‹‹ከኢትዮጵያ ምድር የሚመነጨውን ውሃ በፍትሐዊነት የመጠቀም መብት አለን››  ያሲን መሐመድ(ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኤዢያ ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር እና ተመራማሪ

ውሃ ለሰው ልጅ መሠረታዊ ከሚባሉ ፍላጎቶች መካከል ቀዳሚው ነው። በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ ውሃ የእስትንፋስ መቀጠያ ትልቅ የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ከውሃ ጋር ያልተቆራኘ አንዳችም ነገር ለማግኘት እጅጉን ያዳግታል። የእዚህን የተፈጥሮ ስጦታ ጥቅም ከሰው ልጆች ህልውና ጋር ብቻ እናስተሳስረው ብንል እንኳን፤ እጅግ ብዙ መሠረታዊ ጥቅሞችን ማግኘት እንችላለን። ውሃን ቀለል አድርገን ስንገልጸው ምግብ ንፅህና፣ መጓጓዣ እና ሌሎችም ዝርዝር ጥቅሞችን ይሰጠናል።

እነዚህን መሠረታዊ ጥቅሞች ለመገንዘብ ብዙ መመራመር አሊያም መምጠቅ አይጠይቅም። ሰው ሆኖ ብቻ መፈጠር በቂ ነው። ይሁን እንጂ ውሃ ከዚህም የዘለለ አያሌ አዎንታዊ ጎኖችን የያዘ ነው። ይህንን በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን ሰፋ አድርገን በሀገር ደረጃ ለመመልከት ባህር፣ ውቂያኖስና ወንዞች የሚኖራቸውን ጥቅም ማየት ይቻላል። ይህንኑ መሠረት በማድረግም ውሃ ከአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ፖለቲካዊ ጥቅም አንፃር የሚኖረውን ፋይዳ፣ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለማውራት ወድደናል። በተለይ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ የውሃ ሀብት፣ በባህር በር ጉዳይ ሊኖራት ስለሚገባው ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ መብቶች ከጋበዝናቸው እንግዳ ጋር በስፋት ስንጨዋወት ቆይተናል። ከዚያ አስቀድመን ግን ለርእሰ ጉዳያችን ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ የባህር በር ለአንድ ሀገር ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ የተሠሩ የጥናት ውጤቶች ምን ይላሉ የሚለውን በጥቂቱ ለመዳሰስ እንሞክር።

የባህር ወደቦች መዳረሻ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ዘኮንቨርሴሽን ዶትኮም የተባለ ድህረ ገፅ ጥናታዊ ጽሑፍ ውጤቶችን መሠረት አድርጎ መረጃ አውጥቷል። የመጀመሪያው ሚና የኢኮኖሚ ዕድገት እና ንግድና የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሲሆን፤ የባህር ወደቦች ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥን በማመቻቸት፣ ሀገሮች ወደ ውጭ በመላክና ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው ይጠቅሳል።

ሌላኛው ጥቅም ከፍተኛ ወጪን መቀነስ ሲሆን፤ ይህም የባህር ወደብ ባለቤት መሆን ቀልጣፋ ከውጭ ለሚገቡ እቃዎች፣ የፍጆታ ምርቶች እና ጥሬ ዕቃዎች የመጓጓዣ ወጪን እንደሚቀንስ ይገልፃል።

ይሄው ድህረ ገፅ እንደሚያብራራው፤ ሌላኛው ጠቀሜታቸው ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ነው። የባህር ወደቦችን ማግኘት (ባለቤት መሆን) የአንድ ሀገርን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ ያስረዳል። በተጨማሪነትም ከፖለቲካ አንፃር ስልታዊ ተጽዕኖ እና ነፃነት እንዲኖር ጉልህ የሚባል አስተዋጽኦ እንዳለው ያስረዳል። በዋናነትም የባህር ዳርቻ ተደራሽነት ለሀገር የበለጠ ፖለቲካዊ ተጽእኖን ይሰጣል፣ ይህም በክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ፍላጎቱን ለማስጠበቅ ያስችላል።

እነዚሁ ጥናቶች እንዳረጋገጡት የባህር በር ባለቤት መሆን የጂኦስትራቴጂክ አማራጮችን ያጎናፅፋል። የባህር ወደቦች የአንድን ሀገር የጂኦስትራቴጂክ አማራጮችን በማስፋት፣ ተለዋዋጭ የቀጣና ሁኔታዎችን በብቃት ለመምራት እንደሚያግዝ ጥናቶቹ ያስረዳሉ።

ከላይ ያነሳነው ዝርዝር መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ያሲን መሐመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኤዢያ ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር የሚከተሉትን ማጠናከሪያ ሃሳቦች ያነሳሉ። የዝግጅት ክፍላችንም እነዚህን ጉዳዮች የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በማንሳት የሚከተለውን ምላሽ አቅርቦላችኋል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፦ በሀገር ደረጃ የውሃን ጥቅም እንዴት ይገልፁታል?

ዶክተር ያሲን፦ ውሃ ከግለሰብ እስከ ሀገር ድረስ የማይተካ ሚና አለው። ውቂያኖሶች አንደኛውን የዓለማችን ክፍል ከሌላኛው ክፍል ለማገናኘት ይረዳሉ። የንግድ መርከቦች ከአፍ እስከ ገደፋቸው ቁሶችን ጭነው ከተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ወደብ ጋር እየተፋተጉ ሳምንታት፣ ወራትን ጉዞ የሚያደርጉት በእነዚህ የውሃ አካላቶች ላይ ተመስርተው ነው። የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት የሚሟላው በባህር ላይ በሚካሄዱ የንግድ መስመሮች ነው። መንግሥታት የዜጎቻቸውን ደህንነት፣ ሉዓላዊነት፣ ለማረጋገጥ የግዴታ እነዚህን የባህር ክፍሎች መቆጣጠር ይኖርባቸዋል። ከዚህ አኳያ ስንመለከተው ውሃ ከንፅህና መጠበቂያ፣ ከመጠጥ፣ ከምግብና ከማብሰያነት የዘለለ በዓለምም ሆነ በሀገር ደረጃ ትርጉሙ ላቅ እንደሚል እንረዳለን።

ይህንን መነሻ በማድረግ የዓለማችን ሀገራት የውሃ ሀብት ላይ በስፋት ይሠራሉ። ከዝናብና ከከርሰ ምድር የሚገኝ የውሃ ሀብትን በጥንቃቄ ለመጠቀም ፖሊሲ ያወጣሉ። የሚያዋስናቸውን ባህር ለመቆጣጠርና ከዚያም ጥቅም ለማግኘት አቅማቸውን ሁሉ አሟጥጠው ይሠራሉ። በጥቅሉ ውሃ ለሰው ልጆች የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ተያያዥ ጉዳዮች ቁልፍ ድርሻ ይወስዳል።

ውሃ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ በመሆናችን ብቻ ለምንኖረው ኖሮ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከእዚህኛው ዘመን ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት ውሃ የስልጣኔ መሠረትም ሆኖ የሚታይ ነው። ለምሳሌ በጥንታዊ የጋርዮሽ ሥርዓት ማህበር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አብዛኛውን ኑሯቸው ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ በመሆኑና የሚመገቡትም ፍራፍሬ ለቅመው፤ አደን አድነው እንደመሆኑ መጠን ያን ያህል በስልጣኔ ሳይራመዱ ቀርተዋል። ከዛ በኋላ ግን የነበሩ ክስተቶች በሙሉ ይጓዙ የነበሩት ውሃን ተከትለው ስለነበር ወንዞች አካባቢ ሰዎች ሰፍረው የግብርና ሥራ መሥራት ጀመሩ። በዚህ ደግሞ የመጀመሪያው የስልጣኔ መነሻ ግብርና ሆነ።

ከዚህ ቀጥሎ ያሉ የዓለም ትላልቅ ስልጣኔዎች መነሻቸው ወንዝ ዳር በመስፈር የግብርና ሥራ መሥራት ሆነ። ለምሳሌ የግሪክ የሮም የሜሶፖታሚያ ቻይናና ሌሎችም የስልጣኔ መነሻቸው ግብርና ነው። የግብርና ሥራውን ከተጠቀሙ በኋላ ውሃን መሠረት አድርገው የዞሩት ወደ ትራንስፖርት ዘርፉ ነው። የተለያዩ መጓጓዣዎችን እየሠሩ በወንዞች ላይ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ደግሞ ፖርቹጋሎች በውሃ ከላይ እየተጓጓዙ ወደ አፍሪካ ኋላም ህንድ መድረሳቸው ነው። የማጂላን ጉዞ እና ሌሎችም ሁሉም የዓለምን ስፋት ያዩት እና ጉዞ ያደረጉት ውሃን በመጠቀም ነው።

በጠቅላላው ውሃ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ወንዝ ለግብርና ሥራ ለትራንስፖርት ወዘተ ጠቀሜታው በጣም የጎላ ስለሆነ፤ እኛም በተለያዩ ጊዜያት ቁጭ ብለን ስለውሃና ውሃ ጉዳይ እያነሳን እንወያያለን። ብቻ በአጠቃላይ ቀለል ባለ መልኩ እንደሚገለጸው ውሃ ሕይወት ነው። ለሀገር ደግሞ ዕድገት አሁን ላይ ደግሞ ትልቅ የደህንነት መሳሪያም ጭምር ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ አንጻር አንድ ሀገር ባህር አላት ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው? ጥቅሙስ እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር ያሲን፦ የባህር በር ባለቤት የመሆን ጠቀሜታ ልማት እና ክልላዊ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን መቻል እንደሆነ ጥናቶች ያስረዳሉ። የባህር ወደቦች ንግድን፣ ኢንቨስትመንትን እና ኢንደስትሪላይዜሽንን በማመቻቸት ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦዋቸው ከፍ ያለ ድርሻ እንደሚወስዱ ጥናቶቹ ያብራራሉ። በተጨማሪ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ይገልፃሉ። ወደቦች በአጎራባች አካባቢዎች ልማትን በማበረታታት፣ የሥራ እድል በመፍጠርና እና መሠረተ ልማትን በማሻሻል የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጥናቶቹ ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ሀገር ነች። በዚህም በርካታ ጉዳቶች ያጋጥሟታል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የተሻለ የባህር ዳርቻ ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው። በአሁኑ ጊዜ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የውጭ ዕርዳታ ዋና ወደብ ሆና እያገለገለች ቢሆንም፤ በአንድ ወደብ ላይ መታመን ግን ውስንነት ያመጣል። አደጋ አለው። በተጨማሪ በአንድ አካል ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናው ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሌላንድ ጋር ፍትሃዊ የወደብ አጠቃቀምን በተመለከተ አማራጮችን እየመረመረች ነው። በተጨማሪም ከኬንያ ጋር ያለው የላሙ ፖርት ከተጠናቀቀ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

እንግዲህ የባህር በር ማለት ትርጉሙ ብዙ ከመሆኑም በላይ ጠቀሜታውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ ባህርን በመጠቀም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር በቀላሉ መገናኘት እንችላለን፤ አብዛኛውን የንግድ ሥራም የሚከናወንበት ነው፤ በትራንስፖርቱ ዘርፍም ብዙ መርከቦች ይጓጓዛሉ። የዓለም ንግድ ዋናው መጓጓዣውም በባህር ላይ ነው። በመሆኑም ወደብ ለሀገራት ወሳኝ ሚና ያለውና እጅግም አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። በዚህ የተነሳም ወደብ ያላቸውና የሌላቸው ሀገራት እኩል ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አቅም የላቸውም። በሌሎች ሀገሮች ወደቦች መጠቀም ከክፍያ ጀምሮ ስምምነት ያስፈልገዋል፤ ስምምነቱ ደግሞ ከፍ ዝቅ የሚል ከሆነ ችግሩ የተባባሰ ይሆናል። ይህ በደንብ ሲታይ አማራጭ ወደብ የግድ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ እንደሚባለው የውሃ ማማ ናት? ይህንን ያህል መጠን ያለው ውሃ ያላት ሀገር ከሆነችስ በሀብቷ ምን ያህል ተጠቅማለች ?

ዶክተር ያሲን፦ ሀብቱ ቢኖራትም እስከ አሁን ብዙ ተጠቅማበታለች ለማለት አያስደፍረም። ዓባይን ያየን እንደሆነ ጉዳዩ ሰፊና የብዙዎች ፍላጎት ያለበት ነው፤ ሌላው ባሮ አኮቦ ነው፤ ግን ደግሞ በዚህ ወንዝም አልተጠቀምንበትም። ሌሎች ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት የሚውሉ ወንዞች አሉን። ይህ ቢሆንም የሀብታችንን ያህል ተጠቅመናል ብሎ መናገር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም። ካልተጠቀምንበት የውሃ ማማ ነን አይደለንም እያሉ መከራከር ዋጋ የለውም። መሠረታዊው ጉዳይ ያለውን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ነው።

አዲስ ዘመን፦ ከላይ እርስዎም እንዳሉት የብዙዎች ፍላጎት ያለበትን ዓባይን ጨምሮ ሌሎች ወንዞች አሉን። አንዳንዶች እንደሚሉት ዓባይን ትተን በሌሎች ውሃዎች እንጠቀም ብንል በቂ ውሃ አለን ብለን መናገር እንችላለን?

ዶክተር ያሲን፦ አንደኛ እና ዋነኛው ነገር የምንጠቀመውም ሆነ የምንተወው እነሱ ስላሉ አይደለም፤ የዓባይን ውሃ በተለይም ሌሎች ጎረቤቶቻችንን ሳንነካ መጠቀም መብታችን እና ሕግም የሚፈቅድልን ጉዳይ ነው። ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚመነጨውን ውሃ በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አለን። አሁን እነሱ የሚሉት ሁሉንም እንደ ቀደመው ጊዜ ብቻችንን አግበስብሰን እንሙት ነው። ያላችሁ ይበቃችኋል ዓባይን ለእኛ ተውልን የሚሉት፤ ከዚህ የተነሳ ነው። እኛ ደግሞ ዓባይን የዓለም አቀፉ ሕግ በሚያዘው መንገድ እንጠቀማለን። ነገር ግን ሀገራችን ላይ ያሉ ውሃዎችን ዝናብን ጨምሮ ደግሞ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እያፈለቅን በአግባቡ መጠቀም ይገባናል። ይህ በሆነ ልክ ደግሞ ውሃ የስልጣኔና የሀብት ምንጭ መሆኑን እያስመሰከርን እንሄዳለን ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፦ እንደው እስከ አሁን በውሃ ሃብታችን ላለመጠቀማችን ታሪካዊ ምክንያት ይኖረው ይሆን ?

ዶክተር ያሲን፦ እስከ አሁን እንግዲህ ባለውና አቅም በፈቀደ መጠን ውሃዎቻችንን እያለማን ለተለያዩ ሥራዎች እያዋልን እየተጠቀምን ነው። ነገር ግን ከዚህ በበለጠ ሁኔታ መጠቀም ግን ይቻላልም ይገባልም ማለት እፈልጋለሁ። የውሃ ሀብታችንን በሚፈለገው ደረጃ ላለመጠቀማችን የውስጥ የአቅም ችግር እና ሰፊ የውጭ ተጽዕኖዎች ነበሩብን፤ አሁንም አሉብን። እነዚህን ችግሮች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም እንዴት ባለው መንገድ ተቆጣጥረናቸው ቀጣዩን ሥራችንን መሥራት እንችላለን በሚለው ላይ በቀጣይ ከፍ ያለ ትኩረትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

ለምሳሌ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ እንዳትጠቀም ካደረጋት የውጭ ጫና መካከል በቅኝ ግዛት ዘመን ቅኝ ገዢዎቹ አፍሪካን ብሎም ኢትዮጵያን ያዩበት መንገድ ነው። በእነሱ እይታ ኢትዮጵያ ወንዞቿንም ሆነ የባህር በሮቿን ከተጠቀመች እጅግ ታድጋለች፤ ተፅእኖ ፈጣሪ ትሆናለች ብለው አምነዋል። በመሆኑም ይህንን ሀብቷን ከተጠቀመች ታድጋለች ብለው በማሰብ፤ ከማሰብ አልፈው እንዳታድግ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለማደግ ዋነኛ መሠረት የሚሆነውን የባህር በር እንዳይኖራትም ሆነ የባህር በር እንድታጣ በስፋት ሠርተዋል።

ወንዞቿንም በማልማት ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዳይሆን እና ከድህነት እንዳይወጣ ብዙ መንገዶችን በመጠቀም በስፋት ወደኋላ እንድንቀር ማድረግ ችለዋል። በመሆኑም ይህንን ሁኔታ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ፖለቲከኞች የተለያዩ መንገዶችን እንዲሁም ውይይቶችን በማድረግ ሊፈቱት የሚገባ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ።

ሌላው ከውጭ ተፅዕኖ በተጨማሪ የውስጥ ችግራችን ደግሞ እኛው በእኛው የምንፈጥራቸው አንዳንድ መሰናክሎችም ለዘመናት በውሃ ሀብታችን እንዳንጠቀም እንቅፋት ሆነውብናል። በርግጥ ሌሎችም እነዚህ ናቸው ብሎ ለመዘርዘር ሰፋ ያለ ሥራንና ጥናትን ይጠይቅ ይሆናል። ግን በጠቅላላው ያሉብንን ችግሮች ፈተን የውሃ ሀብታችንን በሚገባ መጠቀሙ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል። የውሃ ሀብታችንን በአግባቡ የምንጠቀምበትን ሁኔታ ካሰፋን እና በሀብታችንም በሚገባን ልክ የምንጠቀምበትን ሁኔታ መፍጠር ከቻልን ከድህነት መውጣትም ሆነ ሀገርን ማሳደግ አዳጋች አይሆንም።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያም የባህር በር ለማግኘት የሄደችበት ርቀት እንዴት ያዩታል ?

ዶክተር ያሲን፦ ውሃ እንግዲህ የስልጣኔ መሠረት ነው ካልን፤ የምንጠቀመው ወደብን አማካይ አድርገን ነው። ሀገራችን ለረጅም ጊዜ ወደብ አልባ ሆና ቆይታለች። አሁን ላይ ደግሞ ወደብ ቢኖር ጥሩ ነው በሚል ጥያቄዎች እየተነሱ ናቸው። እኔ በበኩሌ እነዚህን ጥያቄዎች የምመለከታቸው በጣም በጥሩ ሁኔታ ነው። ጥያቄውም መቅረብ ያለበት ተገቢነት ያለው ጥያቄ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ይህ ጥያቄ ቀርቦ መልስ ቢያገኝ ምናልባትም ጥቅሙ ለመንግሥት አልያም ለሆነ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ነው። በመሆኑም ጥያቄውን አግባብ ባለው ሁኔታ ማቅረብና ሥራውንም ከፍ ባለ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ማስኬድ ደግሞ የሚለከታቸው አካላት ሚናና ኃላፊነት ነው።

በርግጥ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ማሰብ እና መሥራት አለበት። ኢትዮጵያ ወደብ የምታገኝበት ሁኔታ እንዲኖርም ሆነ በወንዞቿ እንድትጠቀም የማይፈልግ ሰው አለ ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም ውሃ የዕድገት መሠረት ነው። ይህንን ትልቅ መሠረት ለመጠቀም ሁኔታዎች ሲመቻቹ ከመቃወም እና ከማደናቀፍ ይልቅ መደገፍ እና ማበረታታት የተሻለ ነው።

ባለሙያዎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት መጠቀም እንድትችል መደገፍ ይጠበቅባቸዋል። ሌላው ሕዝብም ውሃ ለሀገራችን እድገት እጅግ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት የሚፈለግበትን ድጋፍ ማድረግ አለበት።

አዲስ ዘመን፦ በጠቅላላው የሁሉ ነገር መሠረት ነው የሚባለው የውሃ ጉዳይ መታየት ያለበት በምን መልኩ ነው ይላሉ?

ዶክተር ያሲን፦ ውሃ የሕይወት እና የእድገት መሠረት ነው ካልን ሁሉም አካል ውሃ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ በተቻለ መጠን ደግሞ ውሃችንን ከብክነት ከማዳናችንም በላይ ሰፋ ያለ ጥቅምንም ለማግኘት ያግዛል። ሆኖም ግን በተለይም ወጣቱ ትውልድ ማንበብ ማወቅ የግድ ያስፈልገዋል። ኢትዮጵያ ምን ያህል ወንዞች አሏት? እነዚህን ወንዞች በምን መልኩ መጠቀም ትችላለች? ብትጠቀም ምን ያህል ማደግ ትችላለች? የሚሉትን እና ሌሎችም ጥያቄዎችን ለራሱ በማቅረብ እያነበበ ስለውሃ ሀብት እና ሊሠራበት ስለሚገባበት ሁኔታ ማሰብ አለበት።

ከላይ ደግሞ ቢቻል ልጆች ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ጀምሮ ስለውሃ እንዲማሩ በትምህርት ሥርዓት (ካሪኩለም) ውስጥ እንዲገባ መሥራት ያስፈልጋል። በዚህ ደረጃ ባሳወቅናቸው ልክ ደግሞ እያንዳንዷን የምትባክን ውሃ የመቆጣጠር ብሎም ስለውሃ ጥቅምና ጉዳት ይበልጥ የመረዳት አቅማቸው ይዳብራል። በመሆኑም ሁሉም ሰው ለውሃ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል።

ለውሃ ትኩረት ሲሰጥ ዕድገት እንደሚመጣ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለም። ምክንያቱም ዓለም ያደገው በውሃ ነው። ውሃ የዓለም ሀገራት የዕድገት መሠረት ነው። ኢትዮጵያ ግን በተቃራኒው አንደኛ የነበራትን ወደቧን አጥታለች። በሌላ በኩል ብዙ ወንዞች ቢኖሯትም በወንዞቿ በአግባቡ እየተጠቀመች አይደለም። እንዳትጠቀም የተለያዩ የውስጥ እና የውጭ ችግሮች ቢኖሩም፤ ችግሮቹን በማወቅ እና መፈታት ያለባቸውንም በአግባቡ በመፍታት መፍትሔ ማምጣት የግድ ነው።

በውሃ ሀብታችን እንዳንጠቀም ሲያደርጉ የቆዩ እንቅፋቶችን ማንሳት እና ችግሮቹን ማቃለል አንደኛው መፍትሔ ነው። ወደብ የሚገኝበትን ዕድል ማስፋት እና ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን ሌላኛው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዘላቂ ዕድገት እንዲኖር ከታች ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ትውልዱ ውሃን በተመለከተ በጥልቀት እንዲያውቅ መሥራት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ።

ዶክተር ያሲን፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You