በጉራጌ ዞን እናቶች ከድካማቸው ውጣ ውረዱ ከቤት ውስጥ ኃላፊነቶች እንዲያርፉ߹ እንዲደሰቱ የሚደረግበት ከዛም አለፍ ሲል ልጆቻቸው የተለያዩ ስጦታዎችን በማበርከት ምርቃት የሚያገኙበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ባል ሚስቱን የሚያከብርበትና በተራው ምግብ አብስሎ የሚመግብበት ቀን አንትሮሽት በዓል በመባል ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩልም እነዚህ ዓመቱን ሙሉ ቤተሰቡን ለማስደሰት ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ ደፋ ቀና ሲሉ ለነበሩ እናቶች የሚታረድ በሬ እንዳቅሙ የሚገዛበት ሲሆን የጎረቤት እናቶችና ሴቶች ተሰባስበው የተለያዩ የባህል ምግቦች አዘጋጅተው በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል፡፡
ማኅበረሰቡ ‹‹አንትሮሽት›› እያለ በየዓመቱ የሚያከብረው የእናቶች ቀን፣ ከ300 ዓመታት በላይ እንደተካሄደ ይነገርለታል፡፡ በዕለቱ እናቶች ታጥበው፣ ያልተነጠረ ቅቤ ተቀብተው፣ በልዩ የበዓል ልብስና ጌጣ ጌጥ ይዋባሉ፡፡ የእናቲቷ የመጀመሪያ ልጅ ወንድ ከሆነ ወይም ሴት ከሆነች የተለያየ ሥርዓት ይከተላሉ፡፡ ለምሳሌ ሴት የበኩር ልጆች ካለች እናቷን ቅቤ ትቀባለች፡፡ ልጅ የሌላቸው ሴቶች በዓሉን ከጎረቤቶቻቸው ልጆች በሚበረከቱላቸው ስጦታዎች ተደስተው እንዲያሳልፉ ይደረጋል፡፡
በእናቶች ምርቃት የሚጀመረውን በዓል ከተለያዩ ቀበሌዎች የመጡ እናቶች በጉራጌኛ ጭፈራና ዘፈን ያደምቁታል። የአንትሮሽት በዓል በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉትን የመከባበርና የሰላም እሴቶቻችን ይበልጥ እንዲለሙ የሚደረጉበት፣ ሴቶች መብታቸውን እንዲያስከብሩና ተጠቃ ሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል ነው።
በመጨረሻም በዓሉ ልጆች ከእናቶቻቸው ምርቃት የሚቀበሉበት የተጣሉ ካሉ የሚታረቁበትና ፍቅር የሚሞላበት በመሆኑ ሁሉም ይህንን አጎልብቶ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚጠበቅበትን የሚወጣበት እለት ሆኖ ያልፋል።
እናት በወለደችው ልጅና በባለቤቷ የምትከ በርበት አንትሮሽት፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉትን የመከባበርና የሰላም እሴቶች እንዲለመልሙ የሚደረግበትና ሴቶች መብቶቻቸውን እንዲያስ ከብሩ፣ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡና ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት ዕለት ነው።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ክፍል ቸሀ ወረዳ ድረስ በመግባት ባደረገው ጥናት ይህ የሴቶች ቀን ከ 250 እስከ 300 ዓመታት በፊት በእናቶች የተጀመረ በዓል ሲሆን እናቶች በአንትሮሽት ደስታቸው ወደር እንደሌለውም ጥናቱ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩልም እናት እለቱ ሲከበር ጥሩ ምግብ እንዲመገቡ ቅቤ ጸጉራቸውን እንዲቀቡ ይደረጋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ እናቶች ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስታቸው ጥሩ ምግብ መመገቡና አናታቸው በቅቤ ማራሱ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው።