ምዕራባውያን መጨረሻው አስከፊ ወደሆነው የኑክሌር ጦርነት እየተንደረደሩ ነው ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች

ምዕራባውያን መጨረሻው አስከፊ ወደሆነው የኑክሌር ጦርነት እየተንደረደሩ ነው ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች።

ሩሲያ፣ አሜሪካ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና ፈረንሳይ ለዩክሬን የሚያደርጉት ወታደራዊ ድጋፍ ኑክሌር የታጠቁ የዓለም ኃያላን ወደ ግጭት እንዲገቡ እየገፉ ነው ስትል በዛሬው እለት አስጠንቅቃለች።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፈረንጆቹ 2022 በዩክሬን ላይ ያወጁት “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ከ1962ቱ የኩባ ኑክሌር ቀውስ ወዲህ በሩሲያ እና ምዕራባውያን መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉን የሩሲያ እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ።

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ ካፀደቀ ከሁለት ቀናት በኋላ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አሜሪካ እና ኔቶ ሩሲያ ስትራቴጂካዊ ሽንፈት እንዲደርስባት ቋምጠዋል ብለዋል።

ላቭሮብ እንዳሉት ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉት ድጋፍ አሜሪካ እና አጋሮቿን ከሩሲያ ጋር በቀጥታ እንዲጋጩ ጫፍ ላይ አድርሷቸዋል።

“ምዕራባውያን በአደገኛ ሁኔታ ኑክሌር በታጠቁ የዓለም በኃያላን መካከል ወደሚደረግ እና መጨረሻው አስከፊ ወደሆነ ጦርነት እየተንደረደሩ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ላቭሮቭ።

ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የኑክሌር ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ይህን የሩሲያ ማስጠንቀቂያ በትኩረት እንደሚያዩት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ዩክሬን እና ምዕራባውያን አምባገነኗ ሩሲያ ከኢምፔሪያሊዝም ጋር የሚመሳሰል መሬት የመቀማት ጦርነት እያካሄደች ነው፤ በዩክሬን ያለው ኃይሏም ሽንፈት መከናነብ አለበት ይላሉ።

ሩሲያ ይህን ጦርነት የጀመረችው የምዕራባውያን ወታደራዊ ጥምረት የሆነው ኔቶ ወደ ቀድሞ የሶቭየት ሀገራት እየተስፋፋ መሆኑን እና ይህም ለደኅንነቷ እንደሚያሰጋት ከገለጸች በኋላ ነበር።

ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን የሚገኙ አራት ግዛቶችን በከፊል ወደ ግዛቷ የጠቀለለች ሲሆን ግዛቶቹን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቅለል አሁንም እየተዋጋች ትገኛለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You