ዓለም ላይ ምን አዋቂ አለ?

እኔ የኳስ እናቴ ደግሞ የጉንፋን ተጠቂዎች ነን፡፡ ኳስ ሳላይ እና እናቴ ባሕር ዛፍ ሳትታጠን የቀረንበት ጊዜ የለም፡፡ አባቴ በአንድ ቀን በሽታ ይቺን ዓለም ከተሰናበተ ጥር ሲመጣ አስራ ሁለት ዓመቱ፡፡ እህቴ ታማ አይቻት አላውቅም..አለመታመሟን በየሚዲያው ከምትሰማቸው አንቂ ነን ባዮች እና እሷም ከምትሠራበት የልህቀት ማዕከል ጋር አገናኝታ የእግዜርን ውለታ ትበላለች፡፡

ሕመም እንቶ ፈንቶ ሀሳብ ነው የምትለው ዘወትር የእናቴን እህህ ተከትሎ የምትዘባርቀው ዝብረቃ አላት። በእርግጥ ሊሆን ይችላል..እናታችን ላይ ሙድ መያዟን ግን አልወደድኩትም፡፡ የከተማችን አንቂዎች ግን ምን ነካቸው? በቀን ሦስት ጊዜ መብላት ያልቻለን ሕዝብ፣ በሥራ ማጣት፣ በኑሮ መወደድ መግቢያ ያጣውን ወጣት ሚሊየነር ትሆናለህ፣ ቢሊየነር ትሆናለህ እያሉ የቁም ቅዠት መፍጠራቸው፡፡ ጭራሽ እኮ ነብይ መሆን ነው የቀራቸው። እኔ እየሱስ ነኝ ብሎ የበግ ለምድ መልበስ፡፡ ሚዲያውን እሺ ልዝጋው የቤታችንን አንቂ ነኝ ባይ አሰቃቂ እህቴን ምን እንደማደርጋት እንጃልኝ፡፡

በሕይወቴ ውስጥ ልዩ ሆነው ከተቀመጡ ጥቂት ቀናቶች ውስጥ አንዱ አርሰናል ከየትኛውም ክለብ ጋር የተጋጠመበት ቀን ነው፡፡ የዛሬው ደግሞ በታሪኬ ውስጥ ደጋግሞ የማይመጣ አንዳንዴዬ ነው፡፡ ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ቀን ላይ በሕይወት ያለ ብቸኛው ደስተኛ ሰው ሆኜ እውላለሁ፡፡ አርሰናል ያሸንፋል ስል ኪሴ ያለኝን ገንዘብ መድቤ ለምርቃቴ የገዛሁትን አንድ ለእናቱ ሱፍ እስከማስይዝ ደርሻለሁ፡፡ አርሰናል ከተሸነፈ ከእንግዲህ በኋላ ራቁቱን የሚሄድ ሰው ሆኜ ነው የምገኘው፡፡ እንደተወሰደ ሰንብተው የሚደርሱበትን የእናቴን አምስት መቶ ብር እና የእህቴን ሦስት ሺህ ብር ከተደበቀበት ወስጄ ስለአርሰናል ከባላንጣዎቼ ጋር ተወራረድኩ፡፡

እናቴም ሆነች እህቴ የብሩን አለመኖር ሲያዩ ምን እንደሚሆኑ ባላውቅም ግን መገመት እችላለሁ..እናቴ ከሞቱ እልፍ የሰነበቱ በመልክ የማታውቃቸውን የአያቷንና ቅድመ አያቷን ስም ጠርታ..በተለመደ ግን በማይሰማ እርግማኗ ‹ብሬን የወሰደው የአያቶቼ አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋው› የምትል ይመስለኛል፡፡ እህቴ ከእኔ ውጪ ደመኛ እንደሌላት ስለምታውቅና ሁልጊዜ አርሰናልና ማንችስተር ሲቲ ጨዋታ ያላቸው ቀን ቤቱ ውስጥ አንድ ዱብዕዳ በእኔ በኩል እንደሚፈጠር ስለምታውቅ አርሰናል አሸንፎ ብሯን መልሼ በበላሁት ገንዘብ የከተማችን ዘመናዊ ሆቴል ወስጄ እንድጋብዛት የምትጸልይልኝ ይመስለኛል፡፡

ዓለም ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል ጋር እንደገጠመባት ያህል ልብ አንጠልጣይ ትዕይንት የላትም፡፡ እስከዛሬ ድረስ የተሠሩ፣ የተተወኑ ቲያትሮች፣ ድርሰቶች፣ ገፀባሕሪዎች የነዚህን ቡድኖች ያህል ተናፋቂነት የላቸውም፡፡

ከሻወር ቤት ወጥቼ ዘወትር በምታወቅባት ካኒተራዬ ሰውነቴን እያደራረኩ ወደክፍሌ ልገባ በዋናው ቤት በር ሳልፍ ከውስጥ ከወፍራም ሳል ጋር እናቴን አየኋት፡፡ ጉያዋ ውስጥ እሳት ማንደጃ አስቀምጣ ራሷን በነጠላ ሸፋፍና ስትነፈርቅና ስትስል..መቼ ይሆን ይቺ ሴትና ጉንፋን ሆድና ጀርባ የሚሆኑት እያልኩ ነበር፡፡

እናቴ እንደጉንፋን የሚያፈቅራት በሽታ የለም። እድሜ ልኳን ከጉንፋን ሌላ ታማ አይቻት አላውቅም፡፡ እውነት ጉንፋን ግን የሚመጣው በቫይረስ ነው? ነው ወይስ እናቴ ራሷ ጉንፋን አምጪ ቫይረስ ሆና ነው? ከሰውነቷ የሆነ ሶፍትዌር ጎሎ ካልሆነ በስተቀር በዚህ ልክ አንካሳ አይወጣትም፡፡ ሳምንቱን ሙሉ፣ ወሩን ሙሉ፣ ዓመቱን ሙሉ ጉንፋን የሚይዛት ነፍራቃ ናት፡፡ ከአባቴ ጋር ሲገናኙ ለጉንፋኗ ሶፍት ሊያቀብላት ወይም ደግሞ ጉንፋኗን ሰበብ አድርጎ ትኩስ ነገር ልጋብዝሽ ብሏት እንደተወዳጁ አስባለሁ። ይሄ ካልሆነ ደግሞ አጠገቡ ታክሲ ውስጥ፣ ውይይት ላይ፣ አንበሳ አውቶቡስ ውስጥ ተቀምጣ ስትስልና ስታስነጥስ ገልመጥ አድርጓት እሷም ምን ትገላምጠኛለህ? ስትል በላከችለት የመልስ ምት ወግ ጀምረው ይሆናል፡፡ አሊያም አባቴ ራሱ ጉንፋን አምጪ ተዋሲያን ሆኖ የእድሜ ልክ በሽታን አስታቅፏትም ይሆናል፡፡

ጉንፋን የያዛት ሰሞን..ሰሞን እላለሁ እንዴ? መች ደህና ሆና የምታውቀውን ነው? ብታዩዋት እኮ ሰው አትመስልም በቀሰም እንደተነፋች ቄብ ዶሮ ሰውነቷ አባብጦ ስትታይ ጉንፋን ሳይሆን ክፉ ደዌ የመታት ነው የምትመስለው፡፡ ከባሕል መድኃኒት እስከ ዘመናዊ ሕክምና፣ ከስራስር እስከ ብቅላብቅል፣ ከቤት ውስጥ ፌጦና ዳማከሴ እስከ የሰፈራችን እማማ ምንትዋብ አረቄና ግብጦ፣ ከፀሎት እስከ ስለት ድረስ ያልሞከረችው የለም፡፡ የሚቀራት ደም እንደሚፈሳት እንደዛች ሴት የጌታን የልብሱን ጫፍ ነክቶ መፈወስ ነው። ከሁሉም በኋላ ‹ዓለም ላይ ደግሞ ምን አዋቂ አለና ነው? ለጉንፋን ፍቱን መድኃኒት ያላገኙ› ስትል የዘወትር ንግግሯን ታስከትላለች፡፡

እኔ ታዲያ አፌ አያርፍም ‹ኧረ ተይ ተመስገን በይ በየቤቱ በማይድን በሽታ የሚሰቃይ ስንተ አለ..አንቺ ለጉንፋን› እስከምል አትጠብቀኝም..ድምፅዋን ከሰለባት ጉንፋን ጋር እየተናነቀች ‹ለአንድ ቀን እኔ የቻልኩትን ብትችል ጀግና ሴት ስትል በስሜ ሐውልት ታስቀርጽልኝ ነበር› አለችኝ፡፡

ጉንፋን እንዲህ የሚባልለት በሽታ እንደሆነ ዛሬ ገና መስማቴ ነው፡፡ ጉንፋን እንዲህ ከተባለ ስማቸው ሲጠራ የሚቀፉት እነስኳር፣ እነግፊት፣ እነካንሰር፣ እነስትሮክ፣ እነኤድስ፣ እነልብ፣ እነኩላሊት ምን ሊባሉ ነው? ስል ራሴን ጠየኩ፡፡ ታምሜ ስላልሞከርኩት ምን እንደሚባሉ ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ይሄን ጥያቄ ወደእህቴ አዙሬ የምትለውን መስማት እንዳለብኝ ለማወቅ አፍታ አልወሰደብኝም..‹በሽታ የምናምንቴ ሀሳብ እድፍ ነው፡፡ አዕምሮውን በምርጥ ሀሳብ የሞላ ምርጥ ሆኖ እንዲኖር መብት የተሰጠው ነው› እንደምትለኝ አላጣሁትም፡፡

‹ግን እኛ ሰዎች ለምን ተመስገን ማለት አቃተን? ለምን አማራሪዎች ወጣን? ካጣነው ያለን አይበልጥም? ካልተሰጠን የተሰጠን አይልቅም? ሳቅ ያወዛው ፊታችንን በቅያሜ አቀጭመን ለምን ስንል የምንደነፋ? መጥተው በማይጠቅሙን መጥተው ያከበሩንን የመነዘርን..ካልነበርንበት ወደነበርንበት ያመጡንን ኤጭ ወዲያ ስንል የምንዘልፍ..ለምን?

እግዜር የሰውን ልጅ በመፍጠሩ መጸጸቱና በንፍር ውሀ ማጥፋቱ ለምን እንደሆነ አሁን ፍንትው አለለልኝ፡፡ ጉንፋን ሕመም ሆኖ እግዜርን ከዓለም ምሑራን ጋር ደባልቃ የምትዘረጥጠው እናቴ የፈጠራት ቸር ባይሆን ኖሮ ለዳግም ጥፋት ምክንያት ባደረጋት ነበር፡፡

እናቴ ጋር ሁሉም ነገር ባለሞገስ ነው፡፡ ጉንፋን በአቅሙ የበሽታ ማዕረግ ተሰጥቶት ተንቆለጳጵሷል፡፡ በአንድ ጉንጭ ኮረንቲ ሻይ ድምጥማጡ የሚጠፋ፣ በመቶ ሜትር ሩጫ መድረሻ የሚያጣ ጉንፋን በእናቴ ፊት ሲካደም ማየት ከተመስጌን መራቋን ያሳያል፡፡ አላወቅንም እንጂ ኤጭ ባልን ቁጥር ኤጭ ያስባለንን ነገር ወደራሳችን እየሳብን ነው፡፡ አይመስለንም እንጂ..ቁጣ ባዘለ ንግግራችን ቁጣ ፈጣሪያችንን ወዳጅ እያደረግን ነው፡፡ አናምንም እንጂ..ባንገራገረ አፋችን ድካሞቻችንን እያፈቀርን ነው፡፡ መፍትሔው..ለሆነው እና እየሆነ ላለው አንተ ታውቃለህ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ማሸነፊያ አንዳች ጉልበት የለንም፡፡

‹የቱ ጋርም ቢሆን የሕመም ጥሩ እንደሌለው አውቃለሁ። በባሰ አታምጣ ፀሎት ሕመሞቻችን እንዳይሰሙን ማድረግ ግን ይቻለናል፡፡ እናቴ ያጣችው የባሰ አታምጣ የሚል ፀሎት ነው፡፡ ጌታን አግኝታ የልብሱን ጫፍ ዳሶ ለመዳን እየጠበቀች ነው፡፡ እዚህ የሌለ እምነት እዛ የሚኖር ይመስል። ያቺ ደማም ሴት እኮ ስትፈወስና የልብሱን ጫፍ ስትነካ ቤቷ በሰነበተ እምነት ነው፡፡ ከዛ ሁሉ የገበያ ሕዝብ መሐል እሷና መሰሎቿ የዳኑት አስቀድሞ በነበረ ጽናት ነው፡፡ ‹አንተ ታውቃለህ› ማለት ስትጀምር ሁሉ ነገሯ እንደሚስተካከል ማን ሹክ ባላት?

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You