በዕለቱ የሚቀርቡት የምግብ ዓይነቶችም ክትፎ፣ አይቤ፣ የጎመን ክትፎ፣ ዝማሙጃት ሌሎች ናቸው፡፡ ከተበላና ከተጠጣ በኋላ፣ በቀዬው ውብ ድምፅ ያላት ሴት ተመርጣ ለተከበሩ እናቶች እንድታዜም (እንድትዘፍን) ይደረጋል፡፡ እናቶች ከቤተሰባቸው ባሻገር ለኅብረተሰቡ ያበረከቱት ነገር እየተጠቀሰም ይሞገሳሉ፣ ይደነቃሉ፣ እረጅም እድሜ እንዲሰጣቸው ይመረቃሉ፣
እናቶች ዘወትር ከጠዋቱ 12 ሰዓት ተነስተው እንጨት ሲለቅሙ፣ ውኃ ሲቀዱ፣ ቆጮ ሲጋግሩ፣ ልጆቻቸውን ሲንከባከቡ ለባሎቻቸው አስፈላጊውን ሁሉ ሲያደርጉ መዋል የየእለት ሥራቸው ነው።ይህንን ኃላፊነታቸውንም ቤተሰባቸውን ከማስደሰት አንጻር ስለሚያዩት ቅሬታ አያቀርቡም። ነገር ግን ሀገሬው እናቶች ዓመት ሙሉ ለእኛ ሲለፉ እነሱን አንድ ቀን ከኃላፊነቶቻቸው ሁሉ አርቀን እኛ የእነሱን ቦታ ሸፍነን እየሰራን እነሱን ብናከበርና ብናመሰገን መልካም ነው በማለት በየዓመቱ በጥር ወር መጨረሻ በዓሉን ያከብሩታል።
ከላይ የእናቶችን በዓል ላነሳ የወደደኩት የፈረንጆቹ የእናቶች ቀን ላይ በመሆናችን እኛም ከቱባው ባህላችን መካከል አንዱ እናቶችን አንደ ባሕል ወጋችን ማክበሩ መሆኑን ለማሳየት ነው። ዛሬ የጉራጌን የእናቶች ቀን አየን እንጂ ሌሎችም ክልሎች እናቶቻቸውን በዓመት አንድ ጊዜ የሚያከብሩበት በዓል ይኖራቸዋል። ከዚህም ሌላ እድሜያቸውን ሙሉ በእንጦጦ ጫካ ላይ እንጨት ለቅመው ሸጠው ልጆቻቸው ለማሳደግ አሳድጎም ለቁም ነገር ለማብቃት ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ሲከፍሉ ለኖሩት ለዛሬዋ ባለታሪካችን “አትርሽት” ልንላቸው ወደናል።
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሕይወት ገጽታ አምድ ላይ የእድሜ ዘመን ተሞክሯቸውን የሚነግሩን ወይዘሮ ዓለምነሽ አሻንጎ ይባላሉ። ወይዘሮ ዓለምነሽ ገና ከወጣትነታቸው ጀምሮ የሚያወቁትን እንጨት ለቅሞ የመሸጥ ሥራ እስከ አርጅናቸው ዘመን እየሠሩት ይገኛሉ። ከወይዘሮዋ ጋር የነበረን ቆይታ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።
ከተወለዱባት ጋሞ ጎፋ አካባቢ የወጡት ገና የእናታቸውን እቅፍ ሳይጠግቡ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ወላጆቻቸው የሸመና ሥራን ሰርተው ራሳቸውን ለማስተዳደር በማሰብ ተወልደው ያደጉበትን ብሎም ትዳር መስርተው ልጆች ያፈሩበትን ቀያቸውን ትተውና ልጆቻችውን ይዘው አዲስ አበባ በመግባታቸው ነው። ምንም እንኳን እሳቸው ልጅ ቢሆኑም ቤተሰቦቻቸው ስለ አዲስ አበባ የሰሙት ነገር ልባቸውን አሸፍቶታል አዲስ አበባ ገንዘብ የሚታፈስባት ከተማ ናት የሚለው የተዛባ ንግግርም የማየት ጉጉታቸውን ጨምሮታል ታዲያ እንዲህ የተወራላት አዲስ አበባ መጥተው ሲያይዋት እንዳሰቡት እጇን ዘረግታ ሁሉን አልጋ በአልጋ አድርጋ የምትቀበል አልሆነችም።
ከገጠማቸው ችግር መካከልም የመኖሪያ ቤት ማግኘት፤ ሥራ መጀመር፤ ከባዱ የነበሩ ሲሆን በአጠቃላይ ግን ሕይወት የለመዱት ዓይነት አልሆን ብላ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ስለቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።
ለለውጥ ሲሉ ልጆቻቸውን ሰብስበው ከተወለዱባት ቀዬ ነቅለው ወደ አዲስ አበባ የመጡት የወይዘሮ ዓለምነሽ አባት በሽመና ሥራ ተቀጥረው መሥራት ሲጀምሩ እናት ደግሞ እንጦጦ ጫካ ላይ ወጥቶ እንጨት ለቅሞ መሸጥን አማራጭ የሥራ መስክ አደረጉት። የወይዘሮ ዓለምነሽ ቤተሰቦች እንዲህ እንዲህ እያሉ ኑሮን መግፋት አልቀረላቸውም ልጆቻቸውም እያደጉ ራስ መቻል ከተባለም ራሳቸውን እየቻሉላቸው ሄዱ። እነሱም ለልጆቻቸው የሚችሉትን ሁሉ አድርገው እንዳይራቡ እንዳይጠሙ እንዳይታረዙ ብዙ ለፍተው በመጨረሻም ወደማይቀረው ዓለም በሞት ተለዯቸው።
ወይዘሮ ዓለምነሽም ያን ጊዜ በለጋ እድሜያቸው ከእናታቸው ጋር ጫካ እየሄዱ እንጨት መልቀመን ተለማምደውታል። ዛሬ ላይ እናት ብሎ መሸሸጊያ አባት ብሎ መናኸሪያ የላቸውምና አማራጫቸው እናታቸው ይሰሩ የነበሩትን ጫካ ሄዶ እንጨት ለቅሞ መሸጥን መውረስ ነበርና እሱኑ አስቀጠሉ። ይህንን ብቻ አይደለም ከቤተሰቦቻቸው የወረሱት የአባታቸውን የሽመና ሙያም አቀላጥፈው ይችላሉ።
ከእናታቸው ስር ስር እየተከተሉ ጫካ እየሄዱ እንዳደጉት የሚናገሩት ወይዘሮ ዓለምነሽ ገና በአፍላ እድሜያቸው ነበር እንጨት ለቅሞ ሸጦ የማደርን ሥራ የጀመሩት። መጀመሪያ ከእናታቸው ጋር ሆነው የእንጦጦ ጫካን ሲረግጡ ይህ ሥራ የእድሜ ልክ ሥራቸው ሊሆን እንደሚችል አላሰቡም ነበር። ነገር ገን የሕይወት መንገድ በዛው መራቻቸውና ማልደው ከቤታቸው ወጥተው እንጨት ለቅመው ሸጠው ቤት መግባትን የሚያውቁት ብቸኛ ሥራቸው ሆነ።
በሥራው ከሰላሳ ስምንት ዓመት በላይ እንዳሳለፉ የሚናገሩት የወይዘሮ ዓለምነሽን ሥራ የሚጋሩ፣ በሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ቀሪ ሕይወታቸውን የሚገፉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች አሉ። ሴቶቹ ቀን ከሌሊት ይለፋሉ፣ ይጥራሉ፤ በየቋጥኙ ለእንጨት ለቀማ ጎንበስ ቀና ይላሉ። በአማካይ በአንዴ አርባ ኪሎ ግራም የሚመዝን የማገዶ እንጨት ተሸክመውም ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ።
እንደ ወይዘሮ ዓለምነሽ ገለፃ የእንጨት ተሸካሚ ሴቶች ሕይወት ጣጣው ብዙ ነው። ድካም ልፋቱም እንደዚያው፡፡ ከዚህ ባሻገር ለሰው ሠራሽ ችግሮች ተጋላጭነታቸውም የዚያኑ ያህል የከፋ ነው። ምን ይህ ብቻ የእንጦጦን ጫካ ለሴቶቹ የእለተ ጉርስ ማገኛ ቢሆንም በዛው ልክ ክብራቸውን የሚነካ ማንነታቸውን የሚዳፈረ መሆኑ እጅግ በጣም አስከፊ ያደርገዋል።
“…..እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ይህንን ጫካ አውቀዋለሁ። ከእናቴ ጋርም ለብዙ ዓመታት ተመላልሼበታለሁ። እናቴ ካረፈች በኋላም የማውቀው ጫካ ገብቶ እንጨት ተሸክሞ መሸጥን ብቻ ስለነበር ከጫካው አልተለየሁም። ጫካው የእለት ጉርሳችን ነው ልጆቻችንን አብልተን የምናሳድርበት ዋስትናችን ነው። ነገር ግን በውስጡ ብዙ የማይነገሩ ከባድ ችግሮችንም የምናስተናግድ ነን ” በማለት የሥራውን አስከፊነት ይናገራሉ።
