በመዲናዋ ለአንድ ሺህ 921 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለአንድ ሺህ 921 ባለሀብቶች አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትል ግምገማ ዳይሬክተር ወይዘሮ እናትነሽ ታመነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለሁለት ሺህ 514 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለአንድ ሺህ 921 ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡

በዋናነት በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለ149 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ እንደነበር ዳይሬክተሯ አስታውሰው፤ ለ199 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ፈቃድ መሰጠቱን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ለ303 ባለሀብቶች የቦታ ወይም የዘርፍ ለውጥ ያለው የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ለ80 ባለሀብቶች ደግሞ ምትክ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ለአንድ ሺህ 500 ባለሀብቶችም የኢንቨስትመንት ፈቃድ ዕድሳት መከናወኑን አስታውቀዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች 394 ፕሮጀክቶች ከቅድመ ትግበራ ወደ ትግበራ እንዲሸጋገሩ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ 101 ፕሮጀክቶች ደግሞ ወደ ማምረትና ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል ሲሉ አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት አምስት ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸውን ባለሃብቶች ለመመዝገብ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል በመመዝገብ የእቅዱን 157 በመቶ መፈጸም እንደተቻለ ተናግረዋል።

በዘርፉ ለስምንት ሺህ 244 ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ታቅዶ፤ ለ11 ሺህ 354 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

ከኢንቨስትመንት ፈቃድና ፈቃድ ነክ አገልግሎት እንዲሁም ከተለያዩ አገልግሎቶች እና የጨረታ ገቢዎች 18 ነጥብ 34 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ወይዘሮ እናትነሽ አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ቀልጣፋ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመው፤ ተገልጋዩ ባለሀብት ባለበት ሆኖ የኢንቨስትመንት ፈቃድና ፈቃድ ነክ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ የኦን ላይን አገልግሎት ሥራው ተጠናቆ በሙከራ ደረጃ ትግበራ ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You