በዚህ ዓለም ዋጋ ሳንከፍል የምናገኘው ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር የራሱ የሆነ ዋጋ አለው። ልክ እንደምንፈልገው ነገር ማለት ነው። ታዲያ ዋጋው ምንድን ነው? ብዙ አይነት ነገር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በመጀመሪያ በማሰብም ሆነ በስሜት ደረጃ ያሰብነውን ነገር እንደምንሆን ማወቅ አለብን። በሌላ አባባል መድረስ የምንፈልግበትን ቦታ ማወቅና እዛ ቦታ ላይ መድረስ ከፈለግን በቅድሚያ ሃሳቦቻችንን ልንቆጣጠር ይገባል።
የዘራነውን ነው የምናጭደው። አእምሯችሁ ውስጥ የተቀመጡና ወደኋላ የሚጎትቷችሁን ነገሮች ቆራርጣችሁ አስወጧቸው። ምክንያቱም አእምሯችሁ የተፈጠረው እናንተን ወደላይ ከፍ ለማድረግና ያለምንም ገደብ እንድታስቡ ነው።
ነገር ግን እናንተ አእምሯችሁ ያለገደብ እንዳያስብ ገድባችሁታል። አእምሯችሁ ውስጥ ገብተው ሁሉንም ነገር የሚገድቡባችሁ ነገሮች ከየት ነው የመጡት? ካላችሁ ከራሳችሁ ነው እንጂ ከሌላ ከየትም አይደለም። ይህ ማለት እናንተ ፊት የተቀመጡ እድሎች በጣም ብዙና ከምታስቡትና ከምታምኑት በላይ ናቸው።
ከጠባብ አስተሳሰብና ከጭፍን ጥላቻም የራቁ ናቸው። በችግሮቻችሁ ላይ ቀና አመለካከትና አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ራሳችሁን ማስገደድ ወይም ምንም ያህል በችግር ብትከበቡ አዎንታዊ ነገሮችን እንድታስቡ ራሳችሁን ደፋር ማድረግ ይኖርባችኋል። ትላልቅና ልታሳኳቸው የምትፈልጓቸውን ግቦች ቁጭ ብላችሁ አንድ በአንድ መጻፍና የምትፈልጉትን ነገር በሚገባ ልታውቁ ይገባል።
አእምሯችሁ እስከጥግ ድረስ ሄዶ የፈለገውን ነገር እንዲያስብ ፍቀዱለት። ለአእምሯችሁ ነፃናት ልትሰጡት ይገባል። በሃሳባችሁም የትም ቦታ ልትደርሱ ትችላላችሁ። ያ ነው ነፃነት ማለት። ልታሳኳቸው ያሰባችኋቸውን ነገሮች ከሚከለክሏችሁ ነገሮች ዞር ትላላችሁ። እንዲህ አይነቱ ሃሳብ በአእምሯችሁ ከመጣባችሁ አእምሯችሁን ሃሳብ ውስጥ ታስገቡትና ሃሳቡን ከአእምሯችሁ ወዲያውኑ ማውጣት ትችላላችሁ። ማንኛውንም ነገር በሃሳብ ውስጥ ሆናችሁ ልታዩ ትችላላችሁ። ማሰብ ምስሉን መመለክት ማለት ነው።
ከምታገኙት ገቢ ላይ ቢያንስ 10 በመቶ ያህሉን መቆጠብ ይኖርባችኋል። የተሰማራችሁበት የሥራ መስክ ምንም ይሁን ምን እናንተ ካሰባችሁና ካመናችሁ ልታዩት ያልቻላችሁትን ትልቅ እድል ትመለከታላችሁ። ለማደግ ሁሌም ቦታና እድል አለ። ይህ ግን የሚሆነው ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ከሆናችሁ ብቻ ነው።
ምንም አይነት ጥሩ ሃሳብ ቢኖራችሁም ተግባር ከሌላችሁ ባዶ ነው። ህይወት ቀያሪ ናቸው ያላችኋቸው ሃሳቦች ዋጋ ቢስ ይሆናሉ። የሰው ልጅ ሁሉ ሁለት ነገር ሲባሉበት ይሰማል። አንደኛው በጣም አጥብቀን የምንፈልገውን ነገር እናውቃለን። ሁለተኛው ነገር ደግሞ አጥብቀን የምንፈራውን ነገር ይኖራል። ስለዚህ አንድ ትንሽዬ ወረቀት አውጡና ከምንም ነገር በላይ በጣም የሚያስፈልጋችሁን ነገር ፃፉ። የገንዘብ ችግር ላይ ከሆናችሁ ምናልባት ለእናንተ ቀዳሚው ነገር ገንዘብ ሊሆን ይችላል። ህይወታችሁንም ማሻሻል ከፈለጋችሁ ገቢያችሁን ማሳደግ አእምሯችሁ ይሆናል።