በሴቶች ላይ የሚደርሰው አካላዊና ሞራላዊ ጉዳቱ የቱን ያህል ዘግናኝ ቢሆንም ጫካው ገብተው እስኪወጡ ድረስ ወይ ገንዘብ ወይም ሴትነታቸው የሚጠይቁ የጫካው ውስጥ ጎሮምሶችና ደን ጠባቂዎች ከሥራቸው ክብደት በላይ የየእለት ራስ መታታቸው እንደሆኑ ነው ወይዘሮ ዓለምነሽ የሚናገሩት።
“……የኑሮ ውጣ ውረዱ የዚያን ያህል አስቸጋሪ ነው። ልንቋቋማቸው የሚከብዱ ብዙ ችግሮችን መጋፈጡ፤ ለተለያዩ ማህበራዊ ጥቃቶች መጋለጥን መቻል ከእኛ የሚጠበቅ ነው። ዛሬ የሆነ ነገር ደረሰብን ወይም እንጨታችን ተወረሰ ብለን ነገ ከቦታው አንቀረም እንሄዳለን ፤ ምክንያቱም ከዛ ከቀረን የምንበላውም ሆነ ልጆቻችንን የምንበላው እናጣለን” በማለት ይናገራሉ።
በዚህ ዓይነቱ በማያወላዳ የኑሮ ዑደት ውስጥ ሕይወታቸውን እየመሩ ያሉ በርካቶች አሉ። የማገዶ እንጨት ለቅመው፣ ተሸክመውና ሸጠው ቤተሰብ ከማስተዳደር አልፈው ልጆቻቸውን ኮሌጅ ድረስ አስገብተው በማስተማር ለወግ ማዕረግ ያበቁም ቤት ይቁጠራቸው። ከዚህ አድካሚ ሥራ ተላቀው በሌላ የተሻለ ሙያ ዘርፍ በመሰማራት በኑሮአቸው ለውጥ ማየትን የጀመሩ ጥቂት የማይባሉም አሉ። ወይዘሮዋም የልጅነት እድሜያቸው ወደ ትዳር ሲገቡ በዚሁ ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ነበር።
ወይዘሮዋ የአባታቸው የሥራ ጓደኛ ከነበረው የሽመና ባለሞያ ጋር በትዳር ተሳሰሩ። መጀመሪያ ላይ ሁለት ልጆችን ወልደው እየኖሩ እያለ መልካም የሚባል የትዳር ግንኙነት እንደነበራቸው የሚናገሩት ሴት ልጆች እየጨመሩ ሲሄዱ ግን ባለቤታቸው ሥራ አቁመው መስከር ሥራቸው ሆነ።
“……ኑሮን ለመተጋገዝ ከአንድ ሁለት ይሻላል በሚል ከአባቴ ጓደኛ ሸማኔ ጋር ትዳር መሰረትን፤ እሱም ሥራውን ይሰራል እኔም እንጨቴን እያመጣሁ እሸጣለሁ፤ በዚሀም ጥሩ ትዳር ነበረን ልጆችም መውለድ ጀመርኩ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ገን የወለድኳቸው ልጆች ሴቶች ነበሩ፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ባለቤቴን ሊያስደስተው አልቻለም” በማለት ስለ ትዳር ሕይወታቸው ይናገራሉ።
ለብቻ ልጆች ማሳደግ ከባድ ቢሆንም የእንጦጦ ደን ለበርካታ እንጨት ለቅመው ቤተሰባቸውን ለሚያስተዳድሩ እናቶች ባለውለታ ነውና ለሳቸውም በሩን አልዘጋባቸውም፡፡ ዳገት ወጥተውና ቁልቁለት ወርደው ልጅ ማዘል ባልታከተው ጀርባቸው እንጨት ተሸክመው የልጆቻቸውን ጉርስ ችለዋል፡፡ እንደ አቅማቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ልከዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን እንዳልተቀየረ የሁልጊዜ ሸክማቸው ምስክር ነው፡፡
ከባለቤታቸው ጋር ሲኖሩ ቤት ተከራይተው የነበረ ሲሆን እሳቸው በመጠጥ ምክንያት ሥራ ፈትነት ሲሆኑ ቤት ኪራይ የሚከፈል ይጠፋል በዚህ ጊዜ ደግሞ ወይዘሮ ዓለምነሽ ከነልጆቻቸው መውደቂያ ያጣሉ። መቼም ከነልጆቼ ጅብ አይበላኝም በማለት ቤታቸውን ለሁለት አካፍለው በሚያከራዩ ሰዎች ቤት በደባልነት ይገባሉ። ይህ ለሳቸው እፎይታን የሰጠ ቢሆንም ብዙ ርቀትን ግን መጓዝ የቻለ አልሆነላቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከደባላቸው ጋር ስምምነት አጡ። ይህ እንዳለ ሆኖ ጭቅጭቁ የመረራቸው የወይዘሮ ዓለምነሽ ባል አዳባያቸውን በመደብደባቸው ለእስር ተዳረጉ።
ይህ ደግሞ ለወይዘሮ ዓለምነሽ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሉት ዓይነት ነገር ሆነባቸው። መቼም ፈጣሪ ጥሎ አይጥልምና ከብዙ ልፋት በኋላ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት አካባቢ የቀበሌ ቤት አገኙ። አራት ልጆችን ማሳደግ ጀመሩ።
ማልደው ጫካ የሚሄዱት ወይዘሮ ዓለምነሽ እንጨት ለቀመው ተሸክመው ከሸጡ በኋላ ሲመለሱ በቆሎ ወይም አትክልት ይዘው በመግባት የጉሊት ንግድ ይሰሩ ነበር። እንጨት ለቅሞ መሸጥ ሥራን የልጆቻቸው መሳደጊያ ዋና መተዳደሪያቸው አደርገውት የኖሩት እኚህ ሴት ኑሮን ለመግፋት ሲሉ ከአውሬ ጋር እየታገሉ እንጨት ለቅመው በመሸጥ ሕይወትን በእንጦጦ ጫካ ላይ እየገፉ እናት ዛሬ ላይ ልጆቻቸው እንደደረሱላቸው ይናገራሉ።
ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምረው ከመሰሎቻቸው ጋር ተጠራርተው አቀበቱን ወጥተው፤ ቁልቁለቱን ወርደው ቅጠል ጠርገው፤ ጭራሮ ለቅመው ፤ ከእንጨት ቆራጮች የሚተራርፍ የእንጨት ጉራጆችን ለቅመው የገበያው ሰዓት ሳያልፍ ተሸክመው ይሮጣሉ። ይህ ተግባር አንዴም አይደል ደግመው ደጋግመው ለዓመታት ያደረጉት ነው። ከልምዳቸው የተነሳ አድካሚው ጋራን በፍጥነት ሲያልፉ ድካም አይታይባቸውም።
ወይዘሮ ዓለምነሽን የመሰሉ ስንቶች ጎጆአቸው እንዳያዘም፣ ቤተሰቡም ሰብሳቢ አጥቶ እንዳይበተን ጥረዋል ደክመዋል። የሌላ እጅ ጠባቂ ላለመሆን ላባቸው በጀርባቸው እየተንቆረቆረ ለዚያውም በሸክም ጭምር ክንድ እግሮቻቸው እየዛሉ በየጥሻው ባዝነዋል። ያገኟትንም አሳስረው ወጥተው ወርደዋል፤ ከእንጦጦ ጋር ቁርኝታቸው ለዓመታት ዘልቋል። ከመኖሪያ ቀያቸው እንጦጦ፤ ከእንጦጦም ያሰባሰቡትን ይዘው ገዥ አግኝተው እስኪቀናቸው በመሐል ከተማ ሳይቀር ተዛዙረዋል።
ሕይወት ፈተና ብትሆንባቸውም ከእንጦጦ ተሻርከው፤ ብርታትንና ጥንካሬን ተላብሰው በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በየእለቱ እስከ አርባ ኪሎ ሜትር በእግር ጉዞ መመላለሱ የኑሮ እጣ ፋንታ ሆኖባቸዋል። እንጦጦ የየእለት ፈተናና ትግላቸውን ሸሽጎ የእለተ ጉርስ እንካችሁ ይላቸዋል።
በሽሮ ሜዳ ወፍ ገና አልተንጫጫም፤ ሌቱም ቢሆን ለንጋት ሥፍራውን ለመልቀቅ አልተሰናዳም። የቤተሰቡ የእለት ጉርስ የማሰናጃ ወቅት ነውና ወይዘሮ አለምነሽ መኖሪያ ቤታቸው በጢስ ተሟሙቃለች። ከሙቀቱ ውስጥ ወጥቶ መሄድ ባያስመኝም ከእንጦጦ ጋር የያዙት ቀጠሮ እንዳይረፍድ ይሮጣሉ።
የቤት ውስጥ ጣጣውም የወደቀው በወይዘሮዋ ትከሻ ላይ ነው። ቀን ላይ የሚቋደሷትን ስንቅ ቆጣጥረው፣ የሚጠጧትን ይዘው፣ የሥራ ትጥቃቸውንም አሰማምረውና ሌሊት አሥር ሰዓት ከመሆኑ በፊት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ሥራ እንዲህ ከውነው ለአድካሚው ሥራ መንደራቸውን ለኋሊት ትተው ጉዟቸውን ይያያዙታል ወደ እንጦጦ።
ማልደው ከአውሬ ጋር እየተጋፉ ተራራውን መወጣቱ፤ በየመንገዱ ቆመው የሚጠብቋቸው የጫካውን ካቦዎች በገንዘብ ማለፉ፤ ሰው ተተናኮለኝ አልተተናኮለኝ የሚለውን ሰቆቃን መሻገሩ እንዳለ ሆኖ እንጨት የሚሸጡበት አራት ከሎ ቤተመንግሥት አካባቢ ፊት በር እየተባለ የሚጠራው ሰፈር አራት ሰዓት ሳይሞላ ለመድረስ የነበረውን ሩጫ ያስታውሳሉ።
አራት ሰዓት ሳይሞላ እንጨቱ ከተሸጠ በጠዋት አትክልት ተራ በመሄድ ለጉልት ንግድ የሚሆነውን ሽንኩርት ድንች ቲማቲምና ሌሎች አትክልቶችን በርካሽ በማምጣት ለመቸርቸር ይሆናል የሚሉት ወይዘሮዋ ይህ ካልሆነ ግን እንጨቱን በጀርባቸው ተሸክመው ገበያ ፍለጋ መንደሩን ሲያካልሉ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።
መንደርተኛው እንጨት ካልፈለገ ከእንጨት ለቃሚዎቹ ሴቶች ተረክበው ለሚቸረችሩ ሰዎች ከዋጋ በታች በመሸጥ፤ ለልጆች የሚሆን ነገር ቋጥረው በአስራ አምስት ሳንቲም አውቶቡስ ተሳፍረው ወደ መንደራቸው እንደሚመለሱ ያስታውሳሉ።
በየእለቱ የተለያዩ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ ተራራውን የሚወጡት እኚህ ሴት እርጉዝ ሆነው እንኳን ጓዳቸው እንዳትጎድል ሲሉ የእንጦጦን ጫካን ሳይረግጡ እንደማይወሉ ነው የሚናገሩት። ከሶስት አስርተ ዓመታት በላይ በቀናት ከሚቆጠሩ ጊዜዎች በስተቀር በየእለቱ የእንጦጦን አቀበት ሽቅብ እየተመለከቱ ተመላልሰዋል።
አሁን ልጆቻቸው ደርሰው ከድካም ሊያሳረፏቸው እየጣሩ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ዓለምነሽ የመጀመሪያ ልጃቸው አረብ ሀገር ሄዳ ሰርታ ጥሪት መያዝ ከጀመረች መሰነባበቷን ይናገራሉ። የመጀመሪያዋ ተከታይ ወንድ ተምሮ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በማምጣቱ እህቱ ድጋፍ እያደረገችለት ተምሮ ተመርቆ ሥራ እየፈለገ ይገኛል።
አንዱ ልጅ የጤና ችግር የገጠመው በመሆኑ በፀበልና በሆስፒታል በመንከራተት ላይ የሚገኙ መሆኑን ይናገራሉ። አራተኛ ልጃቸው አስራ አምስት ዓመቱ ሲሆን ታዛዥ ሰው አክባሪ እናቱን ጧሪ ልጃቸው ስለሆነ ያመሰግኑታል።
” …..አሁን ልጄም እየደገፈችኝ እንጨት መልቀሙን ባቆምም የታመመውን ልጅ ይዤ እየተንከራተትኩ ነው። ልጄ ፀበልም ሆነ ሐኪም ቤት ወስጄ ስመልሰ ትንሹ ልጅ ምግብ አዘጋጀቶ ቡና አፍልቶ የቤቱን ሥራ ሰርቶ ይጠብቀኛል። ያኔ አህያ በወለደች አረፈች እያልኩ እደሰታለሁ ” የሚሉት ወይዘሮ ዓለምነሽ በልጆቻቸው ድጋፍ ቀንን ለመሻገር ቢጥሩም ኑሮ ቀደዳው እየበዛ እንደሚያስቸግራቸው ይናገራሉ።
አሁን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ እንዲገነባ ካደረጉት የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ሥራዎች መካከል በጉለሌ እንጀራ ማዕከል ውስጥ እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ። መሥራት የሚችል እጃቸውን አጣጥፎ ከመቀመጥ ያዳናቸውን ማዕከል የሚያመሰግኑት እኚህ ሴት ለእሳቸውና ለመሰሎቻቸው ማረፊያ ብሎም ጥሪት ማፍሪያ ማዕከል በመከፈቱ መደሰታቸውን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ በሁለት ቦታ የተከፈቱት እንጀራ መጋገሪያ ማዕከላት በውስጣቸው በርካታ ሥራ እየፈለጉ ያጡ፤ ብሎም በጥረታቸው ልጆች ለማሳደግ የሚታገሉ፤ እንጨት ከመሸከም አንስቶ ልብስ እስከ ማጠብ በየሰው ቤት እየዞር ከባባድ ሥራዎችን በመሥራት ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ሴቶችን ይደግፋል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
እነዚህ ሴቶች በድካምና በጉስቁልና ያለ እድሜያቸው እንዳይሞቱ፤ በሕመም ቤት ውለው ለቤተሰብም ሆነ ለሀገር ሸክም እንዳይሆኑ እንደ እንጀራ መጋገሪያ ማዕከሉ ዓይነት የተለያዩ በአቅማቸው ሰርተው ጥሪት የሚያፈሩባቸውን ተቋማት ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።
ፕሮጀክቶቹ በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት ከጫካ በመልቀም ለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጀምረው የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎች ናቸው::
ጉለሌ እንጀራ ማዕከል ለመዲናዋ ሁለተኛው የእንጀራ ፋብሪካ ሲሆን በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ 551 እናቶች የሥራ እድል የፈጠረ ነው። የእንጀራ ማዕከሉ በውስጡ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ሕንፃዎች፣ የሕፃናት ማቆያ ፣ የእህል ማከማቻ ፣ ወፍጮ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ያካተተ ነው። 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ ተገጥሞለታል፤ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያ ማሽን፤ ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽን፤ ሁለት ወፍጮዎች፤ 551 እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው ይሰሩበታል።
በእንጀራ ማዕከሉ ውስጥ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው እናቶች ከዚህ በፊት በአካባቢው እንጨት በመልቀም ሲተዳደሩ የነበሩ፣ ምንም ገቢ የሌላቸው እና የኑሮ ጫና የበረታባቸው እናቶች ናቸው። ወይዘሮ ዓለምነሽም ለሁሉም እናቶች ይህ እድል መከፈቱ የብዙዎችን ታሪክ ይቀይራል ብለው እንደሚያምኑ ያሰረዳሉ።
እናትነት ሊያውም በድህነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ማሳያ የሆኑትን ወይዘሮ ዓለምነሽ የእናትነት ክብር ይገባቸዋል። ሀብት ንብረት አፍርተው የሚያርፉ ያደርጎት። “አንትሮሽት” የእድሜዎን እኩሌታ በእንጦጦ ጫካ ላይ እንጨት እየተሸከሙ ልጆቾትን ቁምነገር ላደረሱ ለእርስዎ እና እንደእርስዎ በድካም ልጆቻቸውን ለሚያሳደጉ እናቶች ብለናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም