መንግሥት በከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባትና በእጣ በማስተላለፍ፣ ነዋሪዎች ተደራጅተው የመኖሪያ ቤቶችን እንዲገነቡ ቦታ በማቅረብ እየሠራ ነው። የግሉ ዘርፍ በበኩሉ በሪል ስቴት ልማት በመሠማራት የመኖሪያ ቤቶችን እየገነባ ይገኛል። የቤት ባለቤቶች በየቤታቸው ተጨማሪ ቤቶችን በመገንባት በማስፋፋት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ የበኩላቸውን ሲያደርጉ ኖረዋል።
እንዲያም ሆኖ ግን የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎቱ ሊጣጣም አልቻለም። ችግሩ በተለይ በመኖሪያ ቤት ተከራዮች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል። በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪ ባለባት አዲስ አበባ ከተማ ችግሩ ስር የሰደደ ሆኖ በመቆየቱ ተከራዮች ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረጉ ይስተዋላሉ።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋው በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባለው ማህበረሰብ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ቢሆንም መካከለኛ ገቢ ያለውም ቢሆን የችግሩ ሰላባ ሆኗል። ደላላዎችና ስግብግብ አከራዮች የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ እንዲንር እያደረጉ ያልተገባ ጥቅም ሲያግበሰብሱ ኖረዋል። እነዚህ አካላት በትንሹም በትልቁም ምክንያት ዋጋ በመጨመር ህብረተሰቡን እያሰቃዩ ይገኛሉ።
የመኖሪያ ቤቶችን ዋጋ ጨምረው ለማከራየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ተከራዮች ባሉበት የሚጨምሩት ዋጋ አንሷቸው አንዴ ቤቱን ራሳቸው ሊገቡበት ማሰባቸውን፣ ልጆች ወይም ዘመዶቻቸው ከውጭ ስለሚመጡ ለእነሱ ሊያውሉት ማቀዳቸውን፣ በቤቱ ላይ መሠረታዊ እድሳት ሊያደርጉ መሆናቸውን፣ ወዘተ እየጠቀሱ ተከራዮችን በማስወጣት ለሌላ ተከራይ በከፍተኛ ዋጋ ሲያከራዩ ኖረዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት ተከራዮች ብቻም ሳይሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት የተገነዘቡ አካላት ለመንግሥት ሲያስገነዝቡ ቆይተዋል፤ መንግሥትም የችግሩን አሳሳቢነት በመጥቀስ መፍትሔ ማኖር የሚገባ መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህም አለፍ ያለ ርምጃ ሲሰወድም ቆይቷል።
ከተማ አስተዳደሩ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጀምሮ ተከራዮች ላይ የሚደርሰውን የቤት ኪራይ ዋጋ መናር ለመቆጣጠር እየሠራ ነው። ለስድስት ወራት የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር እንደማይቻል መመሪያ አውጥቶ በየስድስት ወሩ በተደጋጋሚ በመተግበር ተከራዮችን ታድጓል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ያወጣው የመኖሪያ ቤት ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅም በሀገሪቱ ስር የሰደደ ችግር ሆኖ የኖረውን ይህን መኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መናር በጊዜያዊነት ለመፍታት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል። በአዋጁ መሠረት በመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ላይ እንዳሻቸው ሲወስኑ የኖሩትን ደላላዎችን የሚያስወጣ ፣ የቤት ባለቤቶች ብቻቸውን ኪራይ እንዳይወስኑ ያደርጋቸዋል።
በሀገሪቱ በቤት ኪራይ ብቻ ሳይሆን፣ ቤት፣ መኪናና በመሳሰሉት ሽያጭ ዋጋ ላይ ጭምር እንዳሻቸው በመወሰን የሚታወቁት እነዚህ ደላላዎች ከመኖሪያ ቤት ኪራይ ተዋናይነታቸው መውጣታቸው በኪራይ ዋጋ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ከወዲሁ እየተገመተ ነው። ደላሎች በሀገሪቱ እየታየ ላለው የኑሮ ውድነት ከዋንኛዎቹ ተጠያቂዎች መካከል የሚጠቀሱ እንደመሆናቸው በአዋጁ አማካይነት በቤት ኪራይ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማሳጣት ማለት የኑሮ ውድነቱን በሆነ መልኩ ማርግብም ይሆናል።
መንግሥት በመኖሪያ ቤት ኪራይም ላይ እየታየ ያለውን የቤት ኪራይ ዋጋ ለማረጋጋት አዋጅ ማውጣቱ፤ እነዚህን ደላሎች ከግብይት ሰንሰለቱ በማስወጣት ጤነኛ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ምህዳር እንዲኖር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በአዲስ አበባም ሆነ በትላልቅ የሀገራችን ከተሞች በግለሰብ ቤት ተከራይቶ የሚኖረው አብዛኛው ነዋሪ በቤት ኪራይ ዋጋ በየጊዜው መናር ሲማረር ቆይቷል። ገቢውና ለመኖሪያ ቤት የሚጠየቀው የኪራይ ዋጋ ጨርሶ የሚመጣን አይደለም፤ ከገቢው አብዛኛውን ለቤት ኪራይ የሚያውለውን ተከራይ ቤቱ ይቁጠረው ብሎ መተው ይቀላል። ተከራዮች ሥራ ውለው የሚገቡት ለቤት ኪራይ ለመክፈል እስከሚመስል ድረስ ከገቢያቸው ከፍተኛ የሚባለውን መጠን እያዋሉ ይገኛሉ።
ተከራዮች ይህንን ክፍያ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ክፍለው እንዳይኖሩ ደላላዎችና አከራዮች ብዙ ጫናዎችን ያሳድሩባቸዋል። በዚህ የተነሳም ከዛሬ ነገ ቤቱን እንፈልገዋለን ልቀቁ ወይም ኪራይ ጨምሩ እንባላለን ብለው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሆነው ነው የሚኖሩት። ይህ ሁኔታ ያስመረራቸው ተከራዮች ከመሀል ከተማ ወደ ዳር ብዙም ወዳልለማው አካባቢ ቤት ሲከራዩ መመልከት የተለመደ ነው።
ይህ ሁኔታ በመኖሪያ ቤት ኪራይ በኩል ያለውን ጫና ለጊዜውም ቢሆን ያቃልልላቸዋል፤ ሁኔታውን የሚቀበሉት ግን ወደ ሥራ ቦታ ለመሄድ ለመምጣት በሚያወጡት ትራንስፖርት ወጪና ጊዚያቸው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ዋጥ በማድረግ ነው።
በእዚህ ሂደት እቃ በመጓጓዝ ሂደት ለትራንስፖርት ከሚያወጡት በተጨማሪ ያልተገባ ዋጋ ለሚጠይቁ እቃ ጫኝና አውራጅ ለተባሉ ሌሎች በላተኞች ሲዳረጉም ኖረዋል። ጫኝ አውራጅ የሚያስከትለው ችግር በተከራይ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ባይሆንም፣ በኪራይ ዋጋ መናር ከስሩ በተነቀለው ተከራይ ላይ ግን ጫናው ከፍተኛ ነው። ይህን ችግር ፍራቻ ብዙዎች ቤት የሚለቁትም ወደ አዲስ ቤት የሚገቡት በሌሊት እስከ መሆን የደረሰበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል።
እነዚህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ፍራቻ ተከራዮች አካራይና ደላላ የጣሉባቸውን የቤት ኪራይ ዋጋ ተሸክመው ለመኖር የሚገደዱበት ሁኔታ በርካታ ነው። እዚህ አናነሳውም እንጂ የአከራዮች ብዙ ያልተገቡ ባህሪዎች በተከራዮች ላይ የሚያደርሱት ችግር ከፍተኛ እንደሆነም ይታወቃል። ይህን ሁሉ ችለውም በቤት ኪራይ ዋጋ እየተፈተኑ ያሉት።
አሁን ተከራዮች ለመኖሪያ ቤት የሚከፍሉት ገንዘብ የወር ደመወዝተኛ ከሆኑ ከገቢያቸው ከ70 በመቶ በላይ መሆኑን በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተሰምቷል። ይህም በአማካይ የተሰላ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። አንዳንዶች ሙሉ ደሞዛቸውን ለመኖሪያ ቤት ኪራይ እንደሚከፍሉ ይነገራል።
ለሌሎች ወጪዎች ሲሉ ደግሞ የትርፍ ሰዓት ሥራ ውስጥ እንደሚገቡ፣ ወይም በተለያዩ ምንጮች የሚደገፉበት ሁኔታ እንዳለም ይገለጻል። ባልና ሚስት የአንዳቸውን ደሞዝ ለቤት ኪራይ ያደረጉበት ሁኔታ እንዳለ ሲነገር ሰምቻለሁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው አዋጅ ከቤት ኪራይ ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ ለበርካታ ችግሮች እየተጋለጠ የሚገኘውና የተረጋጋ ኑሮን ለመምራት ለተቸገረው ለእዚህ ተከራይ እፎይታን ይሰጣል። በአከራይና ደላሎች ብቻ ሲወሰን በኖረው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ላይ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ቁጥጥር ማድረግ ውስጥ መግባቱ የኪራይ ዋጋው እንዲረጋጋ ያደርጋል።
የመኖሪያ ቤት አቅርቦት አንገብጋቢ እና መሠረታዊ የመብት ጉዳይ ነው። መንግሥት የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሟላት በተለያዩ አማራጮች ላይ እየሠራ መሆኑም ይታወቃል። ከዚህ ጥረቱ ጎን ለጎን ደግሞ በየጊዜው እየናረ ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ለማረጋጋት እንዲቻል የተከራዩን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ መኖሪያ ቤቶች የሚከራዩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይህን አዋጅ ማውጣቱ ሊያስመሰግነው ይገባል።
በአዋጁ ላይ እንደተመለከተው፤ አዋጁ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር ግልጽነት፣ ተጠያቂነት ያለውና የአከራዮችንም ሆነ የተከራዮችን ጥቅም እና መሠረታዊ መብቶች ሚዛን በጠበቀ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በአዋጁ መሠረትም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ዘመን ከሁለት ዓመት ማነስ የለበትም። የአንድ ቤት ባለቤትነት በውርስ፣ በሽያጭ፣ በዕዳ፣ ወይም በሌላ ማንኛውም ሕጋዊ ምክንያት ለሌላ ወገን ከተላለፈም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውሉ ሊቋረጥ የሚችለው ለተከራዩ የስድስት ወር ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ ይሆናል።
ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል የኪራይ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ያለ ማስጠንቀቂያ በአከራይ ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖሩ በአዋጁ ላይ ተገልጿል። ተከራዩ የቤተ ኪራዩን በውሉ በተመለከተው የመክፈያ ጊዜ ለመጀመሪያ ከሆነ ከ15 ቀን ካሳለፈ፤ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖም የቤት ኪራዩ በውሉ ከተመለከተው ቀን ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነና ሰባት ቀን ካለፈው፤ ቤቱን ካለ አከራዩ ፈቃድ ከመኖሪያነት ውጭ ለንግድ ሥራ ከተጠቀመበት፤ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በተደጋጋሚ የሚያውክ ከሆነ፣ ቤቱን ለወንጀል መፈጸሚያ የሚጠቀም ከሆነ ቤቱ ላይ አስቦበት ወይም በቸልተኝነት ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ውሉ ሊቋረጥ የሚችል መሆኑ ተመላክቷል።
እነዚህ ሁኔታዎች ተከራዩን ብቻ ሳይሆን አከራዩንም ሊታደጉ የሚችሉ ድንጋጌዎች በአዋጁ መካተታቸውን ያመለክታሉ። አንዳንድ ተከራዮች በአከራዮች ላይ የሚያደርሱትን ሕገወጥ ተግባር ለመቆጣጠርና ለመከላከልም የሚያስችል በመሆኑ ሁለቱንም ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጅ ነው።
ያለምንም ተቆጣጣሪና አስተዳዳሪ በአከራዮችና ደላላዎች ስሜት ብቻ ሲመራ የኖረው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ አብዛኛውን ተከራይ በእጅጉ የፈተነ ቢሆንም፣ ከቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ ሁሉም አከራይ በኪራይ ዋጋ ላይ ተመሳሳይ አቋም አለው ብሎ መደምደም የማያስችልበት ሁኔታ እንዳለም መጠቅስ እወዳለሁ። በቁጥር ቢያንሱም አንዳንድ አካራዮች በቤት ኪራይ ዋጋ ላይ ከተከራይ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን መጥቀስ ያስፈልጋል።
እነዚህ አከራዮች ከተከራዮች ጋር ያላቸው ቤተሰባዊ ግንኙነትና በቤት ኪራይ ዋጋ በኩልም ተነጋግረው የሚወስኑበት እንዲሁም አንዳንድ ተከራዮችም አስበው ዋጋ የሚጨምሩበት ሁኔታ ሲታሰብ ሁሉንም አከራይ በአንድ ቅርጫት ውስጥ መከተት ተገቢ እንዳልሆነ እንድናሳብ ያደርገናል።
እነዚህ አከራዮች ኪራዩ የሚያዋጣቸው መሆኑን አስበው እንጂ ለጽድቅ ብለው አይደለም ከተከራዮች ጋር በገበያ ዋጋና በፍቅር አብረው እየኖሩ ያሉት። እነዚህ አከራዮች ቤት የሚያከራዩበት ዋጋ በቀጣዩ ለቤት ኪራይ የሚወጣ ዋጋ መነሻ ተደርጎ ሊያገለግል እንደሚችል ቢገመት ስህተት አይሆንም።
አንዳንድ ተከራዮች አከራዮችን አመል እንደሚያ ሰወጡም ማሰብም ያስፈልጋል። የተከራዩትን የመኖሪያ ቤት ላልተገባ ተግባር ማዋል፣ በበሮች፣ መስኮቶች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ በኤሌክትሪክ መስመሮች፣ ወዘተ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በሌሊት ቤት ቤቱን ለቀው የሚሄዱና አከራዮች ለቤት እድሳት ከፍተኛ ሀብት እንዲያወጡ የሚያደርጉ ተከራዮችም እንዳሉ ሲታሰቡ አከራዮችን ብቻ መወንጀሉ ተገቢነት እንደሌለው ያስገነዝባል።
ይህ አዲስ አዋጅ እነዚህን ሁለት ወገኖች በሚገባ የሚመለከት እንደሚሆን ይጠበቃል፤ አከራይና ተከራይ በሕግና ሕግ አግባብ ብቻ ዋጋ ተዋውለው የቤቱ መሠረተ ልማቶችም በሚገባ ተጠብቀው የሚቆዩበት፣ ጉዳት ደርሶባቸው ከተገኙም የሚጠገኑበትም ሁኔታንም ያያል ብዬ አስባለሁ።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም