በብሪክስ ጥምረት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር ብሔራዊ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፡– በብሪክስ ጥምረት ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር ብሔራዊ ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ ብሔራዊ ስትራቴጂክ ዕቅዱ የተዘጋጀው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በትናንትናው ዕለት ትኩረቱን በግብርናና ቴክኖሎጂ ላይ ያደረገ በብሪክስ ጥምረት ማዕቀፍ ስር የኢትዮጵያና የሩሲያ የምሑራንና የተመራማሪዎች ጉባኤ ተካሂዷል፡፡

በጉባኤው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ግንኙነት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው። የኢትዮጵያና ሩሲያ ጠንካራ ግንኙነት በብሪክስ ጥምረት ማዕቀፍ ውስጥ ፍሬያማ አጋርነቶችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ስራቴጂክ እቅድ ማውጣቱ የተጀመረው የብሪክስ አባል ለመሆን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ጀምሮ ነው፡፡ ወደ ብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ለመግባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን እየተጠናቀቀ የሚገኝ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር ብሔራዊ ስትራቴጂክ እቅድ ወጥቷል፤ ይህን ለማፅደቅ የመጨረሻውን ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነችባቸውን የስንዴ ምርትና የሌማት ትሩፋትን ይዛ ወደ ብሪክስ ጥምረት ትገባለች ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት የምትወስዳቸው ስትራቴጂ፣ ፕሮጀክቶችና መደጋገፎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዝግጅትና ፍላጎት ለማድመጥ የሩሲያ የባለሙያዎች ቡድን መጥቷል ያሉት  ጃፋር፤ በብሪክስ የኢትዮጵያ ፍላጎቷ ምን እንደሆነ መረጃ መሰብሰቡን ጠቅሷል፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ትኩረት በምትሰጣቸው ጉዳዮች ዙሪያ የመለየት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከሞላ ጎደል የተጠናቀቀ አንድ ሀገር ወደ ዓለም አቀፍ ስብስብ ወስጥ ሲገባ የሚመራበት መርሕ ምንድን ነው? ምን ጥቅም ለማሳካት ነው? እቅዶችንስ እንዴት ይሳካሉ? የሚለውን በእቅድና ስትራቴጂ የተመሠረተ እንዲሆን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያና የሩሲያ የባለሙያዎች ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ውይይት ነው ያሉት አቶ ጃፋር፤ ጉባኤው ኢትዮጵያ በብሪክስ ስር በግብርና፣ ኢኮኖሚ፣ በፖለቲካው ትኩረት እንዲደረግ የምትፈልገውን ምንድን ነው? የሚለውን ለማሳወቅ የሚጠቅም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሞስኮ በሚካሄደው የማጠቃለያ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው የእድገት ጉዳዮችን ለመለየት የዝግጅት ጊዜ በመሆኑ ከብሪክስ አስፈላጊውን ጥቅም ለማግኘት ይረዳታል ነው ያሉት፡፡

በብሪክስ ጥምረት ውስጥ የሩስያ የሙያተኞች ጉባኤ ኃላፊ ቪክቶሪያ ፓኖቫ (ፒኤችዲ) ጉባኤው የኢትዮጵያን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚጠቅምም ገልጸዋል።

ሩሲያ አሁን ያለውን ትብብር ለማስፋትና በብሪክስ ጥምረት ማዕቀፍ ውስጥ ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኗን ጠቁመው፤ ይህ ውይይት ሁለገብ ትብብርን ወደ አዲስ ከፍታ ለማሳደግ ትልቅ ተስፋ እንዳለው አስረድተዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ውይይቶቹ ለጋራ ዕድገትና ልማት እድሎችን በመጠቀም አንገብጋቢ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የጋራ እውቀትንና ሀብቶችን የመጠቀም የጋራ ራዕይን ያጎላል ብለዋል፡፡

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You