ተስፋን ያዘለ ትከሻ …

ልጅነት ደጉ..

ደብረማርቆስ ጎዛምን አካባቢ ከምትገኝ አንዲት ቀበሌ ተወልዳ አድጋለች። ልጅነቷ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ነበር። ከእናት አባቷ ጉያ አልራቀችም። ወላጆቿ በስስት እያዩ እንደአቅማቸው ያሻትን ሁሉ ሞልተውላታል።

ትንሽዋ ትርንጎ ጫኔ ነፍስ ማወቅ ስትጀምር አካባቢዋን ልትርቅ ግድ ሆነ። ጎዛምን ለቃ ዓባይ በረሀን ስታቋርጥ ምክንያቷ የአዲስ አበባ ህይወት ነበር። በዚህ ከተማ አክስቷ ይኖራሉ። ከእናት አባቷ ስትለይ እሳቸው እንደ ልጅ ሊያሳድጓት ሊያስተምሯት ቃል ገብተዋል። ትርንጎ ይህን ካወቀች ጀምሮ በውስጧ ደስታ ሰፍኗል።ከዚህ በኋላ የአክስቷና የአዲስ አበባ ልጅ ትሆናለች።

አዲስ አበባ…

አዲስ አበባና ትርንጎ ከተላመዱ ሰነባብተዋል። ይህ ቦታ ለእሷ ካደገችበት ቀዬ በብዙ ይለያል። እንዲያም ሆኖ እንግድነት አልያዛትም። ልጅ መሆኗ ሁሉን ለምዳ ከብዙዎች እንድትቀርብ አግዟታል። አሁን ትርንጎ የአክስቷ ልጅ ሆናለች። በቤቱ ካሉት ልጆች ብቸኛዋ ሴት ናትና ከሌሎች ልቃ መወደዷ አልቀረም። ይህ እውነት በቀላሉ ሰፈር ቀዬዋን አስረሳት፣ እንደልጅ እየታዘዘች፣እያገለገለች ኑሮን ቀጠለች።

ትርንጎ ጫኔ ትምህርት ቤት ገብታ ቀለም መቁጠር ስትጀምር ጉብዝናዋ ከተማሪዎች ሁሉ የላቀ ሆነ። ከእኩዮቿ በላይ የምታመጣው ውጤት በመምህራኖቿ የሚያስወድድ፣ የሚያስመሰግናት ነበር። ሁሌም የአስተማሪዎቿ አድናቆት ብርታት ጉልበቷ ነው። ‹‹አይዞሽ ባሏት ቁጥር ስለነገዋ ታልማለች። ዶክተር የመሆን ፍላጎቷ፣ ያይላል። ወገኖቿን የመርዳት፣ህይወትን የመታደግ ሀሳቧ ይበረታል።

አሁን ትርንጎ በትምህርቷ ገፍታለች። ዛሬም ቢሆን አብሯት የኖረው ምኞት አልራቃትም። አስረኛ ክፍል ስትደርስ ግን ባሰበችው አልተጓዘችም።አቅጣጫዋ ተለወጠ። ፍላጎቷን በውስጧ እንደያዘች በአካውንቲንግ ተምራ ተመረቀች። እንዲያም ሆኖ ሀኪም የመሆን ህልሟ አልከሰመም። አንድ ቀን ካሰበችው ደርሳ የልቧን እንደምትሞላ ታውቃለች። ትርንጎ በህክምናው መስክ ተምራ ካሰበችው ባትደርስም ለትምህርት ያላት ፍቅርና ብርታት ከማንነቷ አልጠፋም።

አሁን ትርንጎ ልጅነቷ አልፎ ወጣትነቷ አብቧል። ይህ ዕድሜ የሚያምሩበት፣ የሚዋቡበት ነው። አጋጣሚው ደግሞ ብዙዎችን ከብዙዎች ዓይን ይጥላል ። በዚህ ጊዜ በርካቶች ሁኔታቸው ይለያል ።ባህሪያቸው ይለወጣል። አርቀው ያሰቡ ርቀው ይራመዳሉ። ዕድሜ ፈተና የሆናቸው ደግሞ ከመንገድ ይሰናከላሉ።ይህ እውነት የብዙ ወጣቶች የህይወት ገጠመኝ ነው።

ትርንጎ በአንድ አጋጣሚ የወጣትነት ዕድሜዋ ከፍቅር አጋሯ አጣመራት።፡ ወጣቱ አይቶ ገምቶ፣ወዷታል። እሷም ብትሆን ከልብ ወዳዋለች። ቆይታቸው ከፍቅር አልፎ ከቁምነገር ደርሷል። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ሁለቱም ትዳርን አሰቡ። አብሮ መኖርን ተመኙ። ይህ ይሆን ዘንድ የአሳደጊ አክስት ይሁንታ ግድ ይላል። ትርንጎ ወግና ደንቡን አልጣሰችም ። ፍቅረኛዋ ባህሉን ጠብቆ ፣ በሽማግሌ አስጠይቆ እንዲያገባት ፈቅዳለች። የታሰበው አልቀረም። አሳደጊ አክስቷ፣ የሀገር ቤት ቤተሰቦቿ አውቀውና መርቀው በሠርግ ተዳረች። ትርንጎ ወጣትነቷ ሳይፈትናት ለቁምነገር መብቃቷ አስደሰታት ።

ሶስት ጉልቻ…

አሁን ልጅነት ይሉት የለም። የልብ ሀሳብ ለጎጆ ያደላል። የራስ ዕቅድ ለትዳር ይከፈላል።እንዲያም ሆኖ ትርንጎ ዓላማዋን አልሳተችም፣ ትምህርቷን በወጉ ቀጠለች፤ በአቅሟ እየሰራች ቤት ጓዳዋን መደጎም ያዘች። አሁንም አብሯት ያደገው ዶክተር የመሆን ምኞት ከውስጧ እንዲጠፋ አትሻም።

ባለቤቷ ፖሊስ ነው። ሙያው ከብዙዎች ያውለዋል። ከድካሙ የሚያርፈው ፣ ቤቱ ደርሶ ሚስቱን ሲያገኝ ነው። ትርንጎ በኑሮዋ ደስተኛ ነች።እየሰራች ትማራለችና ስለምንም አታስብም። ቶሎ ላለመውለድ በክንድ የሚቀበረውን የእርግዝና መከላከያ ትጠቀማለች። እንዲህ ማድረጓ ለትምህርት በማሰቧ፣ ለነገ ዓላማዋ በማቀዷ ነው።

ይህ እውነት ግን በብዙዎች አልተደገፈም።ትርንጎ ቶሎ ወልዳ ልጅ መሳም የፈለጉ ቤተሰቦቿ በጨቅጭቅ አላኖሯትም። ነጋ ጠባ ስለምን ብለው ሞገቷት።ለነፍስ አባት ነግረው አስወቀሷት። ትርንጎ በምትሰማው ሁሉ ተሳቀቀች።አሁን ለእሷ ሳይሆን ለእነሱ ፍላጎት ማደር ሊኖርባት ነው። በጉዳዩ ደጋግማ አሰበች።በክንዷ የተቀበረውን የእርግዝና መከላከያ ስታስወጣ በይሁንታ ለማርገዝ፣ ወስና ነበር።

እንዲህ ከሆነ ጊዚያት በኋላ ወዳጅ ዘመድ ሆዷን ማየት፣ እርምጃዋን መቁጠር ያዘ። አብዛኞች እንዳሰቡት አልሆነም። ያለምንም ለውጥ ወራት ተቆጠሩ። አለማርገዟን ያወቁ አንዳንዶች አሁንም በጥያቄ አዋከቧት። መልሱ ከእሷ ሳይሆን ከጊዜው ላይ ነበር። ጋብቻቸው አንድ ዓመት ደፍኖ ሶስት ወራት እንደተቆጠሩ ትርንጎ ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች።

ይህ የምስራች ከእሷ አልፎ ለቤተሰቡ ደስታን አቀበለ። እርግዝናው እንደጀመረ ግን የትርንጎ ጤና መቃወስ ጀመረ። ሁኔታው የተለመደ ቢመስልም ለእሷ መቋቋም ተሳናት። በቀን ከአንዴ በላይ ሆስፒታል መመላለስ ልምዷ ሆነ።እንዳሻት ምግብ አለመውሰዷ አቅሟን ፈተነው። ስራና ትምህርቷን ትታ ከቤት ዋለች። ትርንጎ በየጊዜው ደሟን እየተለካች አልትራሳውንድ ትነሳለች። ሽንቷ እየተመረመረ፣ የልብ ምቷ ይታያል። ከህክምናው የቀረባት ምርመራ የለም። እንዲያም ሆኖ ጤና አይሰማትም። ሁኔታው እየከበደ ሲሄድ ገጠር ወላጆቿ ዘንድ ልትሄድ ወሰነች።

ወደ ሀገር ቤት

አሁን ትርንጎ አዲስ አበባን ርቃ ትውልድ ቀዬዋ ገብታለች። የጀመረችውን የህክምና ክትትል ብትቀጥልም ጤና አላገኘችም። አዲስ አበባ ሳለች የታዘዘላትን መድኃኒት አቋርጣለች።ይህ የሆነው በአንዲት ሴት ምክር ነበር።ሴትየዋ በእጇ ያለውን እንክብል እያስተዋለች ሁለተኛ እንዳትወስደው ነግራታለች።

ትርንጎ በወቅቱ ለምን ማለቷ አልቀረም።ነጋሪዋ መድኃኒቱን የምትውጥ ከሆነ በልጇ ጭንቅላት ላይ ችግር እንደሚያስከትል እርግጠኛ ሆና አሳስባታለች። ይህን አምና የተቀበለችው ትርንጎ የሴትየዋን ቃል አክብራ የተሰጣትን መድኃኒት አርቃ ጥላለች። ቀድሞ የነበሯት ተጨማሪ ምርመራዎች እንደ ጅማሬያቸው አልቀጠሉም። አሁን ደግሞ መገኛዋ ‹‹ጎዛም›› ገጠሩ ላይ ሆኗል። ባመማት ቁጥር ጤና ጣቢያ እየሄደች ትታያለች። የእግሯ ማበጥ ፣ የውስጧ አለመመቸት የእርግዝናው የተለመደ ባህሪ መሆኑ ተነግሯታል።

ከቀናት በአንዱ ትርንጎ ድንገቴ ምጥ አጣደፋት። ፈጥኖ ከሀኪም ለመድረስ ጊዜ አልነበረም።እናቶች ተሰባስበው የ‹‹ማርያምን›› ስም እየጠሩ ሊያዋልዷት በር ዘጉ። ጥቂት ጊዜ ከቆየው ምጥ ለመገላገል ብዙ አልቆየችም። በአንድ ሰአት ውስጥ ሴት ልጅ ወልዳ ታቀፈች።

እንዲህ ከሆነ አፍታ በኋላ እንግዴው ልጅ ቦታውን እንዲለቅ ተጠበቀ። በታሰበው ጊዜ መውጣት አልቻለም። ትርንጎ አብዝታ ተጨነቀች፣ ስቃይዋ በረታ። ራሷንም ሳተች። ሁኔታው ያስደነገጣቸው አዋላጆች ሕፃኗን ከቤት ትተው እናትን ጤና ጣቢያ ለማድረሰ ተጣደፉ። ሀኪሞች እጅ ስትደርሰ ባለሙያዎቹ ህይወቷን ለማትረፍ ተሯሯጡ።ለመሞት ጥቂት የቀራት ወላድ እንደምንም ትንፋሽዋ ተመለሰ።

ቤተሰቦቿ የልጃቸውን ህይወት መትረፍ እንዳወቁ ጨቅላዋን ከነበረችበት አንስተው ወደ እናቷ ዕቅፍ አመጧት። ልጅቷ እንደተወለደ ህጻን የእናቷን ጡት አልፈለገችም።ያለ አንዳች እንቅስቃሴ በዝምታ ቆየች።ሁኔታዋን ያስተዋሉ ሀኪሞች ለተሻለ ህክምና በአምቡላንስ ወደ ደብረማርቆስ ሆስፒታል ላኳት።

ህጻኗ ማሞቂያ ክፍል ገብታ ቀናትን ቆጠረች። በጭንቀት ከልጇ ጎን የከረመችው እናት ጥቂት ጠብቃ ትልቅ ተስፋ አገኘች። የህጻኗ ጤና ተመልሶ መንቃቷ ሲታወቅ ልጇን ከነርሶቹ እጅ ተረከበች። እፎታ ተሰማትና ጡቷን አውጥታ ሰጠቻት። ጨቅላዋ እንደፊቱ አልሆነችም። ትንሽዬ አፏን ከፍታ ከወተቱ ማገች ። እናት ደስ አላት። ፊቷ በስስ ፈገግታ ተሸፈነ።

የእናት ዓይኖች…

ትርንጎ ብዙ ዋጋ የከፈለችባትን ልጇን እያጠባች አስተውላ አየቻት።ህጻኗ ክብደቷ ቀለለባት።ቅጥነቷ ከሌሎች ልጆች ተለይቶ ታያት።መላ ሰውነቷ እንደ ወረቀት የነጣ፣የገረጣ መሆኑን አወቀች።እናት ዝም እንዳለች ብዙ አሰበች።ለጊዜው እንዴት ለምን የሚሉት ጥያቄዎች አልተመለሱላትም።ከወለደች በኋላ ድካሟ ቀጥሏል፣ራሷን ስለሚያዞራት ብዙ አትራመድም። በወጉ ያልበረታው ጎኗ ህመም እያስተናገደ ነው።እንዲያም ሆኖ ስለ ልጇ ብዙ እያሰበች ትተክዛለች።

አሁን ትርንጎ ከወለደች ሁለተኛ ወሯ ነው። ከትናንቱ ዛሬ የተሻለ ቢሆንም ከአልጋ አልተነሳችም። ልጇን ታቅፋ ተኝታ ትውላለች። አንድ ቀን እናት እንደ ሁልጊዜው ህጻኗን አተኩራ አስተዋለቻት። ክፉኛ ስትደነግጥ አፍታ አልቆየችም ።ልጅቷ በሚገርም ፍጥነት ጭንቅላቷ እያደገ ፣ከፍታው እየጨመረ ነው።

የህፃኗን ጭንቅላት ደግማ ደጋግማ ዳሰሰችው። ከእኩዮቿ በተለየ ‹‹ትምቡክ›› የሚልና ለመንካት የሚያስፈራ ነው። ብትደነግጥም ዝም አላለችም።ለቤተሰቦቿ ፈጥና አሳየቻቸው። ሁሉም ጭቅላትዋን እያዩ ሀሳባቸውን ሰጡ። አጋጣሚው ከዘር ሊሆን እንደሚችል የገመቱ በረከቱ። ሁኔታው ግን በዚህ አልቆመም። ከምልክቱ በኋላ ህጻኗን ወደ ላይ ወደታች የሚላት ህመም ተባባሰ።ቤተሰቦቿ ከእናቲቱ ጋር ይዘዋት ጤና ጣቢያ ደረሱ።በወቅቱ ያገኟት ሀኪሞች ሁኔታው የተለመደ መሆኑን ነግረው መለሷት።

ትርንጎ የልጇን ክርስትና አጠናቃ የአራስነት ወጉን ጨርሳ ወደአዲስ አበባ ተመለሰች።ወደ ጎጇዋ ስትገባ ደስታዋ እንደ እናት ሙሉ አልሆነም፡፤በልጇ ላይ ያስተዋለችው ምልክት እረፍት እየነሳ አስጨነቃት። ለመጀመሪያው ክትባት ጤና ጣቢያ ስትሄድ በህጻኗ ጭንቅላት በጉልህ የሚታይ ደምስር ዓይን ይስብ ነበር።

በሀኪሞች እጅ የገባችው ህጻን አልጋ ይዛ ለመታከም አልዘገየችም።ለእናት ትርንጎ ያየችው ምልክት ህመም ስለመሆኑ የምታውቀው አልነበረም። ውሎ አድሮ ሙሉ መረጃው ተነገራት። የልጇ ህመም ‹‹የነርቭ ዘንግ ክፍተት›› ወይም ‹‹ሀይድሮሴፋለስ›› የተባለ የጭንቅላት ውስጥ ውሃ መቋጠር ስለመሆኑ አወቀች።

ህክምናው…

ለከፍተኛ ህክምና ወደተለያዩ ሆስፒታሎች የተላከችው ህጻን አልጋ በያዘችበት አጋጣሚ የእሷን መሰል ችግር ያለባቸው ልጆች ጋር ልትሆን ግድ አለ።ይሄኔ ትርንጎ የልጇን ህመም ጠንቅቃ ለማወቅ አጋጣሚውን አገኘች። ህጻን ኤልዳና የመጀመሪያው የጭንቅላት ቀዶ ህክምና ሲደረግላት ገና የሶስት ወር ጨቅላ ነበረች።

እናት ትርንጎ ህጻኗን ለሀኪሞች አሳልፋ ስትሰጥ ከፈጣሪዋ ተማጽኖ ጋር ነበር። ልጇ ያገኘቻት በምክንያት መሆኑን ታውቃለች። ‹‹ትረፊ›› ካላት ከሀኪሟ እንዲያገናኛት ፣ መልሶም በዕቅፏ እንዲያውላት በመሪር ዕንባና ሀዘን እየተማለደች ነው። አራት ሰአታት የፈጀው የቀዶ ህክምና ሲጠናቀቅ ካልነቃችው ልጇ ጀርባ ታላቅ ተስፋን ጠበቀች።

ማግስቱን ኤልዳና በሚጠበቀው ለውጥ ላይ ተገኘች።ንቃቷና የዓይኗ ጥራት መልካም የሚባል ሆነ። ይህ እውነት በብቸኝነት ተኮራምታ ለምታስታምመው እናት ብሩህ ተስፋን አቀበለ። ትርንጎ ልጇ ከሆስፒታል ከወጣች በኋላ ስለህመሙ የሚያስረዳትን የፅሁፍ መረጃ ማንበብ ልምዷ ሆነ። አጋጣሚው በዚህ ህይወት ውስጥ ያሉ ልጆች ተጓዳኝ አካላዊ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል አሳወቃት። እናት ይህን እያሰበች የልጇን ለውጥ ጠበቀች። ኤልዳና እንደእኩዮቿ አይደለችም። ግዜዋን ጠብቃ ለመዳህ፣‹‹ወፌ ቆመች›› ለመባል ተስፋ አይጣልባትም። ትርንጎ በልቧ ይህ እንዳይሆን ተመኘች።

ውሎ ሲያድር እናት በልጇ ቆሞ መሄድ ተስፋ ቆረጠች። የኤልዳና ችግር ጭንቅላቷ ብቻ አይደለም።ወገቧን ጨምሮ መላ አካሏ እንዳይንቀሳቀስ ተይዟል። የአንደኛ ዓመት ሻማዋን ስትለኩስ ህጻኗ ለመቆም ወንበር አልያዘችም፡ለመራመድ አልሞከረችም ።ከመሬት ሳትነሳ በሆዷ ለመሳብ እየታገለች ነው።

አመት አልፎ ሁለተኛው ሲተካ ኤልዳና ለውጥ አልታየባትም። የጭንቅላቷ ከፍታ እንዳለ ቢቆይም እግሮቿና ወገቧ አልተስማሙም። እናት ትርንጎ ሁሌም ቢሆን ልጇን ከሌሎች ጋር አታወዳድርም።ይህ እንዲሆን ታውቃለችና ራሷን በጽናት ታበረታለች።አንዳንዴ ልጇን ስታይ በሀሳብ ትርቃለች። ከአሁኑ የተሻለ ህክምና ፣እንደሚያሻት ይገባታል። መንቀሳቀሻ ዌልቸር እንደሚያስፈልጋት ታስባለች።የምኞቷን ለማሳካት አቅሙ የላትም ።እሷን አዝላና ታቅፋ ከመዋል የዘለለ ምርጫ አላገኘችም።እንደ እናት ልጇ በእግሯ ተራምዳላት እጇን ይዛት ብትሄድ ትወዳለች።

አሁን ኤልዳና ሶስት ዓመት ሆኗታል።በዚህ ዕድሜ ራሷን መቻል የምትጀምርበት ነው። ፍላጎቷን ማሳየት፣የወደደችውን መጠየቅ፣ የጠላችውን ማራቅ ይጠበቅባታል። በእሷ ህይወት ግን እነዚህ ጉዳዮች ሩቅ ናቸው። ሁሉም ጎዶሎዎች የሚሞሉት በእናቷ ትከሻና እጆች ብቻ ሆኗል።

ህጻን ኤልዳና እናቷ ከአጠገቧ እንድትርቅ አትፈልግም።አባቷን ስታይ ደግሞ ከልብ ደስ ይላታል። ልጅቷ በተፈጥሮዋ ንቁ የምትባል ነች።ዜማ እያወጣች ራሷን ታጫውታለች። ጥቂት ቃላቶችን ትሞክራለች። እናት አስባ ካላጎረሰቻት በቀር ራበኝ፣ጠማኝን አታወቅም። መሬት በተቀመጠች ጊዜ በልቧ ለመዳህ የምታሳየው ጥረት ል ብ ይነካል ።

ንፍሮ ሻጯ …

ትርንጎ ከልጇ ወዲያ ሌላ ጉዳይ የላትም። ዛሬ ተምሮ ዶክተር ስለመሆን፣የምታስብበት አይደለም።ወጣ ብላ ለመስራት የሚያስችል ዕድልና አጋጣሚ አልተቸራትም። ቀኑን ሙሉ ልጇን ስትንከባከብ ትውላለች። ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ግን ከቤት ወጣ ማለቷ አልቀረም። ይህ መሆኑ አእምሮዋን መልካም አድርጓል።

አሁን ትርንጎ በቀና ሰዎች እገዛ የባቄላ ንፍሮ እየሸጠች ነው።ከንፍሮው የሚገኘው ጥቂት ገቢ ቤት ጓዳዋን ይደጉማል። ቀድሞ ጨርቅ ሆኖ የምትቸገርበትን የዳይፐር ወጪ ይሸፍናል።ልጇን አዝላ ንፍሮ ስትሸጥ የሚያዩ በርካቶች ስለእሷ ልባቸው እንደተነካ ነው። ሁሌም ልጅነቷ ያሳዝናቸዋል።ልፋት ድካሟ ይሰማቸዋል።

አብዛኞቹ የተሻለ ስራ ሊያስገቧት ይጠይቋታል።እሷ ግን ይህን ታደርግ ዘንድ አይቻላትም።ልጇን ለሰራተኛ መስጠት ይከብዳታል።በህጻናት ማቆያ ለመስጠት ይፈትናታል።ትርንጎ አንዳንድ ሰዎች በጎ ያልሆነ እሳቤ እንዳላቸው አይጠፋትም። እሷን ግን አይዞሽ በርቺ የሚሏት ይበረክታሉ።በዚህ መልካምነት ደግሞ ሁሌም ትበረታለች።

ያልደበዘዘ ተስፋ

ትርንጎ ስለልጇ ጤና የአቅሟን ሁሉ ትሞክራለች።በዚህ ጥረቷ የወንድማማቾች በተሰኘ ድርጅት ኤልዳና ፊዚዮ ቴራፒ እንድታገኝ አድርጋለች።ይህ ሙከራ ለእናት ትርንጎ ታላቅ ተስፋ ሆኖ ነገን በመልካም እንድታስብ ምክንያት ሆኗል።

እሷ አንድ ቀን ልጇ ቆማ እንደምትሄድ ታስባለች።እንዲህ የሚሆነው ግን የመልካም ሰዎች እጅ ሲታከልበት፣ ነው።ትርንጎ የልጇን ቆሞ መሄድ ስታልም ዓይኖቿ በትኩስ እንባ ይሞላሉ፡ የውስጧ ጥንካሬ ይፈተናል፣ ይሄኔ የእኩያ ልጆች ሩጫና ደስታ ወለል ብሎ ይታያታል።ለእሷ ልጇን እያሰበች ስሜቱን መቋቋም፣ከባድ ነው። ያባራ በማይመስል እንባ ፊቷ ይታጠባል።

የዛኔ የታዘዘላትን መድኃኒት እንዳትወስድ የመከረቻት ሴት፣. ገጠር ስትሄድ ያቋረጠችው ህክምና ተዳምሮ ለዛሬው ችግር ምክንያት እንደሆነ ታስባለች።ዛሬ ሁሉም ቢያልፍም ለማያልፍ ጸጸት ዳርጓታል።

የትርንጎ ህልም ይፈታ ዘንድ የለጋስ እጆች በረከት፣የቀና ልቦች መልካምነት የግድ ይላል። ዛሬ የዚህች ሴት ትከሻ ልጅን ብቻ አላዘለም።የነገ ተስፋንም ደርቧል። በህመም ባለች ጨቅላ ታስራ ነገን በተስፋ ለምትጠብቅ ወጣት እናት ‹‹አይዞሽ ባይነት›› የነገውን ዓለም ከህልም ያሳልፋል፣ ከምኞትም ያሻግራል።

መልካምሥራአፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You