የምሁር ዕውቀት የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ፤ ስለዚህ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል ብቁ የሚሆነው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው። ምሁርነትም ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
ምሁር ማለት በልምድ፣ በትምህርትና በልዩ ልዩ መንገድ ያገኛቸውን ማስተዋሎችና ዕውቀት በሃሳብ መልክ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርብ ሰው ነው። ለዚህ ቃል ብቁ ሆነው የተገኙ ጥቂት የሚባል ቁጥር የሌላቸው በስራዎቻቸው በርካቶችን ያስገረሙ ኢትዮጵያውያን አሉ። ከእነዚህም ልዕቀን መካከል በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የመረጃና ደህንነት ባለሙያው ዶክተር አስማማው ቀለሙ አንዱ ናቸው።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የደህንነትና የመረጃ ሥራዎችን በመስራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ዶክተር አስማማው ቀለሙ በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት ፍኖተ ሰላም ከተማ በ1932 ዓ.ም ነበር የተወለዱት። የአርበኛ ቤተሰብ ልጅ የሆኑት ዶክተር አስማማው ከፍተኛ የትምህርት አቀባበል የነበራቸው ስለነበር ከ1 እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአራት አመት ተከታትለው እንደጨረሱ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በፍኖተ ሰላምና በአዲስ አበባ ልዑል በዕደማርያም ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እንዲሁም በማኔጅመንት በ1958ዓ.ም በማዕረግ አግኝተዋል፣ ወደ እስራኤል አቅንተው በሪሶርስ አሎኬሽን ዘርፍ ከቤንጎሪዮን ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል፤ በኢንተርናሽናል ሎው ሌላ የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል። በሆርቲካልቸር ቢኤስሲ ዲግሪ፣ ከዚያም ወደ ቡልጋሪያ አቅንተው ከካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ዶክትሬት) ሠርተዋል።
ከለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ የፖስት ዶክቶራል ፕሮግራም መከታተላቸውን፣ ከቀለም ትምህርቱ እኩል በወታደራዊ ሳይንስ ዘርፍም ብዙ ዓይነት ትምህርቶች መቅሰማቸውንና በፖሊስ ሳይንስ በአድቫንስድ ዲፕሎማ በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቃቸውና የፖሊስ መኰንን ለመሆን መብቃታቸውንም የህይወት ታሪካቸው ያሳያል።
በ1960ዎቹ መጨረሻና በ70ዎቹ መጀመሪያ ከሶማሊያ ጋር በነበረው ጦርነት የተማረኩ ኢትዮጵያውያን በልዩ ኦፕሬሽን ለማስለቀቅ የተወጡት የስድስት ወራት ዘመቻ ስማቸውን በትልቁ ያነሳዋል። እስረኞቹን የማስለቀቅ ሂደቱ ሶማሊያ በኦጋዴን ጦርነት 14ሺህ ንጹሀን ዜጎችን እንደ “ምርከኞች” ወደ ሞቃዲሾ ከአጋዘችበት ታሪክ ይነሳል። በወቅቱ የዚያድ ባሬ ሀሳብ በድርድር ወቅት እነዚህን ዜጎች በመፍታት በልዋጩ የኦጋዴን መሬት ለማግኘት ነበር።
ሶስት አማራጮች ቀርበው እስረኞቹ የት እንደሚገኙ እና ለማስፈታት ዳጎስ ያለ ጥናት አጥንተው ያቀረቡት ዶክተር አስማማው ቀለሙ ነበሩ። ጥናቱን ለመተግበር ሰላዩ አስማማው ተመረጡ። ሶማሊያ በሽፋን ስም የሞዛምቢክ ጋዜጠኛ ሆነው እንዲገቡ ተወሰነ። መንግስቱ ከወዳጃቸው የሞዛምቢክ መሪ ሚሼል ጋር በምስጥር ተነጋግረው ለዶክተር አስማማው ወርቁ የሞዛምቢክ ዜግነትና ፖስፖርት እንዲሰጣቸው ተደረገ።
ሞዛምቢክ የሚገኝ የሚዲያ ተቋም ጋዜጠኛ ሆነው በመመዝገብ ካርድ ተሰጣቸው። የፖርቹጊስና የሞዛምቢክ ክልስ እንደሆኑ እና ሌላ ስምም ተሰጣቸው። አጭር የጋዜጠኛ ስልጠና ተሰጣቸው። የሞዛምቢክ ጋዜጠኛ ሆነው ሞቃዲሾ ገቡ። ዶን በተባለ በሶማሊያ የሚታተም የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ ዚያድ ባሬን አድንቀው ሁለት ጽሁፎች አወጡ። ሰላዩ ሶማሊያ ያሰረቻቸውን ንጹሀን ዜጎች የታሰሩባቸውን እስር ቤቶች አጣሩ። በወቅቱ ከ14ሺህ ሲቪል ዜጎች 3ሺዎቹ ህይወታቸው አልፎ እንደ ነበረ አወቁ።
ስድስት ወራት በጋዜጠኝነት ሽፋን ሞቃዲሾ የቆዩት ሰላዩ 11ሺህ ኢትዮጵያውያን እስረኞች በ20 የሱማሊያ እስር ቤቶች እንደሚገኙ መረጃ ሰብስበው ተመልሰው ለደርግ ሪፖርት አቀረቡ። መንግሥት በኋላ ለሶማሊያ አምባሳደርነት ዶክተሩን ሾመ። የመጀመሪያው ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነውም ሀገራቸውን አገለገሉ። የሞዛምቢክ ፓስፖርት መልሰው የኢትዮጵያ ፓስፖርታቸው ተመለሰላቸው።
የኢትዮጵያ አብዮት እንደፈነዳ (1966) የፖሊስ መቶ አለቃ ሆነው በሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ውስጥ የሠሩት ዶክተር አስማማው፣ የፖሊስ ሳይንስን የተማሩት በአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በ9ኛው ኮርስ ሲሆን፣ በመቶ አለቅነት በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተመረቁት ታኅሣሥ 14 ቀን 1961 ዓ.ም. ነበር። የመረጃና ደኅንነት ሙያን በይበልጥ ለማጠናከር ይረዳቸው ዘንድ በተለያዩ ሀገሮች በተለይም በእስራኤልና በጀርመን ሠልጥነዋል።
ሁለንተናዊ ዕውቀታቸውን ለትውልዱ ለማስረፅም ይረዳ ዘንድ የኮተቤ የደህንነት ትምህርት ቤትን በመመሥረትና በኃላፊነት በመምራት ከመሥራታቸው በተጨማሪ በ1974 ዓ.ም. የስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ታሪክ ይነግረናል።
ይህ ኢንስቲትዩት ሲቋቋም ስለነበረው ሁኔታ ዶክተር አስማማው በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ ከመንግሥት የተሰጠኝ አንድ መኖሪያ ቤት የሚያክል ለመረጃ ደህንነት ሥራ አመቺ ያልሆነ ነበር። ይህ ከረዥም ጊዜ የተቋሙ ግብ አንፃር የማያስኬድ በመሆኑ በወቅቱ ከነበረው ወታደራዊ መንግሥት ጋር እልህ አስጨራሽ ንግግር በማድረግ አሁን ተቋሙ የሚገኝበትን ሰፊ ቦታ መረከብ እንደቻሉ ይናገራሉ።
ሌላው አስገራሚ ነገር ይህ ሰፊ ቦታ ጥበቃ የሚደረግለት ባለመሆኑና ጥበቃ ቀጥሮ አካባቢውን ለማስጠበቅ የሚሆን በጀት የሌለ በመሆኑ ዶክተር አስማማው 200 የሚሆኑ ውሾችን ከቀድሞ ወታደር ወዳጃቸው ጋር በመሆን በማሰልጠን አካባቢው እንዲጠበቅ እንዳደረጉ ይናገራሉ።
በኢህአዴግ የሽግግር መንግሥት ለ12 ዓመታት ያለክስ፣ ያለፍርድ የታሰሩት ዶክተር አስማማው፣ እስረኞች እንዲማሩ፣ ትምህርቱም በዚያው እንዲስፋፋ ማድረጋቸው ይገለጻል። ዶክተር አስማማው ቀለሙ ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ በኋላ በተደረገላቸው ተቋማዊ ጥሪ መሰረት የጤና መታወክ እስካጋጠማቸው ታህሳስ 2016 ዓ.ም ድረስ በብሔራዊ ደህንነት ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የነበሩ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተጋባዥ ሌክቸረርም ነበሩ። በተጨማሪም በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሳል ትንታኔ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በታማኝነት እና በቅንነት ተወጥተዋል።
ዶክተር አስማማው ቀለሙ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ የእድሜ ልክ እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆኑን በተግባር ያሳዩ ባለሙያ ነበሩ።
የቀድሞው መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ ‹‹ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ (ዶክተር )ኮሎኔል አስማማው ሰብዕና እንዲህ አንስተዋል፦ ‹‹በጣም ጎበዝ፣ ታታሪ፣ አዲስ ሐሳብ አፍላቂ ብቻ ሳይሆን ወዲያው በተግባር የሚተረጉም እንደሆነ አስመስክሯል። ሠርቶ አይደክመውም። በጣም ትጉ ነው። በዚህም ምክንያት አለቆቹ ያደንቁታል። በመሆኑም መንግሥቱ ሳይቀር አውቆታል።
ዶክተር አስማማውን የሶማሊያ አምባሳደር እንዲሆኑ ማሰባቸውን ለርዕሰ ብሔሩ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲነግሯቸው ‹‹ጥሩ ምርጫ ነው። በጣም ጎበዝ ልጅ ነው። ማደግ የሚገባው ልጅ ነው። ለእርሱ ተብሎ ሳይሆን ለሥራው። ምንም ሥራ ይሰጠው ከሚጠበቀው በላይ ነው የሚፈጽመው። እኔ እንኳን ለሌላ ሥራ ነው አስቤው የነበረው። ጓድ ተስፋዬን የሚተካ እሱ እንዲሆን ነው ብለዋቸዋል።
ኮሎኔሉ ጠንቃቃነት የሚያሳይ አንድ ሰበዝንም ኮሎኔል ብርሃኑ እንዲህ መዘዋል። ‹‹የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሆንኩ ዶክተር አስማማው ወደ ቢሮዬ ብቅ ብሎ ነበር። በወቅቱ አንዲት የኤሌክትሪክ መሣሪያ ይዞ ነበር። ትንሽ እንደተነጋገርን የቢሮዬ ግድግዳ ጣሪያ በመሣሪያዋ መረመረው። የተደበቀ የድምፅ መቅረጫ ወይም ሌላ ነገር አለመኖሩን ለማረጋገጥ።
ፍተሻውን ሲጨርስ፤ ‹ምንም ነገር የለም ነፃ ነው፤› አለኝ። እኔ ሳልጠይቀው ራሱ አስቦ የምናገረው፣ የምወያየው የምወስነው የምሰጠው ትዕዛዝ በሌላ እጅ እንዳይወድቅ፤ ምናልባትም በጠላት ሰላዮች እጅ እንዳይወድቅ ይኽን በማድረጉ ውለታውን አልረሳውም›› ይላሉ።
በንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከሀገር ግዛት ሚኒስቴር እስከ ዘመነ ደርግ (ኢሕዲሪ) ከደህንነት ሚኒስቴር ቀጥሎም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ ምክትል ሚኒስትርነት ያገለገሉት ዶክተር አስማማው፤ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድራዊ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ የታወቁ ሰው ነበሩ።
የደህንነት ትልቁ ዓላማ ከሚታይና ከማይታይ ሰርጎ ገብ ጠላት ሀገርን መጠበቅና ማዳን ብሎም የሀገርን የመረጃ አቅም ማጎልበት እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አስማማው፤ በማንኛውም ሁኔታ ንቁ መሆንን ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም በማንኛውም ሁኔታ የማይናወጥ ፅኑ አቋም መያዝ የሚጠይቅ ሙያ ስለመሆኑ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ይናገሩ ነበር።
ዶክተር አስማማው በአንድ ወቅት እንዲህ አሉ ”በክርስትና የመጀመሪያው ጥበብ ፈጣሪን መፍራት ነው። በደህንነት ሥራ ደግሞ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሀገርን መውደድ ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ የመንግሥት ሥርዓት ይመጣል ይሄዳል ሀገር ግን የምትቀጥል ናት፤ ስለዚህ አንድ የመረጃና ደህንነት ሰው በርዕዮተ ዓለም የማይበገር ርዕዮተ ዓለሙ ሀገሩ የሆነች በሙሉ ልቡ ሀገሩን የሚያስቀድም መሆን ይኖርበታል” ይላሉ።
በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች አሁናዊ ሀገራዊ፣ ክፍለ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የደህንነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት ዶክተር አስማማው፤ በተለያዩ ጉዳዮች ሙያዊ አስተያየት በመስጠት አንድምታዊ ትርጓሜ ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ከልጅነት እስከ እስር ቤት የዘለቀ አዲስ ነገር ለመማር ለመፍጠርና ቁልፍ ተግባሮችን ለመሥራት በጥናትና ሙከራ ላይ የተመሠረተ መጋፈጥና በግል ተነሳሽነት ታላላቅ ሃሳቦችን መጀመርና ለፍሬ ማብቃት፤ የሚችሉት ዶክተር አስማማው፤ ሀገርን ከምንም ነገር አስቀድመው በሙያቸው ያካበቱትን ያላቸውን ሁሉ በመስጠት ያገለገሉ፤ በጣም ውሱን የሆነ ሀብት ይዘው ያልተመቻቸ ሁኔታ ላይ ሆኖም ቢሆን ተቋም መገንባት የቻሉ፤ የመንፈስ ጥንካሬ የተላበሱ ባልሰሩት ወንጀል ለ12 ዓመታት ለእስር ተዳርገው ከምቾት ወጥተው ተራ ሰው ቢሆኑም በአገዛዝ ወይም በግለሰብ እንጂ በሀገሬ በደል አልደረሰብኝም በማለት ሀገራቸውን ደግም ያገለገሉ፤ በስተእርጅና ጤና ማጣት ሳይበግራቸው ሁሌም ማንበብ፣ መማርና እስከ መጨረሻው ቀናት ለሀገር ያላቸውን እውቀት ከመስጠት ወደኋላ ያላሉ የኢትዮጵያ ባለውለታ ነበሩ።
ዶክተር አስማማው ቀለሙ ባደረባቸው ሕመም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሕክምና ሲደረግላቸው ቢቆዩም ቅዳሜ ሚያዝያ 05/ 2016 ዓ.ም ሌሊት ላይ በ78 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ዶክተር አስማማው ቀለሙ ባለትዳር እና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ። የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ማክሰኞ ሚያዝያ 08/2016ዓ.ም ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
እኛም ለ60 ዓመታት በሙያቸው ሀገራቸውን በታማኝነት ያገለገሉትን የእኚህን የሀገር ባለውለታ ነፍሳቸውን ከደጋጎቹ ጎን ያስቀምጥልን እያልን ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም