አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኗ የብዙ ሀገራትን ትኩረት እየሳበ ነው ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ ተናገሩ። የዑጋንዳ ከፍተኛ የትምህርት ፖሊሲ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ በመገኘት በትምህርቱ ዘርፍ የልምድ ልውውጥ እያካሄዱ ነው።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ(ዶ/ር) እንደገለጹት የልምድ ልውውጡ በዑጋንዳ መንግሥት በቀረበ ጥያቄ በኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ እየተደረጉ ባሉ የለውጥ ሥራዎች ላይ ልምድ ለመቅሰም ያለመ ነው።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ባሉት ደረጃዎች የተደረጉትን የካሪኩለሞች አቀራረጽ፣ የይዘትና የትምህርት አሰጣጥ ለውጦች እና በትምህርት ጥራት በተለይም በፈተና አሰጣጥ ሂደት ላይ ያሉትን አሠራሮች በመመልከት ልምድ ለመውሰድ የተደረገ ነው።
እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆነ ምርጥ ተሞክሮ አለው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው ከልምድ ልውውጡ ኢትዮጵያም ከዑጋንዳ የምትወስዳቸው መልካም ተሞክሮዎች ይኖራሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጡ ላይ የይዘት ለውጦች መደረጋቸውንና ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ ትምህርት አሰጣጡ በተግባር ላይ አተኩሮ በጥራት እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ጥራት በአንዴ የሚመጣ ነገር ባይሆንም ጅማሮዎቹ ጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራን ልማት ላይም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው በመጪው ክረምት በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ 50ሺ መምህራን ሥልጠና እንደሚገቡ አመላክተዋል። በዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ መምህራንም በድህረ ምረቃ፣ በማስተማር ሥነ ዘዴ እና የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲወስዱ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አብራርተዋል።
የዑጋንዳ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ምክትል ኮሚሽነር ጆሴፍ ሙቫዋላ(ዶ/ር) በበኩላቸው መንግሥት የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው ዑጋንዳ ከዚህ ልምድ ትማራለች ብለዋል። በዩኒቨርሲቲ ማጠናቀቂያ እየተሰጠ ያለው የመውጫ ፈተናም ትልቅ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ ያሉትን መልካም ነገሮች በሙሉ ዑጋንዳ ልምድ ወስዳ ትተገብራለች ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፉ በጋራ በመሥራት መልካም አፍሪካውያን እናፈራለን ብለዋል።
አብዛኛው ሀገራት የትምህርት ፖሊሲዎችን ሳያሻሽሉ ለረጅም ዓመታት ይቆያሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ፖሊሲዎችን በየጊዜው በማሻሻል የሚፈጠሩ ስህተቶችን ማረም ያስፈልጋል ብለዋል።
ልዑካኑ በቆይታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን፣ ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲን እንዲሁም የተመረጡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ምልከታ የሚያደርጉ ሲሆን በአዲስ አበባ ያሉ የቱሪዝም መስሕቦችን በተለይም የዓድዋ ሙዚየምን ይጎበኛሉ ተብሏል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም