በኬንያ በደረሰ የሄሊኮፕተር አደጋ የአገሪቱ ኤታማዦር ሹም እና ሌሎች መኮንኖች ሞቱ

የኬንያ ጦር አዛዥ ጄኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላ በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ይበሩበት የነበረው ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ሕይወታቸው ማለፉን ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አስታወቁ። ኦጎላ ከሌሎች 11 ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ሆነው በሄሊኮፕተሩ ሲጓዙ ነው አደጋው የደረሰው። ከአደጋው የተረፉት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሐሙስ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አደጋው ለሀገሪቱ “ትልቅ ኀዘን” ነው ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ ቀደም ብለው የሀገሪቱ የፀጥታ ምክር ቤት አባላቶቻቸውን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ነበር። አደጋው የደረሰው ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡20 ላይ መሆኑን ሩቶ ተናግረዋል። የኬንያ አየር ኃይል የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት የምርመራ ቡድን አሰማርቷል።

ሄሊኮፕተሯ ከተነሳች ከደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰችው ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ በስተሰሜን  ምዕራብ አቅጣጫ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኤልጌዮ ማራክዌት መሆኑን ፕሬዚዳንት ሩቶ ተናግረዋል። የአየር ኃይል አዛዥ እና የመከላከያ ሠራዊት ምክትል አዛዥ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ጀነራል ኦጎላ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር የጦር አዛዥ ሆነው የተሾሙት።

ሩቶ ዋና የጦር አማካሪያቸውን በግዳጅ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል። “እናት ሀገራችን ከጄኔራሎቿ መካከል አንዱ የሆነውን ጀግናዋን አጥታለች” ሲሉ ዊሊያም ሩቶ ለሀገራቸው ሕዝብ ተናግረዋል። በኬንያ ከትናንት ዓርብ ጀምሮ ሦስት የብሔራዊ ሐዘን ቀናት የታወጀ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ይደረጋል።

ጄኔራል ኦጎላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኬንያ መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉት ሚያዝያ 1976 (እአአ) እንደነበር የኬንያ መከላከያ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ዘግቧል። ሥራቸውን የጀመሩት በሀገሪቱ አየር ኃይል ውስጥ ሲሆን፣ ከአሜሪካ  አየር ኃይል ጋር በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት ሠልጥነዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት “አሳዛኙን የሄሊኮፕተር አደጋ ተከትሎ ለኬንያ ፕሬዚዳንት፣ መንግሥት እና ሕዝብ” ኀዘናቸውን ገልጸዋል።

ከአደጋው የተረፉት ሁለት ግለሰቦች በአስጊ ሁኔታ ላይ መሆናቸው እና ሕክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ተገልጿል። የጦር መኮንኖቹ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስበትን ሰሜን ኬንያን ጎብኝተው ሲመለሱ ነው አደጋው የደረሰባቸው። በሽፍቶች ጥቃቶችን ምክንያት የተዘጉ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችን ለማስክፈት ተልዕኮ ላይ ነበሩም ተብሏል። አካባቢውን ለማረጋጋት የተሰማሩ የጦር መኮንኖችንም መጎብኘታቸው ተገልጿል።

እአአ ሰኔ 2021 በዋና ከተማዋ ናይሮቢ አቅራቢያ ሊያርፍ የነበረ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ቢያንስ 10 ወታደሮች መሞታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You