና ያላገኘ ነው።ሕንፃው ከተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ባህሪ ጋር የማይጣጣም ስሪት ያለው በመሆኑ ከዚህ ቀደም ቋሚ ኮሚቴው ተደጋጋሚ ምልከታ በማድረግ የመፍትሔ ሃሳቦችን መስጠቱን አስታውሷል።

በዋናው መስሪያ ቤት ያለው መጨናነቅ እንዲቀንስም በአዲስ አበባ ከተማ ከአምስት ያላነሱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ የመፍትሔ ሃሳብ መስጠቱን በማስታወስ የተሰጠው የመፍትሔ ሃሳብ ለምን መፈጸም አልተቻለም ሲል ቋሚ ኮሚቴው ለአገልግሎቱ ጥያቄ አቅርቧል።በተለይ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የማስፋፋት ሥራዎች መሠራት እንዳለበትም ጠቁሟል።

እንደ ቋሚ ኮሚቴው መስሪያ ቤቱ ተቋማዊ ተልዕኮውን በሙሉ አቅም ለመወጣት እንዳይችል ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት ያለ መሆኑ በምልከታው የተረጋገጠ እንዲሁም በሪፖርቱም የተመላከተ በመሆኑ በተቻለ መጠን ወሳኝ በሆኑ ቦታዎች ላይ የሰው ኃይል ለማሟላት በተቋሙ የተጀመሩ ሥራዎች መፍጠን አለባቸው ብሏል።

የደላላ ሰንሰለትን በመለየት ማቋረጥ እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው፤ አሁንም ከደላሎች ጋር የሚመሳጠሩ ሠራተኞች በመኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አሳስቧል።የሠራተኛ ባጅ አለመኖሩም ሊታሰብበት ይገባል ብሏል።

በምክር ቤቱ የተገኙት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ ተቋሙ ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ጠቁመው፤ ችግሮቹን ለመቅረፍ አዲሱ አመራር በዝርዝር ችግሮቹን መለየቱን ገልጸዋል፤ ተቋሙ የአደረጃጀት ችግር ያለበት በመሆኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ የራሱ አደረጃጀት እንዲኖረው ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የበጀት ችግሩን ጭምር ይፈታል ያሉት የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩንም አመላክተዋል።

በተቋሙ ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ አሁን ላይ ከሚፈለገው የሰው ኃይል ከግማሽ በታች የሰው ኃይል መኖሩንና የሕግ ማዕቀፉ ሲጸድቅ የሰው ኃይል ክፍተቱ እንዲሟላ በምላሻቸው አመላክተዋል።በጊዜያዊነት ችግሩን ለመቅረፍም ሦስት መቶ የሚጠጉ ሠራተኞች በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምቹ ቦታ ለተቋሙ መስጠቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ለአገልግሎት ምቹ ተደርጎ ሥራ ይጀምራል ብለዋል።በአዲስ አበባም በአራቱም አቅጣጫዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለመክፈት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሠራተኞች ዩኒፎርም ዲዛይን መጠናቀቁን ገልጸው፤ ባጅ እና የሠራተኛ መግቢያ በር ለብቻ በማድረግ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ የፓስፖርት ቡክሌት በውጭ ሀገር እየታተመ እንደሚገባ የጠቆሙት የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ ናቸዉ።በኢትዮጵያ ኢ-ፓስፖርትን ለማሳተም ስምምነቱ በመጠናቀቁ ከሚቀጥለው መስከረም ወር ጀምሮ ወደ ሥራ ይገባል።

ኢ-ፓስፖርት ሀገር ውስጥ መመረት ሲጀምር በሚፈለገው መጠን ማተም ስለሚቻል የተገልጋይ ቅሬታ እንደሚቀንስ እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ ወጪን በማስቀረት ችግሮችን ይፈታል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በማጠቃለያቸው ተቋሙ ያለበትን ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ የሕግ ማዕቀፍ ሥራው ቶሎ እንዲጸድቅ ፣አገልግሎቱ ካለበት አንገብጋቢ ችግር አኳያ ግፊት እንዲያደርግ፣ተቋሙን የማዘመን ሥራው እንዲፈጥን፣ለተቋሙ በተሰጠው ቦታ ቶሎ ዝግጅቱ ተጠናቆ ሥራ እንዲጀመር፣የተዘጉ ቅርንጫፎች በድጋሚ እንዲከፈቱ እና ተጨማሪ የክልል ቅርንጫፎች እንዲከፈቱ አሳስበዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You