ኩባንያው በሁለት ዓመታት ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያን ተደራሽ ያደርጋል

  • ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች መመዝገብ ይችላሉ

አዲስ አበባ፡ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያን ተደራሽ እንደሚያደርግ አስታወቀ። ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገብ እንደሚችሉም ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም እና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በምዝገባ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት፤ የዲጂታል መታወቂያ በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2018 ዓ.ም ለ90 ሚሊዮን ዜጎች አገልግሎቱን ለማዳረስ ታቅዷል።

ከዚህም ውስጥ ኩባንያው በወር በአማካኝ 1 ሚሊዮን ዜጎችን በመመዝገብ ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ በማድረግ የሀገራዊ ዕቅዱን 36 በመቶ የሚያከናውን ይሆናል ብለዋል።

አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ደብረ ብርሃን፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ጎንደር እና መቀሌ እንዲሁም ባሕርዳርን ጨምሮ በ29 ከተሞች ላይ የተጀመረ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቀጣይም ለሁሉም ዜጋ በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የዲጂታል መሠረተ ልማት የማስፋፊያ ሥራ እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል።

በአገልግሎቱም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ አስቻይ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ይህም ለአካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የዲጂታል መታወቂያ ፈጣን እና አስተማማኝ የማንነት ማረጋገጫ ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን የሳይበር ማጭበርበርን በመከላከል ለአካታች የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ የፋይናንስ አካታችነትን የሚጨምሩ የአነስተኛ ብድር አገልግሎቶችን ያለዋስትና ለማቅረብ፣ የክሬዲት ግብይት ለማስፋፋት፣ የብድር ምጣኔ ለማሻሻል ያስችላል።

በመሆኑም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ለማከናወን በኩባንያው ይፋ በተደረጉት የአገልግሎት ማዕከላት በአካል በመገኘት፣ ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መታወቂያዎችን በመያዝ ወይም የሰው ምስክር በማቅረብ በነፃ መመዝገብ ይችላሉ።

በተጨማሪም ከከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች፣ የዩኒቨርስቲ፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና የብሔራዊ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ተፈታኝ ተማሪዎች፣ የተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ፣ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች እና ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ያላቸው የውጭ ሃገር ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወን እንደሚችሉ ተገልጸዋል።

የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ያከናወኑ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያቸውን ባሉበት ሆነው ዳታ ብቻ በማብራት በነፃ በቴሌብር ሱፐርአፕ አማካኝነት በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን አማራጭ መኖሩም ተጠቁሟል።

ማሕሌት ብዙነሕ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You