ምንም ችግር የለውም። ተጨማሪ ገቢ እፈልጋለሁ ትላላችሁ። ነገር ግን በቁጥር ይህን ያህል ነው የምፈልገው ብላችሁ ያችን ቁጥር ለይታችሁ ማወቅ አለባችሁ። መኖሪያ ቤት ከሆነ ፍላጎታችሁና ራሳችሁ የገዛችሁት ቤት ውስጥ መኖር ከሆነ ቤቱ ምን አይነት እንደሆነ በአእምሯችሁ ሳሉት፤ እወቁት። በስራ ቦታም ስኬትን እየፈለጋችሁ ሊሆን ይችላል። በህይወቴ እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ እያላችሁ ካሰባችሁ እሱም ይሳካል።
እንደማንኛውም ሰው ደስተኛና በፍቅር የተሞላ ቤተሰብ እፈልጋለሁ ካላችሁ ያም የእናንተ ፍላጎት ነውና እውን ይሆናል። ብቻ በህይወታችሁ ማሳካት የምትፈልጓቸው ነገሮች በዛች ትንሽዬ ወረቀት ላይ ያስፍሩ። የምትፈልጉትን ነገር በደንብ አድርጋችሁ እሳካወቃችሁ ድረስ ማንኛውንም ነገር የማሳካት እድላችሁ ከፍ እያለ ይሄዳል። ስለዚህ የምትፈልጉትን ነገር በደንብ አድርጋችሁ ለዩ፤ግለፁ።
ለጊዜው አንድ ግብ ነው የሚያስፈልጋችሁ። ምክንያቱም መጀመሪያ ይህ ግብ እንደሚሰራና እንደማይሰራ ትሞክሩታላችሁ። በመቀጠል ደግሞ የምትፈልጉትን ሌሎች ግቦች እየጨመራችሁ ትሄዳላችሁ። እምነታችሁ እየጠነከረ እንዲመጣ መጀመሪያ በቀላል ነገር ጀምሩ። ይህ ሲባል ግባችሁን ትቀንሳላችሁ ማለት አይደለም። ምንም ያህል ግባችሁ ትልቅ ቢሆን አንድ ቢሆን ግን ይመረጣል። የፃፋችሁትንም ግብ በወረቀት ላይ አስፍራችሁ በየቀኑ ብዙ ጊዜ እያነሳችሁ ታነቡታላችሁ።
በጠዋት ስትነሱም ስለፃፋችሁት ግብ ማሰብ በቂ ነው። የፃፋችሁትን ግብ ዘወትር ጠዋት ታነቡታላችሁ። በመቀጠል ደስ በሚል ስሜት ውስጥ ሆናችሁ ፃፋችሁት ነገሩን በደንብ ማብሰልሰል ትጀምራላችሁ። ይህ ለራሳችሁ አእምሮ ምልክት ነው። የምትሮጡበት ነገር አላችሁ ማለት ነው። በህይወት ደግሞ የሚያስፈልገን የምንሮጥለትና ልንቆምለት ሚገባ አላማ ያስፈልገናል። ያንን አላማ ካገኛችሁ ወዲያውኑ ከአልጋችሁ መነሳታችሁ አይቀርም። ምክንያቱም ስራችሁ ያ እንደሆነ ታውቃላችሁ። ልባችሁም ወደዛ ይሆናል።
በቀናችሁ ውስጥ ሰአት ካገኛችሁ አላማችሁን የፃፋችሁበትን ወረቀት አንስታችሁ አንብቡ። የፃፋችሁትን ግብ ባነበባችሁ ቁጥር የሰው ልጅ የሚያስበውን እንደሚሆን እወቁ። ይህ ህግ ነው። እናንተም ቁጭ ብላችሁ ግባችሁን ባነበባችሁ ቁጥር ትዝ የሚላችሁ ግባችሁ ነው። ግብችሁ ላይም እንደምትደርሱ ታውቁታላችሁ። ውስጣችሁም በደንብ ያምናል። እውነት ከተባለ በፃፋችሁት ሰአት ላይ እናንተ እዛ ቦታ ላይ ናችሁ።
አላያችሁትም እንጂ መሆን የምትፈልጉትን ሰው እሆናለው ብላችሁ የወሰናችሁ ሰአት ላይ ያንን ሰው ሆናችኋል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም ነገር እያበበና ፍሬ እያፈራ ይመጣል። ስለዚህ ግባችሁን ፃፉት። ከፃፋችሁት በኋላ ስለግባችሁ በደንብ አድርጋችሁ አስቡ። ዞር ዞር ብላችሁ ህይወታችሁን ተመልከቱ። ያንን ግብ እንዳሳካ ሰው ተውኑ።
ዛሬን እየኖራችሁ ትቀጥላላችሁ። አይናችሁ መትረፍረፍን እንጂ ሌላ ነገር እንዲመለከት አታድርጉ። ደስታን ከሆነ ደስታን ብቻ ልብ እንዲል አድርጉ። ልክ እንደማንኛውም ፍጡር እናንተም የምትልጉትን ነገር የማግኘት መብት አላችሁ። የእናንተ የመጀመሪያው ኃላፊነት መጠየቅ ነው። የምትፈልጉትን አውቃችሁ መጠየቅ።
በብዙ ሰዎች ዘንድ አስቸጋሪና ፈታኝ የሚሆነው አዲስ ልማድ መገንባት ነው። አዲስ ልማድ በቀላሉ ሊገነባ አይችልም። ብዙ ጊዜን ይጠይቃል። ነገር ግን እናንተ ያንን ልማድ አንዴ ከፈጠራችሁ በኋላ እድሜ ልካችሁን በዛ ልማድ ውስጥ ሆናችሁ ልትቀጥሉ ትችላላችሁ። ያ ልማድ ሊያሳርፍነም ይችላል፤ ሊያሰቃየንም ይችላላል። ስለዚህ መፍራት አቁሙ! ፈሪ መሆንም የለባችሁም። የሆነ ነገር ይከሰታል ብላችሁ ስትፈሩ ወይም አሉታዊ ሃሳብ በአእምሯችሁ ላይ ሲመላለስ ወዲያውኑ ነው የአእምሯችሁን ምስል ማስተካከል እንዳለባችሁ አእምሯችሁ እያስጠነቀቃችሁ ነው።
አወንታዊ ምስል በአእምሯችሁ ውስጥ እያመላለሳችሁ ራሳችሁን ማየት የምትፈልጉበት ቦታ ላይ ተመልከቱ። አይናችሁን ምን ጊዜም ቢሆን ከግባችሁ ላይ እንዳትነቅሉ። እዛ ቦታ ላይ እንደደረሳችሁ አድርጋችሁ አስቡ። ይህ ሲባል ግን መንገዳችሁ ሁሉ ይለሰልሳል ማለት አይደለም። የራሳችሁን መንገድ ትታችሁ ሁሉም ሰው በሚሄድበት የተለመደና ተራ በሚባል መንገድ መሄድ ትችላላችሁ። እንደዚህ አይነት ስሜቶችም ይመጡባችኋል። ተስፋ የመቁረጥ ወይም ሁሉንም ነገር እዚህ ጋር ርግፍ አድርጌ ልተው የሚል ሃሳብ ይመጣባችኋል። ይህ የተለመደ ነው። የሰው ልጅ ደግሞ ከአወንታዊ ይልቅ አሉታዊ ሃሳቦችን ማሰብ በጣም ይቀሉታል። ወይም በአሉታዊ ሃሳቦች የመሳብ እድሉ ከፍ ያለ ነው።
በዓለማችን በጣም ስኬታማ የሚባሉ ሰዎች 5 በመቶውን የዓለም ህዝብ ይሆናሉ። ሌላው ቀሪው 95 በመቶ የዓለም “ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ተራ ወይም ደግሞ መካከለኛ ነው። ለዚህም ነው ራሳችሁን አወንታዊ ነገር ላይ እንድታስቡ ማስገደድ ያለባችሁ። ራሳችሁን እነዛ 5 በመቶ የሚሆኑ ስኬታማ ሰዎች ውስጥ ማግኘት አለባቸው። ይህን ለሰላሳ ቀን ሞክሯቸው። አእምሯችሁን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩት። እናንተ በምትፈልጉት ነገር ላይ ብቻ አእምሯችሁን እንዲያተኩርና ከቁጥጥራችሁ ውጪ እንዳይሆን አድርጉት።
ማድረግ ከሚጠበቅባችሁ በላይ በደንብ አድርጋችሁ ልትሰሩ ይገባል። ለሰላሳ ቀናት ከአቅማችሁ በላይ እንድተሰሩና እንድትለፉ ይጠበቃል። ይህን ስታደርጉ ግን አንድ ነገር መርሳት የለባችሁም። ቀና አመለካከት ሊኖራችሁ ይገባል። አእምሯችሁ ሁሌም አወንታዊ አመለካከት ሊኖረው ያስፈልጋል። እያማረራችሁና መስራት የማትፈልጉትን ስራ እየሰራችሁ መቀጠል አትችሉም።
እስከዛሬ አድርጋችሁ በማታውቁት ደረጃ በደንብ አድርጋችሁ ስሩ። ይህን ስታደርጉ ግን አንድ ነገር ልብ በሉ። ይኸውም የምታደርጉት ነገር እንዳለ ፍሬ እያፈራ መምጣቱ አይቀርም። ምክንያቱም በዚች ዓለም ላይ የልፋታችሁን ያህን እያገኛችሁ ትመጣላችሁ። ህግ ነው!
አንድ ግብ ስታችሁ እዚህ ነገር ላይ ጠንክሬ እሰራለሁ፣ እዚህ ነገር ላይ እለፋለሁ ብላችሁ ከወሰናችሁ እሆናለሁ ብላችሁ ያሰባችሁትን ሰው ሆናችኋል። ምክንያቱም የሚሄዱበትን ቦታ የማያውቁ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። ከነዚህ ሰዎች የተለያችሁ የምትሆኑበት ግባችሁን ማውጣታችሁና ወደዛ እየሄዳችሁ እንደሆነ መገንዘባችሁ ነው።
አሁን በዚህ መንገድ ላይ እያላችሁ የሆነ አንድ ወጥመድ ውስጥ ራሳችሁን ልትከቱ ትችላላችሁ። እሱም እንዴት ነው የማሳካው የሚለው ጥያቄ ነው። ትኩረታችሁን ሙሉ በሙሉ በዚህ ጥያቄ ላይ ማንሳት አለባችሁ። ምክንያቱም የእናንተ አስተዋፅኦ እዛ ጋር አይደለም። እንዴት የሚለውን የሚያመቻችላችሁ በየእምነታችሁ የምታምኑት ፈጣሪያችሁ ነው። ያን ለእርሱ ተውለት። ከእናንተ የሚጠበቀው ነገር ቢኖር የት መሄድ እንደምትፈልጉ ማወቃችሁ ነው። መንገዱን ፈጣሪያችሁ ያሳያችኋል።
በዚህ ዓለም ላይ የሚያስፈልገው አላማና እምነት ነው። ከዚያ የምትፈልጉትን ነገር ታገኛላችሁ። ነገር ግን ቢያንስ ለሰላሳ ቀናት በደንብ ስሩ። እስከዛሬ ሰርታችሁ በማታውቁት ደረጃ ምንም ነገር በምላሹ አገኛለሁ ብላችሁ ሳትጠብቁ የቻላችሁትን ያህል በደንብ አድርጋችሁ ልፉ። ምን አይነት የሚገርም ህይወት መኖር እንደምትጀምሩ ልብ እያላችሁ ትመጣላችሁ። ለሰላሳ ቀን ፅኑ መሆን አይከብዳችሁም።
ላላመናችሁበትና እምነታችሁን ላልጣላችሁበት ነገር በፍፁም ፅኑ ልትሆኑ አትችሉም። ስለዚህ ለአላማችሁ ፅናትና እምነት ሊኖራችሁ ይገባል።
በዚች ሰላሳ ቀናት ውስጥ ልትወድቁ ትችላላችሁ። የድሮ አመላችሁ ተነስቶ ቀደምት ልማዳችሁን ልተገብሩ ትችላላችሁ። ያኔ ቀናችሁን እንደገና ወደኋላ መልሳችሁ አንድ ብላችሁ መጀመር አለባችሁ። ይህን የምናደርገው ልማድ ለመፍጠር ነው። ምንም አይነት ልማድ ካላችሁ ደግሞ አዲስ የሆነ ልምድ ! የምንፈልገውን አዲሱን ልማድ የራሳችን ማድረግ ከፈለግን እዛ ነገር ላይ ፅኑና ወጥ ልንሆን ይገባል። ሁለቱን ነገሮች አንድ ላይ ካመጣን እምነትም አለን ማለት ነው። ልክ እንደተግባሮቻችሁ ሁሉ ፅፋችሁ የያዛችሁትን ግብ እንዳትረሱ።
ይህን ሁሉ እያደረጋችሁ ትርፍ ሰአት ሊኖራችሁ ይችላል። ባላችሁ ትርፍ ሰአት ለግባችሁ ገንቢ የሆኑ መጽሐፍቶችን አንብቡ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ጭንቀትን አስወግዳችሁ ራሳችሁን ዘና ለማድረግ ሞክሩ። ፍራቻን አስወግዱ። በትናንሽ ነገር ዘና በሉ። በእምነት እንጂ በፍርሃት አትኑሩ!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም