ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤቶች «በስታርት አፕ ኢትዮጵያ» አውደርዕይ

እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂ ፋይዳ ከምንለው በላይ ትልቅ ነው። ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በሁሉም መስክ ማለትም የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ በምግብ እራስን ለመቻል፣ ለጤና ብሎም ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ መታገዝ የግድ ሆኗል።

እንደ ሀገር ለቴክኖሎጂ ልማት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ በመንግሥት ይገለፃል። የዚሁ አካል የሆነ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ከመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ለሦስት ሳምንት በሚዘልቀው ዓውደ ርዕይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ‹‹ስታርት አፖች›› ሥራዎቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

ወጣት አቤል ማስረሻ በዚህ ዓውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። የጀይረር ቴክ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መስራችና ባለቤት ነው። ወጣት አቤል ስለድርጅቱ ሲናገር፤ ሃርድዌርና ሶፍትዌርን አንድ ላይ አቀናጅቶ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ምርቶች ፈጠራ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን የሚሠራ በጅምር ሂደት ላይ ያለ ድርጅት እንደሆነ ይናገራል።

ወጣት አቤል በዚህ “የስታርት አፕ ኢትዮጵያ” ዓውደ ርዕይ ላይ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በብዙ መልኩ ችግራቸውን የሚቀረፍ ኤሌክትሪካል ዊልቸር ይዞ እንደቀረበ ይናገራል። ለዚህ ሥራ መነሻ ስለሆነው ነገር ወጣት አቤል ሲናገር፤ “በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርንበት ወቅት አካል ጉዳተኛ የሆነ ጓደኛ ነበረኝ ይህ ጓደኛዬ ምንም እንኳ ጎበዝ ተማሪ ቢሆንም እኛ ጓደኞቹ አብረን ካልተጓዝን ወደ ክፍል በራሱ ሄዶ ትምህርቱን ለመከታተል ይቸገራል የዚህ ምክንያት ደግሞ ዊልቸሩን የሚገፋለት ሰው አለመኖሩ ነው” ይህ አጋጣሚ ነው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በራሱ መንቀሳቀስ የሚችል ዊልቸር እንዲሠራ ምክንያት የሆነኝ ይላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የእንቅስቃሴ ውስንነት ያለባቸው አካል ጉዳተኞች አሉ የሚለው ወጣት አቤል፤ ጓደኛችንን ጨምሮ አብዛኞቹ (መኗል) ዊልቸር ተጠቃሚዎች ናቸው ይህንን ለመለወጥና በኤሌክትሪካል ዊልቸር ለመተካት ነው ወደዚህ ሥራ የገባነው ይላል።

በገበያ ላይ ስላሉ ተመሳሳይ ምርቶችና አገልግሎቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች ላይ ስለሚስተዋሉ ችግሮች የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ክፍተት እንዳለና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በቴክኖሎጂ ደግሞ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል በመረዳት የተሠራ ሥራ ነው የሚለው አቤል፤ ከፍተኛ ቁጥር ላለው አካል ጉዳተኛ በብዙ መልኩ እፎይታ ሊሰጥ የሚችል ግኝት እንደሆነ ይናገራል።

ሞብዊክስ የሚል ስያሜ የተሰጠውና በድርጅታቸው አማካኝነት ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም የተሠራው ኤሌክትሪካል ዊልቸር መተጣጠፍ የሚችል፣ በኤሌክትሪክ የሚሠራና የራሱ መቆጣጠሪያ (stick) ወይም ሪሞት ያለው፣ ከዚህ ባሻገር በሞባይል መተግበሪያ (አፕልኬሽን) ተጠቅሞ ለማንቀሳቀስ የሚያስችልና ለአጠቃቀም ቀላል እንደሆነ ይገልጻል።

በሞባይል መተግበሪያ ማሽኑ እንዴት አገልግሎት መስጠት ይችላል ለሚለው ጥያቄ ወጣት አቤል ምላሸ ሲሰጥ “የሞባይል መተግበሪያው በመደበኛነት የኤሌክትሪካል የዊልቸሩን አቅጣጫና ፍጥነት ይወስናል፤ ከዛ ባሻገር የአካል ጉዳተኛው የጤና ሁኔታ ክትትል የሚያሻው ከሆነ በውስጡ የተገጠሙ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የግለሰቡን የጤና መረጃ ለሚመለከተው አካል ማለትም ለግል ዶክተሩ ወይም ቤተሰቡ በመላክ አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግለት የሚያስችል እንደሆነ ይናገራል።

ወጣት አቤል እንደሚናገረው፤ እንደ ሀገር ላለው የአካል ጉዳተኛ ቁጥር አብዛኛው ማለትም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው መንቀሳቀሻ ዊልቸር የለውም በዚህ ምክንያት ግድ ካልሆነ በስተቀር እንቅስቃሴያቸው በቤት ውስጥ የተገደበ ነው ወደ ውጭ አይወጡም፤ ይህንን ለመቅረፍ እራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም የሚችሉበት ዕድል እንዲኖር ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ይናገራል።

ቴክኖሎጂው ህፃናት አካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት ያለ ወላጅ ድጋፍ ሄደው ትምህርታቸውን ተከታትለው መመለስ እንዲችሉ፤ አዋቂዎችም የሁለተኛ ወገን ርዳታ ሳያስፈልጋቸው ሥራቸው ሰርተው የሚመለሱበትን መንገድ የሚከፍት ነው የሚለው አቤል፤ የቴክኖሎጂ ውጤቱ ፋይዳ ጉልህ እንደሆነ ይናገራል።

የትኛውም ዓለም ላይ ተቋም ለመቋቋም ያለው ውጣውረድ እልህ አስጨራሽ ነው የሚለው አቤል፤ ነገር ግን በተቻለ መጠን መሰናክሎችን በመሻገር ውጤታማ ለመሆን ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ይናገራል። አሁን ላይ የፈጠራ ሥራውን በስፋት ለመከወን የመሥሪያ ቦታ እጥረት ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ይህንን ችግር ለመፍታት ተቋማት እንዲያግዙ ወይም የመሥሪያ ቦታቸውን እንዲፈቅዱ ወይም የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግሮ ለዚህ ችግራቸው መፍትሔ ከተገኘ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማድረስ እንደማይቸግራቸው ገልጿል።

“ይህ ሥራ ለገንዘብ ትርፍ ብቻ የሚሠራ አይደለም ሠብዓዊነትም ያስፈልገዋል” የሚለው አቤል በአብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰቡ ክፍሎች ውድ ባልሆነ ዋጋ ገዝተው መጠቀም እንዲችሉ ዊልቸሩን ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች በቀላሉ ሀገር ውስጥ የሚመረቱ እንዲሆን በማድረግ ለገበያ የሚቀርብበትን ዋጋ ተመጣጣኝ እንዲሆን እንደሚሠራ ይናገራል።

ወጣት አቤል እንደሚናገረው፤ ድርጅቱ ሲቋቋም ዋና ዓላማው ሃርድዌርና ሶፍትዌርን እያቀናጀ ለአንድ ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ምርት ማምረት ነው። ትልቁ ግብ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ብዙ ያልተነኩ መስኮች አሉ፤ ስለዚህ ባለን አቅም ሁሉ የሰው ችግር ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ቀላል እንዲሆኑ አድርጎ በማቅረብ ያለሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራል።

መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው የሚለው አቤል፤ ነገር ግን አሁንም ዓለም ከደረሰበት የልህቀት ደረጃ አንፃር በረዥም ርቀት ወደኋላ ቀርተን የምንገኝ እንደመሆናችን ከዚህ በላቀ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንደሚገባው ይናገራል።

አቤል እንደሚለው፤ ይህ ዓውደ ርዕይም ሃሳብና በጅምር ያለ የፈጠራ ሥራ ያላቸው ወጣቶች የተገኙበት እንደመሆኑ በጅምር ያለ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ ደግሞ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቅ እንደመሆኑ አብሮ መሥራት የሚፈልጉ እርስ በእርስ እንዲገናኙ ለማድረግ በር ከፋች ስለመሆኑ ይናገራል።

አሁን ላይ ድርጅቱ በጅምር ያለ በመሆኑ ይህ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በተለያየ መልኩ ድጋፍ እንዲያደርጉለት የጠየቀው የፈጠራ ባለሙያው ወጣት አቤል፤ ሰፊ ቁጥር ላላቸው ኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኞች መድረስ እንዲቻል አብሮ ሠራተኞች እንዲሆኑ ጠይቋል።

ሌላው በዚህ አውደርዕይ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች መካከል ከተቋቋመ ሶስት ዓመት ያስቆጠረው ትኦስ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው። የድርጀቱ ባልደረባ ወጣት አማኑኤል አለማየሁ እንደሚናገረው፤ ድርጅቱ በዋናነት ትኩረቱን የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ አድርጎ እንደሚሠራ ይናገራል።

የድርጅቱ የመጀመሪያ ሥራው (ኢት ቦሎ) የሚል ስያሜ የተሰጠው የቴክኖሎጂ ሥራ ነው የሚለው አማኑኤል፤ በአዲስ አበባ ከተማው ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ መኪኖች ይዘት በመመርመር ማለት አደጋ የማድረስ አቅማቸው በመለየት በመዲናዋ ከሚገኙ 60 ከሚሆኑ የመመርመሪያ ጣቢያዎች በጋራ በመሆን ትክክለኛ ዳታቸውን ለመንገድና ትራንስፖርት በማቅረብ የትራፊክ አደጋ መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደ መጀመሪያ ሥራው አድርጎ ወደ ተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶች እንደገባ ይናገራል።

የድርጅቱ ሁለተኛ ሥራ (የእኔ መኪና) የሚል መጠሪያ ያለው የቴክኖሎጂ ሥራ ነው የሚለው አማኑኤል፤ ስለ ሥራው ምንነት ሲናገር፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ መኪና ለመገልገል ቢያንስ ዓመታዊ ምርመራ፣ ኢንሹራንስ፣ የመንገድ ፈንድ ያስፈልጋል እነዚህ ጉዳዮች በየዓመቱ መታደስ አለባቸው ነገር ግን አንድ ግለሰብ ጊዜውን ጠብቆ ለማሳደስ በህመም ወይም በተለያየ ምክንያት እነዚህን ነገሮች መከወን አይችልም፤ ይህ ቴክኖሎጂ ግን በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት ለመኪና ባለንብረት 15 ቀን ቀድሞ ጥቆማ በተደጋጋሚ በመስጠት ችግሩን እንደሚቀርፍ ይናገራል።

ጥቆማ በመስጠት ብቻ አያበቃም የሚለው አማኑኤል፤ በዚህ መተግበሪያ አማካኝነት አንድ ሰው ሞባይል ስልኩን ብቻ በመጠቀም ዓመታዊ ኢንሹራንስ፣ የመንገድ ፈንድና ዓመታዊ ምርመራን ባለበት ሆኖ መፈፀም የሚያስችል ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ በብዙ መልኩ እንግልት የሚቀርፍ በቀላሉ ዘመናዊ አገልግሎት ተደራሽ ያደረገ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እንደሆነ ይናገራል።

ሌላው የድርጅቱ የሥራ ውጤት የእኔ (Delivery)ዕቃ መመላለስ አገልግሎት ይሰኛል የሚለው አማኑኤል፤ ይህም ከተሽከርካሪ ጋር የተገናኙ የወረቀት ጉዳዮችን በሶስተኛ ወገን በኩል መከወን የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ እንደሆነ ተናግሮ፤ የዚህ ቴክኖሎጂ ፋይዳ አንድ ባለንብረት ግለሰብም ሆነ ድርጅት መኪኖቹን በተመለከተ የሚኖሩ የትኞቹም ጉዳዮች ሲኖሩ በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት መጨረስ የሚያስችል አሠራር እንደሆነ ያስረዳል።

ዘመኑ ዲጂታላይዝድ እየሆነ በመምጣቱ ሁሉም ነገር ዘመን አመጣሽ በሆነ ቴክኖሎጂ እየተተካ ነው የሚለው አማኑኤል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ቴክኖሎጂ ትምህርትን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነ ሕዝብ ዘመናዊ ህክምና መስጠት ከባድ ይሆናል። በግብርናውም በቴክኖሎጂ ተጠቅመን ካልሠራን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ መመገብ አይታሰብም፡፡ ትልቅ ቁጥር ያለው ሕዝብ ነው ያለውና ወደ እያንዳንዱ ቤት መድረስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ እንደ ሀገር ለዘርፉ አሁን ካለው በላይ ትኩረት መስጠት ለነገ የማይባል ነው ይላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል መነቃቃት ተፈጥሯል የሚለው አማኑኤል፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ሆኗል። ከዚህ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኘው ሕዝብ ከ30 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። ይህ የሚያሳየው ህብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ የመቀበል ግንዛቤው እያደገ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው። ይህም ለዘርፉ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግሮ፤ አሁንም ሰዎች ቴክኖሎጂን ይበልጥ እንዲጠቀሙ መገፋፋት እንደሚገባ ይገልፃል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለቴክኖሎጂ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው የሚሉት ወጣቶቹ፤ እንደ ሀገር በቶሎ ለመለወጥ ቀላሉ መንገድ ቴክኖሎጂ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ስታርት አፖችን በመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ መሥራት እንዳለበት መልዕክት ያስተላልፋሉ።

በተጨማሪም ቴክኖሎጂ በባህሪው የሚታይ ውጤት ለመምጣት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፤ በጅምር እያለ ከተኮረኮመ ማደግ ስለማይችል አዲስ የተገኘን የቴክኖሎጂ ውጤት የማያዋጣና መጥፎ አድርጎ ወስዶ ከመግፋት ይልቅ በመበረታታት መንግሥት የሚጠበቅበትን የላቀ ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ይናገራሉ።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You