ፕሮጀክቱ ከአካባቢ ጋር የሚስማማ የምርት ሂደት እንዲኖር ያደርጋል

አዲስ አበባ፦ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ለማስወገድ የሚያስችለው ፕሮጀክት ከአካባቢ ጋር የሚስማማ የምርት ሂደት እንዲኖር እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ በሆነ መንገድ ምርቶችን በማምረት ዘላቂ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፉ በኢትዮጵያ በከፍተኛ እድገት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲደረግ የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ በማስወገድ፤ ምርታማነትን በማሳደግ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢንቨስትመንት በመጨመር ከአካባቢ ጋር የሚስማማ የምርት ሂደት እንዲኖር ያደርጋል፡፡

የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በዓለም ላይ በካይ ከሚባሉ ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ያነሱት ሚልኬሳ (ዶ/ር)፤ ፕሮጀክቱ የአየር ብክለትን በመከላከል የመሬት፣ የውሃና የዜጎችን ደኅንነት በመጠበቅ ለኅብረተሰቡ ተስማሚ ምርቶችን ለማቅረብ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ጠቁመው፤ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በዘርፉ በተመረጡ ፋብሪካዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆንና የሚገኙ ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ወደ ሌሎች ዘርፎችም እንዲሰፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ ለዘላቂ የኬሚካል አያያዝ፣ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ለማስወገድና እና የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ለማ ናቸው።

የአካባቢ ደኅንነትን ማስጠበቅ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ ነው ያሉት አቶ ስለሺ፤ በመንግሥትና በልማት አጋሮች የተቀረፀው ፕሮጀክት አከባቢን የማይጎዳና ለኅብረተሰቡ ተስማሚ መሆኑን እንዲሁም የባለሃብቶችን የምርትና አገልግሎት ተወዳዳሪነት ለመጨምር፣ ወጪ ለመቆጠብ፣ ምርታማነትን ለማሳደግና አቅም ለመፍጠር መነደፉን አንስተዋል።

እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፤ በአሁን ወቅት ሀገራት ምርቶች ለመሸመት አካባቢና ሕዝብን ሳይጎዱ መመረታቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ምርቶች በየትኛውም የገበያ መዳረሻዎች የሚቀርቡ በመሆናቸው ብዛት ያለው ምርት በማምረት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

የአፍሪካ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ኔትወርክ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና አስተባባሪ ቤዛዊት እሼቱ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ረገድ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፉ ትልቅ ሚና እንዳለው አንስተው፤ ኔትወርኩ በፕሮጀክቱ አተገባበር ዙሪያ ለተቋሙ በሥልጠና መልክ የቴክኒክና መሰል ድጋፎችን እንደሚያደርግ አመልከተዋል።

እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ፤ በዓለም ገበያዎች አከካባቢን በመጉዳትና ማኅበራዊ እሴትን ሳያማክሉ የሚመረቱ ምርቶች ተቀባይነት እያጡ በመሆኑ፣ ይህ ፕሮጀክት ብክነትንና ብክለትን ባላስከተለ መልኩ በማምረት ኢትዮጵያ በዓለም ገበያዎች ተወዳዳሪ እንድትሆን ይረዳል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You