የአውሮፓ ኅብረት በኢራን የሚሳኤልና ድሮን አምራቾች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተስማማ

የአውሮፓ ኅብረት በኢራን የሚሳኤልና ድሮን አምራቾች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተስማማ። 27ቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በብራሰልስ ከመከሩ በኋላ ነው በቴህራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ከስምምነት የደረሱት።
የኅብረቱ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሸል “ኢራንን ለማግለል የትኛውንም እርምጃ መውሰድ ወሳኝ” ነው ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል። የአውሮፓ ኅብረት ኢራን ለሩሲያ ድሮኖችን በመሸጥ በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው በሚል በርካታ ማዕቀቦችን መጣሉ ይታወሳል።

ኅብረቱ በኢራን ድሮን እና ሚሳኤል አምራች ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የወሰነውም ቴህራን ከ300 በላይ ድሮን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል መተኮሷን ተከትሎ ነው። የእስራኤል ዋነኛ አጋር አሜሪካም በቀጣይ ቀናት በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደምትጥል ይፋ አድርጋለች።

የኢራን ነዳጅ ለውጭ ገበያ እንዳይቀርብ ማድረግ፤ በኢራን የሚሳኤልና ድሮን ፕሮግራም እንዲሁም በሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ላይ ማዕቀብ ለመጣል መታቀዱንም ነው የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫኒ የተናገሩት። ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እስራኤል የአጻፋ እርምጃ ከወሰደች ውጥረት የበዛበት የመካከለኛው ምሥራቅ የጦርነት ቀጣና ይለወጣል በሚል ቴል አቪቭን እያሳሰቡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን “እስራኤል ራሷን ለመጠበቅ የሚያስችላትን ውሳኔ በራሷ ትወስናለች” ነው ያሉት።ኔታንያሁ ከብሪታንያ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ሲመክሩ” እስራኤል ራሷን ለመጠበቅ የትኛውንም እርምጃ ትወስዳለች” ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንም እስራኤል ለኢራን የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት አጻፋውን ለመመለስ ሳትዘጋጅ እንዳልቀረች ተናግረዋል። እስራኤል አጋሮቿ በኢራን የሚሳኤል ፕሮግራም ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉና የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ዘብን በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲመዘግቡ ጥሪ ማቅረቧን አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You