“የጅማ መናኸሪያ በወቅቱ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ለእንግልት ተዳርገናል”-ተሳፋሪዎችና ሹፌሮች

“ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው”የጅማ ከተማ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤት

ጅማ:- የጅማ መናኸሪያ በወቅቱ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ለእንግልት ተዳርገናል ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳፋሪዎችና ሹፌሮች ተናገሩ። የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የጅማ ከተማ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

ከጅማ ወደ አጋሮ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ሹፌር ሰይድ ሻሚል እንደገለጸው፣ የጅማ አውቶብስ መናኸሪያ አገልግሎት በተያዘለት ወቅት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት ባለመሰጠቱ በሥራቸው ላይ ጫና እያሳደረ ነው። አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው መናኸሪያ በሳምንት ከ

ጊዜ በላይ ይሰምጣል። ብዙ ጊዜ መኪናዎች በጭቃ እየተያዙ ትራንስፖርት ይስተጓጐላል፣ መንገደኞች ገብተው ለመሳፈር ይቸገራሉ። በመናኸሪያው ውስጥ ምንም አይነት የመንገደኞች ማረፊያና መፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ መኪና ለማቆምም አስቸጋሪ ነው።

ሌላኛው ከአጋሮ ጅማ የሚሠራው ሹፌር እንግዳወርቅ አብየ ጊዜያዊ መናኸሪያው ጧት እና ማታ በጣም ስለሚጨናነቅ መኪና ለማስገባት ፈተና ነው። ለግጭትና ሌሎች ችግሮች የሚዳርግ ነው። ስለዚህ ዘመናዊው የአውቶቡስ መናኸሪያ ግንባታ ቢጠናቀቅ ከገጠምን ችግር ልንወጣ እንችላለን ብሏል፡፡

ከጅማ ወደ በደሌ አገልግሎት የሚሰጠው ሹፌር ሀኒ ተሰማ በበኩሉ፣ አሁን አገልግሎት እየሰጠን ያለነው በጣም አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ነው። ይህ በመሆኑ መንገድ ላይ በሕገ ወጥ መልኩ ለመጫን ያስገድዳል። ክረምት እየመጣ ነው፣ በክረምት በዚህ ጊዜያዊ መናኸሪያ ለመስጠት እንቸገራለን። ለዚህ አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ሲል ተናግሯል።

መንገደኞቹ ጊዜያዊ መናኸሪያዎቹ የሚገኙበት ቦታ ለትራንስፖርት አመች ባለመሆኑ በሕገወጥ መልኩ ከመጠን በላይ ክፍያ በመፈጸም ለመሳፈር እየተገደድን ነው። ሰለሆነም መፍትሔ ያስፈልገዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የጅማ ከተማ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ኤጀንሲ ሁለት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባሕሩ ጃድ በበኩላቸው ለቀረቡ ቅሬታዎች በሰጡት ምላሽ፣ የከተማው ማኅበረሰብ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

አቶ ባሕሩ እንደገለጹት፤ በከተማው ውስጥ የሚገኘው መናኸሪያ ግንባታ ላይ ይገኛል። ግንባታውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማስረከብ ኦማ ኮንስትራክሽን የተሰኘ ተቋራጭ በ2011 ዓ.ም ውል ቢወስድም በተባለው ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ማስረከብ ስላልቻለ ውል እንዲቋረጥ ተደርጓል። አሁን ላይ የመናኸሪያው ግንባታ በኦሮሚያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኤጀንሲ ቁጥጥር የሚደረግ ሲሆን ኦቢኤም የተባለ ኮንስትራክሽን ከኦማ ኮንስትራክሽን በመረከብ ግንባታውን እያከናወነ ነው።

መናኸሪያው ከፍተኛ የሕዝብ ጥያቄ ያለበት በመሆኑና የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በአጭር ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው። የሚቀረው ሥራ ውስን ሲሆን የአስፓልት ጠጠርና የአስፓልት ንጣፍ ሥራውን ከሁለት ወር በኋላ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንደሚገባ አቶ ባሕሩ አብራርተዋል።

በኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካሪ የጅማ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ ተቆጣጣሪ አቶ ዳኘ አራርሳ እንደገለጹት፣ የአውቶቡስ መናኸሪያው በ2011 ዓ.ም በኦማ ኮንስትራክሽን ውል ወስዶ ግንባታ ቢጀምርም በገጠመው የአቅም ማነስ ሳቢያ ግምባታው በተያዘለት ጊዜ እንዳይከናወን አድርጓል። ውሉ እንዲቋረጥ በማድረግ በ2015 ግንቦት ወር ላይ ኦቢኤም የተባለ ኮንስትራክሽን ተረክቦ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል ወስዶ እየሠራ ነው።

ከኦማ ሲረከብ የሲቪል ግንባታ ሥራው 42 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆሙት ተቆጣጣሪው፣ አሁን ላይ ከ78 በመቶ በላይ ተገንብቷል። የግንባታው መሠረት (Sub base) ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን አሁን ላይ የገጠማቸው ችግር የአስፓልት ጠጠር ምንጣፍ (base course) ግብዓት ላይ የአቅም ማነስ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የቻይና ኮንስትራክሽን አስፓልት ብቻ ለመሥራት ነው እቅድ ያቀረበው ያሉት ተቆጣጣሪው የአስፓልት ንጣፍ ጠጠሩን ለማቅረብ ጥራቱን ለማረጋገጥ ጅማ ዩኒቨርስቲ ተልኮ እየተሠራ ነው።

በውሉ መሠረት ግንባታውን እስከ ግንቦት ወር ድረስ አጠናቆ ለማስረከብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳኘ ፣ አልፎ አልፎ በሚዘንበው ዝናብና በግብዓት አቅርቦት እጥረት ምክንያት በተፈለገው ልክ ሥራው እንዳይከናወን ጫና አሳድሯል። ነገር ግን የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የጅማ ዘመናዊ የአውቶቡስ መናኸሪያ በኦማ ኮንስትራክሽን በ318 ሚሊዮን ብር ወጪ ለመገንባት ውል ወስዶ ግንባታ ቢጀመርም በአቅም ማነስ ምክንያት ኦቢኤም የተባለ ኮንስትራክሽን በ475 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለማጠናቀቅ ድጋሚ ውል ወስዶ እየሠራ ይገኛል።

ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You