ከኪጋሊ ጋር የተደረገው ስምምነት መዲናዋን ይበልጥ ለማስዋብ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባና የኪጋሊ ከተሞች የትብብር ስምምነት መዲናዋን ይበልጥ ለማስዋብ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ሁለቱ ከተሞች የጋራ እቅድ አውጥተው መሥራት እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ጤናው ገለጹ፡፡

አቶ አንዱዓለም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ እና ኪጋሊ በውስን ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የእህትማማችነት ስምምነት ማድረጋቸው ለሁለቱ ከተሞች ዕድገት ጠቃሚ ነው፡፡

ኪጋሊ እንደ አዲስ አበባ ሰፊ ከተማ ባትሆንም በዋናነት የምትታወቀው በሦስት ነገሮች ነው ያሉት አቶ አንዷለም፤ ይህም በዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ፤ በቆሻሻ አወጋገድ እና በአረንጓዴ ልማት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አንዱዓለም ገለጻ፤ ኪጋሊ ከአዲስ አበባ በሰፋፊ መንገዶች ግንባታና ምንም እንኳን የነዋሪው ፍላጎት አሁንም ከፍተኛ ቢሆንም በቤት ልማት ተሞክሮዎችን መውሰድ ትችላለች፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ከኪጋሊ ከተማ የማስዋብ ፕሮጀክቶች ሰፊ ልምድ በመቅሰም አቅሟን ማሳደግ ትችላለች።

ስምምነቱ በጋራ ለመሥራት እንደመግቢያ በር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሁለቱ ከተሞች በተፈራረሙባቸው ዘርፎች የሚገኙ ተቋማት የጋራ ዝርዝር እቅድ አውጥተው ሊሠሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሁለቱ ከተሞች በተፈራረሙባቸው ዘርፎች የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች በጋራ እቅድ አውጥተው ካልሠሩ ውጤቱን መለካትም ሆነ የሚፈለገውን ግብ ማምጣት አይቻልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከተሞቹ ባለሙያዎችን ወደ ኪጋሊ እና አዲስ አበባ በመላላክ ሥልጠና መስጠትና እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በመገምገም ድጋፍ እንዲደረግ በማድረግ ግንኙነቱ ውጤት እንዲያመጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

አቶ አንዱዓለም እንደተናገሩት፤ በተደጋጋሚ በተሠሩ ጥናቶች እንደተስተዋለው፤ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ካሉ ከተሞች ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ውስን ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አይደሉም።

አብዛኛዎቹ ከውጭ ከተሞች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ይዘታቸው ሲታይ ጥቅል ነው፡፡ ይህም ስምምነት ተደረገ ከማለት ውጪ ጥቅም ላይ ሲውል አይስተዋልም ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የሁለቱ ከተሞች ስምምነት በውስን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀው፤ በቆሻሻ አወጋገድ፤ በአረንጓዴ ልማት እና በመሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የተደረገ ስምምነት በመሆኑ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።

በውስን ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገው ስምምነት ፈጻሚ በሆኑ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች እና የከተማ አስተዳደሩ በቅርበት እየተከታተሉ ለማስፈጸም የሚችሉበት አካሄድ ለማበጀት ይረዳል ብለዋል።

በሌላ በኩል ስምምነቱ ከአፍሪካ ሀገር ጋር መሆኑ ሁልጊዜ የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራትን ከማየት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር እርስ በርስ ለመማማር የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባና የሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ የእህትማማች ከተማነት ስምምነት ሰሞኑን ፈርመዋል፤ ስምምነቱን የፈረሙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የኪጋሊ ከተማ ከንቲባ ሳሙኤል ዱሴንግዩምቫ መሆናቸው ይታወሳል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You