የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ክስተቶች የሚበዙበትን የግንቦት ወር ጀምረነዋል፡፡ የግንቦት ወር የደርግ እና የኢህአዴግ፣ የደርግ እና የተቃዋሚዎቹ፣ የኢህአዴግ እና የተቃዋሚዎቹ ወር ነው ማለት ይቻላል፡፡ የታሪክ ግጥምጥሞሹ በታሪክ ክስተቶች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የሚገርመው ገዥዎቹ እና ተቃዋሚዎቹ መሪዎች የተወለዱበትና ያረፉበት ወር ጭምር ነው፡፡ የደርግ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተወለዱት በግንቦት ወር ነው፡፡ የደርግ መንግሥትን የታገለውና የገረሰሰው የኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የተወለዱት በግንቦት ወር ነው፡፡ የኢህአዴግን መንግሥት እና መሪውን አቶ መለስ ዜናዊን ሲቃወሙና ሲታገሉ የነበሩት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ያረፉት በግንቦት ወር ነው። የደርግና የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ታሪክ ቀኑ ሲደርስ እናስታውሳለን፡፡ በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ክስተት የሆኑትን የኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ እና የኢህአዴግ ተቃዋሚ የነበሩትን የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን ታሪክ እናስታውሳለን፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ
አቶ መለስ ዜናዊ ከ69 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 1 ቀን 1947 ዓ.ም ከእናታቸው ከወይዘሮ አለማሽ ገብረልዑል እና ከአባታቸው ከአቶ ዜናዊ አስረስ በዓድዋ ከተማ ተወለዱ። ስለግል ሕይወታቸው ሲናገሩ የማይሰሙት አቶ መለስ፣ ጎልቶ የሚታየው የፖለቲካ ሕይወታቸው ነው፡፡ ቢሆንም ግን ወደ ፖለቲካ ትግል ከመግባታቸው በፊት ስማቸው ለገሰ ይባል እንደነበር ይነገራል። መለስ የሚለውን ስም የወሰዱት በትግል ላይ ሳለ ከተሰዋ የሕወሓት ታጋይ እንደሆነ በአንዳንድ የታሪክና ፖለቲካ ሰነዶች ሲነገር ቆይቷል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በዓድዋ ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት ተማሩ። ከ1961 ዓ.ም እስከ 1964 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ተከታተሉ። በመቀጠል፤ በ1965 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋኩልቲ የሕክምና ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ መለስ ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ የገቡት፡፡ በ1966 ዓ.ም መጀመሪያ በተማሪዎች መማክርት ምርጫ ላይ በመወዳደር የሳይንስ ፋኩልቲን በመወከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምክር ቤት (Student Council) አባል በመሆን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አመራርን ተቀላቀሉ። በመስከረም ወር 1967 ዓ.ም የብሔረ ትግራይ ተራማጆች ማህበር እንደተመሠረተ የንቅናቄው አባል ሆኑ።
አቶ መለስ በ1967 ዓ.ም አምባገነን ነው ያሉትን የደርግ ሥርዓት ለመታገል ወደ ትጥቅ ትግል በመግባት የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አባል ሆኑ፡፡ ከ1967 ዓ.ም እስከ 1969 ዓ.ም በሕወሓት ታሪክ የድርጅት ህልውናን የማረጋገጥ ምዕራፍ ፈተናዎች በፅናት ተሻገሩ።
አቶ መለስ በ1969 ዓ.ም የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ተወካይና የከፍተኛ አመራር አባል ሆኑ። በ1971 ዓ.ም ደግሞ በሕወሓት 1ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመረጡ። ከ1971 ዓ.ም እስከ 1975 ዓ.ም የትግራይን ሕዝብ በብሔራዊና ሕዝባዊ ትግሉ በስፋት ለማሳተፍ በተደረገው እንቅስቃሴ በአመራርነት ተሳተፉ።
አቶ መለስ ዜናዊ ከ1976 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የሕወሓት የትግል እንቅስቃሴን ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ጋር ለማስተሳሰር ከፍተኛ የጥናትና የአመራር ሚና ተጫወቱ። በ1981 ዓ.ም በሦስተኛው የሕወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ የሕወሓት ዋና ጸሐፊ በመሆን ተመረጡ። በ1983 ዓ.ም ኅዳር ወር ደግሞ በኢህአዴግ የመጀመሪያ ጉባኤ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።
አቶ መለስ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ወቅት የኢህአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሆነው ለአንድ ወር ያህል አገለገሉ። ከሐምሌ ወር 1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት በመሆን አገለገሉ።
በ1987 ዓ.ም የተካሄደውን የኢህአዴግ የመጀመሪያውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በመስከረም ወር 1988 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተመረጡ። በመቀጠል በ1992 ዓ.ም ሁለተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በመስከረም 1993 ዓ.ም ተመረጡ።
አሁንም በመቀጠል በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ሦስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በ1998 ዓ.ም መስከረም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ለ3ኛ ጊዜ ተመረጡ። በ2002 ዓ.ም የተካሄደውን አራተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በ2003 ዓ.ም መስከረም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ለአራተኛ ጊዜ በመመረጥ እስከ ዕለተ ሕይወተ ህልፈታቸው ድረስ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በመሪነት አገልግለዋል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘና በሌሎች ጉዳዮች የአፍሪካን ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ፣ በቡድን 8 እና ቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ በማስተጋባት የአፍሪካ ቃል አቀባይ (Spokesman of Africa) የሚል ስያሜ ያገኙ ናቸው፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1995 ዓ.ም ከዩናይትድ ኪንግደም ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ በ2004 ዓ.ም ደግሞ ከኔዘርላንድስ ኢራስመስ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም ደግሞ ከደቡብ ኮሪያ ሃናማ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሣይንስ የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል።
ለኢትዮጵያ ልማት፣ ለዓለም ሰላም፣ ለምሥራቅ አፍሪካ መረጋጋት ላበረከቱት አስተዋፅኦ በሚል ከ10 ያላነሱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት ተቀብለዋል።
የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንትነቱን ጨምሮ ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ በ57 ዓመታቸው ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ
ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሕልፈተ ሕይወት ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ይመሩት የነበረውን መንግሥት አምርረው ይቃወሙ የነበሩ ምሁር ናቸው፡፡ የእርሳቸው ታሪክም ከኢህአዴግ ጋር ይገናኛል ማለት ነው፡፡
ከ25 ዓመታት በፊት ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ነው ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡
ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የሕክምና ባለሙያ ሲሆኑ ኢህአዴግን ለመታገል የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው፡፡ የእኚህን ሰው ሕይወት እና የፖለቲካ ውጣ ውረድ እናስታውሳለን።አስራት ወልደየስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታዬና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ የአስራት አባት አቶ ወልደየስ አልታዬ በፀሐፊ ትዕዛዝ ኃይሌ ወልደሥላሴ አስተዳደር ውስጥ በፀሐፊነትና በአስተዳደር ተግባር የተሰማሩ ነበሩ፡፡ እናታቸውም በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር አሥራት የሦስት ዓመት ሕፃን እያሉ ወላጆቻቸው በፍች ምክንያት ስለተለያዩ ከእናታቸው ጋር ወደ ድሬዳዋ አቀኑ፡፡
አስራት ድሬዳዋ በነበሩበት ወቅት ጣሊያን ኢትዮጵያን ትወራለች፡፡ በዚህ ወቅት በእነ ሞገስ አስግዶምና አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኒ ላይ የተደረገ የግድያ ሙከራን ለመበቀል ከግራዚያኒ በተላለፈ በቀል በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ33 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዶማ፤ በአካፋና በገጀራ ተጨፍጭፈው ተገደሉ፡፡ የአስራት አባት አቶ ወልደየስ አልታዬም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተጨፍጭፈው በአርበኝነት ሞቱ፡፡ እናቱ ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌም የባለቤታቸው ሞት ተጨምሮበት ብዙም ሳይቆዩ ታመው በሞት ተለዩ።
ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ታዳጊ በድሬዳዋ ከአያቱ ጋር አደገ፡፡ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተውም ጎበዝና ፈጣን ተማሪ ነበሩ ይባላል፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ አንደኛ በመውጣትም ተሸላሚ ሆኑ፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ወደ ውጭ ይላኩ ስለነበር አሥራት ወደ ግብጽ ተልከው ተከታትለዋል። ከዚያም በስኮላርሽፕ እንግሊዝ ሀገር ሄደዋል፡፡ እንግሊዝ ሀገር ሕክምና ተምረው ወደ ሀገራቸው በመመለስ በሕክምና አገልግለዋል፡፡
ዶክተር አስራት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የሕክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በመወትወታቸው ምክንያት የጥቁር አንበሳን ሆስፒታል እውን አደረጉ። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት ዶክተር አስራት ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እውን ሲሆን ፕሮፌሰር አስራት ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ፡፡ ከዚያ በፊት በውጭ ባለሙያዎች ነበር፡፡
ፕሮፌሰር አሥራት በደርግ ዘመነ መንግሥት በተደጋጋሚ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን የሄዱበትን ዘመቻ በክብር ለመወጣት በቅተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በ1968 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1969 ዓ.ም እንደገና በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዳጅ ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቀሌ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝተዋል፡፡
የደርግ ሥርዓት ተሸንፎ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት፤ ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም በተደረገው የሽግግር መንግሥት ቻርተር ውይይት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወክለው የተገኙት ፕሮፌሰር አስራት ‹‹ሀገር ላስገነጥል ተወክዬ አልመጣሁም›› በማለት ተቃውሞ አሰሙ። ‹‹ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምንም ጉዳይ ሊወስን፤ ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ አይችልም›› በማለት ጉባኤው እያደረገው ያለውን ውሳኔ ‹‹ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው›› ሲሉ ሞገቱ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ ፕሮፌሰር አሥራት ወደ ፖለቲካው ገቡ፡፡ የኢህአዴግን አገዛዝ ለመታገል ፓርቲ መሥርተው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ከኢህአዴግ ጋር አይጥና ድመት ሆኑ፡፡ ኢህአዴግም እያሳደደ ያሥራቸውና ይፈታቸው ጀመር፡፡ ኢህአዴግ እንቅስቃሴያቸውን ባየ ቁጥር እስርና እንግልቱን አጠናከረው፡፡ ለብቻቸው በማሰር ስቃይና መከራም ያደርስባቸው ጀመር፡፡
የእስር አያያዛቸው የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በ1972 ዓ.ም የጀመራቸው የልብ ሕመም ተባብሶ እንዲሁም የስኳር መጠናቸው በመጨመሩ ከፍተኛ የጤና ችግር ላይ ወደቁ፡፡ ለብዙ በሽተኞች መድኃኒት የነበሩት አስራት ሕክምና ተከልክለው የበሽታ መጫዎቻ ሆኑ፡፡ ከስኳራቸው ከፍ ማለት ጋር ተያያዞ ዓይናቸው ማየት አልቻለም፡፡ ሰውነታቸውም እንደፈለጉ ሊታዘዛቸው አልቻለም። የልብ ድካማቸው ጨምሯል፡፡ ሕክምና እንዲያገኙ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ሳይቀር ደብዳቤ ጻፉ፡፡ መፍትሔ ግን አላገኙም፡፡ የኋላ ኋላ ሲዳከሙ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢወሰዱም ህመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ መፍትሔ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ በመጨረሻም እ.ኤአ ታኅሣሥ 27 ቀን 1998 ዓ.ም ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲታከሙ ተፈቀደ፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ በመድከማቸው አውሮፕላን ውስጥ በሐኪሞች እየታገዙ ወደ ለንደን ሆስፒታል በረሩ፡፡ ከ3 ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ ሆስተን አመሩ፡፡ በአሜሪካ ቅዱስ ሉቃስ ኤጲስቆጳል ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት እንደተሻላቸውና ከልቡ ሲያስባቸው ለነበረው ሕዝብ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ትንሽ እንደተሻላቸው ዘመዶቻቸው ወደሚገኙበት ፊላደልፊያ ከወር በፊት ተዛውረው በነበረበት ወቅት ባልታወቀ ምክንያት ህመማቸው ተባብሶ ተዳከሙ፡፡
ሞትን ድል ሲያደርጉት የኖሩት ሐኪም ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ፊላደልፊያ በሚገኘው ፔኒሲለቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዕለተ ዓርብ በተወለዱ በ71 ዓመታቸው አረፉ። በወቅቱ የፕሮፌሰሩን ሞት ትልልቅ የዓለም መገናኛ አውታሮች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የፖለቲካ ተሳትፏቸው ከሕክምና ሙያቸው በላይ እንዲታወሱ አድርጓቸዋል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ እና ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን የታሪክ አቀባበል ልማዳችን ኋላቀር ነው፡፡ ታሪክን በታሪክነቱ ከማስታወስ ይልቅ መበሻሸቂያና የቡድን የፖለቲካ ፍላጎት መቀስቀሻ ሆኗል፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ አድናቂዎችና ደጋፊዎች የፕሮፌሰር አሥራት ስም እንዲነሳ አይፈልጉም፤ የፕሮፌሰር አሥራት ደጋፊዎች ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊ ስም እንዲነሳ አይፈልጉም፡፡ ይህ ኋላቀር አመለካከታችን ሊቀረፍ ይገባል፡፡ ሁሉንም በሠሩት ሥራ ታሪክ ያስታውሳቸዋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም