ሰዎች መልካም ነገር ሲደረግላቸው አፀፋቸው ምስጋና እና ምርቃት ይሆናል:: በተለይም አዛውንቶች ሲመርቁ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን ወይም የሚያስቡት ነገር የተፈፀመ ያህል ስሜት አለው:: ጥሩ ስሜት ከሚፈጥሩ ምርቃቶች መካከልም ‹‹የጠዋት ጀንበር አትጥለቅብህ (ሽ)›› የሚለው ትርጉም ይሰጣል:: ወንድም ሆነ ሴት፤ ወጣትነታቸውን በዋዛ ፈዛዛ ከማሳለፍ ለቁምነገር ቢያውሉት በማምሻው እድሜያቸው ትርፋማ ያደርጋቸዋል እንደማለት ነው::
ይህም ቢሆን ግን ሁሉም የወጣትነት ሩጫ የሀብት ማማ ላይ ያስቀምጣል ተብሎ ግን አይጠበቅም:: ልፋትና ድካሙ በሚፈለገው ያህል ፍሬ ላያፈራ ይችላል:: ነገር ግን ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም››ና ብለፋም ብደክምም አይሳካም ብሎ አፍላ የወጣትነት ጊዜን በከንቱ እንዲያልፍ ማድረግ የዋህነት ነው:: ጉዳቱም መልሶ ለራስ ነው የሚሆነው::
የዛሬ እንግዳችን ወይዘሪት አበራሽ ማሞ የህይወት መርሀቸው ይህንኑ በመግቢያዬ ላይ ካነሳሁት ሃሳብ ጋር የተያያዘ ነው:: ወይዘሪት አበራሽ፤ ከታዳጊነት እድሜዬ ጀምሮ በኑሮ ተፈትኛለሁ ይላሉ:: ምን ገጠማቸው፤ እንዴትስ ተወጡት፤ አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ናቸው? የሚለውን ከመጀመሪያው ጀምሮ እንዲህ አጫወቱናል ::
አስተዳደጋቸው
ወይዘሪት አበራሽ ማሞ፤ የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ቄራ ተብሎ በሚጠራ ሰፈር ነው:: በእናትና አባት የማደግ እድል አላገኙም:: ለዚህ ምክንያቱ ወላጅ እናታቸው እርሳቸውን ለማሳደግ የገንዘብ አቅም ስላልነበራቸውና አስቸጋሪ በሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው ነው፡፡ በአጋጣሚ ክርስትና ያነሷቸው ወይዘሮ ሙሉነሽ ካሳ ከአካባቢው ላይ ጥሩ ኑሮን የሚኖሩትና ሀብታም ተብለው ከሚጠሩት ግለሰቦች መካከል አንዷ የነበሩ በመሆኑ እናታቸው እርሳቸው እንዲያሳድጓቸው ሰጧቸው::
በክርስትና እናታቸው ቤት ብዙ የቤት ሰራተኞች ነበሩ:: በወቅቱም ሰራተኞች ባሪያ እንደሚባሉም በክርስትና እናታቸው ቤት ሲያድጉ ነው ያወቁት:: እነዚህ በአሰሪዎቻቸው ባሪያ የሚባሉትም ግደበረት ከሚባል አካባቢ ተገዝተው እንደሚመጡም ያውቃሉ:: እርሳቸውም በማደጎ ቢወሰዱም እንደ ልጅ አልነበርም የሚታዩት:: ከቤት ሰራተኞቹ ባልተናነሰ በቤት ውስጥ የታዘዙትን ሥራ ሁሉ መስራት ይጠበቅባቸዋል:: ቤት አጽድተው፣ ለክርስትና እናታቸው ባለቤት ቡና አፍልተው ካጠጡ በኋላ ነው ወደትምህርት ቤት የሚሄዱት::
የትምህርት ሰአት ስለሚደርስባቸው ቁርስ እንኳን ለመብላት ጊዜ የላቸውም:: መደበኛ ቁርስ አያውቁም:: የክርስትና እናታቸው ባል በሚያጎርሷቸው ጉርሻ ነው ትምህርት ቤት ውለው የሚመለሱት:: ትምህርት ቤትም በጊዜ ስለማይደርሱ የአስተማሪ ቅጣት ይደርስባቸዋል:: አንዳንዱ መምህር አሸዋ ላይ በማንበርከክ ነው የሚቀጣው:: ቅጣቱ ተደጋጋሚ ስለሆነባቸው ጉልበታቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል:: አንድ መምህርም ሲገርፏቸው በመግረፊያው አይናቸው ላይ ጉዳት አስከትሎባቸው ለብዙ ጊዜ ታመው ያውቃሉ ::
በወቅቱ በተደጋጋሚ የሚያረፍዱበትን ምክንያት የጠየቃቸውም፣ የሚረዳቸውም አስተማሪ አለመኖሩም ያሳዝናቸዋል:: እርሳቸውም እውነታውን ለመናገር ይፈሩ ስለነበር ቅጣቱን ከመቀበል ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም:: ትምህርታቸውን ላለማቋረጥ እንዲህ ያለውን ፈተና ለመቀበል ተገደው እንደነበር ነው ለትምህርት የከፈሉትን ዋጋ የሚናገሩት::
እንደ ልጅ ይሄን እፈልጋለሁ ያሉበትን ጊዜ አያስታውሱም:: ልብስም የሚገዛላቸው በአሳዳጊያቸው ፍላጎትና ምርጫ ነው:: ይጠሩ የነበረውም በወላጅ አባታቸው ሳይሆን በክርስትና እናታቸው ባል ነው:: በዚህ ሁኔታ ተምረውም አምስተኛ ክፍል ደርሰ ዋል::
ወላጅ እናታቸው እርሳቸው የሚያድጉበት ቤት ይመጡ ነበር:: አመጣጣቸው ልጃቸውን ለማየት ሳይሆን የክርስትና እናታቸው ‹‹ለምን ቤቴን አልፈሽ ትሄጃለሽ እየመጣሽ ምሳ ለምን አትበይም›› የሚል ወቀሳ ስላቀረቡላቸው ነበር:: እናታቸውም ወቀሳውን ተቀብለው በተባሉት ሰአት ምሳ ለመብላት ልጃቸው ወዳሉበት ቤት ይመላለሱ ነበር::
ግን የሚደረግላቸው መስተንግዶ የወቀሳውን ያህል አለመሆኑን ወይዘሪት አበራሽ ይታዘባሉ:: ይናደዳሉ:: ወይዘሪት አበራሽ እንደሚሉት የሚቀርበው ምግብ ከሽሮ ያለፈ አይደለም:: ያም ቢሆን ደጅ ጠንተው ነበር የሚቀርብላቸው:: እንኳን እናታቸው እርሳቸውን ጨምሮ የቤት ሰራተኞች ለባለቤቶቹ ከሚዘጋጀው ምግብ መብላት አይፈቀድላቸውም:: ለሰራተኞች ተብሎ ሌላ ምግብ ይዘጋጃል::
ተመርጦ የሚቀርበውንም ምግብ እናታቸው በሰአቱ አለማግኘታቸው ከንዴት አልፎ አስለቅሷቸው ያውቃል:: እናታቸው እንዳያዩዋቸው ጓሮ ሄደው ነበር አልቅሰው ንዴታቸውን ተቆጣጥረው የሚመለሱት:: እናታቸውም ምግብ መጠበቁ ሰልችቷቸው አንድ ቀን ሳይበሉ ከቤቱ ወጥተው ይሄዳሉ:: ወይዘሮ አበራሽን ይበልጥ ያናደዳቸው ደግሞ የክርስትና እናታቸው ንግግር ነበር:: የባለቤታቸውን ስም ጠርተው ከእርሱ በፊት ምግብ እንዲቀርብላት ፈልጋ ነበር እንዴ? ያሉትን አይረሱትም:: ወይዘሮ አበራሽ እንደሚሉት፤ እናታቸው የክርስትና እናታቸው ባል ተመግበው እስኪጨርሱ ጠብቀው ምግብ መብላታቸው ትርጉም አልነበረውም:: ምክንያቱም ለእናታቸውና ለክርስትና እናታቸው ባል የሚቀርበው ምግብ የተለያየ በመሆኑ::
ወይዘሪት አበራሽ እንደሚሉት፤ ወደፊት ጥሩ የሆነ ህይወት ይገጥመኛል የሚለውን በማሰብ ይሄም ያልፋል ብለው ነገሮችን ለመቋቋም ብዙ ጥረት አደረጉ:: ችግሮችን ተቋቁመው ትምህርታቸውን ለመጨረስና የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ፈለጉ ነገር ግን ከእርሳቸው አልፎ እናታቸው የሰው ፊት የማየታቸው ሁኔታ እስከመቼ የሚለው አእምሮአቸውን እረፍት ነሳው፤ የተገኘውን ሥራ ሰርተው እናታቸውን በኑሮ ማገዝ እንዳለባቸው ተሰማቸው፤ ይህ ሃሳባቸውም አሸንፎ ወይዘሪት አበራሽ ከክርስትና እናታቸው ቤት ወጡ ::
የአንድ ቀን ውሳኔ
ወይዘሪት አበራሽ ካሳደጓቸው ከክርስትና እናታቸው ቤት ለመውጣት ሲወስኑ፤ ተደብቀው ደብተሮቻቸውንና ልብሳቸውን በአጥር ወደ እናታቸው ቤት በመወርወር ነበር፤ የእናታቸውን የቤት ቁልፍ ከጎረቤት ወስደውም ነው ወደ ቤት የገቡት:: እናታቸው ለምን ይሄን አደረግሽ ብለው እንደሚቆጧቸው ስለሚያውቁም ቤት ገብተው አልጋ ስር ነበር የተደበቁት:: እናታቸው ቤት ገብተው ስላላገኟቸው ሁኔታውን ለመጠየቅ ልጃቸውን ወዳሳደጓት ሴት ቤት ሄዱ::
እርሳቸው ገና ለመጠየቅ ሲሉ ሴትየዋ ቀድመው ‹‹ምን ልታደርጊ መጣሽ ልጅሽን እንደሆን ወስደሻል›› አሏቸው:: ያልጠበቁት ነገር ስለነበር ደንግጠው ‹‹ልጄ ጠፋች ማለት ነው›› ብለው ወደቤታቸው ተመልሰው ቁልፍ የሰጡትን ጎረቤት ይጠይቃሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን ወይዘሪት አበራሽ አልጋ ስር እንደተደበቁ ናቸው:: በመጨረሻ እናታቸው እንዳይመቷቸው ተማጽነው ከተደበቁበት ይወጣሉ::
እናታቸው በዚህ ሁኔታ ካሳደጓቸው ሴት ቤት መውጣት እንዳልነበረባቸው በቁጣም በምክርም ጭምር ሊያግባቧቸው ሞከሩ:: እናታቸው ጎረቤት ስለሆኑ ሲወጡና ሲገቡ ሊደርስባቸው የሚችለውን አላስፈላጊ የሆነ ንግግር በማሰብ ጭምር ነበር ልጃቸው ያደረገችውን ነገር ትክክል እንዳልሆነ ለመገሰጽ የሞከሩት:: ወይዘሪት አበራሽ ግን አንዴ ስለቆረጡ እናታቸው የማይቀበሏቸው ከሆነ “አባሳሙኤል” የሚባል ወንዝ ውስጥ ገብተው እራሳቸውን እንደሚያጠፉ ይነግሯቸዋል:: እናታቸውም የልጃቸውን ማምረር በመገንዘባቸው መልሰው ያረጋጓቸዋል::
የወይዘሪት አበራሽ እራስን የመቻል ኑሮ “ሀ” ተብሎ ተጀመረ:: እርሳቸው እንደሚሉት አንድ የአካባቢያቸው ነዋሪ የሆነ ሰው ያገኙና ሥራ እንዲፈልግላቸው ይጠይቁታል:: ሰውየውም ገና ልጅ እንደሆኑና ትምህርት ቢማሩ እንደሚሻል ይመክሯቸዋል:: ደግሞም ምን አይነት ሥራ ሊሰሩ እንደሚችሉም መልሰው ይጠይቋቸዋል::
በሌላ ቀንም መልሰው ይህን ሰው ሥራ እንዲፈልጉላቸው ይጠይቃሉ:: ሰውየውም የሰሙትን ማስታወቂያ ይነግሯቸዋል:: ተቋሙ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ገነት ሆቴል አካባቢ ሲሆን፤ በዚያን ጊዜ የትራንስፖርት ዋጋም ኪስ የሚጎዳ አልነበረም:: በተለይም የከተማ አውቶቡስ ለአንድ ጉዞ 15 ሣንቲም ነበር የሚያስከፍለው:: እናታቸው ሣንቲም ከሚያስቀምጡበት ቦታ ፈልገው እስከ መመለሻቸው 30 ሣንቲም ይዘው ነበር የሄዱት::
ለእናታቸውም ሳይነግሯቸው በራሳቸው ወስነው ሥራ ፍለጋ የሄዱት:: የገና በዓል ዋዜማ ስለነበር እናታቸው ቤት “በእበት” ለቅልቀው፣ እቃ አጥበው፣ ዳቦም ደፍተው እንዲጠብቋቸው አዘዋቸው ነበር ወደ ሥራ የሄዱት:: እናታቸው ህንፃ ኮንስትራክሽን የሚባል ድርጅት ውስጥ የቀን ሥራ በመስራት በቀን 95 ሣንቲም ተከፋይም ናቸው:: የሚገኘው ገንዘብ አነስተኛ ቢሆንም የሚገዛው ነገር ርካሽ በመሆኑ በኑሮ አይቸገሩም:: በስሙኒ ስጋ ይገዛል ሚዛን ስለሌለም በሳህን ተለክቶ ነበር የሚሸጠው በማለት የወቅቱን ሁኔታ ያስታውሳሉ::
የአንድ በግ ዋጋም ሦስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነበር ቆዳ መልስ የሚገዛው:: ቆዳውን በነፃ ስለሚወስድ ያረደበትን ዋጋ አይጠይቅም:: ይሄ በ1970ዎቹ ውስጥ የነበረ ታሪክ ነው:: አሁን ላይ ዶሮ አርዶ በልቶ ማቅረብ የሥራ መስክ ሆኖ በአንድ ዶሮ እስከ 70 ብር የአገልግሎት ክፍያ እየተጠየቀ ነው:: አንድ በግ አርዶ ለመበለት ደግሞ እስከ አምስት መቶ ብር ደርሷል:: ይሄ ሁሉ ለውጥ ብዙ ረጅም ጊዜ የሚባል አይደለም:: የጤፍ ዋጋም ቢሆን አሁን ካለው ጋር በንጽጽር እንኳን የሚቀርብ አይደለም በማለት ትዝብታቸውን ያነሳሉ::
አንድ ኩንታል ጤፍ ከ50 ብር የበለጠ አይደለም:: እንደ ምስር፣ባቄላ ያሉ ጥራጥሬዎች በሳንቲም ነው የሚሸጡት:: ወተትም ቢሆን አቅርቦትም ሆነ ገበያውም ቅሬታ የሚቀርብበት አልነበረም :: ሰዎች እነዚህን ሁሉ ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟሉት በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ነው::
እውነት የማይመስል ግን ደግሞ እውነት የሆነን ነገር ኖሮ ካየው ሰው መስማት ደስ ይላል:: ‹‹ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ›› ይባል የለ ከነአባባሉ:: ኑሮ ድሮና ዘንድሮ ሆኖብን ንጽጽር ውስጥ ጭልጥ ብለን ገባን:: ወደ ወይዘሪት አበራሽ የሥራ ቅጥር ተመልሰናል:: እርሳቸው እንዳሉት ሥራ መቀጠሩ ግድ ነበር:: እናታቸው የቀን ሥራ ከሚሰሩበት ድርጅት ተቀንሰው ቤት ውለዋል:: ምንም እንኳን ኑሮ ርካሽ ቢሆንም ገቢ ከሌለ ችግር ውስጥ መግባት አይቀርምና አሁን እሳቸውም በሙሉ አቅማቸው ተንቀሳቅሰው ሥራ ማግኘት የመኖር ጉዳይ ሆኖባቸዋል:: እስከ እዛ ድረስ እንኳን ከእናታቸው ጋር ለመኖር ያላቸው ገቢ ወላጅ አባታቸው ደብረዘይት አየር ኃይል ተብሎ የሚጠራ
ተቋም ውስጥ ይሰሩ ስለነበር በወር 50 ብር ተቆራጭ የሚልኩላቸው ነው::
ወይዘሪት አበራሽ ሥራ ፍለጋ የሄዱበት መሥሪያ ቤት ሰራተኞች ለሰሩበት ሥራ የቀን ውሎ አበል ክፍያ እየፈፀሙ ነበር የደረሱት:: ወይዘሪት አበራሽም ሥም ሲጠሩ የነበሩትን ሰው ጠጋ ብለው ሥራ እንደሚፈልጉ ጠየቋቸው:: ሰውየውም ልጅ መሆናቸውን አይተው ሊቀበሏቸው ፍቃደኛ አልነበሩም:: ሆኖም ግን የያዙትን የሥም ዝርዝር በመጥራት እንዲያግዟቸው ይጠይቋቸዋል::
እርሳቸውም ፈቃደኛ ይሆናሉ:: ሥም ጥሪው እንዳለቀ ሰውየው የመልእክት ሰራተኛ ትሆናለች ብለው በማሰብ በቀሩ ሰዎች ምትክ ወይዘሪት አበራሽን መዘገቧቸው:: አሁን ወይዘሪት አበራሽ ይጠሩባቸው የነበረው የአሳዳጊያቸውን ስም በወላጅ አባታቸው በአቶ ደስታ ገብረሥላሴ ለመቀየር መልካም አጋጣሚ ተፈጠረላቸው::
ወይዘሪት አበራሽ ሲቀጠሩ የ13 አመት ታዳጊ ነበሩ:: የቀጠራቸው መከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት በኦሮሚያ ክልል በነቀምት መካከል ላይ በምትገኘው አርጆ ደዴሳ ላይ ማሰልጠኛ ጣቢያ ለማሰራት ዝግጅት ላይ ስለነበር ቅጥሩም የተፈፀመው ለዚህ ተቋም ነው:: የደመወዝ ስምምነቱ ለእርሳቸው ግልጽ ባይሆንም ቅጥሩ ኮንትራት እንደሆነና በወር 90 ብር እንደሚከፈላቸው ያውቃሉ:: በማግስቱ ጉዞ ወደ ደዴሳ በመሆኑ ከሰአት በኋላ አበል እንዲወስዱ ተነገራቸው:: ከሚያገኙት ብር ላይ ለእናታቸው 50 ብር እንዲሰጣቸው አስቀድመው ውል በመግባታቸው:: ተቋሙ ውላቸውን ተቀበላቸው:: ቅጥሩ እንደተፈፀመም በቀን የታሰበላቸው የውሎ አበል ስድስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነበር:: ወይዘሪት አበራሽ ለጉዞ የሚሆን ዳቦቆሎ ስንቅ ለመያዝ በእጃቸው ላይ በነበረው 10 ብር በአንድ ብር ከአምስት ሳንቲም አንድ ኪሎ ስኳር፣ በሁለት ብር ከሃምሳ ሣንቲም ዱቄት፣ በሁለት ብር ግማሽ ሊትር ዘይት፣ ገዝተው ነበር ወደ ቤታቸው የተመለሱት::
ወደ አርጆ ደዴሳ ለመሄድ መዘጋጀታቸውን እናታቸው እንዳያውቁ ዳቦቆሎው ጎረቤት እንዲዘጋጅ ነበር ያደረጉት:: ጎረቤታቸው በምስጢር እንዲይዙ ተማፀኗቸው:: በወቅቱ አስቸጋሪ የሆነባቸው ለጉዞ ሲነሱ ለእናታቸው ምን ብለው እንደሚነግሯቸው ነበር:: እትዬ የሺ የሚሏቸው ጎረቤታቸው ዘዴ እንደማያጡና ጉዞአቸውን እንደሚያሳኩላቸው ነገሯቸው::
በቆየው ባህል አንድን ሰው ለማሳመን ወይንም የሚጠይቋቸው ነገር ተቀባይነት እንዲያገኝ ድንጋይ ተሸክመው ወይንም ነጠላቸውን አንጥፈው ነው ልመናቸውን የሚያቀርቡት:: እትዬ የሺም ድንጋይ ተሸክመው ነበር ለወይዘሪት አበራሽ እናት ጥያቄያቸውን እንዲቀበሏቸው የተማፀኗቸው:: በቅድሚያ እሺ ካስባሏቸው በኋላ ወይዘሪት አበራሽ ሥራ አግኝተው ወደ ደዴሳ ማሰልጠኛ እንደሚሄዱ ሲነግሯቸው ግን በጣም ነበር የጮሁት:: ‹‹ አንዲት ልጅ ብትኖረኝ ልጄን ሸጠው ጠበቁኝ›› እያሉ ነበር እያለቀሱ ሲጮኹ የነበረው:: መረጋጋት አቃታቸው:: በሁኔታቸው የተደናገጡት እትዬ የሺ ያሳምናቸዋል ያሉትን ሁሉ ሃሳብ በማቅረብ እንዲረጋጉ ጠየቋቸው:: እንዲያምኗቸውም ሌሎች ለመሄድ የተዘጋጁ የአካባቢው ልጆች መኖራቸውንም ነገሯቸው:: የወይዘሪት አበራሽ እናት ‹‹አፈሳ ካልሆነ በስተቀር እንዴት የአንድ አካባቢ ልጆች ሊሄዱ ይችላሉ›› በማለት ነገሩን አምኖ ለመቀበል ከበዳቸው:: እትዬ የሺ ከብዙ ድካም በኋላ አሳምነዋቸው እንዲቀበሉ አደረጓቸው:: ከተረጋጉ በኋላም ያስፈልጋቸዋል ያሉትን ሁሉ አዘጋጅተው ልጃቸውን መርቀው ሸኟቸው::
የመጀመሪያው የሥራ ቅጥር በአርጆ ደዴሣ
ወደአርጆ ደዴሣ የጉዞ መነሻው ከአዲስ አበባ ከተማ ገነት ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነበር:: ተጓዦች በሰአታቸው ነገኝተዋል:: ወይዘሪት አበራሽ እንደነገሩኝ፤ ከተጓዦች መካከል በእድሜ ትንሿ እርሳቸው ነበሩ:: የተቀሩት እናታቸው የሚሆኑ ሴቶች ናቸው:: ለምን ሥራ እንደተቀጠሩ ሲጠይቋቸውም ቡኮ ቤት፣ እንጀራ ቤት፣ ወጥቤት፣ ረዳት ብለው ስለሚሰሩት ሥራ ነገሯቸው:: ተላላኪ የሚል የሥራ መድብ ያላቸው እርሳቸው ብቻ እንደሆኑ አረጋገጡ::
እናታቸው ሲሸኟቸው አደራ የሰጧቸው ለነዚህ ሴቶች በመሆኑ፤ የአደራ ልጄ የሚለው ስያሜ በጉዞ ላይ እያሉ ነበር የተጀመረው:: ሥራቸው ቦታ ሲደርሱ ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሰራ ማደሪያ ቤት ((ካምፕ) ውስጥ ነበር የገቡት:: መኝታውም ምግቡም ከድርጅቱ በመሆኑ ለግላቸው የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት ካልሆነ በቀር ወጪ የለባቸውም:: ሥራውንም አካባቢውንም በጊዜ ሂደት ለመዱት:: ሥራውንም እየወደዱት መጡ:: በተለይ ደግሞ ለእናታቸው ቡና፣ ከሰል፣ ማር፣ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እየገዙ መላክ መቻላቸው በጣም ነበር ያስደሰታቸው:: ካለእድሜያቸው ትምህርታቸውን ትተው ሥራ ለመቀጠር የፈለጉት እናታቸውን ከችግር ለማውጣት በመሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጉ ነበር ::
ወይዘሪት አበራሽ የሰውነት ለውጥ ማምጣታቸው፣ በተቋሙም ውስጥ በእድሜ ልጅ መሆናቸው እይታ ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው:: ልጅነታቸውን ለመጠቀም ጥረት የሚያደርጉ ወንዶችም እየበዙ መምጣታቸው ግራ እንዲገባቸው እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ:: እርሳቸው እንደሚሉት በቀላሉ እንዳይታለሉም ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር:: አንድ ቀን ግን ማለፍ የማይችሉት ሁኔታ ተፈጠረ:: የአንዲት ሰራተኛ ሽኝት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ነው ነገሩ የሆነው::
ያልፈቀዱት ሰው ባላሰቡት ሁኔታ አስገድዶ መድፈር ፈፀመባቸው:: እርግዝናም ተከሰተ የሆነው ነገር ከእርሳቸው ዓላማ ጋር የሚሄድ ሆኖ ስላላገኙት እና ድርጊቱንም የፈፀመውን ሰው ማነጋገር ስላልፈለጉ የወሰኑት ከአካባቢው መራቅን ብቻ ነው:: ሥራቸውን ትተው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመመለስ ጽንሱን እንደማይፈልጉት ለሀኪም አማክረው ውርጃ አካሄዱ:: እናታቸው እንዳያዝኑባቸው በወቅቱ በሚስጢር ነበር ያደረጉት::
ከአርጆ ደዴሳ ወደ ጋምቤላ እና አፋር ሥራ የቀየሩበት አጋጣሚ
ወይዘሪት አበራሽ፤ በአርጆ ደዴሣ በነበራቸው የአራት ዓመት የሥራ ቆይታ የተለያዩ ነገሮችን ለማወቅ ችለዋል:: በእድሜም ከፍ ማለታቸው ለነገሮች ሁሉ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል:: እንደ አዲስ ሥራ ለመቀጠር ህንፃ ኮንስትራክስን ተመልሰው ሄዱ፤ ድርጅቱ ጋምቤላ ላይ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲያካሂድ ለባለሙያዎች ምግብ የሚያዘጋጁና የተለያዩ የቢሮ ሥራ የሚሰሩ ሰራተኞች ያስፈልጉት ስለነበር ነው ቅጥር የፈፀመው:: ወይዘሪት አበራሽም ወደ ጋምቤላ ሲሄዱ ረዳት የወጥቤት ሰራተኛ ሆነው ነበር:: በክርስትና እናታቸው ቤት ሲያድጉ ምግብ የሚያበስሉ የቤት ሰራተኞች ጋር ይውሉ ስለነበር በማየት ብዙ ነገሮችን በልጅነት አእምሮአቸው መያዝ ችለዋል:: ይህ ሁሉ ተሞክሮ ነው በቀላሉ የወጥቤት ሥራውን ለመሥራት ያስቻላቸው::
በጋምቤላ ረዳት የወጥ ቤት ሰራተኛ ሆነው የሰሩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር:: አቅማቸው ታይቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ዋና ወጥ ቤትነት ተዘዋወሩ:: ከፈረንሳይ፣ ከአሜሪካና ከተለያዩ ሀገራት ለሚመጡ እንግዶች የሚሆን ምግብ እንዲያዘጋጁ ሲታዘዙም የውጭዎቹ የሚመርጧቸው እንደ ፓስታፉሩኖ የመሳሰሉ ምግቦችን አዘጋጅተው ያቀርባሉ:: ‹‹በችሎታዬ ወጥቤቱን ተቆጣጠርኩት:: በሥሬም ሰራተኞች ስለነበሩ አሰራለሁ›› በማለት ነበር ችሎታቸውን የገለጹት::
በጋምቤላ በነበራቸው የሥራ ቆይታ ደስተኛ ነበሩ:: በእረፍት ጊዜያቸውም የሚሰራውን የአውሮፕላን ማረፊያ ሄደው በመጎበኘት ማስታወሻ ፎቶግራፍም ይነሱ እንደነበር ነው የሚናገሩት:: ጋምቤላ በነበራቸው ቆይታ የሚያስታውሱት ከገጠር ማር፣ ፍራፍሬ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ድካም ነበር:: ብዙ ይዘው መጥተው በርካሽ ነው የሚሸጡት:: ስለሚያሳዝኗቸውም ምግብ ይሰጧቸው ነበር::
በቋንቋ ባይግባቡም በሃሳብ ስለሚግባቡ ጥሩ ግንኙነት ፈጥረው ነበር:: አንዳንዶችም ማር በስጦታ ያበረክቱላቸው እንደነበር በማስታወስ የሰው ልጅ ለመቀራረብ፣ ለመዋደድ ቋንቋ፣ ዘር እንደማይገድበው ይህንን እንደ ማሳያ ያቀርባሉ:: ነቀምት ከተማ ለጋምቤላ ቅርብ በመሆኑ ለቤተሰብ ስልክ ለመደወል፣ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት፣ለገበያና ለመዝናናት ይሄዱ እንደነበርም ያስታውሳሉ::
አንድ ጊዜ በወባ ትንኝ ተነድፈው ታመው በአንቶኖቭ አውሮፕላን ወደ ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ተልከው ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ የተመለሱበትን ጊዜ ብቻ ነው በነበራቸው የሥራ ቆይታ የሚያስታውሱት:: የጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ሥራ ሲጠናቀቅ ነው የኮንትራት ሥራው ያበቃው::
ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመመለስ ዝግጅት ላይ እያሉ፤ እህል ውሃቸው ከጋምቤላ እንዲለቁ አላደረጋቸውም ድርጅታቸው እዛው ባሮአኮቦ ፕሮጀክት ስለነበረው የሚፈልገውን ሰራተኛ ሲመርጥ አንዷ ወይዘሪት አበራሽ ሆኑ:: ወይዘሪት አበራሽ ስለፕሮጀክት ሥራዎችም ጠንቅቀው ስለሚያውቁና ባለሙያዎችም እንደሚቀርቧቸው፣ ስለሥራቸውም ለማወቅ ጥረት ያደርጉ እንደነበርና ቀረቤታ መፍጠራቸውም እንደነርሱ የተማሩ ያህል እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸውም ያስታውሳሉ:: የባሮአኮቦ ፕሮጀክት ለመስኖ አገልግሎት የሚውል አቦቦ ላይ ግድብ ነበር የሚሰራው::
አንድ ቀን፤ ከአቦቦ ወደ ጋምቤላ ከተማ በመኪና በመጓዝ ላይ እያሉ፤ የመገልበጥ አደጋ ያጋጥማቸዋል በአጋጣሚ ጆሮአቸው አካባቢ ከደረሰባቸው መጠነኛ ጉዳት በስተቀር የከፋ ችግር አልነበረም:: እርሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ገጠመኝ ቀድሞ ከጋምቤላ ሌላ ቦታ ለመሄድ የነበራቸውን እቅድ አፋጠነው:: አፋር ክልል ዱብቲ መሥራት ነበር ፍላጎታቸው:: የፕሮጀክቱ ሥራ ከባሮ ፕሮጀክት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ቦታ ለመቀየር ቀላል ነበር የሆነላቸው:: ሥራቸው አሁንም ወጥቤት ነው:: የዱብቲው ፕሮጀክት ሥራ ደግሞ ተንዳሆ እርሻ ልማት ሥራ ነው:: የፕሮጀክት ሥራዎቹን የሚያሰራው በወቅቱ የውሃ ሀብት ልማት የሚባል ተቋም ነው::
የሥራ አካባቢ በረሀ መሆን፤
ወይዘሪት አበራሽ ረጅሙን እድሜያቸውን በሥራ ያሳለፉት በረሀ አካባቢ ነው:: ፈታኝ የሆኑ ነገሮችን ማሳለፋቸውን ነው የሚናገሩት :: እባብን ጨምሮ በስም የማያውቋቸው የተለያዩ ነፍሳት በመኖራቸው በነዚህ የመነከስና ለጉዳት የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው:: ሙቀቱም ኃይለኛ ነው:: በተለይም በቤት ውስጥ የሙቀት መከላከያ ማድረግ ካልተቻለ ከባድ ነው:: አንዳንዴ ሙቀቱ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጨምር ለጤና ችግር ይዳርጋል:: ውሃው እንኳን ለመጠጥ ለማዋል ለሰውነት መታጠቢያ ይፋጃል:: ምግብም አንዴ የተዘጋጀው ላንድ ጊዜ ነው መዋል ያለበት እንጂ ይበላሻል::
የማዕድን ሀብት ያዳኑበትና የተከሰከሰ አውሮፕላን ስባሪ ያገኙበት አጋጣሚ
አፋር ዱብቲ ውስጥ ሲሰሩ ነው በፕሮጀክቱ ውስጥ ከሚሰሩት አንዱ የሆነው የሩሲያ ዜጋ የሬሣ ሳጥን አስመስሎ በሰራው ሳጥን ውስጥ የወርቅ ማእድን ያከማቻል:: ወይዘሪት አበራሽ ስላልጠረጠሩ በሩሲያ ቋንቋ ምን እየሰራ እንደሆነ ጠይቀውት በዋዛ ነበር ያለፉት:: ነገሩ እንቅልፍ ነሳቸው:: ስለከነከናቸው ተመልሰው ሲያረጋግጡ የወርቅ ማዕድን ነው ሳጥኑ ውስጥ የከተተው::
ሰውየው ጭኖ ለመሄድ አዘጋጅቷል:: ቴሌ ሄደው በስልክ ለቦሌ አየር ማረፊያ መረጃ በመስጠት ሀብቱ እንዲድን ያደረጉበትን አጋጣሚ አይረሱም:: ሀብቱን በማስመለሳቸው ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉና ሌሎችም አትሌቶች በሩጫ ያገኙት ድል ያህል እንደተሰማቸው ይናገራሉ:: አካባቢው ላይ የወርቅና የነዳጅ ማዕድን ሀብት መኖሩንም እግረ መንገዳቸውን ነገሩኝ:: ኢትዮጵያ ያልተነካ ሀብት እንዳላት አጫወቱኝ::
በጋምቤላ ሲሰሩ ደግሞ በአደጋ አውሮፕላን ተከስክሶ ገደል ውስጥ ይገባል:: ያወቀ ሰው አልነበረም:: እርሳቸውና አንድ ሰው ሆነው ሲፈልጉ እርሳቸው ነበሩ ስባሪውን ቀድመው ያገኙት:: መረጃውን ከሰጡ በኋላ ግን በውስጡ ጀኔራሎች እንደነበሩና አስከሬናቸውም እንዳልተገኘ በባለሙያዎች ተረጋገጠ:: አደጋውም በአሞራ የደረሰ መሆኑ ነው የተገለጸው ይላሉ:: ስባሪው በተራ ሰው የተገኘ መሆኑ ሲነገር ወይዘሪት አበራሽ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ::
ከበረሀ የተመለሱበት አጋጣሚና አሁን የሚሰሩበት መሥሪያ ቤት
ወይዘሪት አበራሽ የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ነው ይሰሩ ከነበሩበት አፋር ዱብቲ የወጡት:: በወቅቱ ከፍተኛ መደናገጥ መረበሽም ስለነበር መውጣታቸውን እንጂ ምን መያዝ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም ነበር:: ወይዘሪት አበራሽ አሁን በቆላማና መስኖ ሚኒስቴር ውስጥ የመልእክት ሰራተኛ ሆነው ነው የሚያገለግሉት::
የቤተሰብ ሁኔታ
ወይዘሪት አበራሽ፤ ያለፈቃዳቸው፣ ስለማንነቱም በቅጡ የማያውቁት ሰው አስገድዶ ስለደፈራቸው:: የሥነልቦና ጫና እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለወንድ ጥሩ የሆነ አመለካከት የላቸውም:: እንዲቀርባቸውም አይፈልጉም:: በኃይለ ቃል ነው የሚያነጋግሩት:: ‹‹አውሬ ሆንኩ›› ሲሉም ለወንዶች ያደረባቸውን ጥላቻ ይገልጻሉ:: ድርጊቱ ከተፈፀመ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ እንኳን ለመርሳት አልቻሉም:: ይህ ደግሞ ትዳር ለመያዝ ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል:: በዚህ የተነሳም ትዳር አልመሰረቱም:: ከትዳር ውጪ የወለዷቸው ሁለት ልጆች አሏቸው::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም