ምክር ቤቱ የጤና፣ የወጪ ንግድና የግብርና ዘርፉን ማነቆ መፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፡– የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጤና፣ የወጪ ንግድና የግብርና ዘርፉን ማነቆ መፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎቹን ያሳለፈው ትናንት ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው፡፡

በጤና ፖሊሲ ላይ ውይይት ያደረገው ምክር ቤቱ፤ በሥራ ላይ ያለው የጤና ፖሊሲ ላለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ማሻሻያ ሳይደረግበት የቆየ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ነባሩ የጤና ፖሊሲ በፀደቀበት ወቅት ከነበረው ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ፣ እየተከሰቱ ያሉ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መበራከት፣ በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ በጤና ዙሪያ የሚከሰቱ ለውጦች ለረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅት በምክንያትነት ተዘርዝረዋል፡፡

በተመሳሳይ ነባሩ የጤና ፖሊሲ ዘርፉ ጥራት እና ፍትሐዊነት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑ እና ከሀገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር የሚጣጣም የጤና ፖሊሲ እንዲኖር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ መቅረቡ ተመላክቷል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ ረቂቅ የጤና ፖሊሲው ላይ በመወያየትና ግብዓቶችን በማከል ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ምክር ቤቱ ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል ሲሆን፤ የግብርና ዘርፍን ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር የበለጠ የሚያስተሳስር፣ የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅና በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም በገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚያግዝ ረቂቅ ፖሊሲ በመሆኑ የተለያዩ ግብዓቶች ተጨምሮበት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ተጠቁሟል።

በሥራ ላይ የነበረው የግብርና ፖሊሲ ከአዳጊ የምርትና ምርታማነት ፍላጎት ጋር አብሮ መጓዝ ስላልቻለ እና ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ማነቆ የሆኑ አሠራሮችን መለወጥ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ፖሊሲው መቀረጹ ተጠቁሟል። በተጨማሪም ፖሊሲው ሀገሪቱ ከምትከተለው ብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር የሚጣጣም እንዲሆን ማስፈለጉ ስለታመነበት መሆኑም ተገልጿል።

የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን የአገልግሎት ክፍያ ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቷል።

ረቂቅ ደንቡ ኮሚሽኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስፋፋት፣ የአገልግሎቶቹን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ ብሎም የተጠቃሚውን ማኅበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጣውን ወጪ በከፊል መሸፈን የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችል ተመላክቷል።

ምክር ቤቱ ውይይት ካካሄደ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You