ማኅበሩ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስኬት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አሳወቀ

አዲስ አበባ፡– ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎች ውጤታማነት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ማኅበሩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሚፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት ቀደም ብሎ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ሰዎችን ከየወረዳው በሚመርጥበት ወቅት አሳታፊነቱንና ፍትሐዊነቱን ለማረጋገጥ ማኅበሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደትም በወረዳ የሚገኙ የማኅበሩ መዋቅሮች በተለይም ከትምህርት ማኅበረሰቡ ጋር ተያይዘው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት ምክክሩ በኢትዮጵያ የቆዩና ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸጋገሩ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል የተናገሩት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ የመምህራን ማኅበሩም የምክክሩን ዓላማ በማመን አብሮ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዶክተር ዮሐንስ እንደተናገሩት፤ አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ቀድሞ ተጎጂ የሚሆነው የትምህርት ዘርፉ ነው፡፡ በዚህም ትምህርት ቤቶች ይወድማሉ፤ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የትምህርት ማስረጃዎችም አብረው ይጠፋሉ፡፡

በመሆኑም ምክክር ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው ተግባራትና ከማኅበሩ በሚፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ትምህርት የአዕምሮ ሥራ እንደመሆኑ የተረጋጋና ሠላማዊ አካባቢን ይፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሠላማዊ አካባቢን ለመፍጠር ማኅበሩ በመገናኛ ብዙኃን፣ በምክር ቤቶችና በሌሎች የውይይት መድረኮች አማካኝነት አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዓመታዊ የመምህራን ምክር ቤቶች ስብሰባ ላይ በተለየ መልኩ አጀንዳ ተቀርጾ ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

በማኅበሩ የውይይት መድረክ በሚኖርበት ወቅት የምክክሩ ኮሚሽነሮች መጥተው ገለጻ እንዲያደርጉ ዕድል መሰጠቱን አብራርተው፤ ይህም መምህራን ስለምክክሩ ያላቸውን ጥያቄና አስተያየት እንዲያቀርቡ በር የከፈተ መሆኑን አንስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት፤ የምክክር ሂደቱ ባለቤቶች በዋናነት ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ሁሉም ዜጎች የምክክሩን ጠቃሚነት ተረድተው እንዲሳተፉ ማኅበሩ የጀመረውን ጥረት ይቀጥላል።

አንዳንድ ሀገራት የምክክር ሂደቱን ጀምረው ውይይቱ አሳታፊ ባለመሆኑ ውጤታማ አለመሆናቸውን አስታውሰው፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምክክር መምህራንና ሌሎች የማኅበረሰቡን ክፍሎች አሳታፊ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You