ሰሜን ኮሪያ በርካታ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች

ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ጠዋት በርካታ “አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ” ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች።

ከፒዮንግያንግ አቅራቢያ የተተኮሱት ባለስቲክ ሚሳኤሎች 300 ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዙ በኋላ ወደ ምሥራቃዊ የደቡብ ኮሪያ የባሕር ዳርቻ መግባታቸውንም ነው ያስታወቀችው።

ጃፓንም የፒዮንግያንግን የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ አረጋግጣለች።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፥ የአውሮፕላኖች እና መርከቦችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ መረጃዎች በፍጥነት እንዲሰበሰቡ አዟል።

ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ወራት እያካሄደችው ያለው የሚሳኤል ሙከራ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ይበልጥ ያባብሳል ያሉት ቶኪዮ እና ሴዑል ከአጋራቸው ዋሽንግተን ጋር ትብብራቸውን አጠናክረዋል።

ፒዮንግያንግ በበኩሏ እንደ ሩሲያ እና ቻይና ካሉ ሀገራት ወዳጅነቷን እያጠናከረች ዓለማቀፍ ጫናውን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በኅዳር ወር 2023 የመጀመሪያዋን የስለላ ሳተላይት በተሳካ ሁኔታ ያመጠቀችው ሰሜን ኮሪያ፤ በቅርቡ ሁለተኛ ሳተላይት ለማምጠቅ መዘጋጀቷን ደቡብ ኮሪያ አስታውቃለች።

ባለፈው ዓርብ የሞከረችው “ግዙፍ” ክሩዝ ሚሳኤልና አዲስ ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤልም ለጎረቤቶቿ ስጋት ፈጥሯል።

ፒዮንግያንግ በሚያዚያ ወር መጀመሪያም “ሃውሶንግ -16ቢ” የተሰኘና ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀም አሕጉር አቋራጭ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መሞከሯ የሚታወስ ነው።

አረሩን ለማስወንጨፍ ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀመው “ሃውሶንግ -16ቢ” አሜሪካን ጨምሮ “በየትኛውም ዓለም የሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ጠላቶች”ን በፍጥነትና በኃይል መምታት ይችላል፤ በፀረ ሚሳኤል የመመታት ዕድሉም ዝቅተኛ ነው መባሉ አይዘነጋም።

አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራው የፀጥታው ምክርቤት እገዳን የጣሰ ነው ቢሉም ፒዮንግያንግ ግን እገዳው ሉዓላዊነቴን የሚጥስ እና ራሴን ከአደጋ የመከላከል መብቴን የሚገድብ ነው ትላለች።

የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ሀገራቱ የሚያደርጉትን ወታደራዊ ልምምድ በሚሳኤል መቃወማቸውንም ቀጥለዋል።

ሩሲያ ባለፈው ወር የመንግሥታቱ ድርጅት በፒዮንግያንግ የኒዩክሌር እና ሚሳኤል ፕሮግራም ላይ የጣላቸው ማዕቀቦች በየዓመቱ እንዲገመገም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

Recommended For You