አቶ ዘሪሁን ተከስተ ከኦቲዝም ጋር የሚኖር ልጅ አላቸው:: ልጃቸው ይህ ሕመም እንዳለበት ሲያውቁ ነበር ትምህርቱን እንዲከታተል ወደ ጆይ የኦቲዝም ማዕከል የላኩት:: ልጃቸው ወደ ማዕከሉ ካቀና በኋላ ብዙ ነገሮችን አውቋል:: ለዚህም እርሳቸው ምስክር ናቸው::
ደመቀች ታደለ ደግሞ የአስራ አንድ ዓመት ልጇ የአዕምሮ እድገት ውስንት አለበት:: ያለማንም ድጋፍ በብዙ ፈተና እያሳደገችው ትገኛለች:: ልጇን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ የብዙ ትምህርት ቤት ደጆችን ረግጣለች:: በደስታ ግን አልተቀበሏትም ነበር:: ልጇም ዕድሜው ለትምህርት በደረሰበት ሰዓት አልነበረም ወደ ትምህርት ቤት ያቀናው:: አስር ዓመታትን ከእናቱ ጉያ ውስጥ ሆኖ ያሳለፈው ብዙ ምክንያቶች አስገድደውት ነው:: በግዜው እርሷ አቅም ስላልነበራት እንዲህ አይነቱ ሕመም ያለባቸውን ልጆች ወደሚያግዙ ማዕከላት ለማስገባት አልታደለችም:: ሆኖም ከብዙ ፈተናና ደጅ ጥናት በኋላ ልጇ ትምህርት ቤት ገብቶላታል::
በሁለቱ ወላጆች መካከል ያለው ልዩነቱ ግልጽ ነው:: ብዙ አቅም የሌላቸው እንደ ደመቀች ያሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማን ሰጥቼ ልውጣ ብለው በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲፈተኑ ይስተዋላል:: ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሠራበት እንደ ሀገር የሚመጣውን ቀውስ ለመረዳት አያዳግትም::
ዓሊ ሳኒ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት እና የአካቶ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው:: በ ‹‹ላይት ፎር ዘ ወርልድ›› በተሰኘ ድርጅት ደግሞ የአካቶ ትምህርት አማካሪ በመሆን ያገለግላሉ:: እርሳቸው እንደሚያብራሩት በኢትዮጵያ የሁሉም አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ቁጥር አናሳ ነው:: የዓለም ባንክ ከሚያስቀምጠው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ለማለት ያስደፍራል:: የትምህርት ተሳትፏቸውን ሲታይ ደግሞ ቅድመ አንደኛ ላይ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎች ቁጥር 0 ነጥብ 9 በመቶ ነው::
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ 10 ነጥብ 6 ከመቶ ነው:: የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ 3 ነጥብ 6 ከመቶ ብቻ ነው:: ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ግን ምን ያህሎቹ ወደ ትምህርት ቤት እንደመጡ ወይም እንደቀሩ በውል የሚያሳይ መረጃ የለም::
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ ኦቲዝም ያላቸውን ልጆች በመንግሥት ትምህርት ቤት እንዲካተቱ ፍላጎት ቢኖርም ድጋፉ በቂ ነው አይደለም:: እንደውም ከኦቲዝም ጋር ተያይዞ ጥሩ ሥራ ሠርተዋል የሚባሉት አንዳንድ ረጂ ማዕከላት ናቸው:: ለአብነት እንደ ‹‹ነህምያ›› የኦቲዝም ማዕከል፣ ‹‹ጆይ›› የኦቲዝም ማዕከል እና ሌሎችም ይጠቅሳሉ:: እነዚህ ማዕከላት በግለሰቦች ተነሳሽነት የተከፈቱ ሲሆኑ አብዛኞቹም ኦቲዝም ያላቸው ልጆች ኖሯቸው ልጆቻቸውን የት መውሰድ እንዳለባቸው ግራ ሲጋቡ በራሳቸው ተነሳሽነት ከፍተው ለሌሎች ጭምር የተረፉ ናቸው::
እነዚህ ማዕከላት ጥቂት ናቸው ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰኑ ናቸው:: በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል አካል ጉዳተኛም ሆኑ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በድህነት ውስጥ ያሉ ናቸው:: እነዚህ ተቋማት ደግሞ በንጽጽር በአብዛኛው በአዲስ አበባ ነው የሚገኙት:: ከዚህ ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወላጆች ተደራሽ እየሆኑ አይደለም::
ኦቲዝም ያላቸው ልጆች እንደማንኛውም ልጅ አካላዊ እድገት አላቸው:: ነገር ግን ሃሳባቸውን የመግለጽ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር የመቀላቀል ችግር ስላለባቸው የልጆቹን ድጋፍ ውስን እንዲሆን እና ለጉዳት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል:: በተለይም ሴቶች የመደፈር ዕድላቸው ሰፊ ነው:: ወላጆችም ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት በግልጽ ማስተማር ይገባቸዋል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ችግር ውስብስብ እንደመሆኑ መንግሥትም በቂ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል::
ዶክተር አሊ(ዶ/ር) እንደሚያስረዱት በመንግሥት በኩል ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ልጆች በአቅራቢያቸው የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማመቻቸት ይጠበቅበታል:: በተመሳሳይ እነሱን የሚያስተምሩ መምህራንም በየትምህርት ቤቱ መመደብ ያስፈልጋል:: አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችንም ማሟላት ይገባል:: በእርግጥ ይህ ሥራ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኃላፊነት በመሆኑ መንግሥት ከበላይ ሆኖ ሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር መሥራት ይጠበቅበታል::
የሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፋቸውን በልዩ ድጋፍ ላይ የሠሩት ረዳት ፕሮፌሰር አሊ ሳኒ በኦቲዝም ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች እንኳን በቂ እንዳልሆኑ ይናገራሉ:: ኦቲዝም ያለባቸውን ልጆች የሚያሳድጉ ወላጆች ጫናን በተመለከተ በሠሩት ጥናት የወላጆች የአኗኗር ሁኔታ እጅጉን የሚፈትን እንደሆነ ያስረዳሉ:: ችግሩን ለመፍታት መንግሥት መሥራት ካለበት ሥራ ጎን ለጎን ወላጆች በኦቲዝም ዙሪያ ሥልጠናዎችን መውሰድ፣ ማንበብ እና ተመሳሳይ ልጆች ካሏቸው ወላጆችን ጋር መወያየት እና መነጋገር ቢችሉ የልጆቻቸውንም ሆነ የራሳቸውን ሕይወት ማሻሻል እንደሚችሉ ያስረዳሉ:: አክለውም ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ነገሮችን መከወን እስከሚችሉ ድረስ ያለመታከት መሥራት እንዳለባቸው በመግለጽ፤ ነገር ግን ወላጆች ልጄ ያለ እኔ መኖር አይችልም ወደሚል ጭንቀት መሸጋገር የለባቸውም ይላሉ::
ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች አንደኛው ፈተናቸው የተግባቦት እንደመሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግግር ሕክምና (ስፒች ቴራፒ) ትምህርት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የሚገለጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ባለሙያዎች መሥራት ቢችሉ ችግራቸውን ለመቀነስ ይረዳል:: የአካቶ ትምህርት ሁሉም አካል ጉዳተኞች እንደ አካል ጉዳታቸው ሁኔታ አካታች የሆነ ትምህርት መስጠት ነው:: ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ፣ የአዕምሮ እድገት ውስንት ላለባቸው፣ ለዓይነ ስውራን እና ለሌሎች አካል ጉዳተኞች የአካቶ ትምህርት ይሰጣል:: ነገር ግን ራሱን የቻለ ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም ) የለውም ይላሉ::
ከዚህ ባለፈ በኢትዮጵያ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ እንጂ የትምህርት ሕግ የለንም:: አካታች እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀው የትምህርት ሕግ ረቂቁ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተላከ አራት ዓመታት ባስቆጠረበት ሁኔታ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አስገዳጅ ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ያስረዳሉ:: ከዚህ ይልቅ ኦቲዝም ሆነ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች ትምህርት ቤት ለማስገባት በማባበል፣ በልምምጥ እና ተፅዕኖ በማሳደር ነው ልጆቹ እየተመዘገቡ ያሉት ዓሊ (ዶ/ር)፤ ይህም ተገቢ እንዳልሆነ ይገልጻሉ::
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም