የዱባይ አየር ማረፊያ በጎርፍ መጥለቅለቁን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ተሰረዙ

የባህረ ሰላጤው ሀገራት አውሎ ንፋስ በቀላቀለ ከባድ ዝናብ መመታታቸውን ተከትሎ በዓለማችን ሁለተኛ የሆነው የዱባይ አየር ማረፊያ በጎርፍ ተጥለቀለቀ። በዚህም የተነሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ሲሰረዙ፣በርካታዎችም ተስተጓጉለዋል።

የዱባይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ “በጣም ፈታኝ ሁኔታዎች” እንደገጠመው አስጠንቅቆ መንገደኞች በጎርፍ የተጥለቀለቁ አካባቢዎችን እንዲያስወግዱም መክሯል። አንድ ግለሰብ መኪናው በጎርፍ በመወሰዱ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል። በኦማን ሳሃም በተሰኘችው አካባቢ ነፍስ አዳኞች የአንዲት ታዳጊ አስከሬን ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም በሀገሪቱ ከእሁድ ጀምሮ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 19 አድርሶታል።

ረቡዕ ዕለት የዱባይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መነሻ እና መድረሻ አድርገው የነበሩ 300 በረራዎች መሰረዛቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መዘግየታቸውን ፍላይ አዌር ዳታ የተባለው የበረራ መረጃ ገልጿል።
በአሜሪካ አትላንታ በመቀጠል ሁለተኛ የሆነው እና 80 ሚሊዮን መንገደኞችን ባለፈው ያስተናገደው የአየር ማረፊያ ከደረሰበት ሁኔታ ለማገገም የተወሰነ ጊዜ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ረቡዕ ዕለት ከአየር መንገዶች ማረጋገጫ ሳይኖር ተርሚናል 1ን እንዳይጎበኙ እና ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዳይመጡም ምክር ሰጥቷል።

በዱባይ መቀመጫውን ያደረገው ኤምሬትስ አየር መንገድ ከከተማዋ የሚነሱ መንገደኞች መቀበሉን ማቆሙን አስታውቋል።ዝቅተኛ ቦታዎች በጎርፍ ተጥለቅልቀው ባሉበት ሁኔታ ከፍተኛ አውሎ ንፋሶች፣ ከፍተኛ ዝናብ እና ንፋስም በቀጣዩ እንደሚጠበቅም ባለስልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።
የኦማን ጎረቤት የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬት ማክሰኞ እለት ያጋጠማት ከፍተኛ ዝናብ በ75 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ሆኖም ተመዝግቧል። የሀገሪቱ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ማዕከል መሠረት በአል አይን ክልል በምትገኘው ካትም አል ሻክላ ላይ ከ24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 254 ነጥብ 8 ሚሊሜትር የዝናብ መጠን እንደነበረም አስታውቋል።

ሀገሪቷ በአማካይ ከ140-200 ሚሊሜትር የዝናብ መጠን የምታገኝ ሲሆን፤ ዱባይ ደግሞ 97ሚሊሜትር ነው። በሚያዝያ ወር ደግሞ ወርሃዊ አማካይ የዝናብ መጠን 8 ሚሊሜትር ያህል ብቻ ነው። የዱባይ ማዕከላዊ ስፍራዎች እንዲሁም በጎርፍ በተጥለቀለቀው የሼክ ዛይድ መንገድ ላይም በርካታ ተሽከርካሪዎች ሲንሳፈፉ ታይተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You