የትብብር ማዕቀፉ መፈረም የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ሀብታቸውን በፍትሐዊነት እንዲጠቀሙ ዕድል ይፈጥራል

አዲስ አበባ፡የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን አፅድቀው የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ኮሚሽን ከተቋቋመ የውሃ ሀብታቸውን በፍትሐዊነት ለመጠቀም እድል እንደሚፈጥር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ባለፉት 25 ዓመታት የሠራቸው ሥራዎችና በአባል ሀገራት መካከል እንዴት ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል በሚለው ሀሳብ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት ውይይት ትናንት ተካሂዷል።

በውይይቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ መሥራችና የዓባይ ተፋሰስ (የናይል ቤዚን) ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የትብብር ማዕቀፉን ስምምነት (CFA) የመጀመሪያ ፈራሚና በፓርላማ ያፀደቀች ሀገር ናት።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ኮሚሽንን ለማቋቋምና የጋራ የውሃ ሀብትን በጋራ ለመጠቀም የተፋሰሱ አራት ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን አፅድቀዋል። በቀሪዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉ ከተፈረመ አባል ሀገራት የውሃ ሀብታቸውን በጋራ ለመጠቀም ዕድል ይፈጥራል ።

እንደ ሀገር ለናይል ቤዚን መጠቀም ባለብን ልክ አልተጠቀምንም ያሉት አብርሃ (ዶ/ር)፤ ወደፊት በትክክል ለመጠቀም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥረናል። የተፈጠረው መደላድል የትብብር ማዕቀፉ ስምምነት እንዲፈረምና የናይል ቤዚን ኮሚሽን ሲቋቋም ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብትን በትክክል እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰሶች ዜጎችን በማስተባበር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ሊኖር የሚችለውን የውሃ ሀብት አጠቃቀም የሚያስተካክልና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ነገር ግን የጋራ ኮሚሽን በማቋቋም ውሃን የመጠቀም መብትን በጋራ ማስከበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

እንደ አብርሃ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከናይል ቤዚን ተጠቃሚ መሆን አለባት። የናይል ቤዚን ባስቀመጠው የአስር ዓመት እቅድ መሠረት በኃይል፣ በምግብ ዋስትና፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ ዕቅድ ይዛ መጠቀም ያለባትን እየተጠ ቀመች ነው። ለአብነትም በአማራ ክልል መገጭና ጣና በለስ የመስኖ ልማትን ለማልማት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ።

የኃይል ንግድን በተመለከተም ከተፋሰሱ አባል ሀገራት ጋር የጋራ ልማት እንዲኖር በኢትዮ-ሱዳንና በኢትዮ-ደቡብ ሱዳን የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ ግሬስ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ወደ ታሰበለት ኮሚሽንነት እንዲሸጋገር የናይል ተፋሰስ ሀገራት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው። የናይል ቤዝን ኢንሼቲቭን (NBI) ወደ ኮሚሽንነት እንዲሸጋገር አባል ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን (CFA) እንደ ብሔራዊ ሕግ ማፅደቅ ይጠበቅባቸዋል።

አሁን ላይ አራት ሀገራት ማፅደቃቸውን በመግለጽ፤ የትብብር ማዕቀፉን ያፀደቁ ሀገራትን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ነው። ኢትዮጵያ ቀድማ ማፅደቋንና ኮሚሽኑ እውን እንዲሆን ተገቢውን እገዛ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ አጠቃቀም እንዲሻሻል እየሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ የተፋሰሱ ሀገራት ዜጎች የኢኮኖሚ እድገት ፈተና ገጥሟቸዋል። እንዲሁም የምግብ ዋስትና ችግር፣ የልማት እድገትና የሕዝብ ቁጥር እድገት አለመመጣጠን ሌላው ችግር መሆኑን በመግለጽ፣ ችግሮችን ለመቅረፍ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብትን በጋራ እንዲያለሙና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You